ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት “የውጭ አገር ዜጎች ወይም በከፊልም ሆነ በሙሉ በውጭ አገር ዜጎች ባለቤትነት ሥር ያሉ ድርጅቶች ወይም የውጭ ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ሥራ ማካሔድ ወይም የባንክ ሥራ የሚያካሒድ ቅርንጫፍ ሊያቋቁሙ አይችሉም።” ከዚህ በተጨማሪ “በኢትዮጵያ ውስጥ በተቋቋሙ ባንኮች አክሲዮን መያዝ” ከሶስት አመታት ገደማ በፊት በወጣው የባንክ ሥራ ማሻሻያ አዋጅ መሠረት ተከልክለው ቆይተዋል። በጳጉሜ 2011 ዓ.ም የወጣው የተሻሻለ የባንክ ሥራ አዋጅ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በባንክ ሥራ እንዲሳተፉ ፈቅዷል። ኢሕአዴግ በሥልጣን ላይ በነበረባቸው አመታት ዓለም አቀፍ ተቋማት የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ባንኮች እንዲከፍት ተደጋጋሚ ግፊት ቢያደርጉም ተቀባይነት ሳያገኝ የቆየ ጉዳይ ነበር።
በቅርቡ መንግሥት የሚያስፈልጉትን “ቅድመ ሁኔታዎች ከጨረሰ እና ባንኮች ከተዘጋጁ” ተግባራዊ የሚሆነው ይኸ እርምጃ ዓላማው “ተጨማሪ ሐብት፤ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ” ማግኘት መሆኑን በምክር ቤቱ ንግግራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጠቅሰዋል። የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ “የሚገቡበት ዓላማ ግልጽ መሆን አለበት። የፖሊሲ ማዕቀፉ ከዚያ ተነስቶ ነው የሚቀረጸው ብለዋል።
በአፍሪካ እና በዓለም አቀፉ ገበያ ሥመ-ጥር የሆኑ ባንኮች ባለፉት አመታት የኢትዮጵያ መንግሥትን ውሳኔ ጆሮ ሰጥተው ሲከታተሉ ቆይተዋል። የቱርኩ ዚራት ባንክ በአዲስ አበባ ቢሯቸውን ከከፈቱ ባንኮች የመጀመሪያው ነው። የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ፣ የጀርመኑ ኮሜርስ ባንክ በአዲስ አበባ ቢሯቸውን ከከፈቱ መካከል ይገኙበታል። የደቡብ አፍሪካው ስታንዳርድ ባንክ እና የኬንያው ኬሲቢ ባንክ ከዚህ ቀደም ዘርፉ ለውጭ ባንኮች ከተከፈተ ወደ ገበያው የመግባት ፍላጎት እንዳላቸው ካሳወቁ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ይህ የውጭ ባንኮችን ወደሃገሪቱ የሚጋብዘው አዋጅ ለሀገሪቱ ምን ይዞላት ይመጣል? ስንል አንጋፋው የኢንሹራንስ ባለሙያ አቶ እየሱስወርቅ ዛፉን ጠይቀናል። ለዛ ባለው አነጋገራቸው ያካፈሉንን ሙያዊ ሀሳብ እነሆ ብለናል።
አቶ እየሱስወርቅ እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያና አለም በፈተና ውስጥ ባሉበት ጊዜ የውጭ ባንኮች በአገር ውስጥ የመከፈት አለመከፈት ጉዳይ ጥያቄ ሆኖ መቅረብ የለበትም። ምክንያቱም መከፈቱ የግድ በመሆኑ ነው። ኢትዮጵያ ከአለም የተለየች ደሴት ሆና ዘለአለም መኖር አትችልም ግዴታ ከሌሎች አገሮች ጋር መገናኘት ይኖርባታል።
“እኛም የኛን አገር ገበያ ለሌሎች ተወዳዳሪዎች ክፍት ማድረግ አለብን። ሌሎችም ለእኛ መክፈት አለባቸው። ይሄ የብዙ ጊዜ ቁጭታችን ነው። አሁን ኢኮኖሚያችን በከፍተኛ ሁኔታ በተጎዳበት በዚህ ጊዜ ለውጭ ባንኮች እንክፈት ወይስ አንክፈት ብለን መነጋገር የለብንም። ቀደም ብሎ ይሄ እንደሚሆን አውቀን መዘጋጀት ነበረብን፤ ይሄ የሆነው እውቀት በማጣት ሳይሆን በቸልተኝነት የተተወ ነው።” የሚሉት አቶ እየሱስወርቅ በህይወት ውስጥ ለውጥ እንደ ማእበል የሚመጣ በመሆኑ ቅደመ ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ። የማይለወጥ ነገር ቢኖር ራሱ ለውጥ ብቻ መሆኑን ገልፀው በሂደት የፋይናንስ ተቋማት አቅማቸውን በማደራጀት ሌሎች ተወደዳሪዎች እንደሚመጡ በማሰብ ጉልበት ያላቸውን ከውስጥ የማብቃት ስራ መሰራት እንደነበረበት ያስረዳሉ። የሰው ሃይል በፋይናንስ ዘርፉ በእውቀትና በልምድ የተደራጀ የሰው ሀይል ለመፍጠር የአለም ባንክ ድጋፍ አድርጓል።
የፋይናንስ ተቋማትን ለማጠንከር ፍትሀዊና እውነተኛ ውድድር ለሁሉም ጠቃሚ መሆኑን ይጠቅሳሉ። በአገሪቱ ውስጥ ግን በተለይም የመንግስት ድርጅቶች በተለያዩ ድጎማዎች ወደ ላይ የሚወጡ እኩል ሜዳ ሳይፈጠርላቸው አሸናፊና ተሸናፊ የሚሆኑበት አግባብ እንዳለ ተናግረዋል። ለአብነትም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በብዙ ድጋፍ ገበያው ውስጥ ከፍ ያለ ደረጃን ይዞ ቢቀመጥም እሱ ብቻ በመደጎሙ ሌሎቹ በተወሰነ ደረጃ ማግኘት የሚገባቸውን እድል የሚያጡ መሆኑን አስረድተዋል። ስለዚህም እውነተኛ ውድድር ለማምጣት በአንድ ጀንበር ሚሊየነር የመሆን ሀሳብ ማሰብ ሳይሆን በዋጋም በአገልግሎት ጥራትም ተወዳዳሪ የመሆን ሀሳብ መጎልበት የሚበረታታ መሆኑን ነው የገለጹት።
በአገራችን ሁኔታ ባንኮች ለውጪ ተወዳዳሪዎች መከፈት አለበት የሚሉት አቶ እየሱስወርቅ፤ ይሄ እርምጃ እንዳውም የዘገየ ነው ሲሉ ይጠቅሳሉ። ኢትዮጵያ እንዳለመታደል ሆኖ አዳማጭ በማጣት አስፈላጊውን ዝግጅት ባለማድረግ የቆየች መሆኑ ጉዳዩ አሳሳቢ ከማድረጉ በቀር ገበያው ውስጥ መግባታቸው አይቀሬ መሆኑን ነው ያስረዱት። የውጭ ባንኮች አከፋፈታቸው ለየት ያለ ቢሆንም የውጭ ተወዳዳሪዎች እየመጡ ጎጇቸውን መቀለስ ሳይሆን እዚህ ካሉት ኩባንያዎች ጋር አብሮ መስራት ቢጀምሩ የተሻለ ይሆናል የሚል ሀሳብ እንዳላቸው ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ በፋይናንስ ዘርፍ ብዙ የገፋች አይደለችም። በዚህ ዘርፍ በአገሪቱ የሚሰጡ አገልግሎቶች በሌሎች አገሮች የሚሰጡ አገልግሎቶችን የሚፎካከሩ የፋይናንስ ተቋማት አለመኖራቸው ነው። የፋይናንስ ተቋማት ማደግና መበልፀግን ተከትሎ ኢኮኖሚውም እያደገ የሚሄድ መሆኑን ይናገራሉ። ኢኮኖሚ አደገ ማለት ደግሞ በፋይናንሱ ዘርፍ የሚጠይቃቸው አገልግሎቶች በዛ ልክ የተሻሻለ ሊሆን የሚገባው መሆኑን ያስረዳሉ።
የውጪ ባንኮች ብዙ ጊዜ ወደ አንድ አገር ሲገቡ በአገሪቱ የሚገኙ ተቋማትን ከገበያ ያስወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይሄ እንዳይሆን ራስን ለተወዳዳሪነት ማዘጋጀት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ያስረዳሉ።
በጎረቤታችን ኬንያ ያሉ በኬድ አንካር የሚባሉ ባንኮችን ለማየት ሲሞከር ከኛ አገር የበለጡ በተወዳዳሪነታቸው የላቁ የውጭ ባንኮችን ከገበያው ማስወጣት የቻሉ መሆናቸውን ለማመልከት ይቻላል። ይህ ሲባል በውድድር አሸናፊ ሆነው መውጣትን የሚያውቁ ባንኮች ወደ አገር ሲገቡ አንደኛ በእውቀትና በቴክኖሎጂ የተሻለ አገልግሎት ለተጠቃሚው በተሻለ ዋጋ የማቅረብና የመስጠት አቅም ይዘው ይመጣሉ። ሁለተኛ እነሱ ራሳቸው ሲመጡ አሁን ላለንበት የኢኮኖሚ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ ይዘው መምጣታቸው በተወሰነ ደረጃ የተወሰነ ጥቅም ይኖረዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን የውጭ የፋይናንስ ተቋማት በአገሪቱ ውስጥ
መሰማራት በሌሎች በአገራቸው ያሉ ተቋሞችን መተማመን ይሰጣቸዋል። ይህም ማለት የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ ያበረታታል። ገበያው ለውድድር የተከፈተ መሆኑን ስለሚያረጋገጥላቻው ሌሎች ኢንቨስተሮች ከስጋት በፀዳ ሁኔታ በአገሪቱ መዋእለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ያደርጋቸዋል ብለዋል። በአጠቃላይ ሲታይ ደግሞ የውጭ ባንኮች ወደአገራችን መግባታቸው ሰፊ ጥቅም ያስገኛል ሲሉ አብራርተዋል – አቶ እየሱስወርቅ።
አሁን በአገሪቱ በፋይናንስ ዘርፍ አዲስ የሚቋቋሙ ብሎም በስራ ላይ ያሉ ባንኮች የውጪ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ መግባት እንደሚያሳስባቸው ሲነግር ይደመጣል የሚሉት አቶ እየሱስወርቅ፤ ነገር ግን የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ ነው ሲባል መታሰብ ያለበት አዲስ ለሚጀመሩ የአገር ውስጥ ባንኮች ወይም ለነባሮቹ አይደለም። ይልቁንም መታሰብ ያለበት የአገር ኢኮኖሚ እንዴት ያድጋል፤ አገር እንዴት ትጠቀማለች፤ በዘላቂነት የተረጋጋ ኢኮኖሚ ላይ እንዴት ልትቆም ትችላለች የሚለው ጉዳይ ነው።
“የእኛ አገር ጉዳይ አሁን ካለው የፖለቲካ ሁኔታ አንፃር ባንኮችም በብሄር ላይ ተመስርተው ሲቋቋሙ ይታያል። በጎጥ ድርጅቶችን ማቋቋም ሩቅ ማየት የተሳናቸው አካላት የሚያከናውኑት ተግባር መሆኑን ያሳያል። ነገር ግን አንድ ድርጅት ሲቋቋም በራስ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ስብስብ ሆኖ ከማንኛውም ተወዳዳሪ ጋር አሸንፌ እወጣለሁ የሚል እሳቤ ሊኖር ነው የሚገባው “ ብለዋል። የአገር ውስጥ ኢንቨስተር ከአገር አልፎ አፍሪካን፤ ከአፍሪካ አልፎ አለምን መድረስ ግባቸው ሊሆን ሲገባ በጎጠኝነት አስተሳሰብ ውስጥ ተወሽቀው አጭር ርቀት ለመጓዝ ማሰብ ነው። በመሆኑም አስተሳሰቡ ሊቀየር የሚገባ ነው።
“ ከ 15 አመት በላይ ስሰራበት በቆየሁበት ናይጄሪያ የመንግስታቱ ድርጅት ያቋቋሙትን አንድ ተቋም እመራ ነበር። በወቅቱ በናይጄሪያ ባንኮችና ኢንሹራንሶች እንደ አሸን የፈሉበት ጊዜ ነበር። ከ 120 በላይ ባንኮች ነበሩ። ከጊዜ በኋላ የዛ አገር መንግስት አንድ ባንክ ባንክ ሆኖ ስራውን ለመስራት ማሟላት የሚገባውን ቁርጥ ያለ ህግ አወጣ። ይህንኑ ተመስርተው ብዙዎቹ ባንኮች መቀናጀት ጀመሩ። በዚህም ጠንካራ ሆነው ቀጠሉ “ ሲሉ ገጠመኛቸውን ያስረዳሉ።
አቶ እየሱስወርቅ እንደሚሉት፤ በኬንያ ያሉ ባንኮች ወደ አገራችን ቢገቡ የኛ ባንኮች እንጭጭ ሆነው ነው የሚታዩት። በአገራችን ያሉ የፋይናንስ ተቋማት በልምድ፣ በካፒታል፣ በእውቀትና በቴክኖሎጂ ገና ናቸው። ለዘርፉ የሚያገለግል ብቁ የሰው ሃይል እንኳን በሌለበት ሁኔታ ተወዳዳሪ መሆን እጅግ በጣም ከባድ ነው። አሁን በኮቪድ 19 ብሎም በጦርነቱ ምክንያት ኢኮኖሚው እጅግ በጣም ተጎድቶ በርካታ ውጥረት ባለበት ጊዜ ባይሆን የሚመረጥ ቢሆንም ነገን የተሻለ ለማድረግ ዛሬ መስዋእትነት መከፈል የግድ በመሆኑ አሁን ላይ ባንኮችን የማስገባት ጉዳይ ወደኋላ የሚባል አይደለም።
የውጭ ባንኮች በመግባታቸው የተሻለ አገልግሎት የማይፈልግ ማን ይኖራል? ሲሉ ጥያቄ የሚያነሱት አቶ እየሱስወርቅ አገሪቱ የተሻለ አገልግሎት በፋይናንስ ዘርፉ ስላገኘች ወይም የውጭ ምንዛሪ ወደአገር ስለገባ ሰዎች ተጎጂ እንደሚሆኑ አድርጎ ማሰብ አይገባም ይላሉ። ስራአጥነትን የሚቀንሱ ቀጣሪዎች፤ ኢንቨስተሮች ወደ አገራችን ስለገቡ እገሌ ተጎዳ እገሌ ተጠቀመ የሚባል ነገር መኖር የማይገባው መሆኑን አሳስበዋል።
በአገሪቱ ውስጥ ያለው አስተሳሰብ መሆን የሚገባው ለምሳሌ አንድ ብስኩቱ ባለበት መጠን ለብዙ በላተኞች እየቆረሱ ከመስጠት ይልቅ ብስኩቱን ከፍ አደርጎ ሁሉም የተሻለውን እንዲያገኝ ማድረግ ነው። የተወሰኑ ቡድኖችን በማሰብ ብቻ መሰራት የለበትም። አገር የእገሌና የእገሊት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ህዝብ መሆኑን ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል። በአጠቃላይ ለፋይናንስ ዘርፉ እድገትና ዘመናዊነት የውጭ አገራት ባንኮች ወደአገሪቱ መግባታቸው ዘርፉን አንድ እርምጃ ወደፊት ያራምዱታል ሲሉ አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ተናግረዋል።
አሥመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2014