‹‹ለመልካም ሥራ ረፍዶ አያውቅም›› የ‹‹ባዩሽ ኮልፌ የበጎ አድራጎት መረዳጃ እድር›› መሪ ሃሳብ ነው። ባዩሽ ኮልፌ በጎ አድራጎት መረዳጃ ማህበር ከዛሬ አስራ አንድ ዓመት በፊት በትምህርት ቤት ጓደኛሞችና በአብሯ አደግ የሰፈር ልጆች አማካኝነት የተቋቋመ ነው። ለመመስረቱ ምክንያት የሆነው “አቅመ ደካማ ተማሪዎችን እንርዳ” የሚለው የጓደኛሞቹ ቅን ሀሳብ ነው።
ጓደኛሞቹ ገንዘብ በማዋጣት በመንደራቸው ደብተርና እስኪሪፕቶ መግዣ ለተቸገሩ እህትና ወንድሞቻቸው በመለገስ የመረዳዳት ተግባራቸውን አንድ ብለው ይጀምራሉ።
በወቅቱ የከፋ ችግር አለባቸው የሚሏቸውን ሃያ ተማሪዎችን ብቻ ለይተው ነበር እርዳታ ያደረጉላቸው። ድጋፍ ያገኙ ተማሪዎች በተደረገላቸው ነገር ደስታ ሲሰማቸው ሲያዩ ደግሞ ይህን የተቀደሰ ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለባቸው ይሰማቸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ከማድረጉ በፊት የ‹‹ባዩሽ ኮልፌ የበጎ አድራጎት መረዳጃ እድር›› በየዓመቱ ለሶስት መቶ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እስከ ማድረግ ደርሶ ነበር። ከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ቤት ምገባና የቁሳቁስ እርዳታ ማድረግ ሲጀምር በትምህርት ቤት ደረጃ በተማሪዎች የተጀመረው መረዳጃ ማህበር ‹‹ባዩሽ ኮልፌ የበጎ አድራጎት መረዳጃ እድር›› የሚል መጠሪያ አግኝቶና አቅሙን አሳድጎ ዛሬ በአካባቢው የሚገኙ አቅም ደካማ የማህበረሰብ ክፍሎችን ወደ መርዳት ይሸጋገራል።
ማህበሩ እያከናወናቸው ያሉ የበጎ አድራጎት ሥራዎች በየቦታው ቢስፋፉና በሌሎችም ላይ ቢጋባ ኢትዮጵያዊ የመረዳዳትና የመተጋጋዝ እሴቶቻችንን ያጎለብታል። በመሆኑ በዛሬው የወጣቶች አምድ ዝግጅታችን የማህበሩ አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስልና በተለይም በዘንድሮው ዓመት መሳ ለመሳ እየተጾሙ በሚገኙት የሁዳዴና የረመዳን አጽዋማት ማህበሩ ምን ምን ተግባራት አከናወነ? በጾም መፍቻው እለትስ ምን ሊያደርግ አሰበ? በሚሉትና በሌሎች ዙሪያ ከማህበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወጣት ሄኖክ ፍቃዱ ጋር ቆይታ ልናደረግ ወደናል።
የ‹‹ባዩሽ ኮልፌ የበጎ አድራጎት መረዳጃ እድር በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 የሚገኝ ነው። መረዳጃ ማህበሩ የራሱን ቢሮ ከፍቶ ሰዎችን እያስተባበረና የተለያዩ የገቢ ምንጮችን እየፈጠረ ለተቸገሩ ወገኖችን የሚረዳ ነው። ክፍለ ከተማው የማህበሩን የተቀደሰ ዓላማና መልካም ሥራ በመመልከት የእውቅና ፈቃድና ጊዜያዊ ቢሮ ሰጥቶታል። ይህም የማህበሩን አባላት ለበለጠ ስራ እንዲነሳሱ አድርጓቸዋል። በትምህርት ቤት ደረጃ በውስን ተማሪዎች የተመሰረተው ይህም ማህበር እያደገ መጥቶ የአባላቱ ቁጥር አራት መቶ ደርሶ የነበረ ሲሆን አንዳንዶች በግል ሥራ ምክንያት፣ ሌሎችም ሰፈር በመቀየር፣ የተቀሩትም በተለያዩ ማህበራዊ ምክንያቶች ከአካባቢው ሲርቁ ቁጥራቸው ያሽቆለቁላል። አልፎ አልፎ ደግሞ ወደ ስፍራው የሚመጡ አዳዲስ ሰዎች በአባልነት ይታቀፋሉ። የሆነው ሆኖ በአሁኑ ሰዓት ከማህበሩ ጋር በንቃት የሚሳተፉት ወጣቶች ቁጥር ከ30 እስከ 50 የሚደርስ ነው።
ወጣቶቹ ወደ ማህበረሰቡ ሲገቡ መጀመሪያ እርዳታ ይገባቸዋል የሚሏቸውን ሰዎች ለመለየት የሚያስችል መመዘኛ አውጥተው ነው። አቅመ ደካማና ጠዋሪ የሌላቸው አዛውንቶች፣ አባወራ የሌላቸውና ያለ ምንም ገቢ ቤት ተከራይተው የሚኖሩ እናቶች፣ የጤና ችግር ያለባቸውና በሰው እጅ ላይ የወደቁ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወዘተ በመለየት ነበር። ተረጂዎች በዚህ መልክ ከተለዩ በኋላ ማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍ ወደ ማድረግ ነበር የተሸጋገሩት።
በዚሁ መሰረት በጣት የሚቆጠሩ ሰዎችን ከመርዳት ጀምረው አሁን ላይ ወደ 70 የሚደርሱ አቅመ ደካሞችና አረጋዊያንን በቋሚነት እየረዱ ይገኛል። እንደ ሽሮ፣ በርበሬ፣ ዘይት፣ ሽንኩርት፣ ከሰል የመሳሰሉትን በየወሩ እየገዙ ይሰጣሉ። ከዚሁ ጎን ለጎን ቤታቸው የፈረሰባቸውን ገንዘብና አቅም በማስተባበር ይሠሩላቸዋል። ከዚህም በአጠጋባቸው ምንም አይነት ልጅ የሌላቸውን ተረጂዎችም ፕሮግራም እያወጡ ቤታቸው ድረስ በመሄድ፤ የሻይ ቡና ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ቤተሰባዊ ስሜት እንድያድርባቸው አብረዋቸው ያሳልፋሉ። የታመሙና ቤት የቀሩ የህብረተሰብ ክፍሎችም እንዲታከሙ የማድረግ ሥራዎችን ይሠራሉ። የሰዎቹን አጠቃላይ ሁኔታ ጽፈው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በመልቀቅ ማህበረሰቡ በቀጥታ እንዲረዳቸው የማድረግ ሥራዎችን ይሠራሉ። በዚህም በርካታ ተረጂዎች ጠያቂ እንዲኖራቸው አድርገዋል። የተጠፋፉ ሰዎችንም የማገናኘት ሥራን ይሠራሉ።
የማህበሩ አባላት መጀመሪያ ለተቸገሩ ወገኖቻቸው ይረዱ የነበረው ከኪሳቸው የአቅማቸውን ያህል በማዋጣት ነበር። የተረጂዎቹ ቁጥር ሲጨምር ግን ገቢ ያስገኛል ያሉትን ሥራ በመሥራት ገንዘብ ያሰባስቡ ነበር። በገቢ ማሰባሰብ ዘመቻ ቀን ሁሉም በሥራ ላይ ይሠማራሉ። ግማሹ ጫማ ሲጠርግ ግማሹም እንደ ሶፍትና ማስቲካ የመሳሰሉትን ይሸጣል፤ ሌሎችም ቁልፍ መያዣዎችና እስክሪፕቶዎች ላይ የማህበረሰቡን መሪ ሃሳብ በማስጻፍ፤ እንዲሁም ለገቢ ማሰባሰቢያ የተዘጋጁ ካርዶችን /ኩፖኖችን/ በመሸጥ የገቢ አቅማቸውን እያሳደጉ ለበርካታ ችግረኛ ወገኖች ደርሰዋል። አሁንም ተመሳሳይ ሥራዎችን እየሠሩ ‹‹ለመልካም ሥራ ረፍዶ አያውቅም›› የሚለውን መርሃቸውን በማሳካት ላይ ናቸው።
የሚያደርጉትን በጎ ሥራ በማህበራዊ ሚዲያ የሚከታተሉ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከአውሮፓና ከአረብ አገራት ድጋፍ እያደረጉላቸው ይገኛሉ። ለጋሾቹ እንደ አቅማቸው የአንድ ወይም የሁለት ሶስት ተረጂዎችን የወር ወጪ ይሸፍኑላቸዋል። ከዚህ ውጭ ግን በቋሚነት የሚያገኙት ገቢ አለመኖሩን ወጣት ሄኖክ ይናገራል። ሁልጊዜ የገቢ ማሰባሰቢያ ዘዴዎች እየተጠቀሙ የተረጂዎቻቸው ጓዳ እንዳይጎድል ይጥራሉ።
የማህበሩ ዋና ዓላማ ሰው ለሆነ በሙሉ ፍቅርና እንክብካቤ መስጠት ነው ዘር፣ ሃይማኖት፣ ሴት፣ ወንድ፣ ትንሽ፣ ትልቅ ሳይል እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን የአካባቢውን ነዋሪዎች እንደአቅሙ ይጎበኛቸዋል። የማህበሩ አባላትም የአንድ ብሔር ወይም የአንድ ሃይማኖት ስብስብ ሳይሆኑ ከሁሉም ሃይማኖትና ብሔር የተውጣጡ ናቸው። ባይሽ ኮልፌ በጎ አድራጎት መረዳጃ እድር ከተደራጀ ጀምሮ በየዓመቱ በጾም ወቅት ለአቅመ ደካሞች እንደየሃይማኖታቸው ድጋፍ ያደርጉላቸዋል።
አሁንም የሁዳዴና የረመዳን የጾም ወራት መሆኑን ተከትሎ አቅመ ደካሞችን በልዩ ሁኔታ እየረዳ ይገኛል። በታላቁ የረመዳን ጾም በደረቅ ዳቦ ብቻ በሚያፈጥሩ ምስኪኖች ቤት እየተገኙ አባላት በአፍጥር ሰዓት ምግብ አዘጋጅተው አብረዋቸው ያፈጥራሉ። ‹‹ቢኖረኝ ኖሮ ይህን አደርግ ነበር›› የሚል ስሜት እንዳያድርባቸው የጎደለውን እያሟሉላቸው አብረዋቸው በደስታ ያሳልፋሉ። ለክርስቲያን እምነት ተከታዮችም ተመሳሳይ ሥራ ይሠራሉ። ለምሳሌ መቁረብ የሚፈልጉ ሰዎች ቢኖሩ አስፈላጊውን ነገር አሟልተውላቸው እንደ ቤተሰብ አቅፈው ደግፈው ያስቆርቧቸዋል።
የማህበሩ አባላት ከዚህ በፊት በነበረው ልምዳቸው ለፋሲካ በዓል ዶሮ እየገዙ ይሰጡ ነበር። ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ ለፋሲካ በዓልና ለረመዳን ጾም ፍቺ ባለጸጎችን እያስተባበሩ በሬ አርደው ስጋ ማከፋፈል ጀምረዋል።
ዘንድሮም ይህን ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ሄኖክ ነግሮናል። ለፋሲካ በዓል ሁለት በሬ ለማረድ አስበው አስቀድመው ቃል ያስገቧቸው ሰዎች አሉ። ‹‹ለመልካም ሥራ ረፍዶ አያውቅም›› በሚለው መርሃቸው መሰረት መልካሞችን እያስተባበሩ አቅመ ደካሞችን የመረዳቱን ሂደት ቀጥለዋል። ይህ አድራጎታቸው ታዲያ ማህበራዊ ችግርን ከመቅረፍ ባሻገር በመንደሩ የመረዳዳት ባህል እንዲዳብር ያስቻለ ጥሩ አጋጣሚ ሆኗል። የወጣቶቹ ቅን አስተሳሳብ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ እየሰረጸ በመምጣቱ ሰዎች ያለማንም ቀስቃሽነት የተቸገሩ ወገኖቻቸውን የመርዳት ባህላቸው እያደገ መምጣቱን ሄኖክ ይናገራል።
ለምሳሌ፡- ለፋሲካ በዓል ከሚያርዷቸው ሁለት በሬዎች አንዱን ገዝተው ለመስጠት ቃል ገቡት የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ አንድ ግለሰብ ናቸው። በዓመት በዓሉ እለት በማህበሩ ሥር የታቀፉ ተረጂዎች ዘንቢላቸውን ይዘው እየመጡ ልክ ሌሎች እንደሚደርጉት የቅርጫ ሥጋ ይዘው ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ ይደረጋል። በቦታው መገኘት ለማይችሉ አቅመ ደካሞችም የማህበሩ አባላት በየቤታቸው እንዲያደርሱላቸው ይደረጋል። ያም ብቻ ሳይሆን ቡና በማፍላትና ምግብ በማብሰል ዓመት በዓሉን ከእነርሱ ጋር ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውን ተናግሯል።
የፋሲካ በዓል ለተረጂዎች የወር አስቤዛ ከሚታደልበት ጊዜ ጋር የተገጣጠመ በመሆኑ የበለጠ ፈካ ብለው እንዲውሉ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል። በእለቱ ለሰላሳ ቤተሰቦች ለእያንዳንዳቸው 2ሺህ ብር ለመስጠት ቃል የገቡ ግለሰቦች መኖራቸውም የጎደሉ ነገሮች ሳይኖሩ ከጎረቤት ጋር ተጠራርቶ በዓሉን በደስታ ለማሳለፍ እንደሚያግዝ ሄኖክ ተናግሯል።
በማህበሩ የሚደገፉ ሙስሊም ወገኖች ጾም በሚፈቱ ጊዜም ተመሳሳይ ሥራ ለመሥራት መታቀዱንና ለዚህም ማህበሩ ሰዎችን የማስተባባር ሥራ እየሠራ መሆኑ ተገልጿል። ተረጂዎቹ በወር የሚያገኙት አስቤዛና የሚሰጣቸው ገንዘብም ይኖራል።
ይህ መረዳዳትና መተጋጋዝ ድሮ የነበረ እንጂ ዛሬ የተፈጠረ አይደለም የሚለው ሄኖክ አሁን ፖለቲካዊ አስተሳሰብ የመጣውን መለያየት አሸንፎ ለመውጣት እንዲህ አይነቱን ነባር እሴትን አጥብቆ መያዝ እንደሚገባ የተማርንበት ጥሩ አጋጣሚ ነው ይላል።
ባይሽ ኮልፌ በጎ አድራጎት መረዳጃ እድር ለተቸገሩ ድጋፍ ማድረግን ብቻ ሳይሆን አብሮ መብላት መጠጣትን፤ ደስታና ሀዘን መጋራትን፣ ትእግስትን፣ ፍቅርን፣ ትህትናን፣ መከባበርን በተግባር ይተረጉማል። እንዲህ አይነቱ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴት በየአካባቢው ተጠናክሮ ቢቀጥል ማህበራዊ መስተጋብርን ከማሳለጥና እና አብሮነትን ከማስቀጠል አንጻር ጠቀሜታው ላቅ ነው ይላል ሄኖክ። በሃይማኖትና በባህል እሴቶች የተገነባ ማህረሰብ በጥሩ መሰረት ላይ የቆመ ሰብእና ስለሚኖረው ሰዎችን ይታደጋል እንጂ በሰዎች ላይ የክፋት እጆችን የመዘርጋት ሞራል አይኖረውም ይላል።
‹‹ባይሽ ኮልፌ በጎ አድራጎት መረዳጃ እድር›› ወደፊት ከዚህ በላይ ማህበራዊ አገልግሎት የመስጠት ራዕይ አለው። በተለይም ሠርተው የመለወጥ አቅምና ችሎታ ያላቸው ሰዎች የሥራ እድል ተመቻችቶላቸው ከተረጂነት እንዲወጡ የማድረግ እቅድ ይዟል። ከራሳቸው አልፈው ነገ ሌሎች ሰዎችን የሚረዱና የሚያግዙ፤ ሰብዓዊነት የሚሰማቸው ዜጎችን የማፍራት እቅድ አለው። አሁንም ከጎዳና ሕይወት ወጥተው እራሳቸውን በመቀየር ሌሎችን እየረዱ ያሉ የማህበሩ አባላት አሉ። ሠርቶ የመለወጥ አቅም አላቸው ለተባሉ ተረጂዎች የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ወደ ሥራ የማስገባቱ ሂደት ትኩረት የተሰጠው የማህበሩ አቅጣጫ ነው። በተረፈ ማህበሩ ነገ ትልቅ የመረዳጃ ማህበር ሆኖ እንደመቄዶኒያ በርካታ አረጋውያንና አቅመ ደካሞችን ሰብስቦ የመያዝ ህልም አለው።
ሄኖክ ከፊታችን በተከታታይ የሚከበሩት የጾም ፍቺ በዓላት በደስታና በፍቅር እንዲያልፉ ምኞቱን እየገለጸ ሁሉም በያለበት ቦታ አቅመ ደካሞችን በመርዳት እና ቤት ያፈራውን ነገር በመካፈል ከጎረቤት ጋር ተጋርቶ ማሳለፍ ይገባል ሲል ጥሪ አስተላልፏል።
ወጣትነት የተሻለ አቅምና የተሻለ አስተሳሰብ የሚፈልቅበት የእድሜ ክልል ነው የሚለው ወጣት ሄኖክ፤ ይህ አቅም በጥበብ ከተመራ ተጨባጭ ለውጦችን ማምጣት የሚያስችል ነው ይላል። እርሱና ጓደኞቹ እንደቀልድ የጀመሩትን ቅን ሀሳብ እዚህ ደረጃ ላይ ሊያደርስ የቻለው ሳይታክቱ በመሥራታቸው ብቻ ሳይሆን ይዘው የተነሱት ዓላማ የተቀደሰ በመሆኑና ሰዎች የመልካም ነገር ተባባሪ በመሆናቸውም ጭምር ነው። በመላ አገሪቱ የሚገኙ ወጣቶች አቅማቸውንና ሀሳባቸውን አቀናጅተው ሰዎችን ቢያስተባብሩ ለበርካቶች መድረስ ይቻላቸዋል የሚለው ሄኖክ እንዲህ አይነቱ ተግባር አብሮነትን አስጠብቆ ለመጓዝ ይረዳል ብሏል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14 ቀን 2014 ዓ.ም