ኢትዮጵያዊ ማህበረሰባዊ እሴቶቻችን፣ የእርስ በእርስ መከባበራችንን የሚያጎሉ፣ የአብሮ መኖር ትስስራችንን የሚያደምቁ ትልቅ ሀብቶቻችን ናቸው። ለግል ችግራችን ትልቅ መፍትሔ የሚሆኑ፣ የእርስ በእርስ ግጭትን በዘላቂነት አጥፍተው መፍትሔ የሚያስገኙ በርካታ እሴቶች አሉን። ይሄ ባህላዊ እሴታችን ገብቶንና ተረድተነው ብንጠቀምበት በእርግጥም ከማንም በላይና በፊት ተጠቃሚዎቹ እኛው ነን። የራሳችንን ችግር በራሳችን መፍታት የምንችልበት ድንቅ እሴት እንዳለን ብዙ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል።
በሁሉም ማህበረሰባችን ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውና ለችግሮች ሁነኛ መፍትሔ የሚያመላክቱ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓትና የዛሬን ዘመን ቀድመው ሲተገበሩ የነበሩ ባህላዊ የአስተዳደር ስርዓቶች፣ እርስ በእርስ የሚያስተሳስሩ አብሮነትን የሚያበረታቱ ልማዶች፣ ልዩ ልዩ ወጎች፣ ትፊታዊ ክንውኖችና ሀገረሰባዊ ትውን ጥበባት መጥቀሱ በቂ ነው። ከወራት በፊት መዲናችን የባህል ሳምንት ስታከብር የባህል ሳምንቱን ለመታደም ተገኝተን ነበር። በባህል ዓውደ ርዕዩ ላይ ያገኘነው የጋሞጎፋ ዞን ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ባለሙያ የሆነው ወጣት ዲያቆን ጮሎ በብሄረሰቡ ልብስ ተውቦ ባህሉን ሲያስተዋውቅ አገኘነውና መቅረፀ ድምፃችንን ይዘን ተጠጋን።
አላሳፈረንም፤ በትህትና ተቀብሎ የትወልድ ቀዬው ወግ፣ ልማድ፣ አጠቃላይ የሆነ የጋሞን ብሄረሰብ ዋና ዋና መገለጫዎች የተመለከቱ መረጃዎችን እንካችሁ ለአንባብያን ብሎናል። ወጣት ዲያቆን እንደነገረን በደቡብ ኢትዮጵያ ጋሞ ጎፋ ዞን የሚገኘው የጋሞ ብሄረሰብ በጠንካራ የስራ ባህል ይታወቃል። የብሄረሰቡ መግባቢያ ቋንቋ ‘ጋሞቾ’ ይባላል።የሽመና ስራ በሀገር ደረጃ የሚወደስበትና ጠቢብ መሆናቸው ያስመሰከሩበት ለአንዳንድ የብሄረሰቡ አባላት መተዳደሪያም
ጭምር ነው። ጋሞዎች አርሶአደርና ከፊል አርብቶ አደር ናቸው። የተለየዩ ሰብሎችና ጥራጥሬዎች ያመርታሉ። መልክዓ ምድሩ ተራራማ ሲሆን፤ ቆላ፣ ደጋና ወይናደጋ የአካባቢው የአየር ንብረት መገለጫ ነው። ለምለም የሆነው የጋሞ ምድር ዓመቱን ሙሉ ሳያቋርጥ ምርት ይሰጣል። ጋሞዎች የሰላም አምባሳደሮች ናቸው። በእርጥብ ሳር በቁጣንና የጋለን ስሜት የሚያበርዱ ፀብንና በጥበብ ወደ ሰላም የሚቀይሩ ድንቅ ህዝቦች ናቸው። አንድ ሰሞን በሰላም ጠሎች በተሸረበ ሴራ ቡራዩ ላይ በተፈፀመው ጥቃት መላ ኢትዮጵያዊያንን አሳዝኖ ያለፈ ክስተት እንደነበር አይዘነጋም።
በዚያን ወቅት ደቡብ ክልል ጋሞ ዞን ላይ ወጣቶች ተቆጥተው ተቃውሟቸውን ለመግለጽ አደባባይ ወጥተዋል። በደሉ ያንገበገባቸው፣ የተፈፀመው አስነዋሪ ድርጊት ያስቆጣቸው ወጣቶች ዳግም ስህተት እንዳይፈፅሙ የጋሞ አባቶች ወጣቶቹ ወደ ጥፋት እንዳያመሩ እርጥብ ሳር ይዘው ጥፋትን የተከላከሉበት መንገድ ከሁላችንም አዕምሮ የማይጠፋ ክስተት ነበር። በጋሞ ባህል የታነጹ ወጣቶች አባቶችን አክብረው ከጥፋት ታቅበዋል።
ይህ ድንቅ የሆነ ባህል የወለደው ሀገራዊ እሴት ነው። ጋሞ ባህሉን ጠንቅቆ የሚረዳ ለባህሉ ክብር መስጠቱን ያረጋገጠበት ልዩ አጋጣሚም ነበር። ማህበረሰብን የሚለውጥ ባህል ህብረተሰብ የሚያንጽ እሴት የተላበሱ ናቸው ጋሞዎች። ለሰላም መፍትሔና ግጭትን መግቻ የሆነው ሀገረሰባዊ ድንቅ ባህላችን ድንገት በሚገጥመን ሁነት ጎልተው ወጥተው ሲታዩ እንጂ ጥናት ተደርጎባቸው ለጥቅም እንዲውሉ ሲሠራ ለማየት አልታደልንም። ባህልና እሴቶቻችን ላይ ጥናት ተደርጎ ፋይዳቸው ተለይቶ ለጥቅም በማዋል ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንደሚኖረው እሙን ነው። የጋሞ ሽማግሌዎች ለሰላም ዘብ በመሆን የተጠቀሙበት ድንቅ ባህላቸው ለዚህ ተጠቃሽ ነው። ጋሞዎች ባህላቸው የፈጠረላቸውን በጎ እሴት ጥፋትን ሲከላከሉበት ተመልክተን ተደንቀናል።
ለዘመናት የቆየ ዘመን ተሻጋሪ በትውልድ የሚከበር ድነቅ ባህል እንዳለቸውም መመስከር ያስችላል። ለሀገር ሽማግሌ ከምንም በላይ ክብር በመስጠትና ታዛዥ በመሆን የሚታወቁት ጋሞዎች በራሳቸው የተበጀ ስርዓት ባለው መልኩ ተዋረዱን የጠበቀ ባህላዊ የአስተደዳር ስርዓት አበጅተው ለረጅም ዘመናት እራሳቸውን በራሳቸው ስያስተዳድሩ የኖሩ ብሄረሰቦች መሆናቸውን ያስረዳል። ይሄም ኢትዮጵያ በማዕከላዊ መንግሥት አስተዳደር ስር መመራት እስከጀመረችበት ዘመን ቀጥሎ ነበር።
ንጉሣዊው የአስተዳደር ስርዓት የነበራቸው ጋሞዎች ለብዙ ዘመናት ባህላቸው በወለደላቸው ስርዓት ተመርተው ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በብሄረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው የሚከበርና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የብሄረሰቡ ንጉሥ “ካዎ” ይባላል። ካዎ (የጋሞ ንጉሥ)፡- ከፍተኛ የስተዳደር እርከን ነው። ሰዎች ከፍተኛ ወንጀል ሠርተው የሚዳኙትና የጎሳዎች ግጭት መፍትሔ የሚያገኙት በካዎ ነው። ለማህበረሰቡ ጥላና መከታ ነው ተብሎም ይታሰባል። የንግሥና ስልጣኑ የተለየ ጉዳይ ካልገጠመው በቀር ሲሞት ለልጁ የሚያወርሰው ተወራራሽ ስልጣን ነው። ከሱ በታች ያሉት ደግሞ በማህበረሰቡ ምርጫና ጥቆማ በንጉሡ ይሾማሉ።
“ካዎ” ወይም ንጉሡ ሁለት ስልጣን ያላቸውና የሱን ትዕዛዝና አዋጅ ለሌሎች የሚነግሩለት ሹመኞች ያሉት ሲሆን የፖለቲካውን ዘርፍ የሚመራው “ኡዱጋ” የተባለ ከንጉሡ ቀጥሎ ያለ የበላይ ስልጣን ባለቤት ሲሆን በዚሁ ደረጃ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን የሚመራው “ማጋ” የተሰኘ የሃይማኖት መሪ ሌላኛው ከንጉሡ ቀጥሎ ስልጣን ያለው አካል ነው። ኡዱጋ፡- በስልጣን የመቆያ ጊዜው የተገደበ ሲሆን ለመመረጥም አካባቢው ላይ ጥሩ ሀብትና ንብረት ያለው፣ በስነ ምግባሩ የተመሰገነ፣ በጦር ሜዳ ውሎው ጅግንነት የተላበሰ ማህበረሰቡ የተቀበለው መሆን ይጠበቅበታል። በየ ዓመቱ ህዝብን እየጠራ ደግሶ ማብላትና የስልጣን ዘመኑ ጥጋብ የበረከተበት
መልካም ነገር የሞላበት ዘመን መሆኑን ማስመስከር ይኖርበታል። ነገር ግን ደግሶ የማብላቱና የስለጣኑ ሐላፊነት ከባድ ስለሆነ በዚህ ስልጣን የሚቆየው እጅግ ላነሰ ጊዜ ነው። ከንጉስ ካዎ የመጣውን ትዕዛዝ ለማህበረሰቡና ለአካባቢያዊ መሪዎች ማስተላለፍ፣ የአካባቢ መሪዎችን መቆጣጠር፣ለንጉሡ የማይቀርቡና ከታችኛው የአስተዳደር አቅም በላይ የሆኑ የፍትህ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ መስጠትና ለንጉሡ አለኝታነት ማስመስከር ዋንኛ ተግባሩ ነው።
ማጋ፡- ይህ የንጉሡ የቅርብ ዘመድ የሆነና በቤተ ዘመድ የሚሾም ነው። የዚህ ተግባርና ሐላፊነት የተለያዩ መስዋትነቶችን ማቅረብ የህዝቡን ሃይማኖታዊ ስርዓት መምራትና ለሀገር በጎ እንዲመጣ ክፉውን እንዲያርቅ ተግቶ መጸለይ ነው። በጎሳዎች መካከል ግጭት ሲነሳ የማስታረቅና የእርስ በእርስ መግባባት እንዲኖር ከፍተኛ ሚና ይጫወጣል። በማህበረሰቡ ዘንድ እጅግ በጣም የሚከበርና ያለው ነገር ሁሉ የሚፈጸምለት ሃይማኞታዊ ተሻሚ ነው። የሚያንጹት ቤት በቅርጽና ስፋቱ የተለየ ሲሆን ሰፋ ያለ ግቢና ብዙ እንግዶችን ማስተናገድ የሚችል መሆን ይጠበቅበታል። ከእነዚህ ስልጣኖች በተዋረድ የተለያዩ የስልጣን እርከኖች ሲኖሩ ቆቃሚ፣ዳና፣ሁዱጋና የመሳሰሉ
መንደርና አካባቢ የሚመሩ ክፍሎችም አሉ። የእነዚህ ዋንኛ ተግባር ከንጉሥ (ካዎ) የሚመጣን ማንኛውንም ትዕዛዝ ተቀብሎ ለህዝብ ማስተላለፍና እንዲተገበር ማድረግ የህዝቡን ፍላጎት በመለየት ለንጉሡ መልዕክት ማስላለፍና የተወከሉበት መንደር መምራት ነው። በአካባቢው የፍትህ ስርዓቱ የሚመራው በሀገር ሽማግሌዎች ሲሆን በዳይ ተበዳይ ቀርበው የሚሟገቱበት ፍትህ የሚሰጥበት አደባባይ ላይ እንደ ጉዳዩ ግዝፈት ከንጉሡ እስከ ተራው ህዝብ ይካፈላል። ይህ ፍትህ መስጫ አደባባይ ጋራ አደባባይ የሚሰኝ ሲሆን ከፍትህ ስርዓቱ ማስፈፀመያነት በተለየ ንጉሡ ትልልቅ ጉዳዮችን በተመለከተ ከህዝብ ጋር ውይይት ለማድረግና ለመመካከር ይህ አደባባይ “ጋራ” ይጠቀሙበታል።
በፍትህ ስርዓቱ ላይ ጋሞዎች አንድ የተለዩበት የምርመራና የማውጣጣት ዘዴ ተክነዋል። አንድ በዳይ ፍትህ ፊት ቀርቦ የሀገር ሽማግሌዎችን አታሎ የሠራውን ጥፋት ወይም የፈጸመውን ወንጀል አይመለከተኝም የማለቱ ጉዳይ በአውጫጭኙ ይከሽፋል። ይህ “ድንቡሾ” የተሰኘ የአውጫጭኝ ስርዓት አንድን ወንጀለኛ ሰነ-ልቦናዊ ሁኔታን በመቆጣጠርና ጫና በመፍጠር እንዲያምን ያደርገዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 8/2011
ተገኝ ብሩ