ሁነቶች ሲበረክቱ መታዘባችን ይበዛል።መታዘባችን ባልከፋ የምንታዘበውን በሚታዘቡት ልክ አለመሆኑ ነው እንጂ ክፋቱ። አንድ ጉዳይ ተመልክቶና ስህተቶችን ነቅሶ አውጥቶ እንዲታረም በማሰብ ትዝብት ማጋራት ጥሩ ነው፤ጥሩ የማይሆነው ግን የምንታዘብበት መንገድ በራሱ ትዝብት ላይ ሲጥለን፤ስለምንታዘበው ጉዳይ ምንም ሳይገባንና ሳናውቀው መሆኑ ነው።
አሁን አሁንማ በማይቀለደው እየቀለድን በማይሾፈው ቁም ነገር እያፌዝን ትልልቅ ጉዳዮች እንደዘበት ማለፍ ጀምረናል። ሰሞኑን ማህበራዊ ጉዳይ ላይ እጅጉን የምንታዘባቸው ትዝብቶች ተበራክተዋል። ከነገር ሁሉ የሚገርመው ጉዳይ ቢኖር የሚታዘቡት ትዝብት መታዘብ ነው።እርግጥ አንድ ጉዳይ ላይ በትዝብት መልክ ሀሳብ የሚሰጠው ነገሩን ለማረም ሆኖ ሳለ፤አሁን ላይ የተላመድነው ግን ቅጥ ያጣ ነቀፌታና ፌዝ ነው።
በጉዳዩ ላይ ሀሳብ ለመስጠት የሚያስብ ሰው እንዴት በጉዳዩ ላይ ምን ያህል እውቀት አለኝ አልያም ደግሞ ስለተባለው ጉዳይ በም መንገድ ሀሳብ ልስጥ ብሎ ቀድሞ ማሰብ ያቅተዋል ጎበዝ። ወገን ምንም ነገር ሳይገባንና ሳናውቅ መተንተን ምን የሚሉት መሳት ይሆን? ወሳኝና ደምዳሚ ያለ እውቀት አውቃለሁ ብሎ የሚዘረዝር በእርግጥ ተንታኝ በዝቷል።
ምንም ያህል መልካም ንግግር ብናደር የቱን ያህል ጥሩ ሀሳብ ብንገልፅ ከዚያ መሀል ተመርጦ አንድ ስህተት አልያም አንድ የተለየ ሀሳብ ወቶ ዋንኛው የመነጋገሪያ ርዕስ ይረሳና እንደዘበት ያን ከመሀል መዞ አጀንዳ በማድረግ በሁሉም ዘንድ ይዟዟራል። ክፉ ልማድ ተፀናውቶናል። በእርግጥም አሳዛኝ ሆነናል። ድሮ ሰዎች አምሮባቸው ስናይ ከአይን ያውጣህ እንል ነበር ዘንድሮ ላይ ምንም ያህል የሚያምር ንግግር የሚያደርግ ሰውን ስናይ አልያም ስነሰማ ከነቀፌታ ይጠብቅህ ማለት መጀመራችን አይቀርም።
ከታዘብናቸው ትዝብቶች ውስጥ አንድ ምሳሌ እንጥቀስ ጎበዝ። በነገራችን ላይ ይህንን ትዝብ የምንታዘበው ሰው ምንም ነገር ላይ መታዘብ የለበትም በሚል እምነት ሳይሆን የሚታዘበው ነገር ጠንቅቆ አውቆ ምክንያታዊ የሆነ ትዝብቱን ያቅርብ በሚል መነሾ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። በእርግጥ በትክክል እና ስርዓት ባለው መንገድ የምንተቻቸው ጉዳዮች ትክክል ናቸው። ጉዳዩን በጥልቀት ማሳየትና ሙያው አስተያየት መስጠትም ይገባል። እኛ እያነሳን ያለነው ማፌዝና ተገቢ ያልሆነ ትችት ላቅርብ የሚለውን ደፋሩን ነው።
አንድ ሰሞን በስፋት ይወራ የነበረው የዝናብ ማዝነብ ወይም ደመና ማበልፀግ ቴክኖሎጂ ምንነት ሳናውቅ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ላይ የቀረቡ ዜናዎች ተመልክተን ነጋሪው አካል የረገምን፤ ዝናብ እንዲዘንብ ተደርጓል ያለን ወገን ያብጠለጠልን ብዙዎች ነበርን። ለዚህ ማሳያው በወቅቱ በማህበራዊ ሚዲያ ይሰጡ የነበሩ አስተያየቶችና ይህንን የሚተቹ ፅሁፎች ናቸው።ኧረ የምን ማህበራዊ መገናኛ ብቻ አንዳንድ ትልልቅ ስም አትርፈዋል የተባሉ ሬዲዮ ጣቢያዎችም ጭምር ላይ ታዛቢዎች በዚያው መንገድ ያለእውቀት የታዘቡትን ትዝብት ምልሰን እንድንታዘባቸው አድርጎናል።
ቆዩኝማ ስለ ደመና ማበልፀግ ቴክኖሎጂ ምንነትማወቅ ስለዚያ ከማብጠልጠል በፊት አይቀድምም ነበር ጎበዝ። ሳይንስ የትኛው ጥግ ላይ ደርሶ ተፈጥሮን በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ እየሞከረ ባለበት በዚህ ወቅት እጅጉን ቀላል የሆነውና ከተተገበረ በዚህም ብዙ ለውጥ በታየበት ደመና የማበልፀግ ብሎም የተጠራቀመውን ደመና ወደ ውሀነት (ዝናብ) መለወጥ በሚችለው ቴክኖሎጂ መተግበር ሲነገረን አልያም ወሬው ሲወራ ብዙ እንላለን።
እንዲህ ነው፤ ቴክኖሎጂው በራሱ ዝናም የሚያመነጭ አይደለም ስለዚህ ድርቅ ሲከሰት ወይም ደመና ሳይኖር በፍፁም በዚህ ቴክኖሎጂ ዝናብን ማዝነብ አይቻልም። ነገር ግን ከፍ ብሎ የተጠራቀመው ደመና ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ወደ ሌላ በንፋስ ከመበተኑ በፊት ቀድሞ ወደ ዝናብነት መቀየር ይችላል። እናም የሆነው ይህ ነው።
“ድርቅ ሲኖር ያላዘነባችሁ አሁን ፈጣሪ ሲሰጥ እኛ ሰጠን አላችሁ” እየተባለ ብዙ ተብሎ ነበር። በወቅቱ የተገለፀው ዜና ትክክል እንኳን ባይሆን ሊሆን የሚችል ጉዳይ አይደለም አልያም በፍፁም ሊሆን አይችልም ብሎ መሞገት ነው ክፋቱ። በእውቀት የተመሰረተ በመረጃ የታገዘ አስተያየት እኮ ገንቢ ነው። ከተስተካከለ ሥራም ላይ ስህተት አይጠፋምና እሱን ለማረም እጅጉን ጠቃሚ ነው። እኛ የጠላነው መለመዱን የምንኮንነው ያኛውን ነው።
አንድ እውነት አለ ብለን የተነገረውን እውነት የሚጣረስ ጉዳይ ከሆነ እዚያ እውነት ላይ ተቁሞ አሳማኝ በሆነ መልኩ መሞገት የእውነትነቱ ማስረጃዎች አቅርቦ በተሳሳተ መንገድ የቀረበበትን ሁኔታ ማስረዳት ሲቻል እንዴት ባልተጨበጠ ማስረጃ ስለተነገረው ጉዳይ መተቸት አልያም አስተያየት መስጠት ይቻላል?ወገን ምክንያት አልባነታችን አንዱ የታዘበውን ትዝብት እኛም ተቀባብለን ማራገባችን እጅጉን ያሳስባል፤ ሁኔታችን እጅጉን ያስተዛዝባል።
ሀሳብ ከማን መጣ ሳይሆን ሀሳቡ ምንድነው ብሎ መመርመርና ጠቀሜታው አልያም ፋይዳው ምን ላይ ነው የሚለው መመርመር ይገባል። ካልሆነ ሰውየውን አይተን አባባሉን መጥላት አልያም ግለሰቡን አይተን ተገቢው ባይሆን ያለው ልክ ነው ማለት ሁለቱም ስህተቶች ናቸው። ሁለቱም ትዝብቶች ለትዝብት ይዳርጋሉ። በተለይ በተለይ መራር ቀልድና መራር ትዝብት ላይ የሚጥል መታዘብ እውቀት አልባ የሆነ የመረጃ ክፍተት የሚታይበት ግልብ የሆነ አስተያየት ይመስለኛል በሚሉት መነሻ የሚቀርብ ትችት ነው።
በመፍትሄ መልክ የሚቀርቡልን የተለያዩ ምክሮች አልያም አስተያየቶችማ ዛሬ ላይ ማብጠልጠሉን ተክነንበታል። በወጉ እንኳን ጉዳዩን መግለጥ ሳንችል ነው ወደ ማብጠልጠላችን የምንገባው። እጅግ ደግሞ የሚገርመው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚዘዋወሩ ቅንጭብ ንግግሮች ተመርኩዘው የሚሰጡ አስያየቶችና ትዝብት መሰል ስላቆች የሚታዘበውን አካል አቅም ፍንትው አድርገው መግለፃቸው ነው።
ጉዳያችን ሁሉ በፌዝ ማሳለፍ ወይን ዋንኛ የምንላቸው የጋራ ጉዳዮቻችን ዘንግተን ፌዝና ቧልት ይሁነኝ ብለን መመላለሳችን የጤና ይሆን ? እንጃልን ያሳስባል። እንደው ምን ይሻለን ይሆን ወገን። ጉዳዮችን ሁሉ ምናይበት መነፅር የምንታዘብበት ሁኔታ ስለ ጉዳዩ አልያም ስለ ተግባሩ ያለን እይታ ትርጉም ሰጥተን ነው የምናወራው። ከማን ምን እንደምንጠብቅ እኛው መድበናል። አልያም ማን ምን ለማለት እንደፈለገ ከንግግሩ ተነስተን ማብራሪያ ከራሳችን እይታና አመለካከት አንፃር ለአባባሉ መስጠታችን ይገርማል።
እንዴት አንድ ማገናዘብ የሚችል ስለ ጉዳዮች መረዳትና ማሰላሰል የሚችል አካል አንድን የሌላን ወገን አባባል እንዲህ ነው ብሎ በራሱ አተያይ ሊገመግም ይችላል። ከመነሻው አንድን ጉዳይ ስንሰማ በሚዛን አስቀምጠን ካልሆነ በተዛባ መልኩ ካየነው የቀና መስሎ ሊታየን ፈፅሞ አይችልም። የሰዎችን ሀሳብ ነቀፋና ስላቅ ለማቅረብ ብቻ የምንከታተልም በርክተናል። ሲናገር መሳሳቱን የምንፈልግ በንግግሩ ካልተሳሳተም ለንግግሩ የተጣመመ ትርጓሜን የምናበጅ ጉደኞች እኮ ሆነናል።
ይህ ደግሞ ከትክክለኝነት እጅጉ እንድንርቅ ያደርገናል። ሰውየው ገና ከማውራቱ በፊት የምንጠብቀው ጉዳይ አለ። ያንን ጉዳይ ሳያነሳ ከቀረና እኛ ያሰብነውን ካልገለፀ የሰውየው ንግግር አይጥመንም። ምክንያቱም እኛ ስለሰውየው የምናስበውና ይላል ብለን የምንጠብቀው እኛ የምናስበው ስለሚሆን።ወገን ምክንያት አልባነት ከባድ ነው። ነገራችን ይጣፍጥ ዘንድ ጉዳያችን ይሳካ ዘንዳ የምናነሳውና የምንጥለውን በደንብ መለየት ይገባል። በተለይ የምንተቸውና የምንነቅፈው ጉዳይ መታረሙን አስበን ስለጉዳዩ የበለጠ አውቀንና ተረድተን ቢሆን ገንቢና ጠቃሚ ይሆናል። ለማንኛውም ለዛ ያለው ንግግር የምንናገር ከሚታዘቡዋቸው ታዛቢዎች ይጠብቃችሁ ማለትን ወደድኩ። ቸር ያሰማን፤አበቃሁ።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1 /2014