እዚህ “ኢንስፔክሽን” የሚለውን ፅንሰ ሀሳብ እንደ ወረደ ነው ሥራ ላይ ውሎ የምናገኘው። ባለሙያዎች ቀጥተኛውን አግኝተው እስኪነግሩን ድረስም እኛ “ከስጋት ነፃ” በሆነ መልኩ ይህንኑ እንጠቀማለን (“ኢንስፔክሽን”ን “ቁጥጥር”፣ “ኢንስፔክተር”ን “ተቆጣጣሪ”፣ “ኦዲተር” የሚሉት/የማይሉት እንዳሉ ሆነው) ማለት ነውና እንቀጥል።
ኢንስፔክሽን በማንኛውም ዘርፍ እስኪባል ድረስ ተፈላጊና አስፈላጊ ፅንሰ ሀሳብ ነው። “የማይገባበት የለም” እስኪባልም ድረስ ጨው ነው። የራሱ የሆኑ “ስታንዳርዶችን እና ማዕቀፎች” አሉት። “የትምህርት ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት” የሚባል ዘርፍና የዘርፉ ሹም ሁሉ አለው። አንዳንዶች ጋ ሀይራርኪው እስከ “ኢንስፔክሽን መምሪያ” ድረስ ይዘልቃል። “የአጠቃላይ ትምህርት ኢንስፔክሽን የሥራ ሂደት ኃላፊዎች”ም አሉት። የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆችም ይሁን ዩኒቨርሲቲዎች ለ”ኢንስፔክሽን” ያላቸው ቦታ በ”ከ – እስከ” የሚወሰን አይደለም። “ሱፐርቪዥን”ም እንደዛው። ችግሩ በአገራችን የእነዚህ ፅንሰ ሀሳቦች ዘለግ የለ እድሜና እየተስተዋለ ያለው የትምህርት ጥራት ማሽቆልቆል አለመጣጣሙ ነው።
ከጥቂት አመታት በፊት “በአገር አቀፍ ደረጃ ሊያሠራ የሚችል፣ ወጥነት ያለውና ለትምህርት ጥራት መሻሻል አስተዋፅኦ ሊያበረክት የሚችል የኢንስፔክሽን ስታንዳርድ ባለመኖሩ በአገሪቱ የሚገኙ የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች የተለያዩ መለኪያዎችን ሲጠቀሙ መቆየታቸው” ችግር እየፈጠረ እንደነበር፤ ይህንንም ለመቅረፍ “ የኢንስፔክሽን ማዕቀፍ” ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የትምህርት ሚኒስቴር (የኢንስፔክሽን ማዕቀፍና ቼክሊስት ለማዘጋጀት ደብረ ዘይት በከተመበት ጊዜ) ገልፆ እንደነበር አይዘነጋም። ይህ የሚነግረን ያለው ቃሉ እንጂ “የኢንስፔክሽን ሥርዓት ለመዘርጋት” የሚያስችለው፤ መተግበሪያው አይደለም ማለት ነው። ጉዳዩን አጥብበን ወደ አዲስ አበባችንም ስናመጣው ያው ነው። ለዚህ ደግሞ ከሚከተለው አንቀፅ በላይ ማሳያ የለም።
“በበጀት አመቱ በስታንዳርድ ኢንስፔክሽን ሞዳሊቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በከተማ አስተዳደሩ ስር በሚገኙ 87 የግል እና የመያድ ኮሌጅ ላይ ስታንዳርድ ኢንስፔክሽን የተሠራ ሲሆን ኮሌጆቹ ከግብአት፣ ከሂደትና ከውጤት አንፃር ያገኙትን ውጤት በዝርዝር በመተንተን ለባለድርሻ አካላትና ለኮሌጆቹ ያሉበትን ደረጃ በሚያሳይ መልኩ በማዘጋጀት በኢንስፔክሽኑ የተገኙትን ጥንካሬዎችና ክፍተቶች እንዲሁም ለክፍተቶቹ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በተገቢው በመለየት የተግባሩን አፈፃፀም ሊያሳይ በሚያስችል መልኩ […]” ማዘጋጀቱን ይነግረናልና “ለመጀመሪያ ጊዜ …”ን ታዝበን፤ የኢንስፔክሽንን ፋይዳ ተገንዝበን ልናልፈው እንገደዳለን። አናታችንን ሲያዞር የኖረውን የትምህርት ጥራት ችግርም ችግሩ ከስረ መሠረቱ ምን እንደሆነ (ቢያንስ በከፊል) እንረዳለንና ለጠቅላላ እውቀትም ቢሆን የዚህ ጽሑፍ አንባቢያንን “በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት፣ የሙያ ብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ባለስልጣን የ2013 በጀት አመት የግልና የመያድ ኮሌጆች የውጭ ኢንስፔክሽን ትንተና ማጠቃለያ ሪፖርት” በሚል ርእስ በባለስልጣኑ የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ማረጋገጥ ዳሬክቶሬት የተዘጋጀውን ሰነድ እንዲመለከቱ እንጋብዛለን። (በነገራችን ላይ፣ በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ ተቋማት አማካኝነት ለውይይት የሚቀርቡ ሰነዶች ብዙዎቹን አሠራሮች “ለመጀመሪያ ጊዜ …” ሲሉ ነው የሚነበቡት። እውነት ከሆነ መሀል ላይ ኢትዮጵያ አርጋ፤ ወይም ሱባኤ ገብታ ነበር ማለት ነው።
እዚህ ላይ ግን፣ ከዚሁ ሰነድ ርቀን ሳንሄድ ሰነዱ ስለ “ኢንስፔክሽን” አላማ፣ ወሰንና ፋይዳ በ”ፓወርፖይንት” ያስቀመጠውን እንመልከት።
የኢንስፔክሽን ግኝት ትንተና አላማ “ኮሌጆች የሚጠበቅባቸውን ተፈላጊ የት/ስልጠና የጥራት የአፈጻጸም ደረጃ ማሟላታቸውን ለማረጋገጥና ኮሌጆቹና ባለድርሻ አካላቶች በግኝቶቹ ላይ የበኩላቸውን አወንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ለማስቻል እና በየደረጃው የተጠያቂነት ሥርዓትን ለማስፈን”፤ የትንተናው ወሰን “ይህ የስታንዳርድ ኢንስፔክሽን ትንተና ሰነድ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚገኙ ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 4 የሚያሰለጥኑ የግልና መንግሥታዊ ያልሆኑ (መያድ) ኮሌጆች ላይ ያተኮረ ይሆናል፡፡” እንዲሁም ኢንስፔክሽኑ ለቴ/ሙያ ት/ስልጠና ጥራት ያለው ፋይዳን “በከተማ አስተዳደሩ ስር በሚገኙ የቴ/ሙያ ት/ስልጠና ኮሌጆችን በ2013 ዓ.ም ከስታንዳርድ ኢንስፔክሽን አገልግሎት አንፃር ያሉበትን ደረጃ ለማሳወቅ” በማለት ያሰፍረዋል። የኢንስፔክሽን አላማ፣ ወሰንና ፋይዳ እነዚህ ሲሆኑ፤ “ኢንስፔክሽን” የትኩረት መስኮችም አሉት፤ መለኪያዎችም እንደዛው።
ከላይ የጠቀስነው ሰነድ “የኢንስፔክሽን የትኩረት መስኮች” መለኪያዎችንም ግብአት፣ ሂደትና ውጤት መሆናቸውን ከገለፀ በኋላ እያንዳንዳቸው የየራሳቸው የትኩረት መስኮች እንዳሏቸውም አስቀምጧል። (1 እና 2 በግብዓት /Input/ አቅጣጫ፤ 3 እና 4 በሂደት /Process/ አቅጣጫ፤ እንዲሁም 5 በውጤት /Outcome/ ትይዩ መቀመጣቸውን ከወዲሁ ማስታወስ ያስፈልጋል።)
የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና የተቋሙና የኮሌጁ ሕንፃዎች (Training Facilities)፣ የሰው ኃይልና የፋይናንስ አቅም (የትኩረት መስክ 1)፤ የጥራት ማሻሻያ ለውጥ ትግበራ እና ምቹ የስልጠና አካባቢ (የትኩረት መስክ 2)፤ የውጤት ተኮር አሰለጣጠን ሂደት (የትኩረት መስክ 3)፤ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ማሰልጠኛ ተቋሙ/ ኮሌጁ ከባለድርሻ አካላትና ከማህበረሰብ አገልግሎት ጋር ያለው ግንኙነት (የትኩረት መስክ 4)፤ ብቁ፣ ተወዳዳሪና ሥራ ፈጣሪ ባለሙያ ማፍራት የሚችል ጥራቱ የተረጋገጠ ተቋም/ ኮሌጅ መፍጠር (የትኩረት መስክ 5)።
በማጠቃለያው ቀዳሚ መስመር ላይ “ኢንስፔክሽን የተቋማትን/የኮሌጆችን ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት ጠንካራ ጎኖችን በበለጠ ለማጠናከር፣ ክፍተቶችን ለማረም ወይም ለማስተካከል ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡” የሚለው ይህ ሰነድ ከላይ ያልነውን ብቻ አይደለም የሚለው፤ የኢንስፔክሽንን ወሳኝ ሚናንና የሕግ ማእቀፍ የተበጀለት መሆኑንም “በኢንስፔክሽን መመሪያ ቁጥር 03/2012 ዓ.ም ገፅ 18 ተራ ቁጥር 16 ንዑስ ቁጥር 3 ላይ በተቀመጠው መሠረት አንድ ኮሌጅ ደረጃ 1 ሆኖ ከ40% በታች ውጤት ካገኘ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚዘጋ በማስቀመጡ ዳሎል ቢዝነስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ እና ባዮስ ቢዝነስ ኮሌጅ ደረጃቸው ከ40% በታች በመሆኑ በቀጥታ እንዲዘጉና ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረግ ይኖርበታል።” ሲል ከነ ውጤቱ ያስቀምጣል። ከዚህ የምንረዳው ለተቋማት ዋናው ህልውናቸው የኢንስፔክሽንን ፈተና ማለፍ ወይም አለማለፍ መሆኑን ሲሆን፤ ጥያቄው በየ ጥጋ ጥጉ፣ ጋራ ሸንተረሩ፣ ወንዝና ተራራው … ያሉት እነ እንቶኔ ከዚሁ ከኢንስፔክሽን አኳያ ፈተናውን አልፈው ነው ወይስ ታልፈው ህልውናቸው እዚህ ድረስ ሊዘልቅ የቻለው የሚለው ሲሆን፤ መልሱን ሳይሆን አስተያየቱን ለባለሙያ ትተነው እናልፋለን። (“እውነት እዚህ አገር ኢንስፔክሽን ቢኖር ኖሮ ተቋማት በአደባባይ የዲግሪ መቸብቸቢያ ገበያቸው እንዲህ ይደራ ነበርን?” በማለት የሚጠይቁ አስተያየት ሰጪዎችን አስተያየት እዚህ አላካተትንም እንጂ፤ ብናካትትማ …)
ይህንን ሀሳብ እዚህ ልናነሳ የቻልነው በዚሁ ሰነድ (ፓወርፖይንት 18) ላይ “[…] 3 ኮሌጆች ከ80% በላይ ውጤት በማግኘት የጥራት ስታንዳርዱን ያሟሉ በመሆናቸው ተሞክሮዎቻቸውን የሚያሰፉበትንና በላቀ ደረጃ ስታንዳርዱን እንዲያሟሉ የሚደገፉበትን አቅጣጫ ልንከተል ይገባል፡፡” የሚል በመኖሩ ሲሆን፤ “3 ኮሌጆች” ብቻ ለሚለው አፅንኦት በመስጠት ነው። “የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል” ይባላል። የትምህርት ነገርስ? ያወያያል፤ ያነጋግራል፤ ያመራምራል።
ትምህርትን ከማስፋፋት ጎን ለጎን ጥራቱን ለማረጋገጥ የሚረዳ ስሌቶችን በመንደፍ በትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማሩ አጋዥ የሆኑትን የትምህርት ግብዓት፣ ሂደትና ውጤት በማሻሻል የተማሪዎችን እውቀት፣ ክሂሎትና አመለካከት ለማጎልበት በ1999 ዓ.ም የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ፓኬጅ ተቀርፆ በሁሉም የአገራችን ክልሎች በመተግበር ላይ ነው፡፡ ፓኬጁ የመምህራን ልማት፤ የሥርዓተ ትምህርት፣ መጻሕፍትና ምዘና፤ የትምህርት ቤት መሻሻል፣ የትምህርት አመራርና አስተዳደር፤ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ እንዲሁም የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር መርሀ ግብሮችን አካቷል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የመርሀ ግብሮቹን አፈጻጸም ለመገምገም የሚያስችል የኢንስፔክሽን ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኗል፡፡
ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት በትምህርት ቤቶች የሚካሄድ ተከታታይ ኢንስፔክሽን የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻልና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡ የኢንስፔክሽን የግምገማ ውጤት የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ፓኬጅ በተለይም ደግሞ የትምህርት ቤት ማሻሻያ መርሀ ግብር አተገባበርን በተመለከተ መረጃ የሚሰጥ ሲሆን በዚህም ትምህርት ቤቶች ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫ መሆን ያለባቸውን ለመለየት እንዲረዳቸው የሚያካሂዱት ግለ-ግምገማ ተገቢውን ሂደት የተከተለ መሆኑን ለመፈተሽና የማሻሻያ ሃሳቦችን ለመጠቆም የበኩሉን ድርሻ ያበረክታል፡፡
የኢትዮጵያን ትምህርት፣ ትምህርት ፖሊሲና አጠቃላይ ሥርዓተ ትምህርቱን በተመለከተ በየጊዜው የተለያዩ መረጃዎችን የምናገኝ ሲሆን፤ አንዱም በ2016 የወጣውና “ዓለም ባንክ በዲሴበር 7/2012 በ221 ገጽ በዘጠኝ ምዕራፍ በሰጡት መግለጫ አንኳር ነገሮችን አንስተዋል። እነዚህም አንኳር ጉዳዮችን በሰፊው በማተት የችግሩን አሳሳቢነት በማጉላት መንግሥት በአስቸኳይ እርምት መውሰድ እንዳለበት በአንክሮ ያስጠነቀቀ ሲሆን ችግሩንም በአፈጣኝ መግታት ካልተቻለ በአገርና በሕዝብ ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ችግር በግምገማው አስቀምጧል።” የሚለው ነው። ከላይ እንደተመለከትነው ከሆነ ይህንን የሚያክል ችግር ከመፍታት አኳያ፣ ምንም እንኳን ብቸኛው ባይሆንም፣ ኢንስፔክሽን የመሪነት ሚናውን ይጫወታል ማለት ነው።
ሁላችንም እንደምናውቀው፣ በአገራችን ትምህርትን የተመለከቱ አደረጃጀቶች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። “አዳዲስ የትምህርት አደረጃጀቶች” በሚል ሁሌም ሲጣልና ሲነሳ፤ የዛሬው ለነገ ሳይሆን ሲቀርና ለሌላ አዲስ ቦታውን ሲለቅ ነው ስናይና ስንሰማ የኖርነው። ኮማንድ ፖስት፤ አንድ ለአምስት፤ BPR (መሠረታዊ የሥራ ሂደት)፤ የመምህራን ውጤት ተኮር፤ የልማት ሰራዊት፤ ተሀድሶ፤ የለውጥ ሰራዊት፤ ተማሪን ያማከለ የመማረ-ማስተማር ሂደት፤ ሪፎርሜሽን (Reformation) … እና የመሳሰሉ አደረጃጀቶች አየሩን ቢናኙበትም የሚፈለገው ጋ ደርሰው ውጤትን ሊያስገኙ ግን አልተቻላቸውም። ለምን? ከተባሉት፣ ከተነገሩትና ከተደረጉ ጥናቶች የምንረዳው አቢይ ጉዳይ ቢኖር እነዚህ ሁሉ አደረጃጀቶች በበቂ የኢንስፔክሽን ተግባርና ባለሙያው ካልተደገፉ ምንም ዓይነት ውጤት ሊያመጡ አለመቻላቸውን ነው።
ጉዳዩ ምን ላይ እንዳለ፣ የት እንደ ደረሰ ባይታወቅም “የትምህርት ጥራት ችግርን ለመፍታት “የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ምክር ቤት” ማቋቋም አስገዳጅ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። ምክር ቤቱ በአገሪቱ የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራትን ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲያረጋግጡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ምሩቃንን ለማፍራት ፋይዳ የሚኖረው ገለልተኛ ምክር ቤት መሆኑ ተነግሯል። በሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በተዘጋጀው የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ምክር ቤት ምስረታ ላይ . . .” የሚል ዜና ይኸው ጋዜጣ በአንድ ወቅት ማስነበቡ ይታወሳል። ጥራት ጉዳይ እዚህ ድረስ አሳሳቢ ሆኗል ለማለት ነው።
በአጠቃላይ፣ በሌላ ዝግጅት በዚሁ በኢንስፔክሽን ጉዳይ ላይ ከባለሙያ ጋር ቆይታ የምናደርግ መሆናችን እንዳለ ሆኖ፤ ከላይ ከቀረበው መረጃ መረዳት እንደሚቻለው ለአንድ ተቋም ውጤታማነት የኢንስፔክሽን (በተለይ የውጪ) ሥራ ድርሻው በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በመሆኑ ከተነሳንበት አኳያ ጉዳዩን ከትምህርት አንፃር ተመለከትነው እንጂ በሁሉም ተቋም ተግባራዊ ሊደረግ የሚገባው መሆኑን መረዳት ይቻላል። በተለይ፣ በተለይም በትምህርቱ ዘርፍና ትውልድ ላይ እየደረሰ ካለው አደጋ (ብዙዎች “የትምህርት ጥራት ኪሳራ” ይሉታል) አኳያ ኢንስፔክሽንን ጨምሮ በርካታ ሥራዎች ሊሠሩ ይገባል እንላለን። “አዲስ አበባን በትምህርት ጥራት አርአያ የማድረግ እንቅስቃሴ” በሚልና ሌሎች ጽሑፎቻችን ለመግለፅ እንደ ሞከርነው ሁሉ በያዝነው አመት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየሠራ ያለው ተግባር የሚበረታታ ሲሆን፤ ሌሎችም የእሱን አርአያነት በመከተል የትምህርቱን ዘርፍ በፍጥነት ሊታደጉት ይገባል። ለዚህ ደግሞ ዓይነተኛው መሣሪያ ኢንስፔክሽን ነውና “ቺርስ ኢንስፔክሽን!!!” እንላለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10 /2014