ኢትዮጵያ ከሜልቦርን እስከ ቶክዮ ኦሊምፒክ በተሳተፈችባቸው መድረኮች 23 የወርቅ፣ 12 የብርና 23 የነሐስ በድምሩ 58 ሜዳሊያዎችን መሰብሰቧ ይታወቃል:: ከእነዚህ ውስጥ 22 የሚሆኑት (8 የወርቅ፣ 4 የብር እና 10 የነሐስ) ሜዳሊያዎች በሴት አትሌቶች የተመዘገቡ ናቸው:: በቶኪዮው የ2020 ፓራሊምፒክም በ1ሺ500 ሜትር በአትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ ለመጀመሪያ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ መገኘቱ ይታወሳል::
አትሌቲክስ እግር ኳስ ስፖርቶች እንደማሳያ ተነሱ እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በበርካታ ስፖርቶች በአንጻራዊነት በሴቶች የሚመዘገበው ውጤትና ተሳትፎ እያሻቀበ ይገኛል:: በእግር ኳስ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ከጫፍ ደርሶ የነበረበትን ሁኔታም እዚህ ሊጠቀስ ይገባዋል:: ይኸውም በተለያዩ የስፖርት ማኅበራት በሚደረጉ አህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የሴት ብሔራዊ ቡድኖች ተወዳዳሪነት በግልጽ እየታየ ይገኛል::
ይህ የሚያሳየውም በሴቶች ስፖርት ጥቂት በመሥራት ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ነዉ:: ከዚህ እውነታ በመነሳት፣ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እንዲሁም የውድድር መድረኮችን በማስፋት ሴቶች የመወዳደር እድል እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ የመላ ኢትዮጵያ ሴቶች ውድድር ራሱን ችሎ እንዲካሄድ ተደርጓል::
ከመደበኛ ዓመታዊ ውድድሮች ባለፈ ሴቶችን ብቻ ማዕከል አድርገው በተለያዩ ስፖርቶች መሰል ውድድሮችን ማድረግ በሌሎች ዓለማትም የተለመደ ነው::
በአሜሪካ እአአ ከ1987 ጀምሮ በጥር ወር መጨረሻ የሴቶች ስፖርት ቀን በሚል ውድድሮች ይካሄዳሉ፤ ውድድሮቹ ታላላቅ ሴት ስፖርተኞችን የሚዘክሩና ዕውቅና የሚሰጡ ናቸው፤ ሌሎች የተለያዩ መርሐ ግብሮችንም ማንሳት ይቻላል::
በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ መርሕን መሠረት አድርገው ከሚካሄዱ ጥቂት ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ውድድር ዘንድሮ ለ4ኛ ጊዜ እየተካሄደም ይገኛል:: ይህ የመላ ኢትዮጵያ ሴቶች ውድድር በኮቪድ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ተቋርጦ የቆየ ሲሆን፤ ዘንድሮ በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሃዋሳ ከተማ ከሚያዝያ 01 ጀምሮ እስከ 10/2014 ዓም እየተካሄደ ነው::
በውድድሩ ስድስት ክልሎችንና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች ተወካዮቻቸውን እያሳተፉ ቢሆንም የተቀሩት ግን በወቅታዊና ሌሎች ችግሮች ምክንያት አለመካፈላቸውን በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የውድድርና ስልጠና ዳይሬክተር ወይዘሮ አበባ አማረ ይጠቁማሉ:: ውድድር እየተካሄደባቸው ያሉ ስፖርቶችም አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ቮሊቦል፣ ዳርት፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቼስ፣ ፓራሊምፒክ፣ መስማት የተሳናቸው ዊልቸር ቅርጫት ኳስ እንዲሁም የባህል ስፖርቶት ናቸው:: ቁጥራቸው ከአንድ ሺ በላይ የሚሆኑ ስፖርተኞችና አሰልጣኞቻቸውም በዚህ ውድድር ላይ ተካፋይ ናቸው::
ከዚህ ቀደም ከስፖርተኛ ተገቢነት ጋር በተያያዘ ይነሳ የነበው ቅሬታ ለማስወገድም በዚህ ውድድር 10 ከመቶ የሚሆኑ ተሳታፊዎች ከክለቦች፣ ከስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ውድድሮች ከተሳተፉ ስፖርተኞች ተካፋይ እንዲሆኑ ተደርጓል:: ከዚህ ባለፈ ያሉት 90 ከመቶ የሚሆኑ ተወዳዳሪዎች ተተኪ ስፖርተኞች መሆናቸውንም ነው ዳይሬክተሯ የጠቆሙት:: በዚህም ተተኪ ስፖርተኞች ልምድ ካላቸው ጋር ልምዳቸውን እንዲለዋወጡ ከማገዝ ባለፈ ለውጤታማነትም የራሱ ሚና ይኖረዋል ይላሉ::
እንደአገር በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች በተለይ በሴቶች በኩል የተሻለ ውጤታማነት እየታየ መሆኑን የሚያነሱት ዳይሬክተሯ፣ ለስፖርተኞቹ ግን የተለየ እገዛ እየተደረገላቸው አለመሆኑን ይጠቁማሉ::
በዚህ መልኩ ውጤታማ ከሆኑ ደግሞ በአህጉርም ሆነ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በይበልጥ ስኬታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ለማድረግ ጥቂት የውድድር ዕድል ሊፈጠርላቸው እንደሚገባ አመላካች ነው:: በመሆኑም በየስፖርት ዓይነቱ ከሚካሄዱት መደበኛ ውድድሮች ባለፈ የውድድር መድረክ እንዲያገኙ ውድድሩ ይካሄዳል:: ሌላው ውድድሩን ተከትሎ ሚኒስቴሩ ለክለቦች እንዲሁም ለስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላት ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፤ በውድድሩ ስፍራ ተገኝተው ስፖርተኞችን ለመመልመልም አመቺ ይሆናል::
ከውድድሩ ጎን ለጎን ሲምፖዚየም፣ ማኅበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች እንዲሁም ከጾታዊ እኩልነት ጋር በተያያዘ ግንዛቤ የማስጨበጥ መርሐ ግብሮች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ነው ዳይሬክተሯ የገለጹት::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5 /2014