ብዙዎች ርቆ የተሰቀለን ተስፋ፣ ተደብቆ በተቀመጠ ዳቦ ይመስሉታል። በእነሱ እምነት የተደበቀውም ሆነ፣ የተሰቀለው ጉዳይ በጊዜው ከጥቅም ካልዋለ ፋይዳ ቢስ ይሆናል። እውነታውን እንመርምር፣ እንየው ካልን ደግሞ የእነሱ እሳቤ ከአንድ ጥግ ሊያደርስን ግድ ይላል። አዎ! የተሰቀለውም ይሁን፣ የተደበቀው ነገር ጊዜውን ጠብቆ ከታሰበው ካልዋለ ውጤቱ እነሱ እንዳሉት ፋይዳ ቢስ ይሆናል።
መነሻችንን ሳንዘነጋው ርዕሳችንን ርቆ ከተሰቀለው ተስፋ ላይ እናድርግ። ወደሰሞንኛው ኢኮኖሚያዊ ጉዳያችን። ማጋነን አይሁንብኝና፤ ዛሬ አብዛኛው ብቻውን እያወራ የሚሄድበት እውነት የኑሮ ጫናውና የመጪው ጊዜ ስጋቱ ነው ለማለት ያስደፍራል። እንዲህ ኑሮ ሽቅብ ወጥቶ ሕይወት ቁልቁል ሊደፋ በቀረበበት አፍታ ይህን ማሰቡ ላያስገርም፣ ላያስደንቅ ይችላል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በየጊዜው ጣራ የሚነካው የሸቀጦች ዋጋ ‹‹ባለህበት ቁም›› የሚለው እንኳን ጠፍቶ የዋጋው መጠን ከተሰቀለበት መውረድ ቀርቶ ባለበት መርጋት ሲያቅተው ማየታችን ቀጥሏል። ይሁን እንጂ ሁሌም እንደሚሆነው ልማድ ዛሬም ሽቅብ የተሰቀለውን ወቅታዊ የዋጋ ንረት ከነበረበት ለማውረድ የሚተጋ ወሳኝ አካል አልተገኘም። ዛሬም አዲስ ችግር፣ አሁንም የኑሮ ውድነት፣ ሁሌም ሀሳብና ብሶት ልማዳችን ሆኗል።
እውነት፣ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ኅብረተሰቡ በየጊዜው ለሚቀልዱበት ሕገወጦች ብርቱ ክንድ መፍጠር አልተቻለውም። ዛሬም እንደትናንቱ የሚጠየቀውን እየከፈለ፣ የተሰጠውን እየተቀበለ በኑሮ ጫና መንገዳገዱን ቀጥሏል። ለመኖር መብላትን፣ አቅምን የመጠነ ገቢና ወጪን ይጠይቃል። ሆኖም ኑሮ እጅግ ፈታኝ በሆነበት ጫንቃ ሰፊው ኅብረተሰብ ከገቢው ያልተመጠነ፣ ከአቅሙ ያልተናበበ ሕይወትን ሊመራ ተገዷል። የዳቦ ሲሉት የዘይት፣ የእህል ዋጋ ሲባል የቤት ኪራይ፣ የትምህርትቤት፣ የትራንስፖርት፣ የየዕለት ሸቀጦችና ሌሎችም ፍጆታዎች ሁሌም ሊያልፋቸውና እንደዋዛ ሊተዋቸው የማይቻለው ግዴታዎች ናቸው።
ማንኛውም ሰው ለኑሮው የሚያሻውን ፍላጎት አቅሙ በፈቀደው መጠን የማሟላቱ እውነት የተለመደና የነበረ ሂደት ነው። በሕይወት ጉዞ ማንም ሰብአዊ ፍጡር ለራሱና ለቤተሰቡ የሚበጀውን ማድረግና ማሟላቱ አዲስ ሆኖ አያውቅም። እንዲህ ሲሆን ግን በአቅሙ የሚሸከመውን፣ በፍላጎቱም የሚችለውን እየለካ መሆን ይኖርበታል። አሁን ላይ እየሆነ ያለው ግን ከዚህ በተለየ ነው።
ዛሬ ተጠቃሚው የምኞቱን ቀርቶ የፍላጎቱን እያገኘ አይደለም። ለዕለት ጉርሱ ‹‹ሞላሁ፣አሟላሁ›› ሲል የቤት ኪራዩ ሸክም ይሆነዋል። እሱን ተወጣሁት ባለ ጊዜም በየአፍታው ሽቅብ የሚወጣው የዕለት ፍጆታ ወጪው ይፈትነዋል። ቀዳዳውን ሞልቶ ዛሬን ሲያመስግን ደግሞ የነገው ሕይወት በስጋት ተሞልቶ ይቆየዋል።
ቀደም ሲል በነበሩ ተሞክሮዎች የገበያው ሁኔታ ምክንያትና አጋጣሚዎችን የሚከተል ነበር። የዛኔ ወቅቱን ያልጠበቀ የምርት አቅርቦት ሲኖር፣ ዋጋ መጨመሩ ብርቅ አልነበረም። አውደ ዓመት ሲቃረብና ነዳጅ ጨመረ ሲባልም የተወሰነ ልዩነት መፈጠሩ የተለመደ ነው። ከዓመታት አንዴ ጠብ የምትለው የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ጭማሪም ሰበብ ሆኖ ለገበያው የዋጋ ልዩነት እንደምክንያት ይጠቀስ ነበር። እንዲህ ዓይነቶቹን አጋጣሚዎች እንደነጋዴው ሁሉ ሸማቹም ሲለማመዳቸው ቆይቷል። እስከዛሬም በአቅሙ እየሸመተ፣ በፍላጎቱ እየመጠነ፣ የኑሮውን መልክ ሲያስተካከል ቆይቷል። የዘንድሮው እውነታ ግን ከመቼውም ጊዜ የተለየ ነው። ጊዜና ምክንያትን እያሳበበ እንደግዴታ ጥቂት እያሰለሰ የሚጨምረው ዋጋ ለጆሮ እስኪከብድ መጋነኑን ቀጥሏል። የነፃ ገበያን አጋጣሚ ተንተርሰው እንዳሻቸው ዋጋን የሚቆልሉ ነጋዴዎች ዛሬም ‹‹ይብቃችሁ›› ባይ አላገኙም። የተጠየቀውን ከፍሎ በሚገዛቸው ሕዝብ ላይ ያሻቸውን እያሸከሙ ያሰቃዩታል።
ከሰሞኑ ለሁሉም አነጋጋሪ የሆነው የምግብ ዘይት ዋጋ መናር ብቻ አልሆነም። የአውደዓመትን መዳረሰ ተከትሎ ‹‹መጣሁ›› የሚለው የቅቤ፣ የዶሮና ስጋ ጉዳይም በእጅጉ አሳሳቢ ሆኗል። በቅርቡ ከሰነበተው ዋጋ በእጥፍ የጨመረው የሽንኩርት ገበያ ምክንያትና ሰበብ አልተበጀለትም። ከነበረው ቆይታ ተስፈንጥሮ ድንገት ዋጋው ሲያሻቅብም እንደተለመደው ለምንና እንዴት ባይ አልተገኘም። አሁንም አትራፊዎች ይቸበችባሉ። ዛሬም ተጠቃሚው ይበዘበዛል። ትናንት በአስርብር የሚገዛው አንድ እስር ጎመን፣ ዛሬ መጠኑ ቀንሶ፣ ዋጋው በእጥፍ ጨምሯል። ዱቄት፣ ስኳር፣ ፍራፍሬ፣ የሕፃናት ምግቦችና ሌሎችም በነበሩበት ዋጋ ውለው አላደሩም። በአቅምና በፍላጎት ላይ የተመሠረተ ኑሮ የተረሳ ያህል እንደታሪክ መቆጠር ይዟል፤ ‹‹ነበር›› በሚል ትውስታ።
ትናንት በኪሎ እየመዘነ፣ በሊትር እየለካ ወር የሚያደርስ ሁሉ ዛሬ ወደ ችርቻሮ፣ ባስ ሲልም ወደ እፍኝ ቋጠሮ ግዢ ሊገባ እየተገደደ ነው። አሁን ልጆች ይዘው ቤተሰብ ለሚመሩ፣ ነገን ለሚያስቡ በርካቶች ሕይወት፣ ፈታኝና አዳጋች ሆናባቸዋለች። በየቀኑ የዋጋ ማሻቀቡ ልማድና ግዴታ በሆነበት በአሁኑ ጊዜ የሕገወጦች ህልምና ዕቅድ መለምለም ይጀምራል። በየሰፈሩ ተወሽቀው ከሕግ ዓይኖች የሚደበቁ አንዳንዶች በርካሽ ዋጋ የሚገዙትን ሸቀጥ ደብቀው ማቆየት ልማዳቸው ነው። እንዲህ ዓይነቶቹ ራስ ወዳድ ነጋዴዎች የኑሮ ውድነት በደራበት፣ ችግሩ መነጋገሪያ በሆነበት ሰሞን ከዋጋ ጭማሪ ጋር ብቅ ማለት ልማዳቸው ነው። ያም ሆኖ ለነዚህ ስግብግቦች መላና መፍትሄው ርቋል። ይህን ማሰቡ ነውር ይመስል ድርጊታቸው ሕጋዊ የሆነ ያህል አመታትን ቆጥሯል።
ይህ ዓይነቱ ልማድ ከኅብረተሰቡና ከሚመለከታቸው አካላት ዓይን የተሰወረ አይደለም። ይሁን እንጂ ሁሌም በሕገወጦቹ ላይ ትርጉም ያለው ርምጃ ሲወሰድ አይስተዋልም። ዛሬም እንደዋዛ የሚሰቅሉትን የዋጋ ጭማሪ በነበረበት ጸንቶ እንዲቀጥል የእጅ አዙር ስምምነቱ ይጸድቅላቸዋል። በየጊዜው የሚጫንበትን የኑሮ ውድነት የሚሸከመው ነዋሪ ስለነገው የሚሆነውን በስጋት እያሰበ ኑሮውን ቀጥሏል። በየቀኑ ሽቅብ የሚወረወረውን የዋጋ ጭማሪ በአግርሞት ከማስተዋል ባለፈም መፍትሄ የማፍለቅ አቅሙን ተገፏል። በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ በርካቶች ስለወደፊት የሚሆነውን አያውቁም። ዛሬን ጎርሰው፣ ነጋቸውን በተስፋ ያልማሉ። ለእነሱ ሕይወት ማለት በፈተና የታጠረ፣ በኑሮ ውድነት የታበሰ ግዴታ ሆኗል።
አሁን ላይ መንግሥት የቤት ተከራይና አከራዮችን አስመልክቶ ከወራት በፊት የተገበረውን አሠራር ዳግም ተመልሶበታል። ለሦስት ወራት ያህል አከራዩ በተከራዩ ላይ ዋጋ እንዳይጨምር፣ ‹‹ቤቴን ለቃችሁ ውጡ›› እንዳይል ጭምር ገደብ አስቀምጧል። ይሄም የመንግሥት ፍላጎትና ሀሳብ የኑሮውን ውድነት ለማቃለልና ገደብ የለሹን የቤት ኪራይ ጭማሪ ፈር ለማሳያዝ በመሆኑ እንዲህ ማድረጉ አይከፋም። መንግሥት ለብዙኃን ጥቅም አስቦ መተሳሰብን ማስተማሩ እሰዬው የሚያስብል ነው። ይሁን እንጂ ከዚህ አሠራር ጀርባ ሊፈጠር የሚችል ተጽዕኖን ከግምት ማስገባቱ ደግሞ አስፈላጊ ይሆናል።
ገደቡ በተጣለባቸው ወራት በነበሩ ተሞክሮዎች እንደታየው ተከራዮች ለጊዜውም ቢሆን ከአከራዮቻቸው የዋጋ ጭማሪ ተጽዕኖ መላቀቅ ችለዋል። በየምክንያቱ ኪራይ እንጨምር ለሚሉትም ቢሆን የጊዜ ልጓም ተበጅቷል። እውነታው ግን እንዲህ መሆኑ ላይ ብቻ አይደለም። የጊዜ ገደቡ በተነሳባቸው ጥቂት ጊዜያት ነባሩ የቤት ኪራይ በእጥፍ ጨምሮ ኢኮኖሚን አናግቷል። ይህ ያልተለመደ አጋጣሚም የበርካቶችን አቅም ፈትኖ ለችግር አጋልጧል። ሁኔታውን እንደግዴታ ተቀብለው የቆዩ አንዳንድ የቤት ባለቤቶች እንደዕቅዳቸው ያልተጠቀሙባቸውን ጊዜያት በሚያካክስ ስሌት ጥቅማቸውን ሲያስመልሱ ተስተውሏል።
ይህ ሁሉ ሲሆን የኑሮ ጫናው የሚከብደው በብሶተኛው ነዋሪ ላይ መሆኑ ግልጽ ነው። ዛሬ ላይ ቆሞ ስለነገው አዳር የሚጨነቀው ተጠቃሚ በየቀኑ በሚያጋጥመው የኑሮ ውድነት ሕይወትን መግፋት፣ ኑሮን መቋቋም ይሳነዋል። በቤት ኪራይ ፍለጋ፣ በዕለት ፍጆታዎች የዋጋ ንረት መከራን እንዲገፋ ይገደዳል።
ይህ ሁሉ ሲሆን ታዛቢና ሀይ ባይ ከጠፋ ደግሞ መተዛዘን ይሉት ልማድ፣ ነገን ማሰብ ይባል ዕቅድ ትርጉም የለሽ ይሆናል። ነገን በጋራ እንገነባታለን፣ ሕይወትን በእኩል እንጋራባታለን የምንላት አገራችን መመኪያችን መሆኗ ቀርቶ ስደትና ራስን መጥላት ይከሰታል። ዛሬ ላይ በእጅጉ መልኩን የቀየረው የኑሮ ውድነትና ያለመተሳሰብ እውነት መዳረሻው ከብሶት ጥግ ይሆናል። ታዛቢ ዓይኖች ሲጠፉ፣ የሕግ ገመድ ሲላላ፣ ሕገወጥነት ይሰፋል። መንግሥት ለዚህ ዓይነቱ ግልጽ ችግር እጁን ሊዘረጋ፣ ዓይኖችን ሊከፍት ግድ ይላል። ሕገወጦችን ከመታዛብ ባለፈ በሕግ አግባብ መዳኘቱ ለአገር ለወገን ይበጃል። አገራችን የጋራችን፣ ችግሩም የሁላችን ነውና።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8 /2014