በአንድ የሸገር መንደር መብራት ከጠፋ ወደ አንድ ሳምንት ሆነው፤ ልጆች ከትምህርት ቤት መልስ ለማጥናትና የቤት ሥራ ለመሥራት ተቸገሩ። ወላጆች በቀላሉ ምግብ የሚሠሩበትና የሚያበስሉበት አጡ። የበሰሉ ምግቦችን ለመግዛትና አንዳንዴም ወደ ሁዋላ ተመልሰው በከሰልና በእንጨት ማገዶ ለማብሰል ተገደዱ። በእዚህ አይነት ሁኔታ ጉድጉድ ሲሉ ልጆች ደግሞ ምግቡ ቶሎ እንዲደርስ በዙሪያቸው ሲንቀሳቀሱ ክፉ ጊዜ የመጣባቸው መሰለ።
በምሽት አባወራ ዜና ለመስማት ኮረዶችና ጉብሎችም በድራማ በዘፈንና ስፖርት ዘና ለማለት የሚያስቡበት ቴሌቪዥን መብራት ስለሌለ ጥቁር ሰሌዳ መሰለ። እሱም በሻማ፣ በባትሪ፣ በሶላር መብራት ነው የሚታየው።
የቴሌቪዥን ፕሮግራም መጥፋቱ ግራ የገባው ህፃን ልጅ ‹‹ማሚ መብላት ዛሬም አታመጪም?›› ሲል በኮልታፋ አንደበቱ መጠየቁን ሰዎች ሲናገሩ ሰምቻለሁ። ብላቴናው አንደበቱ መብላት ያለው መብራትን ነው።
ይህን ዘገባ ለመጻፍ የተነሳሳሁት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መብራት ጠፍቶባቸው አስር ቀናት የሆናቸው ሰዎች ለዚህ ጋዜጣ ያቀረቡትን ቅሬታ በዜና አንብቤ ነው። የሚገርመው ግን ዜናው ከተዘገበም በኋላ የአገልግሎቱ ሰራተኞች ለተጨማሪ አምስት ቀናት ኤሌክትሪክ ለመቀጠል ሰዎቹን ሲያጉላሉ ነው የሰነበቱት።
ምን ይህ ብቻ። ሰሞኑን በአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሶስት ባለሙያዎች የአንድ ግለሰብን የኤሌክትሪክ መስመር ከቆጣሪው ቆርጠው ሃይል በማቋረጥ መልሶ ለመቀጠል ጉቦ ጠይቀው ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጧል። ወንጀሉ የተፈፀመው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ጨው በረንዳ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን፣ ተበዳይ ነው ለፖሊስ አመልክቶ ብሩን ሲሰጥና ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ ያስያዛቸው። ጎበዝ! እነዚህ ቀበኞች አደብ ለማስገዛት እንዲህ አይነት ብርቱዎች ያስፈልጉናል። ለዚህ ዘገባ መጻፍ ይህም ሌላው ምክንያቴ ነው።
ጉቦ ለመጠየቅ በሚል ሆን ብሎ የኤሌክትሪክ መስመር መቁረጥ ትልቅ ወንጀል ነው። እነዚህ ተጠርጣሪዎች ተያዙ እንጂ ይህን መሰሉ ድርጊት በስፋት እየተፈጸመ ስለመሆኑ ህብረተሰቡ ሲገልጽ ይሰማል።
የኤሌክትሪክ ሀይል ለከተማ ነዋሪዎች መብራት ብቻ አይደለም፤ ራትም ነው። ገቢው የሚገኘው አንድም በመብራት ነው። ዛሬ ዛሬ ደግሞ ወጪ ለማድረግም መብራት ያስፈልጋል። ይህን ሁሉ ታሳቢ በማድረግ አገልግሎቱ ለአፍታም መቋረጥ የሌለበት ቢሆንም፣ በአገራችን ግን ለአፍታ አይደለም ለቀናት ለሳምንት ለሳምንታትም ይጠፋል። የአንድ ቤት መብራት ብቻ ሳይሆን የመንደር መብራት ጭምር ለረጅም ጊዜ ይጠፋል። ይህ ሲሆን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሲበርደውም ሲሞቀውም አይስተዋልም።
አንደ አገር፣ አንደ አካባቢ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ በተፈጠረ ችግር አገልግሎቱ ቢቋረጥ አይደንቅም። በተለያዩ አሳማኝ ምክንያቶች ቢጠፋና መመለስ የሚቻልበት እድሉ እያለ ጉቦ ካልተከፈለ/ በእነሱ አጠራር /የሻይ ካልተባለ/ የማይመለስበት ሁኔታ ግን በእጅጉ ያነጋግራል። አንዳንድ የአገልግሎቱ ሰራተኞች የተቋረጠ የኤሌክትሪክ ሀይል እንዲቀጠል በሃላፊዎቻቸው እየተነገራቸውም ፈጥነው አይፈጽሙም፤ ለእዚህም ጉቦ ይፈልጋሉ። ይህን የተመለከቱ ቅሬታዎችን ከህብረተሰቡም ከመገናኛ ብዙሃንም ነጋ ጠባ በስፋት ማዳመጥ ተለምዷል።
ቆጣሪ ያልቆጠረውን ሂሳብም ክፍሉ ብሎ መጠየቅ፣ የማይከፍሉ ከሆነ መብራቱን እንቆርጠዋለን እያሉ ማስፈራራትም አለ። የባሰ አታምጣ። አንድ እማወራ ልጃቸውን ትምህርት ቤት ከላኩ በኋላ የመንግሥት ሠራተኛ በመሆናቸው ለሥራ ይገባሉ። ጎረቤታቸውም ከባለቤታቸው ጋር ለግል ሥራ ስለሚሄዱ ግቢው ዝግ ይሆናል። ቆጣሪ አንባቢው መጥቶ ግቢው ዝግ መሆኑን አይቶ በመላምት የአገልግሎት ክፍያውን ቆጣሪውን ሳያይ መዝግቦ ይሄዳል። የመብራት የአገልግሎት ሂሳቡ ሲመጣ ሁለቱም በአንድ ቆጣሪ የሚጠቀሙ ተከራዮች 3 ሺህ 800 ብር እንዲከፍሉ ይጠየቃሉ።
እነዚህ ሰዎች የሂሳቡ መብዛት አሳሰባቸው፤ ግራ ገባቸው፤ በየወሩ ከአንድ ሺህ 500 የዘለለ ከፍለው አያውቁም። በቃ እንከፍላለና እንደፈረደብን ምን እናደርጋለን ሲሉ፤ አንደኛው ሄጄ ቆጣሪው ይመርመርልኝ ክፍያው በዛብኝ እላለሁ አሉ። እንዳሉትም ኤሌክትሪክ ኃይል ሄደውም አስረዱ፤ ኃላፊው ቀና ስለነበሩ፤ ጉዳዩን አይተው የቆጠረውን ጠርተው ጠይቀው ሁለተኛ በመላምት እንዳይሠራ ጭምር አስጠንቅቀው ሸኙት። የተገልጋዩ የክፍያ ሂሳብ ሲታይ ግን 1ሺህ 400 ብር ነበር፤ ይህም ተነግሯቸው ከፈሉ።
በዚህ ላይ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ትልቁ ችግር ነው። ይህ አንደ አገር ያለ ችግር ሊሆን ይችላል። አንድ መንደር ከተማ ላይ ሲጠፋ ሌላ ምንም ስለማይባል። ሁኔታው ግን ለኪራይ ሰብሳቢዎቹ ሰርግና ምላሻቸው ነው። የሚፈልጉትን ጉርሻ ለማግኘት ብለው ቶሎ መልቀቅ የሚችሉትን መብራት ያቆዩታል።
ያሉበት ህፀፆች ተዘርዝረው አያልቁም። መብራት ሲቋረጥ 905 በተደጋጋሚ ደውላችሁ ስልኩንም ላያነሱላችሁ፣ አንስተውም ከሆነ ላይመጡላችሁ ይችላሉ። መስሪያ ቤታቸው በአካል ስትሄዱ በቃ ሠራተኛ እንልክላችኋለን የሚለው የተለመደ ምላሻቸው ነው።
ዕድለኛ ሆናችሁ ሠራተኞቹ ከመጡ ደግሞ ብልሽቱን አይተው አንዳንዶቹ መጀመሪያ ‹‹ ቀላል ነው፤ ይሰራል፤ ግን የሻይ የቡና ትሉናላችሁ›› የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። ሌሎች ደግሞ ችግሩ ብዙ ነው ብለው ማስደንገጥ ይጀምራሉ። ይህ ሁሉ የሚሆነው ጉቦ ለመቀበል ነው። ደመወዛቸውን ከመሥሪያ ቤታቸው እየተቀበሉ በተጨማሪ ከተገልጋዩ ክፍያ መጠየቅ የለመዱት ነው።
መብራት ተቋርጦባቸው ወዲያው የሚቀጠልላቸውም እንዳሉም ይሰማል። እነዚህ ደግሞ ጉቦ ሰጥተው የሚያስቀጥሉ ናቸው። ለእዚህም ነው አንዳንዶች መብራት ጠፍቶ አያያዙ አላምር ሲላቸው ገንዘብ እናዋጣ ወደሚለው ፈጥነው የሚገቡት። ጉቦ መክፈላቸው ትክክል አይደለም፤ መመላለሱን፣ ለትራንስፖርት የሚወጣውን፣ መብራት ባለመኖሩ ሳቢያ እቤት ውስጥ የሚጠፋውን ሀብት አስበን ነው ሲሉ የሰማሁዋቸው አሉ። ትክክለኛው መንገድ ግን መብታቸውን ማስከበርና ማጋለጥ ነው።
ይህን የለመዱት የአግልግሎቱ ሰራተኞች ሁሉም ደንበኛ በእዚህ መልኩ የሚከፍላቸው አርገው እስከ መገመት ደርሰዋል። ቀበኞቹ በቀላሉ ሊሰሩ የሚችሉትን ጭምር ከባድ ችግር አርገው በመንገር ገና ለቀናት ሊጠፋ አንደሚችልም በመግለጽ ህብረተሰቡ በጉቦ እንዲያስቀጥል ለማድረግ ግፊት ያሳድራሉ። ይህን ይህን የተመለከቱ ታዲያ አገልግሎቱን የመብራት አገልግሎት ከማለት ይልቅ የ‹‹መብላት አገልግሎት›› እያለ እስከ መጥራት ደርሰዋል ይባላል።
ሕዝብ ለማገልገል የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መሥሪያ ቤት ተገልጋዩን በማጉላላትና ክፍያ በመጠየቅ ሲያንከራትት መስማት ገራሚ ነው። ይህ ችግር ከተቋሙ ጋር ቆይቷል፤ አንድ ሰሞን ችግሩን ለመፍታት እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ሲገልጽ ነበር፤ በአንዳንድ ቦታ በካርድ መብራት የመሙላቱ ሁኔታ ትንሽ ማሻሻል አሳይቷል፤ አሁን የሚሰማው የአገልግሎት ችግር ግን መስሪያ ቤቱ እንዳልተለወጠ ያመለክታል።
በእዚህ ወቅት እነዚህን ቅሬታዎች መስማት የኤሌክትሪክ አገልግሎት አሁንም ኪራይ ሰብሳቢዎች የተሰገሰጉበት መሆኑን ያመለክታል፤ ችግሩ ‹‹ሃይ›› የሚለው በማጣቱም እሮሮውም ቀጥሏል፤ የእነዚህ ቀበኞች ድርጊት የመስሪያ ቤቱን ስም በእጅጉ እያጎደፈው ነው። ቀበኞቹ ድርጅቱን የብልሹ አስተዳደር ተምሳሌት እንዲሆን ማድረጋቸውን ቀጥለውበታል።
የኤሌክትሪክ ሀይል ለአፍታም መቋረጥ በሌለበት አለም ውስጥ ነው ያለነው። የኤሌክትሪክ ሀይል ለብርሃን ብቻ አይደለም የሚፈለገው። በኪሳችን ይዘን ከምንዞረው ሞባይል አንስቶ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ሀይል እስከሚፈልጉት ተቋማት ድረስ ያስፈልጋል። በተገልጋይ ላይ ይህን ያህል አንግልት መፈጸም፣ ጉቦ ለመቀበል ማንገላታት ከአንድ አገልጋይ መስሪያ ቤት አይጠበቅም፤ ህዝብ አንዲማረር ማድረግ ትርጉሙ ብዙ ሊሆን ስለሚችልም መስሪያ ቤቱ በመልካም አስተዳደር ላይ አተኩሮ መስራት አለበት፤ ወቅቱም ይህን ለመስራት ያመቸ ነውና ሊጠቀምበት ይገባል። በጥሩ ስም ሊጠራ ሲገባው ፣‹‹የመብላት አገልግሎት›› አገልግሎት እየተባለ መዘባበቻ መሆን አልነበረበትም። አገልግሎቱ ስሙን ማደስ ይኖርበታል።
ይቤ ከደጃች. ውቤ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12 /2014