ዘመነ መሳፍንት በብዙ አጋጣሚዎች ይጠቀሳል፡፡ የየአካባቢው የጎበዝ አለቆች የበዙበትና አገር የተበታተነችበት ዘመን ነበር፡፡ ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ በኢትዮጵያ ታሪክ ስማቸው ደምቆ የታየው ያቺን የተበታተነች ኢትዮጵያ አንድ በማድረጋቸው ነው፡፡ ዘመነ መሳፍንትን አንኮታኩተው ኢትዮጵያን አንድ አደረጉ፡፡
እኚህ ጀግና በዚህ ሳምንት ይታወሳሉ፡፡ ለኢትዮጵያ አንድነትና ዘመናዊነት ቆራጥ አቋምና ወኔ የነበራቸው ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ የፋሲካ ማግሥት መቅደላ አምባ ላይ ከእንግሊዞች ጋር ውጊያ ገጥመው ድሉ የእንግሊዞች ሲሆንና እጃቸውን እንዲሰጡ ሲጠየቁ አሻፈረኝ ብለው ራሳቸውን የሰውት በዚህ ሳምንት ሚያዚያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም መሆኑም ዛሬ በሳምንቱ በታሪኩ አምዳችን እንድናስታውሳቸው አድርጎናል፡፡
የአፄ ቴዎድሮስ ሠራዊት እና በሎርድ ኔፒዬር የተመራው የእንግሊዝ ሠራዊት ጦርነት ገጥመው ድሉ የእንግሊዞች ሲሆን፣ አፄ ቴዎድሮስ በእንግሊዞች እጅ ከመውደቅ ራሳቸውን ማጥፋትን መርጠው ሽጉጣቸውን ጠጥተው ሞቱ፡፡ ቀብራቸውም በመቅደላ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተፈጸመ፡፡ እኛም የዚህን ጀግና ታሪክና ሥራዎች እናስታውሳለን፡፡
ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ የጀግና ምሳሌ፣ የቆራጥነትና ወኔ ማሳያ ናቸው፡፡ ስለጀግንነትና ቆራጥነት ሲነሳ በአጼ ቴዎድሮስ ይመሰላል፡፡
የታሪክ ባለሙያዎችና ምሁራን የሚሉት አንድ ነገር አለ። አጼ ቴዎድሮስ የጦር ጀግና ብቻ አልነበሩም። ዘመናዊነትንና ሥልጣኔን የሚመኙ ባለራዕይ ነበሩ፡፡ ለዚህም የደበረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ጋፋት ኢንዱስትሪ በሚል የቴክኖሎጂ ንቅናቄ ጀምሯል፡፡ በየጊዜው ውይይቶችንም ያዘጋጃል። ዩኒቨርሲቲው ባዘጋጀው አንድ የውይይት መድረክ ላይ ተሳታፊ ነበርኩ፡፡ ብዙ ምሁራን ሲያነሱ የሰማሁትም አጼ ቴዎድሮስ የቴክኖሎጂ ራዕይ የነበራቸው መሆኑን ነው፡፡ ንባብና ሥልጣኔን ያስተዋውቁ ነበር፡፡ አብዛኛው ታሪካቸው ግን የሚታወቀው ከጦር ጀግንነት ጋር የተያያዘው ነው፡፡
ስለ አጼ ቴዎድሮስ የታሪክ ጸሐፊዎችና ተመራማሪዎች በተለያየ ጊዜ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ እነዚህ የታሪክ ጸሐፊዎች የአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆኑ የውጭ አገራት ጸሐፊዎች ጭምር ናቸው፡፡ ጥቂቶችን መጠቃቀስ እንችላለን።
ፕሮፌሰር ዶናልድ ክራሚ
‹‹ቴዎድሮስ የዘመናዊ ሥልጣኔ ሐሳብ የገባው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ንጉሥ ነበር።»
ቫልድማየር፡
‹‹ቴዎድሮስ፣ ኃይልና ታላቅነት ሳያንሰው፣ የምቾትና የቅምጥል ኑሮ የማያታልለው እንዲህ ያለ ንጉሥ ከቶ የት ይገኛል? የሁላችንም እምነት እግዚአብሔር ኃይሉን የለገሠው የሕዝቡንም ቁሣዊና መንፈሣዊ ደኅንነት ለማረጋገጥ የታጨ መሣሪያ መሆኑ ነው።»
በፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የታሪክ መጽሐፍ ላይ እንደሰፈረው፤ መረጃ ቴዎድሮስ ለአገራቸው ዕውቀት መስፋፋት የነበራቸውን ጉጉት ለንግሥት ቪክቶሪያ በጻፉት ደብዳቤ፡-
(1) ጥር 1858፣«የኢትዮጵያ ሰዎች ድንቁርነታችን ዕውርነታችን ሳይሰሙት አይቀርም።»
(2) መጋቢት 1858፣ « አሁንም እኔ የምፈልገው ዕውር ነኝና ዓይኔ እንዲበራ ጥበብ ነው።»
(3) ሚያዝያ 1858፣ « የኢትዮጵያ ሰዎች ዕውር ነኝ፤ ዓይናችንን ያበሩልን ፤ እግዚአብሔር በሰማይ ያብራለዎ!»
(4) ሚያዝያ 1859፣ «ከብት አለመፈለጌ ክብር ሆኜ አይደለም፤ ዕውር አህያ ነኝና ለጥበብ ዓይኔን ትከፍቱልኝ ብየ ነው እንጂ፣ በእግዚአብሔር ኃይል፤» ብለዋል፡፡
ከእነዚህ ደብዳቤዎች አንድ ነገር እንረዳለን፡፡ ይኸውም አጼ ቴዎድሮስ ለእውቀት ሽግግር የነበራቸውን ከፍተኛ ፍላጎት። ለአገሪቱ ዘመናዊነት ያደረጉት ጥረት እዚህ ላይ ግልጽ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለእርሳቸው የተጻፉ አንዳንድ መጻሕፍት እንዳሰፈሩትም አጼ ቴዎድሮስ ከራሳቸው በላይ ለሌላው ያስባሉ፡፡ የግል ሕይወታቸው አያሳስባቸውም። ከአገር ውስጥ የታሪክ ጸሐፊዎችም ተክለጻድቅ መኩሪያ ‹‹ ቴዎድሮስ፣ ሞትን የናቁ፣ ድሎትን የራቁ» ናቸው ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ታስረው ከነበሩት እንግሊዛውያን ውስጥ አንዱ የነበረው ዶክተር ሔንሪ ብላንክ ስለአፄ ቴዎድሮስ ‹‹ለመጀመሪያ ጊዜ በ1852 ዓ.ም አፄ ቴዎድሮስን ሳገኛቸው ዕድሜያቸው 48 ይሆን ነበር! በሰላም ጊዜ ለስላሳ ሆነው ደስ የሚያሰኙ በተቆጡ ጊዜ ደግሞ በርበሬ መስለው
የሚያስደነግጡና የሚያሸብሩ እሳተ ገሞራ የሚወረውሩ ነበሩ! በድንገት ሲቆጡ መላ አካላቸው የሰውን ልጅ ከፍ ካለ ድንጋጤ ላይ ይጥላል! ጠይሙ ገላቸው ሲኮሰኩስ ..ስሱ ከንፈራቸው ሲንቀሳቀስና ፀጉራቸው ሲዘናፈል በጠቅላላ ሰውነታቸው የአንበሳነት ፀባይ የያዘ አስደንጋጭ ይሆናል!›› ብሏል፡፡
አፄ ቴዎድሮስ የንግሥና ስያሜ ያቸው ቴዎድሮስ እንዲሆን የመረጡት ‹‹ቴዎድሮስ የሚባል ንጉሥ ሲነግስ ኢትዮጵያን እስከ ባህር ያሰፋታል፤ ፍርድና አስተዳደርንም ያስተካክላል›› የሚባል ትንቢት ስለነበር ሕዝቡ ‹‹ይህ ትንቢት የእርስዎ ነው›› እያሉ አሞካሿቸው። ‹‹ስሜን ቴዎድሮስ በሉ›› ብለው እንዳወጁ ታሪካቸውን ጽፎ በ1985 ያሳተመው ደራሲ ጳውሎስ ኞኞ ይነግረናል፡፡
ጳውሎስ ‹‹ቴዎድሮስ እንዴት ያሉ ሰው ነበሩ?›› የሚለውን ጥያቄ በመፅሐፉ አንስቶ ‹‹ሁሉንም ፀባይ አሟልተው የያዙ ሰው ነበሩ። ይህም ማለት ደግ ናቸው፣ ክፉም ናቸው፣ ሩህሩህ ናቸው፣ ጨካኝም ናቸው፣ ፍርድ አዋቂ ናቸው፣ ፍርድ ገምድልም ናቸው›› ሲል ማስረጃ እያጣቀሰ ይገልፃ ቸዋል።
እስኪ የአፄ ቴዎድሮስን ፍርዶች እንመለከትና በዘመኑ የነበረውን የፍትህ ስርዓት በመጠኑ እንቃኝ። አጼ ቴዎድሮስ በሰጧቸው ፍርዶች መነሻነትም በትንቢት ተነግሮላቸዋል። እንደተባለው ፍርድና አስተዳደርን በማስተካከል ረገድ ምን ያህል ተሳክቶላቸው ነበር የሚለውን የራሳችንን ግንዛቤ እንይዛለን። ፍርዶቹ አንዳንዶቹ አስገራሚ፣ አንዳንዶቹ አሳዛኝና አስደንጋጭ አንዳንዶቹም አስተማሪ ናቸው።
የጋይንቱ ችሎት
አፄ ቴዎድሮስ ጎንደር ጋይንት ላይ ሰፍረው ሰለ ወታደሮቻቸው በአርሶ አደሩ ላይ ‹‹ተሰሪ›› አገቡአቸው። ተሰሪ ማግባት ማለት አርሶ አደሩ ወታደሮቹን እንዲቀልብ በየቤቱ መመደብ ማለት ነው። በወቅቱ የተደራጀ ጦር ሰራዊትና ለጦር ሰራዊቱ የሚመደብ የመንግሥት ባጀት ስላልነበር የነገስታቱ ጦር በየደረሰበት ያለው ሕዝብ እንዲቀልበው ይታዘዝ ነበር። ከእነኚህ የጋይንት እና የአካባቢው አርሶ አደር እንዲቀልባቸው ከታዘዘላቸው የቴዎድሮስ ወታደሮች መሀል አንዱ ወታደር አንዱን አርሶ አደር ገደለው። የሟች ዘመዶች ለአፄ ቴዎድሮስ አመለከቱ። አፄውም ወታደሮቻቸውን አፈርሳታ አስቀምጠው ገዳዩን እንዲጠቁሙ አዘዙ። ሆኖም ወታደሮቹ በሙሉ በአንድ ላይ አድመው ገዳዩን አናውቅም ብለው በቄስ እየተገዘቱ ስለወጡ ገዳዩ ሊታወቅ አልቻለም።
ቴዎድሮስ ገዳዩን ወታደር ለማወቅ የተደረገው ሙከራ ባለመሳካቱ ተናደው ‹‹ወታደር ብላ! ባላገር አብላ! ያልኩ እኔ
ነኝ። ደመኛህም እኔ ነኝና እኔን ግደል›› ብለው ተነስተው ለከሳሽ ነገሩት። ከሳሽም ምኑ ሞኝ ‹‹እኔ ንጉስ መግደል አይቻለኝም›› አለ። ቴዎድሮስ እንግዲያውስ ደም በከንቱ ፈሶ አይቀርም ብለው ለሟች ወገኖች የደም ካሳ ገንዘብ ከፍለው አሰናበቷቸው።
የንጉሱ ትዕዛዝ
ቴዎድሮስ ለአንድ ታማኝ ወታደራቸው ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላልፈው ‹‹በፈርቃ በር በኩል እርጉዝ ሴት እንኳን ብትሆን እንዳታልፍ ጠንክረህ ጠብቅ›› አሉት።
ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ ሌላውን ወታደራቸውን ጠርተው ‹‹ፈረስ እያለዋወጥክ ይህን ወረቀት የጁ አድርሰህ በስድስት ቀን ውስጥ በአስቸኳይ ተመለስ›› ብለው አዘዙ። መልክተኛው ወታደር መልዕክቱን ለማድረስ ፈርቃ በር በሚባለው ቦታ ማለፍ ግድ ሆነበት። ፈረሱን እየጋለበ ፈርቃ በር ደረሰ። አስቀድሞ ማንንም እንዳያሳልፍ የታዘዘው የፈርቃ በር ዘበኛም የንጉሱን መልዕክት እንዳያልፍ ከለከለው።
መልዕክተኛው ‹‹ከንጉሡ በስድስት ቀን የጁ ደርሼ እንድመለስ በአስቸኳይ ተልኬ ነው ልለፍ›› አለው።
የፈርቃ በር ጠባቂም ‹‹ከንጉሥ ከተላከ አትከልክሉት ይለፍ የሚል በማህተም የተደገፈ የይለፍ ደብዳቤ ካለህ አሳየኝ እና አሳልፍሃለሁ ካልሆነ ግን እኔም የንጉሥ ትዕዛዝ ስላለብኝ አታልፈም›› ሲል መለሰለት።
መልዕክተኛው ወታደርም የንጉሥ ትዕዛዝ ሆኖበት በግድ አልፋለሁ ብሎ መንገድ ሲጀምር ጠባቂው ወታደር በጥይት ተኩሶ ገደለው።
የሟቹ መልዕክተኛ ወገኖችም ጉዳዩን ከሰሱና ለፍርድ አፄ ቴዎድሮስ ዘንድ ቀረቡ። በችሎት የተቀመጡት ፈራጆች ሁሉ ገዳይ ላይ ፈረዱ ‹‹እምቢ አልፋለሁ ቢልህ ለንጉሥ ማመልከት ሲኖርብህ እንዴት የንጉሥ መልዕክተኛ ትገላለህ! ለጥፋትህ ሞት ይገባሃል›› ሲሉ ፈረዱበት።
አንድ አስተዋይ ፈራጅ ከተቀመጡበት ተነስተው ‹‹መታየት የሚገባው ከንጉሡ የተሰጠው ትዕዛዝ ነው። ንጉሡ የፈርቃ በር ጠባቂን ጠርተው ያለኔ ፈቃድ እርጉዝ ሴት እንኳን እንዳታልፍ ብለው አዘዙ። መልዕክተኛውን ደግሞ በአስቸኳይ የጁ ደርሶ እንዲመጣ በማዘዛቸው በዚያ በፈርቃ በር በኩል ማለፍ ነበረበት። ስለዚህ ጥፋቱ የሚመለከተው ንጉሠ ነገስቱን ነው። ነገር ግን ብርሃን ናቸውና ምን ይደረግ›› ብለው ተቀመጡ።
እዚህ ጋር እንግዲህ በዚያ ዘመን የነበረውን ንጉሥ የሚያስተች ዲሞክራሲ ሳናደንቅ አናልፍም። የአስተዋዩ ፈራጅ ንግግር ብቻ ሳይሆን የንጉሡም ምላሽ የሚደንቅ ነው።
አፄው ምን አሉ መሰላችሁ! ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው ‹‹እንዲህ ነው መሸምገል፣ ሁለት ፀጉር ማብቀል›› ብለው የአስተዋዩን ፈራጅ ፍርድ ካደነቁ በኋላ ‹‹በደለኛው እኔ ነኝ ፍረዱብኝ›› ብለው በተከሳሹ ወታደር ቦታ ወርደው ቆሙ። ከዛም ፈራጆች በሰጡት ፍርድ መሰረት ለሟች ወገኖች 500 ብር የደም ካሳ እንዲከፍሉ አፄ ቴዎድሮስ ላይ ፈረዱና ጉዳዩ በዚህ ተቋጨ።
የአጼ ቴዎድሮስ ነገር ጳውሎስ ኞኞ እንዳለው ነው፡፡ ደግ ናቸው፣ ክፉም ናቸው፣ ሩህሩህ ናቸው፣ ጨካኝም ናቸው፡፡ ከወኔ እና ጀግንነታቸው በተጨማሪ ለሥልጣኔና ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ጥረት ያላቸው ባለራዕይ ነበሩ፡፡ እኚህን ጀግና እነሆ ታሪክ ሲያወድሳቸው ይኖራል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9/2014