የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን በየአመቱ ከሚያካሂዳቸው ትልልቅ የውድድር መርሃግብሮች አንዱና ዋነኛው የሆነው የኢትዮጵያ ውሃ ዋና ቻምፒዮና ከትናንት በስቲያ በቢሾፍቱ ከተማ ተጀምሯል። በመኮንኖች ክበብ የመዋኛ ገንዳ እየተካሄደ የሚገኘው የ2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ ክለቦችና ክልሎች ውሃ ዋና ቻምፒዮና በወጣትና ልምድ ባላቸው ዋናተኞች መካከል በተለያዩ የውድድር አይነቶች ጠንካራ ፉክክር እያስተናገደ ይገኛል።
በውድድሩ የአማራ፤ የጋምቤላ እና የሲዳማ ክልሎች ተሳታፊ ሲሆኑ የድሬዳዋ ከተማ እና የቢሾፍቱ ከተማ ተወዳዳሪዎችም በተለያዩ ፉክክሮች ተሳታፊ ናቸው።
በክለብ ደረጃ ዳዊት እምሩ የህንፃ ተቋራጭ፤ ሳምሶን ውሃ ዋና ስፖርት ክለብ እና ኦሮሚያ ፖሊስ የሚሳተፉ ሲሆን አቻላ ያኮቤ በግል ተወዳዳሪ በመሆን አቅርቧል።
የውሃ ዋና ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰረት ደምሱ ውድድሩ በዋነኛነት ሁለት ዓላማዎችን ይዞ እንደሚካሄድ ገልጸዋል። ውድድሩ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የውሃ ዋና ስፖርተኞች ያሉበትን ወቅታዊ ብቃትና ደረጃ ለመለየት እንደሚረዳ የጠቆሙት ወይዘሮ መሰረት፣ በውድድሩ ጥሩ ብቃትና አቅም ማሳየት የቻሉ ስፖርተኞች በቀጣይ ለሚከናወኑ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ኢትዮጵያን እንዲወክሉ ለመመልመል እንደታሰበ አስረድተዋል።
“የስፖርት ልዩ ባህሪያት ሰላምን ለማስፈን ፣ መቻቻልን ፣ ሕግ መክበርን፣ አገርን መውድድን፣ የማሕበራዊ እና የልማት ትስስርን ለመፍጠር ትልቅ አቅም አለው” ያሉት ፕሬዚደንቷ ይህ ቻምፒዮናው የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት ፣ ለ2022 አህጉራዊና ዓለም አቀፍዊ ቻምፒዮና አገራችንን በመወከል ምርጥ ስፖርተኞች የሚመረጡበት ስለሆነ ተወዳዳሪዎች ጠንክረው በመወዳደር አቅማቸውን ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
በውድድሩ የመክፈቻ ሥነሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የቢሾፍቱ ከተማ አፈጉባኤ ወይዘሮ ሎምሸት እንዳለ በበኩላቸው “ከተማችን ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ተቻችሎ ፣ ተከባብሮ በእኩልነት የሚኖሩበት ፣ የሰባት የተፈጥሮ ሀይቅ ባለቤትና የቱሪስት መዳረሻ ከተማ ስለሆነች ከተለያዩ ክልሎች እና ከተማ መስተዳድሮች የመጣችሁ ልዑካን ቡድን እንኳን በሰላም መጣችሁ በማለት” በቆይታቸው ከጎናቸው እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
በውድድሩ መክፈቻ እለት ከባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከውሃ ዋና ስፖርቶች ፌዴሬሽን ሃላፊዎች የተገኙ ሲሆን በሁለቱም ፆታች በተለያዩ ዘርፎች ስምንት የማጣሪያ ውድድሮች ተከናውነዋል።
ቻምፒዮናው በተለያዩ የውድድር አይነቶች በሁለቱም ፆታ በነፃ ቀዘፋ፣ በጀርባ ቀዘፋ፣ በደረት ቀዘፋ፣ በቢራቢሮ ቀዘፋ፣ በድብልቅ ቅብብል ፣ በነፃ ቅብብል፣ በቅልቅል- ድብልቅ ቅብብል፣ በቅልቅል- ነፃ ቅብብል እና በግል ድብልቅ የፉክክር አይነቶች የሚካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቀልቤሳ ኤባ ገልጸዋል።
በውድድሩ መክፈቻ እለት በተደረገው የ200 ሜትር ነፃ ቀዘፋ ሴቶች የፍፃሜ ውድድር አማራ ክልል 1ኛ፣ ኦሮሚያ ፖሊስ 2ኛ እና ቢሾፍቱ ከተማ 3ኛ በመሆን ማጠናቀቅ ችለዋል።
‘’ስፖርት ለሰላም ለህብረ ብሔራዊ አንድነት’’ በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው የ2014 ዓ.ም የክልሎች እና የክለቦች የውሃ ዋና ቻምፒዮና እስከ ሚያዝያ 8/2014 ዓ.ም በተለያየ የውድድር አይነቶች በርካታ ፉክክሮችን አስተናግዶ አሸናፊዎቹ የሚለዩ ይሆናል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2014