
ሌላው በዚህ ሳምንት የሚታወሱት ሰው ደግሞ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ናቸው፡፡ አርቲስቱ ያረፉት ልክ በዛሬዋ ቀን ከአሥርት ዓመታት በፊት ሚያዚያ 2 ቀን 2004 ዓ.ም ነው፡፡
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የተወለዱት በቀድሞው አጠራር ሸዋ ጠቅላይ ግዛት፤ በአሁኑ ሰሜን ሸዋ በምትገኘው አንኮበር ጥቅምት 13 ቀን 1925 ዓ. ም ከአባታቸው አቶ ተክሌ ማሞ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ፈለቀች የማታወርቅ ነው፡፡
የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ፣ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርታቸውን በእንግሊዝ አገር በሚገኘው የሥነ ጥበብ አካዳሚ በሥነ ስዕል በቅርፃ ቅርጽና በሥነ ሕንፃ ዲዛይን ተከታትለዋል፡፡
በነበራቸው የሥነ ስዕል ዝንባሌ ታላላቅ ሥራዎችን የሰሩ ሲሆን፤ ወጣትነት ዘመናቸው በ1957 ዓ.ም ከክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል ጋር ከኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ እጅ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ተሸላሚ ለመሆን ችለዋል፡፡ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የአራት ዓለም አቀፍ አካዳሚዎች አባል ሲሆኑ በተሰማሩበት የሥነ ሥዕል ጥበብ በዓለም ላይ ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱ ታላላቅ ሰዎች የሚሰጠውን ‹‹የዓለም ሎሬት›› የተሰኘውን ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ ከዘጠና ሰባት በላይ የዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ከተለያዩ ተቋማት አግኝተዋል፡፡
በስዕሎቻቸውም፤ ሥርዓተ አምልኮን፣ ማኅበራዊ አኗኗር የማኅበረሰቡን ደስታና ሃዘንና ጀግንነቱን ሥልጣኔውንና አገር ወዳድነትን የሚያንጸባርቁ ሥራዎችን አበርክተዋል፡፡ በተለይም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካላቸው ጥልቅ ፍቅርና እምነት በመነጨ ለተለያዩ ቤተ ክርስቲያናት እንዲሁም በስቱዲያቸውና በጸሎት ቤታቸው የሚገኙ መንፈሳዊ ስዕላትን አበርክተዋል፡፡ ከሠሯቸው መካከልም በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ በግድግዳ ላይ የተሠሩ መንፈሳዊ ስዕላትን በቀለም ቅብ፣ በባለቀለም ጠጠሮች፣ በክርክም መስታወቶችና በሞዛይክ ከታወቁትና ስመ ጥር ከሆኑት ሰዓሊ ብላታ እምአዕላፍ ኅሩይ ጋር ሠርተዋል፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሙዚየሞች ውስጥም ስዕሎቻቸው በክብር ተቀምጠውላቸው በጎብኚዎች እየታዩ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ረገድም በስዕሎታቸውና በቅርፃ ቅርጾቻቸው አማካይነት ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ሲሆን ‹‹ቪላ አልፋ›› የተሰኘው ባለ 22 ክፍሎች መኖሪያ ቤታቸውና የግል ስቱዲያቸው ውስጥ ይህንኑ ለማንጸባረቅ ጥረት አድርገዋል፡፡
በቪላ አልፋ ስቱዲዮ ውስጥ የአክሱም ሐውልት፣ የጎንደር ፋሲለደስ፣ የሐረር ግንብ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ ቅዱሳት ስዕላት፣ የተወለዱበት አንኮበር የሚገኘው ቤተ መንግሥት የሚያስደንቁ ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና አገራዊ እሴቶችን አካቶ የያዘ ነው፡፡ ቪላ አልፋ ዛሬም በሥዕል ማሳያነት እያገለገለ ይገኛል፡፡
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በአንድ ወቅት ለኢትዮጵያ ሬዲዮ እንደተናገሩት፤ በልጅነታቸው የሰማይ ደመናን አንጋጠው በመመልከት ይመሰጡ ነበር፡፡ ደመናው የተለያየ አይነት ቅርጽ ሲሰራ በተፈጥሮ ይደመማሉ። ማነው እንዲህ በተለያየ ቅርጽ የሚሰራው እያሉ በልጅነት አዕምሯቸው ይጠይቃሉ፤ ይፈላሰፋሉ፡፡ ይህን የሰማይ ደመና መመሰጥ ወደ መሬት አውርደው እርሳቸው ደግሞ የሥዕል ሸራ ላይ መመሰጥ ጀመሩ፡፡ እነሆ የዓለም ሠዓሊም ሆኑ፡፡
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አፈወርቅ ተክሌ እነሆ በእነዚህ ሥራዎቻቸው ይታወቃሉ፡፡
በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ መግቢያ የሚታየው በመቶ ሃምሳ ካሬ ሜትር ላይ የተሳለው ትልቅ የመስታወት ስዕል፣ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሚገኘውን የመጀመሪያውን የ‹‹ዳግም ቀረበው›› ፍርድ ስዕል፣ በሐረር የልዑል ራስ መኮንን ሐውልት፣ በአዲግራት የ‹‹ዳግም ምጽዓት›› ፍርድ ስዕል፣ በለንደን ‹‹ታወር ኦፍ ለንደን›› የቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎት ቤት ከብር እና ከእንጨት የተሠራ የመንበር መስቀል፣ በሩሲያ፣ አሜሪካ እና በሴኔጋል ኤግዚቢሽን ላይ የቀረበው ‹‹የመስቀል አበባ›› ስዕል፣ ‹‹እናት ኢትዮጵያ››፣ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ምስል እና ‹‹ደመራ›› ተጠቃሾች ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 2 ቀን 2014 ዓ.ም