ዓለማችን በተቃራኒ ነገሮች የተሞላች ነች። ዛሬ ብታስደስተን ነገ ታሳዝነናለች። እነዚህን ተቃራኒ ነገሮች መሰረት ያደረገው ኑሮም መቼም ቢሆን ጎዶሎ አያጣም። ዛሬ ቢሞላ ነገ መጉደሉ አይቀርም። በመሆኑም በራሱ የሰው ልጅ ፈተና ነው። ህመም ሲታከልበትም ጫናው የበለጠ ይከብዳል። ሆኖም ጫናውን ለማሸነፍ የሚፍጨረጨሩ ሰዎች አይጠፉም። የዛሬ እንግዳችን አንዱ ናቸው።
እንግዳችን ማቲዎስ አላሮ ይባላሉ። በሙያቸው ወታደር ነበሩ። ወታደር ማቲዎስ እንዳወጉን ታዲያ ያኔ በዘመነ ደርግ 503 ነበልባል በሚባለው የጦር ግብረ ኃይል ባልደረባነት ለመጀመሪያ ጊዜ መከላከያ ሠራዊትን በቅጥር ሲቀላቀሉ የ20 ዓመት አፍላ ወጣት ነበሩ። ወታደር ማቲዎስ የውትድርናውን ዓለም በመቀላቀል ለመጀመሪያ ጊዜ በሥራ ገበታ ላይ የተሰማሩትም በዚሁ በ20 ዓመት አፍላ የወጣትነት ዕድሜያቸው ነበር።
ይሄ ዕድሜ የወጣትነት ከወጣትነትም የአፍላ ወጣትነት ወቅት እንደመሆኑ ፈታኝ ነው። ወቅቱ ችኩልነት፣ ስሜታዊነት፣ ትዕግስትና እርጋታ በደምሳሳው የማመዛዘን አስተውሎት ያንሰዋል። በዚህ ዕድሜ ክልል ያለ ሰው ፍላጎቶችም ዘርፈ ብዙና የተለያዩ ናቸው። አወዳደቁ እንዲያምርና ሕይወቱ በስኬት ጎዳና እንድትጓዝ የግድ የሚመራና ምክሩን የሚለግሰው ሰው ሁሉ ሊያስፈልገው ይችላል። ሆኖም እሳቸው ወደ ውትድርና ሙያ ሲገቡ ይሄ አልነበራቸውም።
‹‹ሆኖም በውትድርናው ዓለም ከገባሁ በኋላ ከወታደራዊ ስነስርዓት ጀምሮ አጠቃላይ ሕይወቴን በስርዓት ልመራበት የሚያስችለኝ ዕውቀት ቀስሜያለሁ›› የሚሉት ወታደር ማቲዎስ ከዚህ ጎን ለጎን አፍላው የወጣትነት ዕድሜያቸው ገፋፍቶና አሸንፏቸው ዘና ፈታ ከሚያደርጉ ነገሮች አጋልጧቸው እንደነበርም አጫውተውናል። ተጋላጭነቴን እንዳላስተውል የወጣትነት አፍላ ዕድሜዬ ዓይኔን ጋርዶኝ ነበር ማለት እችላለሁ›› ሲሉም የወጣትነት ዕድሜ ክልልን ጫናና ክብደት ገልፀውልናል። ይሁን እንጂ፣ ፈጣሪ የወጣትነት ዕድሜያቸው ለገዳዩ ኤች አይቪ/ኤድስ በሽታ ካጋለጣቸው በኋላ የሚገጥማቸውን የሕይወት ውጣ ውረድ ግብግቦች በሙሉ ታግለው ሕይወታቸውን የሚያሰነብቱበት ዕውቀት አልነፈጋቸውም።
እንግዳችን እንደ አንዳንዶቹ በኤች አይቪ ኤድስ በሽታ የተያዙ የሕብረተሰብ ክፍሎች በቫይረሱ መያዛቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሰሙ አልደነገጡም። ደንግጠውና ተስፋ ቆርጠውም የአልጋ ቁራኛ ሆነው አልቀሩም። ሕይወታቸውን ለማጥፋትም አልተነሳሱም። ይልቁኑም ቀጣይ የሕይወት ዘመናቸውን እንዴት አድርገው ማሰንበት እንዳለባቸው መንገድ ቀየሱ። የመጀመሪያው ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ራሳቸውን ገልጠው ሕብረተሰቡ ለበሽታው እንዳይጋለጥ ግንዛቤ መፍጠር ነበር። ሁለተኛው በዚህ አጋጣሚ የሚያገኝዋቸውን የትኞቹንም ዓይነት ሥራዎች መሥራትና ገቢ ማግኘት ነበር።
ይሄኛው ሥራቸው በበሽታው ምክንያት አልጋ ላይ የዋሉትን የሕብረተሰብ ክፍሎች ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ መንከባከብንም ያካትታል። ‹‹ምንም ገቢና አቅም የሌላቸውና ከነፃ እንክብካቤ ጀምሮ ድጋፍ የሚሹ የኤች አይቪ/ኤድስ ሕሙማን እንዳሉ ሁሉ ገንዘብ ኖሯቸው የሚደግፋቸው ወገን አጥተው አልጋ ላይ የዋሉ የቫይረሱ ሕሙማን አሉ›› የሚሉት ወታደር ማቲዎስ ምንም ገቢ ለሌላቸው በነፃ ከሚያደርጉት እንክብካቤና ምክር ባሻገር ገንዘብ ላላቸው ህሙማን እቤት ለቤት ከሚያደርጉት ምክርና እንክብካቤ ድጋፍ ገቢ እንደሚያገኙም ነግረውናል። በተረፈ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ ግንዛቤ ማስጨበጡና ህሙማኑን መንከባከቡ ፋታ አይሰጣቸውም እንጂ፣ ፋታ ካገኙ ከጉልበት ሸከማ ጀምሮ የሚያገኝዋቸውንና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎችን በንክኪ ለበሽታ የማያጋልጡ ሌሎች ሥራዎችንም ይሰራሉ።
ወታደር ማቲዎስ በሽታን አሸንፈው ሕይወታቸውን ለማሰንበት በሚያደርጉት ጥረት ከሚያገኙት ገቢያቸው ወጣ ስንል የፀረ-ኤች አይቪ/ኤድስ ህክምና መድኃኒት ተጠቃሚ በመሆናቸው በአሁኑ ወቅት ጤንነታቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል።
ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንዳለ ያወቁት በ1990 ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ ሲሆን ቀደም ብሎ በበሽታው ምክንያት ሕይወቱን ያጣውና ‹‹በእኛ ይብቃ ትውልድ ይዳን›› በማለት የራሱን ተሞክሮ እያቀረበ ጭምር ሕብረተሰቡ ከቫይረሱ ራሱን እንዲጠብቅ ሲያስተምር የነበረው “የዘውዱ ኢኒሼቲቭ” ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ወገኖች ማህበር አባል ናቸው።
የፀረ-ኤች አይቪ/ኤድስ ህክምና መድኃኒት ተጠቃሚ ከሆኑ 11ኛ ዓመታቸውን አገባድደዋል። ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ መኖሩን አውቀው ውስጣቸው ይሄንኑ አምኖና ተቀብሎ ራሱን በማረጋጋት ሌላውን የማዳን ተልዕኮ ካስታጠቃቸው ጀምሮ በማህበራቸው አማካኝነት በአራቱም ማእዘን የአገሪቱ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ሕብረተሰቡን ግንዛቤ ማስጨበጥ የጀመሩት በ2000 ዓ.ም ነው። ለአብነት ‹‹በእኛ ይብቃ ትውልድ ይዳን›› የሚለውን የሕይወት መርህ አንግበው ወደ ወሎ፣ ሳይንትና ላሊበላ ተጉዘው ግንዛቤ ያስጨበጡበትን ሁኔታ ይጠቀሳል።
የኤች አይቪ በሽታን ገዳይነት ቀበሌ፣ ወረዳና ዞን ዘልቀው ብዙዎች በበሽታው መርገፉቸውን ጠቅሰውና በዱር በገደሉ እየዞሩ እራሳቸውን ዋቢ በማድረግ እዚህ ቀውስ ላይ እንዳይወድቁ በመምከርና በመዘከር ሲያስተምሩ ቆይተዋል። በዚህ ተግባራቸው ከተማሪ እስከ አርሶ አደር ያውቃቸዋል።
እኛም ያገኘናቸው በዚሁ ከተቀደሰ ስራቸው አንዱ በሆነው ተግባር ላይ እያሉ ነው። በተለይ የኤች አይቪ/ኤድስ ቀን በሚከበርበት ወቅት የራሳቸውን ተሞክሮ ዋቢ አድርገው ለበዓሉ ተሳታፊዎች ግንዛቤ የሚያስጨብጡበት ጊዜም ብዙ ነው።
ወታደር ማቲዎስ እኛ ባገኘናቸው ወቅት እንዳወጉን ታዲያ ቋሚ የሚባል አድራሻዬ ነው ብለው የሚናገሩት ቂርቆስ ክፍለ ከተማን ቢሆንም በክፍለ ከተማው በስማቸው ተመዝግቦ የቤት ቁጥር የተሰጠው መኖሪያ ቤት የላቸውም። እየኖሩ ያሉት ዛሬ አንዱ ቤት፣ ነገ አንዱ ቤት በማደር ነው። በአብዛኛው ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች እየተዘዋወሩ ህብረተሰቡን በማስተማራቸው አዲስ አበባ ላይ እምብዛም አለመቀመጣቸው ጠቅሟቸዋል። በእርግጥ እንዲህ ባለው ሁኔታ መኖር እንኳን ለህሙማን ለጤናማም ሰው ይከብዳል።
ይሄ የአኗኗር ሁኔታቸው መድኃኒታቸውን ሳያቋርጡ በመውሰድ ጤናቸውን እንዲጠብቁ ለማድረግ ብዙም የሚያመቻቸው እንዳልሆነም አጫውተውናል። በየቀኑ ጠዋት አንድ ማታ አንድ እንክብል ፀረ-ኤች አይቪ/ኤድስ መድኃኒት ይወስዳሉ። በእርግጥ ቀንና ሰዓቱ እንዳይስተጓጎልባቸው በአውቶብስ፣ በባቡርና በእግር እየተጓዙ ባሉባቸው መንገዶች ላይ ጭምር የሚወስዱበት ሁኔታ አለ።
እንደሚናገሩት በአሁኑ ወቅት ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ አለ። ይሁን እንጂ፣ ግንኙነት ቢያደርጉ ለሌላ ሁለተኛ ሰው በማያስተላልፉበት ሁኔታ ነው። ነገር ግን ሕዝብን በተለይም አገር ተረካቢውን ዜጋ ከሞት ለመታደግ እንደመዝመታቸው እንደ አንዳንድ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ያለና በሽታው እንዲስፋፋ አስተዋጾ የሚያደርጉ ኃላፊነት የጎደላቸው ግለሰብ ወገኖች ከተቃራኒ ጾታ ጋር ግንኙነት እንደማያደርጉ እንዲሁም እንዴት በቫይረሱ እንደተያዙ በዝርዝር አጫውተውናል።
ያጫወቱን ከወጣትነት ዘመናቸው ጀምረው ነው። የወጣትነት ዕድሜ ዘመናቸው ታዲያ በተሰለፉበት የጦርነት አውደ ግንባር ማሸነፍን ብቻ ሳይሆን መዝለል፣ መጨፈርና፣ ከዚያችም ከእዚችም ጋር መዝናናትና መውጣትን ወይም አንሶላ መጋፈፍንም እንደ ጀብድ ይቆጥሩት ነበር።
በተለይ የእረፍት ቀናቶች በሆኑት ቅዳሜና እሁድ መጠጥ በመጠጣት አንሶላ ተጋፈው ገደብ የሌለው የወጣትነት የወሲብ ፍላጎታቸውን ለማርካት በየጉዟቸው መካከል የሚያገኝዋቸው እንደነ ሽሬ፣ ሽራሮ፣ አክሱም፣ ዓድዋ … ውስጥ የሚገኙ ትንንሽ ከተሞች አልበቃ ብሏቸው እስከ መቐለ ድረስ በመዝለቅ ከጓደኞቻቸው ጋር “ዓለማቸውን ይቀጩ” እንደነበር ዛሬ ላይ በቁጭት ያስታውሳሉ።
ብዙዎቻችሁ ያውም በወጣትነት ዘመን እንደ ወታደር ማቲዎስ ዘና ማለት ያስደስታል እንጂ ምን ያስቆጫል ትሉ ይሆናል። ነገር ግን ያውም በዓለማችን ምንም ዓይነት መድኃኒት ባልተገኘለት ኤች አይቪ/ኤድስ በሽታ ዘመን እንዲህ ዓይነቱ መዝናናት መዘዙ ብዙ ነው ብቻም ሳይሆን ለተዝናኚው እጅግ አስጊና አሳሳቢም ነው።
በተለይ ወደ ኋላ ላይ መብላትና መጠጣቱ፣ እየጨፈሩና እየተዝናኑ መደሰቱ፣ መሳቅ፣ መጫወቱ፣ ይሄ ቀራት የማይሏትን ለግላጋና ውብ ወጣት በየደቂቃው በዓይነ ህሊና በመሳል ማየቱና ማስታወሱ ለዛው እየደበዘዘና መልኩ ወደ አስፈሪ አውሬነት እየተለወጠ ትዝታው ቢረግፍ እንኳን በፍፁም ማስታወስ በማይፈልጓቸው ሁኔታዎች እየተተካ አያሌ ቁጭቶችንና ፀፀቶችን ይፈጥራል።
31ኛውን ክፍለ ጦር በመወከል በተለያዩ አውደ ግንባሮች በተካሄዱ ታላላቅ ጦርነቶች ተካፍለው ዓይናቸው ሳይጠፋና አንድም የአካል ክፍላቸው ሳይጎድል በአፍላ ዕድሜቸው ድልን በድል ላይ ደራርበው ይቀዳጁ የነበሩት ወታደር ማቲዎስም ዛሬ ላይ በውስጣቸው የተፈጠረባቸው ይሄው ዓይነት ስሜት ነው።
ደርግ ወድቆ ኢህአዴግ ስልጣን ቢይዝም አፍላው የወጣትነት ጉልበታቸው ባለመንጠፉ ወታደር ማቲዎስ በሠራዊቱ ውስጥ አገራቸውን በሙያቸው ከማገልገል አልተገደቡም። በእዚህ መካከል በእረፍት ጊዜያቸው ወጣ እያሉ ከጓደኞቻቸው ጋር የለመዱትን መዝናናትና መጨፈርም አልተውም።
እንዳጫወቱን በተለይ በ1990ዎቹ ዓ.ም አካባቢ አንዳንድ ትናንሽ የህመም ስሜቶች ይሰሟቸው ጀምረው ነበር። እነዚህ ስሜቶች ቀስ በቀስ ወደ የሰውነት ክብደት መቀነስና ድካም ተለውጠው የነበሩ መሆናቸውንም ያስታውሳሉ። ቀስ በቀስም ህመሙ እየፀናባቸው ድካሙ እየባሰባቸው መጣ። አልፎ አልፎም አልጋ ላይ ያውላቸው ጀመር።
በእዚህ ሁኔታ ያውም እንደ ደራሽ ውሃ ድንገት አንድ ዕለት ግዳጅ በሚሰጥበት የወታደር ቤት በሆነው መከላከያ ሠራዊት ውስጥ መኖር ደግሞ አይታሰብም። እንደውም ወታደር ማቲዎስ ለእዚሁ ሰግተው ህመማቸውን ምስጢር አድርገውና ቻል አድርገው በውስጣቸው ይዘውት ነው እንጂ ውሎ ማደርም አይቻልም። እናም በእዚሁ አጋጣሚ እዛው ሠራዊቱ ውስጥ እያሉ ተመርምረው ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ መኖሩን አወቁ።
‹‹በእርግጥ ያኔ ምንም ሥራዬን ባውቀው ውጤቱን አምኜ መቀበል አልቻልኩም ነበር›› የሚሉት ወታደር ማቲዎስ ድንጋጤው ህመሙን አባብሶባቸውና ረዘም ላለ ጊዜ ለአልጋ ቁራኛነት ተዳርገው እንደነበርም ያስታውሳሉ። በእዚሁ ምክንያትም ከሠራዊቱ በክብር ለመሰናበት በቁ። ነገር ግን ሲሰናበቱ የተሰጠቻቸው አምስት ሺህ ብር ለአንድ ሳምንትም አልበቃቻቸውም።
ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ መኖሩን ካረጋገጡ በኋላ ለአንዴ እንኳን ወደ ሆስፒታል በመሄድ ሕክምና አላገኙም። እናም ውሎ ሲያድር አንድም ሕክምና አለማግኘታቸው፤ ሁለትም የገንዘብና ገንዘብ ሊገዛው የሚችለው የተመጣጠነና የበለፀገ ምግብ ማጣታቸው ህመማቸውን በማባባስና ሰውነታቸውን በማሰልሰል የበለጠ ገዘገዘው። ሲዲፎራቸው ወደ 21 አሽቆልቁሎ በመውረድ ለቃሬዛ እንዲበቁም አደረጋቸው።
ወታደር ማቲዎስ እንዳወጉን ታዲያ በሰው ሸክም የሄዱበት ሆስፒታል ውስጥ ያገኟት የጤና ባለሙያ የኤች አይቪ/ኤድስ የደም ምርመራ ልታደርግላቸው ፈቃደኝነታቸውን ጠየቀቻቸው። እሳቸው ግን ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ አንዳለባቸው በለሆሳስ ነገሯትና የፀረ-ኤች አይቪ/ኤድስ ሕክምና መድኃኒት መውሰድ ጀመሩ። የቫይረሱ ሎድ ምርመራ አድርገው እንዳረጋገጡት መድኃኒቱን ሳያቋርጡ በመውሰዳቸው አሁን ላይ የሲዲፎራቸው መጠን ከ21 ወደ 900 ማደግ ችሏል።
የጤንነት ሁኔታቸውም በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል። ይሄ ሊሆን የቻለው ራሳቸውን አሳምነው ኑሮና በሽታን ተቋቁመው ራሳቸውን ለማሰንበት በሚያደርጉት ጥረት እንደሆነም ምክራቸውን ይለግሳሉ።
መልካም ንባብ!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1 /2014