የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ክብርን በተደጋጋሚ በመጎናጸፍ እንደርሱ የደመቀ ተጫዋች የለም። እርሱ ተጫዋች በነበረበት ዘመን ከዓለም ምርጥ የመሃል ሜዳ ተጫዋቾች መካከል ተጠቃሽ ሲሆን፤ ታላቁ ብራዚላዊ የእግር ኳስ ሊቅ ፔሌ ከፊፋ ምርጥ ተጫዋቾች መካከል አንዱ መሆኑን ድምጹን በመስጠት አስመስክሮለታል። ለአገሩ ብሄራዊ ቡድን ተሰላፊ ሆኖ በርካታ ታሪኮችን ከማጻፍ በዘለለ ከሆላንድ፣ ስፔን፣ ጣሊያን እና ብራዚል ክለቦች ጋር በተጫዋችነት ስኬታማ ጊዜያትን አሳልፏል። ጫማውን ከሰቀለ በኋላም ወደ አሰልጣኝነቱ ጎራ በማለት የጣሊያን፣ የቻይና፣ የስፔን እና ካሜሮን ክለቦችን መርቷል። በሆላንድ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ታሪክ ምርጥ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ክላረንስ ሴዶርፍ ዛሬ መዳረሻውን አዲስ አበባ ላይ አድርጓል።
ሴዶርፍ እአአ 1976 እግር ኳስን የሙጥኝ ባለ ቤተሰብ ውስጥ ተወለደ፤ ሁለቱ ታላላቅ ወንድሞቹ እግር ኳስን ሲያዘወትሩ አባታቸው ጆን ሴዶርፍም የቀድሞ ተጫዋች ነበሩ። ይህም ትንሹን ሴዶርፍ ወደ እግር ኳስ ያስገባው ሲሆን፤ በ6 ዓመቱ በሚኖርበት አካባቢ የሚገኘውን የእግር ኳስ ማሰልጠኛ ማዕከል ተቀላቅሏል። ከቆይታ በኋላም እንደወንድሞቹ ሁሉ እርሱም የአያክስ ወጣቶች አካዳሚን በመቀላቀል በስልጠና ላይ ቆይቶ እአአ በ1992 የመጀመሪያ ጨዋታውን አካሄደ። በወቅቱ የክለቡ ትንሹ ተጫዋች እርሱ ይሁን እንጂ በአሰልጣኙ ዘንድ ቀዳሚ ተመራጭ ለመሆን ጊዜ አልፈጀበትም።
የክለቡ ቁልፍ የመሃል ሜዳ ተጫዋች በመሆን በቆየባቸው ዓመታትም ከክለቡ ጋር በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችሏል። ከእነዚህ መካከል በ35ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በመግባት ለክለቡ ባበረከተው አስተዋጽኦ የጣሊያኑን ኤሲሚላንን በመርታት እአአ የ1995 የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ማንሳቱ ተጫዋቹ በክለቦች ዓይን እንዲገባና የምርጥ ተጫዋችነት ሕይወቱ ይበልጥ እንዲያብብ ምክንያት ሆኗል። በቀጣዩ ዓመት የሴሪኤ ውን ክለብ ሳምፕዶሪያን ቢቀላ ቀልም ቆይታው ግን ከአንድ ዓመት የዘለለ ሊሆን አልቻለም።
በመሆኑም ክለቡን ከተሰና በተ በኋላ ወደ ስፔን በመሻገር በሪያል ማድሪድ ማሊያ በላሊጋው ታየ፤ በመጀመሪያው ዓመት ቆይታውም የላሊጋውን ዋንጫ ከክለቡ ጋር በመሆን ለማንሳት ችሏል። በነጫጮቹ ቤት በነበረው የሶስት ዓመታት ቆይታ በጥቅሉ አራት ዋንጫዎችን ሲያነሳ፤ እአአ 1998 ያሳካው የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ነበር። ተጫዋቹ ከሁለት ክለቦች ጋር ትልቁን ዋንጫ በማስመዝገብ ስኬቱን ማጣጣም ችሏል። እአአ የ1999/2000 የውድድር ዓመትም ከክለቡ ጋር በመለያየት ፊቱን ዳግም ወደ ጣሊያን በማማተር፤ በ23 ሚሊዮን ዩሮ የኢንተር ሚላን ንብረት ለመሆን ቻለ። ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ ግን ሌላኛው የጣሊያን ክለብ የኤሲሚላን ተጫዋች ሆነ።
በቀጣዩ ዓመትም ለክለቡ ከ26 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያ የሆነውን የኮፓ ጣሊያን ዋንጫ በማንሳት የታሪኩ አካል ለመሆን በቃ። በእግር ኳስ ሕይወቱ የተሻለ ጊዜን ባሳለፈበት ክለብ በዚያው ዓመት የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን የክለቡ ንብረት ለማድረግ በቃ። ይኸውም ተጫዋቹ በሶስተኛ ክለቡ ያገኘው የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ሲሆን፤ በታሪክ ብቸኛው ተጫዋች እንዲባልም ምክንያት ሆነው። ቀጣዩን ዓመትም የሴሪኤውን ዋንጫ በማንሳት ስኬቱን ቀጥሎ ከአራት ዓመት በኋላ በእግር ኳስ ታሪኩ አራተኛውን የአውሮፓ ቻምፒዮስ ሊግ ዋንጫ ከክለቡ ጋር አነሳ። በዚህ ወቅት የእርሱ ሚና እጅግ ከፍተኛ ሲሆን፤ በዚያው ዓመት የሱፐርካፕ ዋንጫን በማንሳት በክብር ላይ ክብርን ለመጎናጸፍ ቻለ። ይኸውም በፊፋ እና በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ምርጥ ተጫዋችነት ምርጫ ውስጥ በመካተት የወቅቱ ምርጥ የመሃል ተጫዋች ተሰኘ።
በኤሲሚላን ቤት ለአስር ዓመታት ቆይታ ያደረገው ክላረንስ ሴዶርፍ በእግር ኳስ ሕይወቱ ይበልጥ የሚታወቀው በቻምፒዮንስ ሊግ ስኬቱ ነው። እአአ 2012 የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ 20ኛ ዓመቱን ባከበረበት ወቅትም ምርጥ በሚል በደረጃ ካስቀመጣቸው 20 ተጫዋቾች መካከል ሴዶርፍ ሰባተኛ ላይ ይገኛል። ይህንን ተከትሎም የዘንድሮው የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ጉብኝት በተጫዋቹ ይታጀባል። ዋንጫው መዳረሻ ካደረጋቸው ጥቂት የአፍሪካ ከተሞች መካከል አንዷ የሆነችው አዲስ አበባም ዛሬ እንግዳዋን ትቀበላለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 2 ቀን 2014 ዓ.ም