የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ የክልል ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎች ጭምር የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች በስፋት ይነሳል። በሁሉም አካባቢዎች ዋነኛ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ከሆኑትና በመንግሥት አቅም ከሚሰሩት የመሰረተ ልማት ግንባታዎች መካከል የመንገድ፣ የመኖሪያ ቤት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ዝርጋታና የንጹህ የመጠጥ ውሃ በዋናነት ይጠቀሳል።
ሕይወት ላላቸው ነገሮች ሁሉ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት መሰረት ልማቶች መካከል ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው ንጹህ የመጠጥ ውሃ አንዱ ነው። ‹‹ውሃ ሕይወት ነው›› የተባለውም ያለ ምክንያት አይደለም። የሰው ልጆችን ጨምሮ እንስሳትና እጽዋቱ ሁሉ ከውሃ ውጭ ሕይወት የላቸውምና ነው። ይሁንና በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ዜጎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ እጥረት ሲገጥማቸው መመልከት የተለመደ ቢሆንም በአንጻሩ ደግሞ መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት ሲያደርግም ይስተዋላል። በዛሬው ዕትማችንም ልናስነብባችሁ የወደድነው በንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት ችግር ላይ ባለው የዲላ ከተማ ሕዝብ የውሃ ጥሙን ማርካት እንዲችል ታስቦ እየተሰራ ባለው ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ዙሪያ ነው።
የዝግጅት ክፍላችን በዲላ ከተማ በተገኘበት ወቅት የከተማ አስተዳደሩን ከንቲባ አግኝቶ ፕሮጀክቱ መች እንደተጀመረ፣ ምን ያህል ወጪ እንደሚጠይቅና መች እንደሚጠናቀቅ ጭምር አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴው በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መረጃዎችን እንደሚከተለው አጠናቅሯል።
በአገሪቱ ከሚገኙ የክልል ከተሞች መካከል በልምላሜዋና ከፍተኛ የሆነ የንግድ እንቅስቃሴዋ የምትታወቀውና በደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን የምትገኘው ዲላ ከተማ ከፍተኛ የሆነ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ችግር የሚታይባት ለመሆኗ በየሰው ደጃፍ የተኮለኮሉት ቢጫ ጀሪኪናች ምስክሮች ናቸው። በከተማዋ የሚታየውን ንጹህ የመጠጥ ውሃ እጥረት ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ ምን እየሰራ ነው ስንል ላነሳነው ጥያቄ የዲላ ከተማ ዋና ከንቲባ አቶ ተስፋጺዮን ዳካ የሚከተለውን ብለዋል።
እንደሳቸው ገለጻ፤ በአሁን ወቅት ከተማዋ ከሚያስፈልጋት ንጹህ የመጠጥ ውሃ መጠን በታች እያገኘች እንደሆነ በመጥቀስ ዜጎች በንጹህ የመጠጥ ውሃ ችግር ውስጥ ከፍተኛ ችግር እያሳለፉ ነው ያለ ቢሆንም ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።
በዲላ ከተማ ከፍተኛ የሆነ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እጥረት አለ። አጠቃላይ የከተማው ሕዝብ ለአንድ ቀን ብቻ 25 ሺ ሜትር ኪዩብ ንጹህ የመጠጥ ውሃ የሚያስፈልገው ቢሆንም በአሁን ወቅት የከተማ አስተዳደሩ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት በከተማ ደረጃ 2993 ሜትር ኪዩብ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ብቻ እያቀረበ ይገኛል። ይህም ከፍላጎቱ ጋር ሲነጻጸር እጅግ ሰፊ ልዩነት እንዳለውና ዘርፉ ክፍተት ያለበት ለመሆኑ ማሳያ ነው።
ይሁንና ችግሩን መቅረፍ የሚያስችል ግዙፍ የሆነ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በከተማዋ ተጀምሯል። ፕሮጀክቱ ከ298 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ሲሆን ፕሮጀክቱ ዕውን እንዲሆን ማህበረሰቡን ጨምሮ ከተማ አስተዳደሩ በከፍተኛ ትኩረት እየተከታተለው እንደሆነ አቶ ተስፋጺዮን ተናግረዋል። በተለይም ማህበረሰቡ ፕሮጀክቱ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ በጣም በቅርበት እየተከታተለና እየጠየቀ መሆኑን በማንሳት በአሁን ወቅትም አጠቃላይ የፕሮጀክቱ የሥራ እንቅስቃሴ 33 በመቶ ደርሷል። ከዚህ በኋላም ቀሪ ሥራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉና ወደ ፍጻሜው ለመድረስ የሚሠራ ይሆናል።
ለመስመር ዝርጋታው በርካታ የፕላስቲክ ቱቦዎች ወደ ከተማው የገቡ እንደመሆናቸው በቀጣይ የመስመር ዝርጋታው ይከናወናል ያሉት አቶ ተስፋጺዮን፤ ወደ መስመር ዝርጋታው ሲገባ ትልቅ ችግር የሚገጥማቸው ይሆናል። በተለይም ከግለሰቦች ይዞታ ጋር በተያያዘ አጥሮችን፣ ግቢዎችንና ሰብሎችን የመንካት ሁኔታ ይፈጠራል። ይህም በሥራው የሚጠበቅ ችግር ነው።
በመጀመሪያው ዲዛይን 24 የሚደርሱ ዓለም አቀፍ የአስፓልት መንገዶችን ይቆርጥ እንደነበር አስታውሰው ይህም በአንድ በኩል የውሃ ልማት ሲረጋገጥ በሌላ በኩል ደግሞ የመንገድ መሰረተ ልማትን ማፍረስ ተገቢ እንዳልሆነ በማመን ዲዛይኑን መቀየር ተችሏል። በአዲስ መልኩ በተጠናው ዲዛይንም የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ከ24 የአስፓልት ቆረጣ ወደ 12 ዝቅ ማድረግ ተችሏል። ይህም ወጪን ከመቆጠብ ጀምሮ በመንገድ መሰረተ ልማት ላይ ይደረስ የነበረውን ጉዳትም መቀነስ አስችሏል።
የሕዝብ የሆነው ይህ ፕሮጀክት ውጤታማ መሆን እንዲችልና በተቀመጠለት የጊዜ ገደብና በጀት ተጠናቅቆ አገልግሎት እንዲሰጥ የሁሉም አካላት ርብርብ ያስፈልጋል። ከተማ አስተዳደሩም በተቻለው አቅም ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እያደረገ ይገኛል። ዞኑ፣ ከተማ አስተዳደሩና የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅትም እንዲሁ ተገቢውን በጀት እየከፈሉ መሆኑን አቶ ተስፋጺዮን ይጠቅሳሉ። ክልሉም አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ነው። በተለይም ከተማ አስተዳደሩ አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በመክፈል ሶስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር የሚቀርበት መሆኑን አስረድተዋል።
የዲላ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት አምስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር መክፈል የነበረበት ቢሆንም ከሚያቀርበው ውሃ አንጻር የሚያገኘው ገቢ አነስተኛ እንደሆነ ተናግረው ፕሮጀክቱ ተግባራዊ መሆን ሲችል ተጠቃሚው አጠቃላይ የከተማው ሕዝብ እንደመሆኑ ተቋሙን በመደገፍ ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ርብርብ ማድረግ ከሁሉም የሚጠበቅ በመሆኑን ይናገራሉ።
ሕዝቡ ከንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ተጠቃሚ መሆን እንዲችል በርካታ ሥራዎች የተሰሩ ሲሆን የተወሰኑ ግብዓቶች ማለትም ፓምፕ፣ ጀነሬተሮችና ሌሎች ግብአቶች ጅቡቲ ወደብ ላይ መድረስ እንደቻሉ የጠቆሙት አቶ ተስፋጺዮን፤ ከጅቡቲ ወደ ዲላ ከተማ እስኪዘዋወር የሚወስደው ጊዜ እንዳለ ሆኖ በቀሪዎቹ ወቅቶች በተጠናከረ መንገድ ሙሉ አቅማቸውን አሟጠው መሥራት ከቻሉ በቀጣይ ስድስት ወራት ፕሮጀክቱን በማጠናቀቅ መሰረታዊ የሆነውን ንጹህ የመጠጥ ውሃ ጥያቄ ለመመለስ ጥረት የሚደረግ መሆኑን ነው ያስታወቁት ።
ለተግባራዊነቱም ከተማ አስተዳደሩ ህብረተሰቡን በማንቀሳቀስ የሚጠበቅበትን ሥራ መሥራት ይኖርበታል ያሉት አቶ ተስፋጺዮን፤ በተለይም ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ የውሃ መስመር በሚያልፍባቸው አካባቢዎች ከይገባኛል ነጻ የማድረግ ሥራ አንዱ ነው። ይህ ሥራ በሚሠራበት ወቅትም ህብረተሰቡ ሊደግፍ እንደሚገባ አመላክተዋል። ህብረተሰቡ የረጅም ጊዜ ጥያቄው የነበረውንና ሕይወት የሆነውን ውሃ ለማግኘት የሚጠበቅበትን ግዴታ ለመወጣት በተለይም አጥርና ሰብሎችን ማንሳት የውሃ መስመሩ እንዲያልፍ የማድረግ ሥራ በመሥራት ከከተማ አስተዳደሩ ጎን ቢሆኑ መልካም ነው በማለት ጥሪ አድርገዋል ።
ከፕሮጀክት ጥራት አንጻር ከፍተኛ ክትትል በማድረግ ጥራቱን የጠበቀ ሥራ እንዲሠራም ከፍተኛ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ያነሱት አቶ ተስፋጺዮን፤ የፕሮጀክቱ አማካሪ መሃንዲሶች ጋር ክፍተት የነበረ መሆኑን አስታውሰው፤ በአሁን ወቅት ክፍተቱን ለመድፈን መሃንዲስ መቀየር እንደተቻለና አዲስ የተቀየረው መሃንዲስም ጥሩ ክትትል እያደረገ ያለበት ሁኔታ መኖሩን አመላክተዋል። ከዚህ በተጨማሪም በዘርፉ ዕውቀት ያላቸውን አመራሮች ጭምር በማማከር አስተያየት እንዲሰጡ በማድረግ ችግሮችን በፍጥነት እየታረሙ ነው።
ከከተማ አስተዳደሩ በተጨማሪ ክትትሉ በዋናነት በፕሮጀክቱ መሃንዲስ፣ በከተማው የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ፣ በዞኑ ውሃ መምሪያ ኃላፊ እንዲሁም በአማካሪ መሃንዲሶች ጭምር ከፍተኛ የሆነ ክትትል እየተደረገ ያለበት ሁኔታ መኖሩን አስረድተው፤ የህብረተሰቡ ሚና ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ያነሱት አቶ ተስፋጺዮን፤ ህብረተሰቡ ፕሮጀክቱ የራሱ መሆኑን አምኖ በተለይም መስመሩ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች ሁሉ የተቀመጡ የውሃ ማስተላለፊያ ቱቦዎችን መጠበቅ እና ንብረቱ የራሴ ነው በማለት ልዩ ጥበቃ ሊያደርግላቸው እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል።
ፕሮጀክቱ ተጠናቅቆ ከሚሰጠው አገልግሎት ባሻገር በግንባታው ሂደት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ መሆኑ ያነሱት አቶ ተስፋጺዮን፤ ከጉልበት ሥራ ጀምሮ ለተለያዩ አካላት ግብዓት ከማቅረብ አንስቶ በርካታ አገልግሎት ላላቸው የአካባቢው ማህበረሰብ ክፍሎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። በግንባታው ዘርፍም ተሳታፊ የሆኑትም የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ሲሆን ፕሮጀክቱ ያልተጠናቀቀ እንደመሆኑ በቀጣይ በመስመር ዝርጋታም እንዲሁ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል በመሆኑ በአካባቢው የሚገኙ ሰዎች ሥራን ሳያማርጡ የተገኘውን የሥራ ዕድል ተጠቅሞ ገቢ ማግኘት እንዲችል በማለት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በዲላ ከተማ የሚስተዋለውን የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ በ2013 ዓ.ም ታኅሳስ ወር ላይ የተጀመረው ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት 18 ወራት የሚፈጅ የኮንትራት ጊዜ ተወስኖለታል። ሥራው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን በርካታ ሥራዎች የተሰሩ ቢሆንም ወደ መጠናቀቅ ሳይደርስ ከሁለት ወራት ያነሰ ጊዜ ብቻ ቀርቶታል።
ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ መጓዝ እንዳይችል የተለያዩ መሰናክሎች ማጋጠማቸውን አንስተዋል። በተለይም አገር አቀፍ በሆነው የሲሚንቶ ግብዓት እጥረት የግንባታ ሂደቱ ተቋርጦ ቆይቷል። በዚህ ምክንያትም ከስድስት እስከ ሰባት ወራት በግንባታው ሂደቱ ላይ መስተጓጎል ተፈጥሯል። ከዚህ በተጨማሪም ከውጭ በሚገቡ ግብዓቶች አማካኝነት በጨረታ ሂደት ወደ ኋላ የቀረ ሲሆን በአሁን ወቅት ግን የጨረታ ሂደቱን በማለፍ አስፈላጊው ግብዓት ወደ አገር ውስጥ ብሎም ወደ ከተማው እየገባ ይገኛል።
የዲላ ከተማ ሕዝብ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥ የዘመናት ጥያቄው የሆነውን ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማግኘት እንዲችል በከፍተኛ ትጋት እየተሠራ ስለመሆኑ የዝግጅት ክፍላችን በቦታው ተገኝቶ በጎበኘበት ወቅት መረዳት ችሏል። ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ በሁለት ክፍሎች ተከፋፍሎ እየተሠራ ያለ ሲሆን የመጀመሪያው የሥራ ክፍል ጥልቅ ጉድጓዶችን መቆፈር እንደመሆኑ በአራት የተለያዩ ሳይቶች ላይ አራት ጥልቅ ጉድጓዶች ተቆፈረዋል። በሁለተኛው የሥራ ክፍልም እንዲሁ 219 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ የሲቪል እና የኤሌክትሮ መካኒካል ግንባታ ሥራው እየተከናወነ ይገኛል። በአጠቃላይ ከማማከርና ከሌሎችም ሥራዎች ጋር ተያይዞ ፕሮጀክቱ ከ298 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የሚጠይቅ ነው።
ወጪው የሚሸፈነውም ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር፣ በክልሉ፣ በከተማ አስተዳደሩ፣ በዞኑና በዲላ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ዘርፍ የሚሸፈን ስለመሆኑም መረዳት ተችሏል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15 /2014