ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ የሥራ ዘመን አምስተኛ መደበኛ ስብሰባውን ከትናንት በስቲያ ሲያደርግ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርን የስምንት ወራቅ ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርቧል። በወቅቱ በርካታ የምክር ቤት አባላት የኑሮ ውድነቱን የሚያባብሱ ሕገወጦች ላይ ተገቢው እርምጃ አልተወሰደም፤ በዚህም የተነሳ የሸቀጦች ዋጋ መቆጣጠር አልተቻለም፣ በነዳጅ ላይ ከፍተኛ እጥረት ይስተዋላል ፣ የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችን አንስተዋል። የንግድና ቀጠናዊ ትስሰር ሚኒስትሩ አቶ ገብረመስቀል ጫላም ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።
እኛም የምክር ቤቱን ውሎ መሰረት በማድረግ ከተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ ጥቂቱን በማንሳት የተሰጣቸውን ምላሽ ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ንባብ።
ጥያቄ፡- የአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚመራበት የንግድ ፖሊሲ ሥርዓት ዝግጅት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? የተለያዩ ዘርፎች አዋጅ ወጥቶላቸዋል ነገር ግን አዋጁን ለማስፈጸም የሚያስችል መመሪያና ደንብ ያልወጣላቸውና ወደ ስራ እንዲገቡ ያልተደረገበት ምክንያት ምንድን ነው? ለአብነት የተሻሻለው የንግድ ሕግ በአዋጅ ደረጃ ነው ያለው ፤
አቶ ገብረመስቀል፡- በ1952 ዓ.ም በኢትዮጵያ የወጣ የንግድ ሕግ አለ፤ ይህ ሕግ የተሟላ እና ብዙ ህጎችንም በውስጡ የያዘ እንዲሁም በርካታ መንግሥታትን ያገለገለ ነው። ነገር ግን ዘመኑ የቴክኖሎጂ ከሆነ በኋላ ህጉ ይህንን መሸከም የማይችል በመሆኑ ባለፉት የተወሰኑ ዓመታት እንዴት አድርገን ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር እናጣጥመው የሚለው ሲጠና ነበር።
ይህንን ህግ ለማሻሻል ጥናት በሚደረግበት ጊዜ ጎን ለጎን የሚወጡ አዋጆች ደንቦች መመሪያዎች እየተሻሻሉ ነበር። በመሆኑም አሁን ላይ ህጉን በምናይበት ጊዜ ከሞላ ጎደል አሁን ያለውን አሰራር የሚሸከም ነው። አንድ መመሪያ በተለይም ከንግድ ህጉ ጋር የተያያዘና የሚሻሻል አለ።
በመሆኑም የንግድ ሕጉ አሁንና ቀድሞ በነበረው ልዩነቱ ምንድን ነው? የሚለውን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ እንዲሁም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች እንዲያውቁት በየክልሎቹ ሥልጠና እየተሰጠ ነው። በመሆኑም ይህ የንግድ ሕግ የተሻሻለው ከዲጂታላይዜሽንና ከዘመናዊነት አንጻር ከኦን ላይን ሲስተም ጋር የተያያዘ ጉዳይ ካልሆነ በቀር በመሰረታዊነት የሚቀየር ነገር አልተገኘም።
በሌላ በኩልም በዚህ ስምንት ወራት ውስጥ እቅድ ይዘን በፖሊሲ ጉዳይ ላይ የሰራናቸው ሥራዎች አሉ። ለምሳሌ የንግድ ፖሊሲ እኛ ስንመጣ ያልተጀመረ ነበር፤ አሁን ጀምረን አጠናቀን በሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ አቅርበናል። ሌላው ብሔራዊ የጥራት ፖሊሲ ሲሆን ይህም በመጠናቀቅ ላይ ከመሆኑም በላይ ሕብረተሰቡ እየተወያየበት ነው።
ጥያቄ፡- በፍጆታ እቃዎች ላይ የመንግሥት ድጎማን በተመለከተ ማለትም ዘይት ስንዴ ስኳርና ሌሎችም ከቀረጥ ነጻ የማስገባትና በዘርፉም የተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመደጎም የተሻለ እንዲያመርቱ እየተደረገ ነው። ነገር ግን ለተጠቃሚው ሕብረተሰብ ፍትሃዊ ስርጭት የሌለ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ለከፍተኛ የኑሮ ውድነትና የዋጋ አለመረጋጋት ችግር ተዳርጓል። ይህንን ሁኔታ ለማሻሻል ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ገብረመስቀል፡- ከመሰረታዊ ሸቀጦች ጋር በተያያዘ መንግሥት በተለይም ዘይት ስኳር ስንዴ በማቅረብ የሕብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ትልልቅ ውሳኔዎችን ወስኗል። ለምሳሌ ዘይትን ለማምረት ወደ 4 መቶ ሚሊዮን ዶላር መድቦ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ዘይት ከቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲያስገቡ ሆኗል። ይህ ቢሆንም ፍላጎቱ ትንሽ ባለመሆኑ ውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲያስገቡ እድል ተሰጥቷል። የውጭ ምንዛሪ የሂሳብ ቁጥር (አካውንት) ያላቸው ኢትዮጵያውያን እንዲያስገቡ ፍቃድ ተሰጥቷል።
የኑሮ ውድነትን ለማስተካከል በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንዴት ችግር እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም አንዳንድ ነገሮችን በማስረጃ አስደግፌ መናገር እፈልጋለሁ። በአሁኑ ጊዜ በተለይም በዩክሬንና በራሺያ መካከል የተፈጠረው ጦርነት ትልልቅ የዓለምን ንግድ የሚያዛቡ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ነው። ለምሳሌ ዩክሬን ከፍተኛ የሆነ የምግብ ዘይት የምታቀርብ አገር ናት፤ በአሁኑ ጊዜ ትልልቅ ፋብሪካዎቿ ማምረት በማቆማቸው ምክንያት በአገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ የዘይት እጥረት ተከስቷል። ይህ ብቻም አይደለም። ራሺያም በተመሳሳይ ፋብሪካዎቿ እያመረቱ ባለመሆኑ ብዙ ነገሮች ከገበያ እየጠፉ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው።
በሌላ በኩል በዚህ ጦርነት ምክንያት ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያዎች በተለይም ወደዩክሬን የሚያደርጉትን በረራ አቋርጠዋል የንግድ እንቅስቃሴውም ተገድቧል። ይህ ጦርነት በዚህ ከቀጠለ በተለይም ምርትን ለዜጎቻቸው የማቅረብ ችግር ሊያጋጥም ይችላል በሚል አንዳንድ ዘይት አምራች አገሮች ምርቶቻቸውን የመያዝ ሁኔታን እያሳዩ ነው። በመሆኑም መሰረታዊ ሸቀጦች በዓለም አቀፍ ደረጃ እጥረት አስከትሏል።
በመሆኑም ይህ ጥላ በአገራችንም እየታየ ነው። ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ አብዛኛውን የሸቀጥ ምርታችንን ከውጭ የምናስገባ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ገቢ ምርቶች አቅርቦት ላይ ጫና ይፈጥራል። በመሆኑም መሰረታዊ ችግሮቹ እንግዲህ ዓለም አቀፍ ጫናው እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያ ሰፊና ትልቅ አገር ስትሆን ፍላጎቶቿም በዛው ልክ ሰፊ ናቸው። ይህንን ፍላጎት የሚመጥን የአቅርቦት ችግር አለ።
በሌላ በኩል የአገር ውስጥ የገበያ እንቅስቃሴ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በተፈጠሩ በርካታ ኬላዎች ምክንያት አላስፈላጊ ቀረጥ እየበዛ በመምጣቱ በምርቶች ላይ የተጋነነ ዋጋ ጭማሪ እየታየ ነው። ሌላው ስር የሰደደ ሌብነት አለ፤ ለዚህ ሌብነት ደግሞ የምርት እጥረት መኖሩ ለሌቦች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ በየደረጃው ባሉ የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥም የሚታይ በመሆኑ ይህንንም መፍታት ያስፈልጋል ፤ ሌላው ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ላይ የተከሰተውን የምርት እጥረት ተገን በማድረግና ሊቀጥል ይችላል በሚል አቅራቢዎች ምርቶቻቸውን ደብቀዋል። በመሆኑም በእነዚህና ሌሎች ምክንያቶች የምግብ ሸቀጥ ዋጋ ንሯል፤ የኑሮ ውድነት ከፍ ብሏል።
ይህንን ለማስወገድ ደግሞ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን በዚህም የአቅርቦትን ችግር ለመሙላት በተለይም ከዘይት ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል ተገዝቶ በተለያዩ ምክንያቶች አገር ውስጥ ያልገባ 10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት በተቻለ ፍጥነት ወደ አገር ውስጥ እየገባ ነው።
ሌላው የዓለም የአቅርቦት ሁኔታ እጥረት የሚታይበት ቢሆንም ካለበት ቦታ እንዲመጣ መንግሥት ያለውን ሀብት ቅድሚያ ሰጥቶ መድቦ ተጨማሪ የምግብ ዘይት እንዲገባ ስምምነት ተደርሶ ግዢ እየተፈጸመ ነው። በአዲስ አበባና በአዳማ አካባቢ በተካሄደው ኦፕሬሽን 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ተይዞ ወደስርጭት እንዲገባ ሆኗል። በመሆኑም ከዘይት ጋር በተያያዘ ያለው ሁኔታ ይህ ነው።
ጥያቄ፡- ነዳጅን በሚመለከት በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ እየታየ ያለው የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት በነዳጅ አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል፤ በመሆኑም አሁን ያለውን የነዳጅ አቅርቦት እጥረትና የዋጋ መዋዠቅ ለመቋቋም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ምን እያደረገ ይገኛል?
አቶ ገብረመስቀል፡- ነዳጅ ከዚህ ቀደም ድፍድፉ በርሜል ስድስት ዶላር ነበር። አሁን ግን 106 ዶላር ደርሷል። እነዚህ ሁሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋጋቸው እየናረ ያሉ ነገሮች ኢትዮጵያ ላይ ቀጥተኛ የሆነ ጫናን እየፈጠረ ነው። ይህም ቢሆን ግን መንግሥት ካለው ሀብት የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ ለሕዝቡ መሰረታዊ የሚባሉ የፍጆታ እቃዎችን ለማሟላት ጥረት እያደረገ ነው።
በአሁኑ ወቅት በክልሎች አካባቢ ጉምሩክ የሚያውቃቸው ኬላዎች ካልሆኑ በቀር ሁሉም ኬላዎች እንዲነሱ ሆኗል። በመሆኑም አሁንም ገመድ አስረው መኪና የሚያስቆሙ ከጉምሩክ እውቅና ውጪ ያሉ ሁሉ ሕገወጦች ናቸው።
ሌብነትንም ቢሆን ለመቋቋም ብሎም እንደዚህ አይነት ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረትን በሚፈጥሩ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው። የሕግ ክፍተቶችንም በደንብ በማየት እንዲስተካከሉ ማድረግ ያስፈልጋል። በየደረጃው ያለው የመንግሥት መዋቅር እየተመሳጠረ አንዳንድ ጊዜ ምርቱ ታች ድረስ የደረሰ ቢሆንም እንኳን ሕዝቡ ጋር እንዳይደርስ በሚያደርጉ ላይ የማጥራት ስራ እንሰራለን። ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወሰድም እንሰራለን። በጠቅላላው የንግድ ሥርዓቱን በማዘመን ከሌቦች ከአሻጥረኞች ለመከላከል በተለይም የስርጭት ሥርዓቱን በዘመናዊ ሁኔታ ማስኬድ ሲስተም መዘርጋት ይጠይቃል። ይህንንም ለመስራት የተለያዩ ጥረቶች ይደረጋሉ።
ነዳጅ ከአጭር ጊዜ አንጻር የአቅርቦት ችግር የለብንም። ምክንያቱም ለተራዘመ ጊዜ የሚቆይ ውል ገብተን ነው የምንሰራው፤ በመሆኑም በተፈጠረው የዓለም ሁኔታም ቢሆን የአቅርቦት ችግር አይገጥመንም። የሚገጥመን የዋጋ ልዩነት ነው። ይህንን የዋጋ ልዩነት መዋዠቅ ለማስተካከል ሁለት መሰረታዊ ውሳኔዎች በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተወስኗል።
አንደኛው እኛ ደሃ አገር ብንሆንም ነዳጅን ከውጭ አገር ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ አውጥተን ነው የምናስገባው። ነዳጅ ለኢኮኖሚ ለምርትታማነት ያለውን ፋይዳ በመረዳት የምንሸጠው ደግሞ ከዋጋው ከ 50 በመቶ በላይ ሰብረን ነው። ይህም ቢሆንም ግን ዋጋው ከጎረቤት አገሮች መሸጫ ዋጋ ጋር ተመሳሳይ ስላልሆነ እኛ ጋር 30 ብር የሚሸጥ ናፍጣ አሁን ላይ ጅቡቲ 100 ብር ስለሚሸጥ እኛ ከጅቡቲ የተነሳው ነዳጅ ጫኝ መኪና ተመልሶ ጅቡቲና ሶማሌ ላንድ ነዳጁን እያራገፈ ስለሆነ ዋናው ጉዳይ የነዳጅን ዋጋ ወደ ዓለም አቀፍ ዋጋ ጠጋ ማድረግ ነው። አለበለዚያ እኛ ሁል ጊዜ ነዳጅን በዶላር እየገዛን ዋጋው ከፍ ወዳለ አገር በኮንትሮባነድ እየወጣ ነው። በመሆኑም ይህ ሁኔታ በዝርዝር ተጠንቶ የዋጋ ማሻሻያ ሊደረግ ያስፈልጋል።
ዋጋ ማሻሻያ በሚደረግበት ጊዜ ዝቅተኛው የሕብረተሰብ ክፍል በተለይም ከትራንስፖርት ጋር ተያይዞ እንዲሁም የሚያስከትለውን የኑሮ ውድነት ጫና ለማቃለል የሕዝብ ትራንስፖርት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች የታለመ ድጎማ እንዲያገኙ ውሳኔ ተላልፏል። በመሆኑም በጊዜ ሂደት የገበያውን ሁኔታ እያስተካከልን የነዳጅ የመሸጫ ዋጋ ቢያንስ ከአካባቢው አገሮች ጋር እንዲስተካከል ማድረግ ያስፈልጋል።
ሌላው በተለይ ቤንዚንን ከኢታኖል ጋር በማቀላቀል የምናስገባውን የነዳጅ መጠን በተወሰነ ደረጃ ማሻሻል ይቻላል፤ ይህም በቀጣይ እየታየ የሚሄድ ነው። ነዳጅ ውድ ምርት ነው። እኛ ግን እንደ ውድ ምርት አናየውም። በመሆኑም እያንዳንዱ ተሽከርካሪ ያለው ዜጋ ነዳጅን በቁጠባ መጠቀም መቻል አለበት። በቁጠባ መጠቀም የማንችል ከሆነ በቀጣይ ነዳጅ በኮታ ልንሰጥ የምንችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። በመሆኑም ይህ እንዳይሆን ለነዳጅ የሚወጣውም ገንዘብ የአገሬ ነው በማለት በቁጠባ መጠቀሙ ይሻላል። ከዚህ ባሻገርም ቅዳሜና እሁድ የሕዝብ ትራንስፖርት መጠቀም እንዲሁም የእግር ጉዞን መልመድ ልንገባ ካልነው ችግር ይታደገናል።
ነዳጅ እንደ መሰረታዊ ሸቀጥ መንግሥት የሚቆጣጠረው ነው። ዋጋ ይወሰናል። ማንም ከዛ ዋጋ በላይ ከሸጠ ሕገወጥ ነው። ይጠየቃል። ስርጭቱንም ብንመለከት አዲስ አበባ እንኳን ከሚገባው ነዳጅ 45 በመቶውን ብቻ ነው የሚጠቀመው ፍትሃዊ አድርገን እናሰራጭ ብንል አንዳንድ ቦታ ላይ ነዳጅ ያጥራል። ሌላው ጋር ደግሞ ሳይሸጥ ቁጭ ይላል ፤ በመሆኑም ተጠቃሚን ፍላጎት ያደረገ የነዳጅ ስርጭትን ነው የምንጠቀመው።
ይህ ፍላጎትን ተከትሎ እንዲሄድ እንዴት ነው መቆጣጠር የምትችሉት የሚል ጥያቄ ሊመጣ ነው፤ ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት ቁጥጥር የሚካሄደው በየጊዜው ምርመራ ይደረጋል። ዘንድሮ እንኳን በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል ላይ አምና ተመሳሳይ ወቅት ከተጠቀሙት ከፍ ያለ የነዳጅ አጠቃቀም ታይቶ ነበር። በመሆኑም ይህንን ከሚመለከታቸው ጋር ተነጋግረን ኮታ ገደብን። ነገር ግን ሶማሌ ክልል ላይ አሁን ካለው የድርቅ አደጋ ጋር ተያይዞ የክልሉ መንግሥት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ጥቂት ድርቁን ታሳቢ ያደረገ መጠነኛ ጭማሪ ተደርጓል።
ጥያቄ፡- በግብርና ምርቶች ላይ የሚታየውን ሕገወጥነትና ኮንትሮባንድ ንግድ ምክንያት መንግሥት ማግኘት የሚገባውን ገቢ ከማጣቱም በላይ የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት በሚፈለገው ደረጃ ላይ ለመድረስ ከፍተኛ እንቅፋት ሆኗል ይህንን ችግር በዘለቄታዊ መልኩ ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምን ያህል ቅንጅታዊ አሰራር እየተሰራ መሆኑ ቢገለጽ?
አቶ ገብረመስቀል፡- በግብርና ምርቶች ኮንትሮባንድ የተነሳ አገራችን የሚገባበትን ጥቅም እያገኘች አለመሆኑ እየተነገረ ነው። ነገር ግን ዘንድሮ ብቻ ከውጭ ንግዳችን ያገኘነው የምንዛሪ መጠን ታይቶም ተሰምቶም የማያውቅ እጅግ በጣም ብዙ ነው። በዚህም 4 ቢሊዮን እንገባለን ብለን እየሰራን ነው፤ እንደምንገባም አመላካች ነገሮች አሉ። በመሆኑም የውጭ ምርታችን ከፍተኛ መሻሻል እያሳየ ነው። ነገር ግን ኢኮኖሚው ባደገ መጠን የወጪ ምርት ገቢ እየመጣ ነወይ ከተባለ አይደለም። ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች ሊነሱ ይችላሉ፤ ነገር ግን ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ አንዱ ነው።
እነዚህን ነገሮች ለማስወገድ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራን ነው አንደኛው ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ውስጥ ያልገቡ ምርቶች አሉ። ለምሳሌ ሽምብራ፣ ኑግ፣ ባቄላ፣ ዳጉሳ እና ለውዝ ሲሆኑ እነዚህ ግን ያለሕግና ሥርዓት እንደተፈለገ የሚሸጡና የሚወጡ ምርቶች ነበሩ። ዘንድሮ ግን እነዚህ ምርቶች እንደሌሎች ወጪ ምርቶች ወደአስተዳደር ሥርዓት እንዲገቡ ሆኗል። በመሆኑም በኮንትሮባንድ ማውጣት አይቻልም።
በተመሳሳይ የቁም አንስሳቱንም ቢሆን እንደ ሌሎች ወጪ ምርቶች ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ አልተወሰነላቸውም ነበር ፤ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ስራው አንዴ ወደ ግብርና ሌላ ጊዜ ወደ ንግድ እየመጣ ያልተረጋጋበት ሁኔታ ነበር። በመሆኑም እያንዳንዱ የቁም እንስሳ አይነቱ ክብደቱ ተለይቶ ምን ያህል ገንዘብ ሊያመጣ ይገባል የሚለው ተወስኖ መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ ተገብቷል። ይህ ከሆነ በኋላ በአንድ ወር ውስጥ ከቁም እንስሳት ብቻ 2 ሚሊዮንና ከዛ በላይ ገቢ እየመጣ ነው። ይህ ገቢ ደግሞ በፊት በኮንትሮባንድ ይወጣ የነበረ ገቢ ነው ማለት ነው።
በመሆኑም ሕገ ወጥ ኬላዎች እንዲነሱ ኮንትሮባንድ ላይ ከፍተኛ የሆነ ቁጥጥር እንዲደረግ ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው። ከዚህ ሌላ መላው ሕብረተሰብ በኮንትሮባንድ ላይ ያለውን አመለካከት እንዲያሰፋ በማድረግ ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ ነው።
ከውጭ ንግዳችን የምናገኘው ገቢ እያደገ ነው። ነገር ግን በሚፈለገው ልክ ነወይ ቢባል አይደለም። በተለይም ተቋማዊ አቅምን ከመገንባትና አስተሳሰብን ከማሳደግ አንጻር የሚሰሩ ሥራዎች አሉ እነሱንም አጠናክረን እንቀጥላለን።
ጥያቄ፡- አገራችን ከአገዋ የገበያ እንድትሰረዝ መደረጉ ምን ዓይነት ተጽዕኖ አሳደረ? ይህንን እድልስ የሚተኩ ሌሎች አማራጮች እየታዩ ነወይ ?
አቶ ገብረመስቀል፡- አገዋ በዓመት እስከ 258 ሚሊዮን ዶላር ከጨርቃጨርቅና ጫማ በመላክ የምናገኘውን ገንዘብ ነው። ከጥር 1 ቀን ጀምሮ ያጣነው። ይህንን የአሜሪካን መንግሥት ከግምት እያስገባ አስተያየት እንዲያደርግ በኤምባሲም በኩል ሥራዎች እየተሰሩ ነው። ተስፋ አልቆረጥንም። ከዛ በተረፈ ግን በተለይም በአውሮፓና በኤዢያ አገሮች ነባር ደንበኞች አሉን ፤ በእነሱ ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው፤ ከዚህ በተጨማሪ ጎረቤት አገሮች የእኛን ጫማ ስለሚፈልጉ አፍሪካ አገሮች ደግሞ ጨርቃጨርቅ ምርቶችን ስለሚፈልጉ እነዚህ ላይ ሰፋ ያለ ስራ እንሰራለን። ጎን ለጎንም ደግሞ አዳዲስ ገበያዎችን የማፈላለግ ነባር ገበያዎችን ደግሞ የማጠናከር ስራዎችን እየሰራን ነው። በቀጣይም ደግሞ ከአሜሪካን ኤምባሲ ጋር እየተነጋገርን ነው።
ጥያቄ፡- ያለበቂ ምክንያት ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር ባለመደረጉ ሕብረተሰቡን ለከፍተኛ የኑሮ ውድነት ሊዳረግ ችሏል። በመሆኑም ከፍተኛ የዋጋ ንረት በታየባቸው የሲሚንቶ ቆርቆሮና ብረት በመሳሰሉ ምርቶች ላይ የዋጋ ማረጋጋት ለማድረግ ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ገብረመስቀል፡- ከሲሚንቶ ከብረት ከቆርቆሮና ከሌሎች ግብዓቶች ጋር በተገናኘ ሕገወጥነት የሚስተዋልባቸው ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው። ለምሳሌ አሁን ካለው የሲሚንቶ ዋጋ ጭማሪ ጋር በተያያዘ ብንመለከት ችግሩ የተፈጠረው ከምርት አቅርቦት ችግር ጋር በተያያዘ ነው። ዋና ዋና ሲሚንቶ አምራች የሆኑ ፋብሪካዎች በአቅማቸው ልክ እያመረቱ አይደለም። ስለዚህ የምርት አቅርቦት ችግር ተፈጥሯል። ችግሩን ለመፍታት የድንጋይ ከሰል የሚባለው ግብዓት በውጭ አገር እስከ 3 መቶ በመቶ ድረስ ጭማሪ አሳይቷል። በአገር ውስጥ ግን 50 በመቶ ያህል ብቻ ነው ጭማሪ ያሳየው። በመሆኑ የማዕድን ሚኒስቴር የግብዓት ሰንሰለቱን ለማስተካከል ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው።
በዚህም የድንጋይ ከሰልን በብዛት ለማምረት ከውጭም የአገር ውስጥ ባለሀብቱም እንዲሰማራበት ለማድረግ የተለያዩ የማሳመን ስራዎች እየተሰሩ ነው። ሌላው የድንጋይ ከሰል ከሚወጣባቸው አካባቢዎች ምርቱን ለመጫን ከፍተኛ የሆነ የጸጥታም ችግር መኖሩ ከፍተኛ የሆነ ማነቆ ሆኗል። እነዚህ ችግሮች በሲሚንቶ አቅርቦት ላይ ጫና አሳድረዋል። ለጊዜውም የጸጥታ አካላት በየአካባቢው ያሉ የንግድ ቁጥጥር ግብረ ሃይል የንግዱ ማህበረሰብ በጋራ ቁጥጥር ማድረግና ሌባውን ማጋለጥ መቻል አለባቸው።
ብረትም በዓለም ላይም ጨምሯል። ያሉን ፋብሪካዎች መቶ በመቶ እንኳን ቢያመርቱ በአገሪቱ ያለውን ፍላጎት ለማሟላት አንችልም። በመሆኑም ከብረት ጋር በተያያዘ የአገር ውስጥ ፋብሪካዎች እንዲያመርቱ ማድረግ ከውጭም የሚገባበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል። በጠቅላላው እነዚህን ምርቶች በምናነሳበት የንግድ ሕጉ በሚፈቅደው ልክ ሥርዓቱን መቆጣጠር መቻል አለብን።
ከዛ ውጪ ግን ምርቱን በማከማቸትና በመደበቅ ገበያውን በሚያውኩ አካላት ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃን በየደረጃው እንወስዳለን።
ጥያቄ፡- አገራችን እየገጠማት ያለውን ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖ ለመቋቋም ቀጠናዊ ትስስር አቋራጭ መንገድ መሆኑ የሚታወቅ ነው ፤ በመሆኑም ይህንን ሁሉን አቀፍ ለማድረግ ምን እየተሰራ ይገኛል?
አቶ ገብረመስቀል፡- የተጀመሩ ስራዎችን በተቻለ ፍጥነት እያስኬድን ነው። በተለይም የአፍሪካ የነጻ የንግድ ቀጠና ሥርዓት ከፈረሙት አገሮች ኢትዮጵያ አንዷ ናት ፤ አሁን ደግሞ ከ5 ሺ በላይ የሚሆኑ እቃዎችን በምን ዋጋና በምን አይነት ጥራት እንደሚቀበሉ ዝግጅታችንን አጠናቀናል ፤ በዚህ ማዕቀፍ ኮሜሳም አለ። በዚህም ላይ ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው ያለው። ስለዚህ እነዚህን ስራዎች አጠናክረን የምንቀጥልበት ነው የሚሆነው።
ስለ ሰጡን ቃለ ምልልስ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስም እናመሰግናለን፡፡
አቶ ገብረመስቀል፡- እኔም አመሰግናለሁ
ዕፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን መጋቢት 29 /2014