የፈጠራ ሰዎች ሁል ጊዜ ችግር ፈቺ ግኝቶችን እያስተዋወቁ ኋላ ቀር አሠራርና አኗኗራችንን በመግራት ወደ ዘመናዊነት የሚያሸጋግሩን ባለውለታዎቻችን ናቸው። ዛሬ በተለያዩ ዘርፎች ዓለምን እየለወጡ የሚገኙት የፈጠራ ውጤቶች በአንድ ወቅት በአንድ ግለሰብ ወይም በአንድ ቡድን ተደጋጋሚ ሙከራና ጥረት እውን የሆኑ ናቸው። በትራንስፖርት፣ በጤና፣ በሥነሕንጻ፣ በቴሌኮም ወዘተ የፈጠራ ሰዎች ያበረከቷቸው የምርምር ውጤቶች ምን ያህል እየጠቀሙን እንዳሉ መረዳት አይከብድም። ይህ ደግሞ እስከ ዛሬ ከነበረው ፍጥነት በእጅጉ ጨምሮ ወደ ፊትም የሚቀጥል ይሆናል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፈጠራና ክሂል እንደ አገር መበረታታቱን ተከትሎ አንዳንድ ወጣቶች አዳዲስ አሠራሮችን ለማስተዋወቅ መንፈሳቸው ተነቃቅቷል። አንዳንዶች የራሳቸውን አዲስ ሥራ ሲፈጥሩ ሌሎችም “ጎግል” እያደረጉ የሚያዩቱን ቴክኖሎጂ በአካባቢያቸው ከሚያገኙት ቁስ አስመስለው በመሥራት አኗኗራችንንና አሠራራችንን ለማዘመን ሲጥሩ ይታያል። ቀደም ባለው ዝግጅታችን ጎግል አድርገው ባገኙት ግንዛቤ የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወን የሚረዳ ሶፍት ዌር ያበለጸጉ፣ የወርቅ አፈር የሚያጥብ ማሽን የሠሩና ሌሎችንም በዘርፉ ጥረት ያደረጉ ወጣቶችን አስተዋውቀናችኋል።
ከሰሞኑ በተካሄደ አንድ ሁነት ላይ ደግሞ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ ያተኮሩ ሥራዎች ተቃኝተው ነበር። ‹‹የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራዎችን በማበልፀግና በማስፋፋት ኢንዱስትሪውን እናዘምናለን›› በሚል መሪ ሃሳብ በዘርፉ የተሠሩ ሥራዎች የትውውቅና ሥርፀት መርሐ ግብር ተካሂዷል።
በዚህ መርሐ ግብር ላይ ለኮንስትራክሽን ዘርፍ መዘመንና መሳለጥ የሚያገለግሉ መተግበሪያዎችን ጨምሮ ከ14 በላይ ሥራዎች ለታዳሚዎች ይፋ ተደርገው ከሥራው ባለቤቶች ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል። ሥራዎቹ በግለሰቦች፣ በዩኒቨርሲቲዎችና በኮሌጆች አማካኝነት የተሠሩ ናቸው።
በዛሬው የወጣቶች አምድ ዝግጅታችን የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ በተመጣጣኝ ወጪና በፍጥነት ተገጣጣሚ ቤቶችን መሥራት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ይዞ የመጣ ወጣት መምህርን እናስተዋውቃችኋለን።
ወጣት ወንድማገኝ ገለታ ይባላል፤ መምህር ነው። የመጀመሪያ ዲግሪውን ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአርክቴክቸራል ኢንጅነሪንግ ተመርቋል። አሁን በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ አርቴክቸር ትምህርት ክፍል በመምህርነት እያገለገለ ይገኛል።
ወጣቱ የሠራው ዲዛይን በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዘንድ ተፈላጊና ተወዳጅ ሆኗል። በተናጠል የተሠሩ ቤቶችን ገጣጥሞ ህንጻ ማድረግ የሚያስችል አሠራርን ለአገራችን ያስተዋወቀ ነው።
የተናጠል መኖሪያ ቤቶቹ ግብዓቶች በኢንዱስትሪ ውስጥ ከተመረቱ በኋላ የትም ሥፍራ ላይ ተገጣጥመው ሕንጻ መሆን የሚችሉና በውስን ቦታ ላይ በርካታ አባ ወራዎችን ማስፈር የሚያስችሉ ናቸው።
ቤቶቹ ከኮንክሪትና ከብረት ግብዓት ተመርተው በብሎን ይገጣጠማሉ። እያንዳንዱ ቤት ሲገጣጠም ምን ያህል እንደሚሸከም ጥንካሬው በሳይንሳዊ መንገድ የተረጋገጠ ነው። እያንዳንዱ ክፍል የላይኛውን የሚሸከም ስትራክቸራል ዲዛይን ተሠርቶለታል። በተገጣጣሚ ክፍሎቹ አስክ “ጂ ፕላስ 7” (ከወለል በላይ እስከ 7 ፎቅ) ድረስ መሥራት እንደሚቻልም ተመላክቷል።
በአሠራሩ ላይ ተጨማሪ ቴክኖሎጂዎችን ለማከል እና የሚታዩ ግድፈቶችን ለማረም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር እየተመከረበት ይገኛል። የኮምፒውተር ሲሙሌሽን ሥራውም ተጠናቋል። ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ቢደረግ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የበርካታ ዜጎችን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ይመልሳል ተብሎ ታምኖበታል።
የመኖሪያ ቤት ፈላጊዎች ቤት ለማግኘት በርካታ ዓመታትን ሳይጠብቁ የቤት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ተብሏል። ከዋጋ አንፃርም የተሻለ መሆኑ ተገልጿል።
የቤት ዋጋ በየጊዜው የሚጨምር እንደሆነ ቢታወቅም ታህሳስ 2014 ዓ.ም በተደረገው ጥናት መሠረት ይህ ተገጣጣሚ አሁን ባለው የቤት ዋጋ መነሻነት በካሬ ሜትር 17ሺህ ብር ቅናሽ አለው። በዚህ ስሌት ሲታይ ሦስት እጥፍ ከሌላው መደበኛ የቤት ዋጋ የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል።
መኖሪያ ቤቶች ተደራርበው ሲሰሩ የቦታ ጥበት ችግርን ያቃልላሉ። ይህ ፕሮጀክትም እንዲህ አይነት መፍትሔ ሰጪ መሆኑ ተመራጭ ያደርገዋል። በተገጣጣሚ ቤቶች የሚቆመው ሕንፃ የፊኒሽንግ ሥራዎችን ስለሚያጠናቅቅ የጅብሰምና የልስን ሥራዎች አያስፈልጉትም። ፕሮጀክቱን ወደ ሥራ ለማስገባት እንደመነሻ ለማሽንና ለኢንዱስትሪው ሼድ ግንባታ 28ሚሊዮን ብር ማስፈለጉ በጥናቱ ተመላክቷል።
በሙሉ አቅሙ መሥራት ሲጀምር 12 ማሽነሪዎችን በማቆም ፋብሪካው በሳምንት እስከ 7 ወለል ያላቸውን አራት አፓርታማዎች መገንባት የሚያስችሉ የተገጣጣሚ ቤቶችን ግብዓት ያመርታል። ይህንንም ለማስጀመር 500 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት ማድረግ ይጠይቃል ተብሏል።
አንዷን የቤት ክፍል ለመሥራት የሚወስደው ስድስት ሰዓት ብቻ ሲሆን በ24 ሰዓት ውስጥ ሦስት እራሳቸውን የቻሉ የቤት ክፍሎችን ማምረት ይቻላል። የተመረተው ግብዓት ማድረቂያ ክፍል ገብቶ ለስራው ዝግጁ መሆኑ ሲረጋገጥ ወደ ቦታው ተወስዶ የሚገጠም ይሆናል። የቤቶቹ ጥንካሬም ከሕንፃዎች እኩል ያገልግሎት እድሜ እንዲኖራቸው የተደረጉ ናቸው።
የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኮሌጅ የሥራውን ተተግባሪነት በማየትና የተገጣጣሚ ቤቶች መሥሪያ ኢንዱስትሪ በአገር ውስጥ ቴክኖሎጂ ብቻ እንደሚገነባ በመተማመን ፕሮጅክቱን ወደ ተግባር ማስገባት እንደሚቻል ማስተማመኛ ቃል ሰጥቷል።
አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥራውን ከልሶት በመጠናቀቅ ላይ ስላለ ወደ ትግበራ የሚገባበትን መንገድም በመነጋገር ላይ እንዳሉ መምህር ወንድማገኝ ገልጿል። ከአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የዚህን ፈጠራ ማረጋገጫ /ፓተንት/ የማግኘቱ ሂደት እየተጠናቀቀ መሆኑ ተነግሯል።
28 ሚሊዮን ብር ፋይናንስ አድርጎ ሥራውን የሚደግፈው አካል ስለጠፋ በቀላሉ ሊፈታ የሚችለው የቤት ችግር አሁንም አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ መቀጠሉን መምህር ወንድምአገኝ ተናግሯል። በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ ጉዳዮች የሰዎች የዘላለም ጥያቄ ሆነው ሳይመለሱ ሲቀሩ ያማል የሚለው መምህር ወንድማገኝ የሰዎች የመኖሪያ ቤት ጉዳይ የሀብትና የገንዘብ ብቻ ሳይሆን የነፃነት ጉዳይ ነው ብሏል።
እርሱ ይዞ የመጣው ሥራ መንግሥት በፖሊሲ ደረጃ ያስቀመጣቸውን በርካታ ነገሮች መሬት ላይ ለማውረድ የሚያግዝ እንደሆነ ተናግሯል። በዚህ ሥራ ላይ ደፈር ብሎ ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልግ አካል የተሻለ መጠቀም የሚያስችል እድል እንዳለውም ጠቁሟል።
በ24 ሰዓት ውስጥ ሦስት የቤት ክፍሎችን መገንባት ወይም በሳምንት ውስጥ ባለ ሰባት ወለል አራት አፓርታማዎችን መገንባት ምን ያህል ገንዘብን ሊያስገኝ እንደሚችል መረዳት አይከብድም፤ ነገር ግን ከግልም ይሁን ከመንግሥት ተቋም ደፍሮ የሚገባ አካል በመጥፋቱ መመለስ የነበረባቸው የመኖሪያ ቤት ጥያቄዎች ሳይመለሱ ቀርተዋል፤ ይገኝ የነበረውም ገቢ ባክኗል ብሏል።
እስካሁን ባለው መረጃ ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባቸው ዋና ዋና የግንባታ ግብዓቶች 60 በመቶ እንደሚሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ ያለው የሥራው ባለቤት ይህ የቤት ግንባታ ከአገር ውስጥ ምርቶች ወደ 70 በመቶ የሚሆነውን የግንባታ ግብዓት መጠቀሙ ሌላው መልካም ጎኑ እንደሆነ ጠቅሷል።
ቤቶቹ እርስ በእርስ የሚደራረቡት በብሎን እየታሰሩ ስለሆነ አሥፈላጊ በሆነ ጊዜ በባለሙያና በመሣሪያ እገዛ ተነቅለው ወደ ሌላ ስፍራ እንዲሄዱ ከተፈለገም ምቹ ናቸው፤ ይህም ከመደበኛ ሕንፃዎች ይለያቸዋል ተብሏል።
በወቅቱ መርሐ-ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ጫልቱ ሳኒ በዘርፉ ለሚታዩ ችግሮች ተገቢውን ምላሽ መስጠት የሚችለው አገር በቀል ዕውቀትና ልምድ ነው የሚል ፅኑ አቋም አለን ብለዋል። የውጪ ቴክኖሎጂዎችን ብቻ ተመርኩዞ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪ ማድረግ እንደማይቻል ገልጸዋል።
ስለሆነም በጥናት ላይ በመመሥረት አገር በቀል ዕውቀቶችን፣ ግኝቶችን፣ የምርምር ውጤቶችንና ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋትና በማላመድ እንዲሁም በየደረጃው በማስረፅ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነት ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
መኖሪያ ቤትን ጨምሮ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያችን የምንገለገልባቸው መሠረተ ልማቶች በአመዛኙ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ውጤት ናቸው ያሉት ሚኒስትሯ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ለአገር ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋፅዖ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነም ጠቅሰዋል።
ዘርፉ የአገሪቱን ልማት ለማፋጠንና የፈጠራ ሥራዎችን ለማበረታታት እንዲሁም ሥራ አጥነትን ለመቀነስ ብሎም ዜጎች ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚጫወተው ሚና ቀላል አለመሆኑን ሚኒስትሯ ባደረጉት ንግግር ገልፀዋል።
ኢንዱስትሪው ከሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ባሻገር ከግብዓትና ከቴክኖሎጂ አንፃርም በአመዛኙ በውጪ ምርት ላይ ጥገኛ ሆኖ መቆየቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚፈለገው ልክ ተወዳዳሪ እንዳይሆን ካደረገው ምክንያት አንዱ ነው ብለዋል።
ይህን ችግር ለመፍታት በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የትምህርት ተቋማት፣ የምርምርና ስርፀት ማዕከላት እንዲሁም በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሠማሩ የግልና የመንግሥት ተቋማትን በማስተሳሰር መሥራት ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል።
በዚህ መንገድ የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች በኢንዱስትሪው ውስጥ ሲሰርፁ የዘርፉን ችግር ከመፍታትና ተወዳዳሪነትን ከማሳደግ አኳያ ጉልህ ጥቅም አላቸው ብለዋል። ፈጠራዎቹ በሥርፀት ኢንዱስትሪው ውስጥ ገብተው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ሁሉም አካላት በርብርብ መሥራት ይገባቸዋልም ነው ያሉት ሚኒስትር ጫልቱ።
በአገር በቀል ፈጠራ ባለቤቶች መካከል የልምድ ልውውጥና የዕውቀት ሽግግር በማድረግ ለበለጠ የፈጠራ ውጤት እንዲተጉ ይደረጋል ያሉት ሚኒስትሯ ኢንዱስትሪውንም የፈጠራ ውጤቶች ማዕከል በማድረግ በሂደት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳካት ታሳቢ ተደርጎ መሠራት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።
የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ታምራት ሙሉ በበኩላቸው የአገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚጠበቀው ልክ ተወዳዳሪ ካልሆኑባቸው ምክንያቶች አንዱ በአብዛኛው የምንጠቀማቸው ቴክኖሎጂዎች በውጭ አገራት ቴክኖሎጂዎች ላይ ጥገኛ ስለሆኑ ነው ያሉ ሲሆን፤ ይህ ሁኔታ እንዲሻሻል በዘርፉ ያሉ ዕውቀቶች እንዲዳብሩ፤ ፈጠራዎችም እንዲበረታቱ ማድረግ ያሥፈልጋል። ስለዚህም ለፈጠራ ባለሙያዎችና ተቋማት ዕውቅና በመስጠት ለበለጠ ሥራ እንዲነሳሱ ማድርግ እንደሚስፈልግም ገልጸዋል።
ለዚህም መነሻ ይሆን ዘንድ የፈጠራ ባለሙያዎችን የሚያበረታቱ መድረኮች ማዘጋጀት እንደጀመሩ እና የፈጠራ ሥራዎቹ የዘርፉን ችግር የሚያቃልሉ ሆነው ሲገኙ በፋይናንስ እንዲደገፉ ለማስቻል አጋር አካላት በቦታው ተገኝተው እንዲከታተሉ መደረጉን አቶ ታምራት ተናግረዋል።
በመድረኩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማትና የኮንስትራክሽን ሥራዎች ማኅበራት፣ የፋይናንስ ሴክተሮችን የሚመሩ አካላትና ሌሎችም ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርጓል።
የተካሄደው የኮንስትራክሽን ዘርፍ የፈጠራ ሥራዎችን የማስተዋወቅና የማስረፅ ሁነት አስገዳጅ እንዲሆን አመርቂ ምክንያቶች አሉ። ዋነኛው ምክንያት ግን ኢትዮጵያ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ ከምትገለገልባቸው 60 በመቶ የሚሆኑት የግንባታ ዕቃዎች ከውጪ አገራት የሚገቡ መሆናቸው ነው።
መንግሥት በአሥር ዓመት ዕቅዱ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነውን የግንባታዎች ግብዓት ለመተካት አቅዶ እየሠራ መሆኑን ይናገራል። ሆኖም እስካሁን ያሉት መረጃዎች እና የቅርብ ጊዜ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት የአገሪቱ የኮንስትራክሽን ሥራ ግብዓቶች አብዛኞቹ ከውጪ የሚገቡ ናቸው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ አማራጭ ተወስዶ እየተሠራበት ያለው በዘርፉ የአገር በቀል የፈጠራ ሥራዎችን በማበረታታት፣ በማስተዋወቅና በማስረፅ የግንባታ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ ምርቶች መተካት ላይ ነው።
እኛም አገር በቀል ግብዓትና እውቀትን ተጠቅመው ከኋላ ቀር አሠራርና አኗኗር ሊያላቅቁን የሚጥሩ ግልሰቦችንና ተቋማትን እያከበርን የሚመለከተው አካልም በሚችለው ሁሉ ከጎናቸው ቢቆምና አስፈላጊውን ማበረታቻ ቢያደርግላቸው አገርና ሕዝብ ይጠቀማሉ በማለት ተሰናበትን። ከእውቀት አፈራሽ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር ወደፊት!!!
ኢያሱ መሰለ እና ውብሸት ሰንደቁ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7 /2014