የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሕግ ትምህርት ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀዋል:: ከዚያም በተለያዩ አካባቢዎች ተመድበው ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል:: በተለይም ግጭቶች ሲከሰቱ በነበሩባቸው አካባቢዎች ሁኔታዎችን ተመልክተው በሕግ ዓይን እልባት እንዲያገኙ ሠርተዋል:: በኦሮሚያ ክልል ቡድኖ በደሌ ዞን ቦርቻ ወረዳ ዓቃቤ ሕግ፣ በኦሮሚያ ክልል ቡድኖ በደሌ ዞን ደዴሳ ወረዳ ዓቃቤ ሕግ፣ ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የቡራዩ ከተማ ወረዳ ዓቃቤ ሕግ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ቶሌ ወረዳ ዓቃቤ ህግ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የቀርሳ ማሊማ ወረዳ ዓቃቤ ሕግ ሆነው ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል:: በአሁኑ ወቅት ደግሞ ጠበቃ ሆነው በመሥራት ላይ ናቸው-የሕግ ባለሙያው አቶ በፍርዴ ጥላሁን ፡፡
በዛሬው ዕትማችን የኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችና መፍትሔዎች አስመልክቶ ሰፊ ሙያዊ ሃሳብ ሰጥተዋል:: አገሪቱ ውስጥ እየሆኑ ባሉ ነገሮች በዓለምአቀፍ ጉዳዮችን ለመዳሰስና መፍትሔን ለማመላከትም ሞክረዋል የሕግ ባለሙያው::
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ቦታዎች በአገሪቱ የሚስተዋለውን የፀጥታ ችግር መሰረታዊ መነሻው ምንድን ነው?
አቶ በፍርዴ፡– የአገራችን ችግር ዘርፈ ብዙ ነው:: ከሁሉም በላይ እንደ አገር ደሃ መሆናችን እዚህ ደረጃ ለመድረስ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል:: ድህነትን የወለደው ደግሞ አለመሰልጠን ነው:: እንደ አገር ወይም እንደ ሕዝብ ሥልጣኔ ይቀረናል፤ ገና ከስልጣኔ ማማ አልቀረብንም:: ዓለም ከደረሰበት የስልጣኔ መንደር ለመድረስ ብዙ መጓዝ፤ ብዙ መመራመር፣ ብዙ ማንበብ ይጠበቅብናል:: ይህ ሁኔታ ችግራችን ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሆን አድርጎብናል:: ጠቅለል ሲደረግ አንድ ሕዝብ የሥልጣኔ ማማ ላይ አልደረሰም የሚባለው አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ያልተማረ አሊያም ደግሞ ከትምህርት ገበታ ላይ ያልተገኘ ሲሆን ነው፡፡
ያልሰለጠነ ማኅበረሰብ የዘረኞች መፍለቂያ ይሆናል:: ጥቂቶች ብዙኃኑን ወደፈለጉት አቅጣጫ እንዲወስዱትም ዕድል ይሰጣል:: ዘረኛ ስትሆን መጀመሪያ እንደ ሰው ከማሰብ ሙሉ ለሙሉ ትወጣለህ:: በአንድ ጎራ ብቻ የማሰብና ውግንናው ለጥቂቶች ብቻ ይሆናል:: እንደ አገር ማሰብን ትተህ እንደ አካባቢ ብቻ ታስባለህ:: ሁሉም በራሱ አካባቢ ልክ ብቻ ማሰብ ሲጀምር ነገሮች ሁሉ ከዘረኝነት አንጻር ይመነዘራሉ::
ፖለቲካ በለው ኢኮኖሚ፣ ያኔ ስለ አገር ማሰብ ስለሚቀር ዜጎችን የሚያስተሳስሩ ነገሮች ይሸረሸሩና የሚያራርቁ ሁኔታዎች ሰፊ ቦታ ይይዛሉ:: በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለ ሕዝብ ያሳለፈውን ታሪክ ሳይቀር እያነሳ የወደፊቱን ለመተንበይ ይቸገራል የነገውንም ይረሳል:: የዘረኝነት አስተሳሰብ በነገሰበት አገር ውስጥ ሁልጊዜ የሥልጣን ሹክቻና የፖለቲካ ቁማር ይኖራል:: ይህ ደግሞ ደም መፋሰስን፤ በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ ቀድሞ ለሰለጠኑና ለበለጸጉ አገራት ጥገኛ እንድንሆን ያስገድደናል፡፡
ሌባ በራሱ ዘር ባይኖረውም ሌቦች ለመስረቅ ሲሆን ከየትኛውም ብሔር ጋር ይደራጃሉ:: ሕጋዊ ተጠያቂነት ሲመጣባቸው ግን ተጎጂ መስለው በብሔራቸው ውስጥ ይደበቃሉ:: እነዚህ ቡድኖች ሕዝቡን ከአንዴም ሁለት ጊዜ ይጎዱታል፤ አንደኛ የድሃውን ሕዝብ በጀቱን ይቀራመቱበታል:: መሬቱን፤ ገንዘቡን ይሰርቁታል:: ሁለተኛ በሰረቁት ገንዘብ መልሰው ሕዝቡን ያፋጁታል:: በዚህ ሂደት በአቋራጭ የበለጸጉ ቱባ ባለሃብቶችና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ አንዳንድ ሌቦች ጋር በማበር በጋራ ይሠራሉ:: እነዚህ አካላት ለአገር አደገኛ እና በቀላሉ የማይነቀሉ ካንሰር ናቸው:: የተሸከማቸው ሕዝቡ ራሱና መንግሥት ናቸው:: መንግሥትና ሕዝብ ሳይተባበሩ ማጥፋት አይቻልም::
መፍትሔው፤ የአገር አንድነትና ሥልጣኔ የሚመጣው ሁሉም የአገራችን ሕዝብ በውስጡ የተሸሸጉትን ሌቦችና የፖለቲካ ቁማርተኞችን ከመንከባከብ ይልቅ በአንድነት ተነስቶ ማጥራት ሲችል ብቻ ነው:: ይህን ለማድረግ ደግሞ ማኅበረሰቡ መማርና ማወቅ አለበት:: ነገሮችንም በሰከነ መንገድ ሊመለከት ይገባል:: በስሜት መነዳትና ሕጋዊ አሰራሮችን ያልተከተሉትን መንጥሮ መፋረድ ይገባል:: ኃይል ከመጠቀም እና በጭፍን ጥላቻ ከመዋጥ ይልቅ በእውቀትና ሳይንስ ላይ የተመሠረተ አመክንዮ በማቅረብ ወደ ትክክለኛው አውድ መመለስ ይገባል የሚል የፀና እምነት አለኝ::
አዲስ ዘመን፡- በሕግ ዓይን ሲታይ በአሁኑ ወቅት በስፋት የሚሰሙትና በብዛት የሚፈፀሙት ወንጀሎች እንዴት ይዳኛሉ?
አቶ በፍርዴ፡- በአገራችን ከሞላ ጎደል ለየትኛውም ወንጀል መቅጫና ማስተማሪያ የሆኑ ሕጎች አሉ:: ከመደበኛ የወንጀል ሕግ በ1996 ከወጣው ጀምሮ እስከ ጸረ ሽብር አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 1176/2012) በአገሪቱ ሕግ አውጪ አካል ጸድቀው በሥራ ላይ ያሉ አያሌ የወንጀል ሕጎች አሉ:: እንደኔ አመለካከት ችግሩ የሕግ ሽፋን ሳይሆን የአተገባበር ችግር ነው:: በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ በጣም አሰቃቂ ወንጀሎች በቡድንም ሆነ በግል እየተፈጸሙ ይገኛሉ:: ነገር ግን ተጠያቂነት ሲሰፍን አይታይም:: ወንጀል እየበዛ ተጠያቂነት እየቀነሰ ነው:: ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ ወንጀለኞች በየብሔራቸው ጉያ ሥር ስለሚደበቁ ይመስለኛል:: በሌላ በኩል ተጠያቂ የሆኑ ወንጀለኞች በወንጀላቸው ልክ ተጠያቂ እየሆኑ አይደለም::
ብዙ ጊዜ ለፖለቲካ መረጋጋት ሲባል ብዙ ወንጀለኞች ይለቀቃሉ:: አንድ ወንጀለኛ ሲቀጣ ሌላ ተመሳሳይ ወንጀል ለመሥራት ሀሳብ ያለው ሰው ተምሮ እንዲጠነቀቅ ነው:: ይህ የፖለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ ባለች አገር ውስጥ የሚጠበቅ ቢሆንም የሕግ የበላይነትን ማስከበር ግን አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው::
ፍሬ ሃሳቡ ሕግ፣ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ማርቀቅ ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ የሚቀር ጉዳይ አይደለም:: ሕግ ከመሠረታዊ ፅንሰ ሃሳቡ ጀምሮ እስከ አተገባበሩ ድረስ ያለው ጉዳይ ብዙ ጉዳዮችን ያካተተ ነው:: በአንድ አገር ሕግ ሲረቅ መመሪያ ሲወጣ፣ አዋጅ ሲደነገግ የማኅበረሰቡ ንቃተ ሕሊና፣ አገሪቱ ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ፣ ቀጣናዊ ሁኔታዎችና ሌሎች ጉዳዮችም ከግምት ውስጥ ይገባሉ:: ኢትዮጵያም በዚህ አውድ ውስጥ የምትንቀሳቀስ አገር ናት:: ይሁንና አልፎ አልፎ ከዚህ ሁሉ ያፈነገጡ ድርጊቶች ሲስተዋሉ መደናገጥ አይገባም:: ሁኔታዎችን ለማረምና ወደ ትክክለኛው መስመር ለማስገባት አማራጮችን መጠቀም ተገቢ ነው:: በሕግ ዓይን ሲታይ በርካታ አማራጮች አሉ:: ከሥር መሠረቱ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ አንደ አስፈላነቱ ደግሞ ሕግ ገቢራዊ የሚሆንበትን አማራጭ መመከት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እጅግ ፀያፍ ወንጀሎች እየተስተዋሉ ነው:: በተለይም ከሃይማኖትና ባህል በጣም ያፈነገጡ አሉ። ይህን የሚዳኝ ሕግ በኢትዮጵያ አለ?
አቶ በፍርዴ፡- እነዚህን ድርጊቶች የሚዳኙ ሕጎች አሉ:: ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል:: አንደኛው አንድ ሰው እጅግ በጣም ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በሰዎችና በንብረቶች ላይ ለሚፈጸሙ ወንጀሎች መደበኛው የወንጀል ሕግ አለ:: ለምሳሌ አንድ ሰው ሆነ ብሎ ጭካኔ በተሞላበት አገዳደል ሰውን የገደለ ከሆነ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 539 ሥር በዕድሜ ልክ ወይም በሞት ይቀጣል:: ነገር ግን ወንጀሎች በተፈጸሙ ልክ ሥራ ላይ እየዋለ ስለመሆኑ አጠያያቂ ሊሆን ይችላል:: ብዙ ጊዜ አሰቃቂ ሁኔታዎችንና ክስተቶችን እንሰማለን፤ እንመለከታለን:: ነገር ግን በሕጉ አግባብ ፍትሕ እየተበየነ ነው ወይ? ለሚለው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ማግኘት የሚከብድ ይመስለኛል::
ሁለተኛው ሰዎች በግልም ይሁን በቡድን በመሆን ፖለቲካዊ፤ ሃይማኖታዊ ወይም የርዕዮተ ዓለም ዓላማን ለማራመድ ወይም ለማሳካት አሊያም ለማስረጽ ሲባል በሰው ሕይወትና አካል እንዲሁም በንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ ወይም ለማድረስ መሞከር በሽብር ወንጀል እንደሚያስቀጣ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል የወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/20 አንቀጽ 3 እና በተከታይ አንቀጾች ተደንግጓል:: እነዚህን እንደ ምሳሌ አነሳሁ እንጂ ሁሉንም የወንጀል ድርጊቶች ለመዳኘት የተደነገጉ ሕጎች አሉ::
በጥቅሉ ሲታይ ከሃይማኖትም ሆነ ከባህል ያፈነገጡ ድርጊቶች ሲከሰቱ በወንጀል ሆነ በፍትሐብሔር በየደረጃው የተቀመጡ የቅጣት እርከኖች መኖራቸውን መዘንጋት የለበንም:: ይሁንና ማኅበረሰቡ እነዚህን በምን ያክል ይረዳቸዋል የሚለውን ማጤን ይገባል:: የኢትዮጵያ
አብዛኛው ማኅበረሰብ ከመደበኛው እውቀት መስመር ጋር አልተገናኘም:: ይሁንና ውስብስብ ወንጀሎች ደግሞ በስፋት ሲፈፀሙ ይስተዋላሉ:: በመሆኑም ማኅበረሰባችን ከፍ ያለ የሕግ ንቃተ ሕሊና እንዲኖረውና ማንኛውም ወንጀል ከመፈፀሙ በፊት እንዲከላከል ባለድርሻ አካላት በትጋት መሥራት ይጠበቅባቸዋል የሚል ሐሳብ አለኝ::
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ከሕግ ጥሰት ጎን ለጎን የኑሮ ውድነት እየተባባሰ ነው። ዓለም አቀፍ እና አገር አቀፍ መነሻ አኳያ ይህን እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ በፍርዴ፡- ይህን ጉዳይ ጠቅለል አድርገን ስንመለከት ችግሩን ለሁለት መክፈል የሚቻል ይመስለኛል:: አንደኛው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገትና የሕዝብ ቁጥር ዕድገት የሚመጣጠን አይደለም:: የኢኮኖሚ ወይንም የምጣኔ ሃብቱ እድገት በሕዝብ ቁጥር እድገት ልክ ፈጣን አይደለም:: እንደዚህም ሆኖ ላለፉት ሰባትና ስድስት ዓመታት የፖለቲካ አለመረጋጋትና የእርስ በርስ ጦርነት አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል::
በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ከ120 ሚሊዮን በላይ ነው:: ከዚህ ውስጥ አብዛኛው ወጣት ነው፤ ወጣት ደግሞ ትኩስ የሰው ኃይልና ሥራ ፈላጊ ነው:: ይህ ደግሞ በአንድ በኩል ዕድል በሌላ በኩል ደግሞ የአገሪቷ ኢኮኖሚ በዚሁ ልክ ካላመነጨ ትልቅ ሸክምና በሂደት አደገኛ ሁኔታዎችን ሊፈጥር የሚችል ነው:: በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ያለው የወጣቱ ኃይል ቁጥር ጉልበቱ ለአገር እድገት እንዲውል ካልተደረገ ለአገር ጥፋት የማይውልበት ምክንያት የለም:: ምክንያቱም የማንም የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ መሣሪያ ይሆናል:: ስለዚህ የኢኮኖሚ ምጣኔው እና የሕዝብ ቁጥር እድገት የሚመጣጠን መሆን አለበት:: ይህ ደግሞ ከረጅም ጊዜ አንጻር በኢኮኖሚና ሕዝብ ብዛት ምጣኔ ፖሊሲ ሊመራ ይገባል::
የሰለጠነው ዓለም የሕዝብ ብዛትና ኢኮኖሚው እየተናበበ እንዲሄድ በጥንቃቄ ይሠራሉ:: ይህንኑ የሚከታታልና የመፍትሔ አማራጮችን ብሎም ፖሊሲዎችን የሚቀርጽ ራሱን የቻለ አካል አለ:: አዝማሚያዎችን በማየት የመፍትሔ ሃሳቦችን በስፋት ያመነጫሉ:: ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች አገር ብትሆንም ይህን ሃብት በአግባቡ መጠቀም የሚችል ማኅበረሰብ እስካልተፈጠረ ድረስ የሕዝብ ብዛቱን የሚቆጣጠር ጠንከር ያለ አሠራር ሊኖር ይገባል:: ይህን ለመሥራት ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት፣ የመንግሥት አካላትና ጉዳዩ ጉዳዬ ነው ብለው የሚከታተሉ ግብረሰናይ ድርጅቶች ጭምር ተናበው ሊሠሩ ይገባል፡፡
ሁለተኛው ወቅታዊ ችግሮች ናቸው:: እነዚህም ከላይ መግቢያ ላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የፖለቲካ አለመረጋጋትን ተገን በማድረግ የግል ኪሳቸውን ለማደለብ ኅብረት በፈጠሩ ሌቦች የሚከሰት ሰው ሠራሽ የኑሮ ውድነት ነው:: በአሁኑ ጊዜ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ሞልቶ የተረፈ ምርት ባይኖርም ያለችውን በመደበቅ ሕዝቡን ያማርራሉ:: ሌላው ዓለም አቀፍ ክስተቶች ናቸው:: ከሁለት ዓመት በፊት የተከሰተው የኮቪድ በሽታ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ብዙ የዓለም አገራትን ኢኮኖሚ ፈትኖታል:: ይህ ጠባሳ ለመሻገር በራሱ ብዙ ዓመታትን መጓዝና መሥራት ይጠይቅ ነበር፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በዩክሬን እና በራሺያ መካከል የተፈጠረው ጦርነት በተዘዋዋሪም ይሁን በቀጥታ ዱላውን በኛ ላይም አሳርፏል:: ከእነዚህ አገራት በርካታ የአፍሪካ አገራት የዳቦ ቅርጫታቸውን ለመሙላት ሲሉ ስንዴ በስፋት ይሸምታሉ፤ ዘይትንም እንዲሁ በስፋት ይገዛሉ:: በአሁኑ ወቅት ግን የእነዚህ አገራት ጦርነት ሕመሙ መቆሚያ አልተበጀለትም:: የዓለምን ገበያ በእጅጉ እያጋየው ይገኛል:: በተለይም ደግሞ በኢኮኖሚው ያልፈረጠመው የአፍሪካ አህጉር እጅግ በከፍተኛ ደረጃ እየተጎዳ ነው:: ይህ ደግሞ ከኮቪድ ተፅዕኖ ጋር ተጨምሮ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው:: ስለዚህ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከውስጥም ከውጭም ትልቅ ፈተና ገጥሞት ይገኛል:: አሁን ያለው የኑሮ ውድነት ሲታይ በሰው በውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎች መካከል ያለ ሲሆን የውጭው ጫና የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ እና እንቅስቃሴ ከግምት ውስጥ በማስገባት መቋቋም ይገባል:: ውስጣዊ ችግሩን ደግሞ ጠንከር ባለ የሕግ አግባብ፣ ቁጥጥርና ክትትል ብሎም ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ማቃለል የሚቻል ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኑሮ ውድነት የሚያባብሱ ነጋዴዎች፣ ባለሃብቶችና የሚመለከታቸው አካላትእንዴት ይዳኛሉ?
አቶ በፍርዴ፡- የንግድ ውድድርን ለመቆጣጠር እና ለሸማቾች ጥበቃ ለማድረግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 813/2006 ይህን ለመከላከል ከሚያግዙትን መካከል አንዱ ነው:: ስግብግብ ነጋዴዎች ሰው ሠራሽ የኑሮ ውድነት ለመፍጠር ምርቶችን ሲደብቁ በሕገ ወጥ መንገድ ሲያከማቹ የሚዳኙት በዚሁ አዋጅ ነው::
ሸማቹ ኅብረተሰብ የሕግ ጥበቃ ያስፈልገዋል:: ነገር ግን በተደራጀ መንገድ ስለሚሠራ አዋጁ በሚፈለገው ልክ ሥራ ላይ እየዋለ ነው ለማለት አያስደፈርም:: በሌላ በኩል የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 እና በ2013 ዓ.ም እንደገና ተሻሽሎ የወጣው የንግድ ሕግም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለያዝነው ጉዳይ ያገለግላሉ:: ትልቁ ጉዳይ እነዚህን ሕጎችና አዋጆች በተግባር እንዴት እየተፈፀመ ነው የሚለው ነው:: በዚህ ላይ ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈፃሚው እና ሕግ ተርጓሚው አካል ምን ያክል ተናበው እየሠሩ ነው የሚለው ይሆናል:: በሌላ በኩል ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን መሰል ሰው ሠራሽ ችግሮችን በማጋለጥ የሚሄዱት ርቀትና የሚኖራቸው ሕጋዊ ከለላ እስከምን ድረስ ነው የሚለውን መመርመር ይገባል:: ሕጎች፣ ድንጋጌዎች እና አዋጆች ብቻቸውን ችግሮችን ለመቋቋም አያስችሉም::
አዲስ ዘመን፡- የሚወጡ ሕጎች የኑሮ ውድነትንና ያልተገባ ጥቅምን ማጋበስ በመከላከል ረገድ ውጤታማ ናቸው ማለት ይቻላል?
አቶ በፍርዴ፡– እኔ እስከምረዳው ድረስ ችግሩ ያለው ሕጎቹ ላይ ነው ለማለት ያስቸግረኛል:: ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ ሌብነት የሌለበት የመንግሥት መዋቅርና የሥራ ዘርፍ የለም:: ለምሳሌ እነዚህ ሕጎች ከአምስት ዓመት በፊት ነበሩ:: ነገር ግን ያኔ የኑሮ ውድነቱ እንደዚህ ጣርያ አልነካም ነበር:: ስለዚህ ሕዝብና መንግሥት በመተባበር ሌብነት ላይ ካልዘመቱ አዳዲስ ሕጎችን ብቻ በማውጣት የኑሮ ውድነትን መቀነስ አይቻልም::
አዲስ ዘመን፡- የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲፈጠር በማድረግ ረገድ የአገሪቱ ሕግና አዋጆች ምን ላይ ማተኮር አለባቸው? ምን ይጎድላቸዋል? ምን ጠንካራ ነገር አላቸው?
አቶ በፍርዴ፡– ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት አሁን በዚህ አገር ያለው ችግር የሕጎችና የአዋጆች አይደለም:: በሥራ ላይ ያሉትን ሕጎችና አዋጆች በቅጡ ሥራ ላይ ሳናውል ስለጉድለታቸው መገምገም ምንም ፋይዳ የለውም:: ለመረዳት ያግዝ ከሆነ ብዙ ክፍተቶች ሊኖሩ ይችላሉ:: መሠረታዊ ጉዳዩ ግን ከእነክፍተቱም ቢሆን ምን ያህል ተግባራዊ እየተደረጉ ነው የሚለው ነው:: የሚረቀቁ ሕጎች የማኅበረሰቡ የንቃት ሕሊና ደረጃ፣ የሕግ አፈፃፀምና አጠቃላይ አገራዊ ሁኔታዎች አንዱ ከሌላው ጋር የሚነጣጠሉ አይደሉም:: በመሆኑም አንዱን ለማሻሻል ሌላውንም ማሻሻል ተገቢ ነው::
አዲስ ዘመን፡- የኑሮ ውድነት መባባስና የሕግ ጥሰቶች መባባስ ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው?
አቶ በፍርዴ፡- በጣም ግንኙነት አላቸው:: ምክንያቱም አብዛኛው የኑሮ ውድነት ሰው ሠራሽ ነው:: ሰው ሠራሽ የኑሮ ውድነት ደግሞ የሚከሰቱት ሕጐችን በመጣስ ነው:: ስለዚህ የሕግ ጥሰቶች ባይኖሩ የኑሮ ውድነቱ ባይጠፋም እንኳን ይቀንሳል:: በመሆኑም የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የሕግ ጥሰቶችን መቆጣጠር እጅግ አስፈላጊ ነው ብዬ እገምታለሁ:: ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ግን በተወሰኑ አካላት ብቻ የሚሳካ አይደለም:: በመንግሥት መዋቅር የተመለከትን ከሆነ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ላይኛው እርከን ድረስ የተናበበ አሠራር መኖር አለበት:: እንደ ማኅበረሰብ የሕግ ጥሰት የሚፈፅሙትን የሚፀየፍና አሳልፎ ለሕግ አካላት የሚሰጥ መሆን አለበት:: ጥፋቶችንም በተገቢው የሚዳኙበት አሠራር ወጥነትና ሐቀኝነት በተሞላው መንገድ ሊቀረፁና ሊተገበሩ ይገባል::
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የሚስተዋለው የክልል መንግሥታት እና የፌደራል መንግሥት መስተጋብር እና ትስስር አሁን ለሚስተዋለው የአገሪቱ ችግር ምክንያት ናቸው ማለት እንችላለን?
አቶ በፍርዴ፡- አንድ ክልል ከሌላው ክልል ጋር ያለው መልካም ትስስር ለአገሪቱ ሰላም በጎ አስተዋጽኦ አለው:: በተቃራኒው በክልሎች መካከልም ሆነ በፌዴራልና በክልሎች መካከል በክልሎችና በፌዴራሉ ሕገ መንግሥቶች ላይ የተመሠረተ ትብብር ከሌለ አሁን የምናየው ውጥንቅጥ መፈጠሩ አይቀርም:: ወደፊትም በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ችግሮች መኖራቸው ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው:: ስለዚህ በነዚህ አካላት መካከል ያለው ግንኙነት በሕግና በሕዝቦች ወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት:: በክልል መንግሥታት አሊያም በፌደራል እና ክልል መንግሥታት መካከል ያለው ግንኙነትም በዘፈቀደ የሚመራ ወይንም በጥቂቶች ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን ሕጋዊና ተቋማዊ መዋቅር ወይም መሠረት ያለው መሆን አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡-በቀጣይ የተረጋጋች አገርና ኢኮኖሚ ያላት አገር ለመፍጠር ምን መሠራት አለበት?
አቶ በፍርዴ፡- ሁሉንም ያሳተፈ ብሔራዊ ምክክር በቶሎ መደረግ አለበት:: ምክክሩ ግን መፍትሔ የማያመጡ አደናቃፊ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድ የተቃናችና ከኋላቀርነት የተላቀቀች አገርን ለማስረከብ የታለመ መሆን አለበት:: ባለፉ ትርክቶች ላይ በመመሥረት ከመቆራቆዝ በመውጣት ብሩህ ተስፋ ያላት አገርና ትውልድን የሚገነባ አዲስ እሳቤ መምጣት አለበት:: የዘውጌ አስተሳሰቦችን በመግራት የኢትዮጵያ አንድነት የሚጠናከርበት በዚያው ልክ ደግሞ የብሔር ብሔረሰቦችና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሥርዓቱ የሚከበርባት አገር መፍጠር ላይ ማተኮር ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ተጨማሪ መልዕክት ካለዎት?
አቶ በፍርዴ፡– ያለኝ መልዕክት አንድ ብቻ ነው:: ኢትዮጵያ ከብዙ ትውልዶች በቅብብሎሽ ለእኛ የተላለፈች አገር ነች:: አባቶቻችን ያስረከቡንን አገር የበለጠ አቃንተን አበልጽገን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባናል እንጂ የፈረሰች አገር ማስረከብ አንችልም:: የፊተኞች ነበርን አሁን የኋለኞች ሆነናል:: ያለፈው ትውልድ ለእኛ ያሰበልንን ግማሽ ያህል እንኳን ለቀጣዩ ትውልድ እናስብ የሚል ሃሳብ አለኝ::
አዲስ ዘመን፡- የዝግጅት ክፍላችን እንግዳ ሆነው በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያለዎትን ሙያዊ ሐሳብ ስላካፈሉን እናመሰግናለን፡፡
አቶ በፍርዴ፡– እኔም የዝግጅት ክፍላችሁ እንግዳ በመሆኔ ደስተኛ ነኝ አመሰግናለሁ::
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2014