ወደ ክፍለ አገር እየሄድኩ አውቶቡስ ውስጥ ቁጭ ብያለሁ። በእድሜ ተዋረድ የተሳሉ አያሌ ነፍሶች ሽንጠ ረጅሙን አውቶቡስ ሞልተውታል። ካለፈለፈ የሚያመው የሚመስለው አንድ ወያላ ለግብዣ በተመቸ ድምጽ ተሳፋሪ ይጣራል። ሀዋሳ…ሻሸመኔ እያለ።
ጸጉሩን እየቆነደደ፣ እጁን በልብስ የተሸፈነ ገላው ውስጥ እያስገባ እያስወጣ፣ ወደዚያ ወደዚህ እየማተረ ይቁነጠነጣል። መኪናው ከሞላ ቆይቷል የት ላይ ሊጭን እንደሚጣራ ግራ ገብቶኝ በመስተዋቱ አሻግሬ አየዋለሁ። አፉ አያርፍም.. ሲያወራ ነው የማየው። አጠገቡ ካሉት ወዳጆቹ ጋር በአንድ ጊዜ ከሁሉም ጋር ይገባባል። ገረመኝ..ግን ለሀጢያት የበረታ ይመስለኛል። ሰው መቀመጫ አጥቶ በቆመበት አውቶቡስ ውስጥ ሌላ ተሳፋሪ መጥራቱ ማንነቱን እንድታዘብ አደረገኝ።
ከአውቶቡሱ የፊት በር አካባቢ ሹፌሩንና ረዳቱን ከበው የቆሙ አራት የሚሆኑ ወያላዎች ያንሾካሹካሉ። የሚሉትን ለመስማት ጓጉቼ ነበር.. አልተቻለኝም። በተቀመጥኩበት ግን እገምታለሁ..ግምት አንድ..ህገ ወጥ ስራ ሊሰሩ እያሴሩ መሰለኝ። ግምት ሁለት.. ትርፍ ለመጫንና ከታሪፍ በላይ ለማስከፈል እያደቡ መሰለኝ።
ግምት ሶስት.. እንዴት ብለው መንገድ ላይ የሚያስቆማቸውን ትራፊክ ማለፍ እንዳለባቸው እየመከሩም መሰለኝ። ከዚህ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? በሞላና መቀመጫ በታጣበት አውቶቡስ ውስጥ የነዛ ወያላዎች ተልዕኮ ሕዝብ ከማስጨነቅ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? እያልኩ አስባለሁ። ትኩረቴን ሳልነፍጋቸው በተቀመጥኩበት እከታተላቸው ጀመር። ለዚህ ምስኪን ተሳፋሪ ባህር የሚከፍሉ፤ እኚህን ፈርኦናውያን ወያላዎች ባህር የሚያሰምጥ አንድ ሙሴ መጥፋቱ አናደደኝ።
ያ ለፍላፊ ወያላ ወዲያ ወዲህ ተንጎራዶ ሁለት ተሳፋሪዎችን አግኝቶ ከቆሙት ጋር ቀላቀላቸው። የልቡ ደረሰ መሰለኝ እንደ እሱ የክፋት ሀሳብ ካነገበ የአውቶቡሱ ረዳት ጋር ሂሳብ መክፈያ ደረሰኝ ይዘው ትኬት መቁረጥ ጀመሩ። በዚያ ሰዓት ከረዳቱና ከዛ ለፍላፊ ወያላ ፊት በቀር የሁሉም ተሳፋሪ ፊት ሀዘን አጥልቶበት ነበር።
ከተሳፋሪዎቹ ወደ ረዳቱ የሚወናጨፉ የማይሰሙ አንዳንድ ጉርምርምታዎች ይሰሙኛል። በታሪፍ ይሆናል ስል አሰብኩ… እንዳሰብኩትም አልቀረም ያ ሁሉ ድምጽ አልባ ጉርምርምታ በረዳቱ ያልተገባ የታሪፍ ጭማሪ ነበር። መንግስት የሚያውቀው ታሪፍ መቶ ሰላሳ አምስት ብር ሆኖ ሳለ ያ ረዳት ግን ሁለት መቶ ሀምሳ ብር ነበር ሲያስከፍል የነበረው። ተናደድኩ… እውነት ተናደድኩ… ለዚህ ድሀ ሕዝብ ሙሴን መሆን አለመቻሌ ራሴን እንድታዘበው አደረገኝ።
አገራችን ሰው ነው ያጣችው… ልክ እንዲህ እንደ አሁኑ ክፉ ነገርን የሚቃወም ሰው። እያዩ ዝም ማለት ወንጀልን ከማስፋፋት ባለፈ አገርን በእጅጉ የሚጎዳ ድርጊት እንደሆነ የገባኝ ሁለት መቶ ሃምሳ ብር መክፈል አቅቷቸው የሚያለቅሱ ድሆችን ሳይ ነበር። ውስጤ የሆነ የእልህ ስሜት ተፈጠረ..። የነዛን ድሆች እንባ አይቶ ዝም የማይልና፣ የነዛን ራስ ወዳድ ረዳትና ወያላ ተግባር የማይታገስ እልህ።
በዚህ መሀል ቆብ የደፉ አንድ መነኩሴ በሚያሳዝን ድምጽ ወደ ረዳቱ እያዩ ‹ልጄ እኔ ዘዋይ ነው የምወርደው፣ 250 ብር የለኝም… እባክህ ግማሹን ልክፈልህ‹ ብለው ሲማጸኑት ሰማሁ።
እንዴት እንዳመናጨቃቸው… እናት እንደዛ ስትመናጨቅ፣ መነኩሴ እንደዛ ሲገፉ ያን ቀን ነው ያየሁት። ‹ከፈለጉ ይውረዱ… ሌላ ሰው እጭናለሁ› አለ። በዚህ መሀል አንድ ሞገደኛ ድምጽ ተሰማ ‹አንተ ለምን በሥርዓት አታናግራቸውም? ወንጀል መስራትህ ሳያንስ ትልቅ ሰው ታመናጭቃለህ እንዴ? ይቺን ተናግሮ መናኽሪያ ግቢ ውስጥ ወዳለው የትራንስፖርት ስምሪት ክፍል በመሄድ ስለተፈጠረው ነገር ሁሉ ተናገረ።
‹ማህበረሰቡን በታማኝነት የማገልገል ግዴታችሁን እየተወጣችሁ አይደለም። ማንም ባልተገባ ታሪፍ ተሳፋሪን ሲበዘብዝ ዝምታን መርጣችኋል። የተጠያቂነት ሀላፊነታቸሁን አልተወጣችሁም። እናንተ የምትመሩት ማህበር የሙያ ስነምግባር የላችሁም› ሲል ለሚመለከተው አካል አቤቱታውን አቀረበ። ይሄን የሰማው ስራ አስኪያጅ አጠገቡ ያለውን ድምጽ ማጉያ በማንሳት የመኪናውን ታርጋ ቁጥር በመጥቀስ ከመናኽሪያ ግቢ እንዳይወጣ ለጥበቃዎች ትዕዛዝ አስተላለፈ። ያ መኪና ከመቀጣትም አልፎ መንግስት በሚያውቀው ነባር ታሪፍ እንዲጭን ተገደደ።
በዛ ልጅ ሙሴነት አርነት ወጣን። በዛ ልጅ ሙሴነት ባህር ተሻገርን። ያ ልጅ የነዛ ድሀ ነፍሶች እንባና የነዛ ራስ ወዳድ ረዳትና ወያላ እኩይ ስራ የነቀነቀው ባላደራ ነፍስ ነበር… ያም ልጅ እኔ ነበርኩ። ጭቁኖችን እንደመርዳት፣ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ እንደመሆን በዚህ ዓለም ላይ ምን ደስታ አለ? ሰውነት ቢለካ፣ ማስተዋል ቢመዘን ማረፊያው አገርና ሕዝብ ይሆኑ ነበር ስል እያሰብኩ በጀግንነት ወደ ቦታዬ ተመለስኩ። ወደ መኪናው ስገባ ከረዳቱና ከወያላው ፊት በቀር የሁሉም ተሳፋሪ ፊት ደስታ ነግሶበት ነበር። ደስ አለኝ… ለዛ ሁሉ ተበዳይ ሳቅ በመሆኔ።
ከተቀመጥኩበት ሰዓት መኪናው እስኪንቀሳቀስ ድረስ ስለዝምታና ጩኸት እያሰብኩ ነበር። ዝዋይ ደርሰን ለምሳ እስከወረድንበትና እኚያ መነኩሴ በስራዬ ተደስተው እግዚአብሔር ይባርክህ እስካሉኝ ጊዜ ድረስ ስለ ሰውነት እያሰብኩ ነበር። ሁሉም ነገር ያለቦታው ስህተት ነው። ቦታው እየመሰለን በብዙ ነገር ላይ ስህተት ሰርተናል።
ለካ ዝምታ መብትንና ሀላፊነትን አሳልፎ መስጠት ነው። ለካ ዝምታ መሸነፍ ነው። ለካ ካለመናገር ደጀዝማችነት ይቀራል። ለካ ዝምታ ሳይሆን መናገር ነው ወርቅ እያልኩ። ሰው በወጉ ማሰብ ካልቻለ የጫካ እንስሳ ነው። ሰው ተፈጥሮውን ካልተረዳ የአጋንት ባሪያ ነው። ሰው በሀሳቡና በተግባሩ በጎነት ከሌለው አውሬ ነው። አምላክ በሀጢአታችን አዝኖ ከነፍሳችን እስከራቀበት ጊዜ ድረስ የሰው ልጅ እንደ እግዚአብሔር ነበር እያልኩ።
እስከዛሬ ድረስ እንደ አገርም ሆነ እንደ ዜጋ የተጎዳንባቸው ነገሮች ሳንናገር ዝም ያልንባቸው እንደሆኑ ዛሬ ነው የገባኝ። ሕዝባችን እውነት ጠፍቶታል፣ እውነትና ውሸት ተደበላልቆበታል።
ሰው በጠራራ ጸሀይ ሲዘረፍ እያየን እኔ ላይ ካልደረሰ በሚል ዝም የምንል አራዳ መሳይ ፋራዎች ብዙ ነን። የሌሎች መብት ሲነካ እያየንና እየሰማን በእኛ ላይ ካልደረሰ ብለን የማንናገር አለን። አገር ማለት በእኔና በሌላው ሰው የያገባኛል ስሜት የምትጸና እንደሆነች የገባን ጥቂቶች ነን።
ሌሎች በሚለፉባትና ሌሎች በሚደክሙባት አገር ላይ በነጻነት እየኖርኩ እንደሆነ ሳስብ እንደ ዜጋ ለአገሬ አንዳች ባለማዋጣቴ ሀፍረት ተሰማኝ። ከዚህ በኋላ ባለው ሕይወቴ ለአገሬና ለሕዝቤ ሙሴን ለመሆን እያሰብኩ ሀዋሳ ደረስኩ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መጋቢት 30 /2014