ኢትዮጵያ በታሪኳ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረች ስትሆን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷም እንዲሁ ማንም ቅራኔ የሚያስገባበት አልነበረም። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ምንም ዓይነት ዲፕሎማሲያዊ ጫና በሌሎች አገራት ላይ ፈጥራ አለማወቋ ነው። ሌሎች አገራት ግን በተለይም ምዕራባውያን በተለያየ መልኩ የጫና ዱላቸውን ሲያሳርፉባት ይስተዋላል። ለዚህም በዋናነት የሚጠቀሰው አሁን ላይ ይጸድቃል አይጸድቅም ክርክር ውስጥ የገባው ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ነው። ይሁን እንጂ ይህንንም ቢሆን በድል እንደምታልፈው የቀደሙ ተሞክሮዎቿ ያስረዱናል። በጉዳዩ ላይ ሰፊ ማብራሪያ እንዲሰጡን አቶ እንዳለ ንጉሴ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የጋበዝን ሲሆን፤ ያሉንንም እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአሜሪካ እና አንዳንድ የአውሮፓ አገራት በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ጫናዎች እየተደረጉ ይገኛሉ፤ ለመሆኑ የእነዚህ ጫናዎች ዋነኛ ምክንያት እና ፍላጎት ምንድነው ይላሉ?
አቶ እንዳለ፡- ማንም ሰው ሲታይ ሙሉ እንዳለመሆኑ ሁሉ ዓለምም ስትታይ ሙሉ አይደለችም። ግለሰብ እና ዓለም ብቻ ሳይሆን ቡድን እና አገርም በራሱ ሙሉ አይደለም። በግልም ሆነ በቤተሰብ እንዲሁም በአገር ደረጃ የሚጎድለውን ነገር ለመሙላት ከሌላው ጋር በጥሩም በመጥፎም ጊዜ ይገናኛል። አንድ አገር የሚጎድለውን ለመሙላት ከሌላ አገር ጋር ይገናኛል። ከውስጥ በሕግ ይመራል፤ ከውጪ ደግሞ ፖሊሲ ያወጣል። ይሔ ፖሊሲ የተለያዩ ነገሮችን ከግምት ያስገባል። የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሲባል እንደአጠቃላይ የሚወጣ አለ። በተጨማሪ በልዩ ሁኔታ ተዘርዝረው የሚወጡ ፖሊሲዎች አሉ። ስለዚህ ኢትዮጵያ ስትታይ ከአምስት እስከ ስድስት ሺህ ዓመት የመንግሥትነት ታሪክ ያላት አገር ናት።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ዲፕሎማሲ ልምዷም ከፍተኛ እንደሆነ እንረዳለን። ዲፕሎማሲ የሚኖረው አገር ሲኖር ነው። ከሌላው አገር ጋር የምንገናኘው በጣም የረዥም ጊዜ ልምድም ያላት አገር ናት። እንደሕዝብም እውቅና አለው። ዲፕሎማሲ የሚጀምረው ከሉዓላዊነት ነው። የተባበሩት መንግሥታት የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ የሚናገረው ስለሉአላዊነት ነው። በመሆኑም ዲፕሎማሲም ሆነ ግንኙነቱ ሊጀመር የሚችለው ሉአላዊነትን ካመንን በኋላ ነው። የኢትዮጵያ ሉአላዊነት ከአምስት ሺህ ዓመት በላይ ልምድ ያላት አገር ነች። አሜሪካ ገና ወጣት ናት። ስለዚህ የሁለታችን ግንዛቤ እኩል አይደለም።
ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማንም ስለሉአላዊነት ሊያስተምረው አይችልም። ምክንያቱም ከማንም በላይ ያውቃል። ሉአላዊነት ማለት የመወሰን ነፃነት ነው። የውስጥ ጉዳይም ሆነ የውጭ ጉዳያችን ላይ የመወሰን ነፃነት ለማንም የሚሰጥ አይደለም። የእዚያ አገር ብቻ ነው። ስለዚህ ሉአላዊነት ለእዚያ ሕዝብ ብቻ የሚሰጥ ነው። ይሔ ደግሞ ውስጥ ያለውን ድንበር ላይ ያለውን ባሕር ላይ ያለውን አየር ላይ ያለውን በሙሉ ያካትታል።
የተባበሩት መንግሥታት የቅርብ ጊዜው ቻርተር እንኳን ሲታይ (Noninterference in the domestic affairs of other state) ይላል። ይህ ተግባራዊ የሚሆነው በሌሎች አገሮች ጣልቃ ባለመግባት ነው። ጣልቃ በሚገባበት ወቅት ግጭት ይፈጠራል። ይህ እንዳይሆን ሌሎችም ሕጎች አሉ። የቬና ኮንቬንሽንም ሆነ ሌሎች በርካታ ሕጎች አሉ። ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ከሌላው የተሻለ ልምድ አላት። ኢትዮጵያ ከነፃነት ጋር ተያይዞ ለሌላው ዓለም የምታበረክተው ነገር አላት። በዓለም፤ ለዓለም ሕዝቦች ነፃነት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው እና ለአንድ ሕዝብ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ እንደኢትዮጵያ ያስተማረ አገር የለም። ይህ ለአሜሪካውያንም ጭምር ነው። አሜሪካ በቀኝ ግዛት ውስጥ ሆና እንኳ ኢትዮጵያውያን በነፃነት ውስጥ ነበሩ።
አሜሪካኖቹ ከ70 ዓመታት በላይ ተገዝተዋል። ስለዚህ ከዲፕሎማሲ ጋር ተያይዞ የምናሰበው እኩል አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። እነርሱ የነፃነት ቀናቸውን ሲያከብሩ እኛ ግን የምናከብረው የድል ቀን ነው። ይሔ በጣም ትልቅ ልዩነት ነው። ስለዚህ በግለሰብም ሆነ በአገር ደረጃ የምናደርገው ነገር በሙሉ ከዚህ ሒደት ይነሳል።
ወደ አሜሪካ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ስንመጣ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ከ100 ዓመት በላይ ያስቆጠረ ረዥም ታሪክ ያለው ነው። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ አገራቱ ለጋራ ጥቅማቸው በጥሩም ሆነ በመጥፎም ጊዜያት ተባብረው ሲሠሩ አይተናል። በዲፕሎማሲ ትምህርት ላይ እንደሚገለፀው ነፃ ምሳ የለም። ማንም አገር ትንሽም ነገር ቢሆን ከሌላ አገር የሆነች ነገር ከተቀበለ መልስ መሥጠት የግድ ነው። ስለዚህ አሁን አሜሪካኖች እያንዳንዱን ነገር ሲያደርጉ ቋንቋቸው ላይ ሌላውን ለመርዳት ነው የሚል ቢሆንም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያደርጉት ለራሳቸው ጥቅም ነው። ይህ ደግሞ መርሕ አለው። ሕግና ደንብ አለው።
አሜሪካ እንደምታደርገው ኢትዮጵያ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ ከማንኛውም አገር ጋር በምታደርገው ማንኛውም ዓይነት ግንኙነት በማንኛውም አገር ላይ ጣልቃ ገብታ አታውቅም። ለማንኛውም አገር ይሔ የኔ አይዶሎጂ ነው ተቀበል ብላ አስገድዳ አታውቅም። ወይም ደግሞ መፈንቅለ መንግሥት አድርጋ ሌላ አገርን ጎድታ አታውቅም። ኢትዮጵያውያንም ይህንን አይወዱም።
ጥሩ ጎኖች እንዳሉን ሁሉ አሜሪካኖችም በዲፕሎማሲያቸው ባህሪ ምክንያት የሚያሳዩአቸው ወጣ ያሉ ባሕሪዎች አሉ። በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌላ አገር ላይም ነው። ይሔ ባህሪያቸው አንድ አገር በተቸገረ ሰዓት ከጎን ሆነው አይገኙም። ኢትዮጵያ በእነዚህ መቶ ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ችግር ገጥሟት ያውቃል። በዚህ ጊዜ ውስጥ የአሜሪካ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጎን ሆኖ አያውቅም። ነገር ግን የአሜሪካ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ግን ስለማይጋጭ ሕዝብ ለሕዝብ የከፋ ግንኙነት የለም።
በአፍሪካ ቀንድ ኢትዮጵያን ያልያዘ አገር ጥቅሙን ማስከበር አይችልም። ስለዚህ ኢትዮጵያ ከስትራቴጂክ አቀማመጧ የተነሳ የተለያዩ አገራት ጥቅማቸውን ለማስከበር ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት ማድረግ ይፈልጋሉ። ኢትዮጵያ ትልቅ ሕዝብ እና ሀብት ያላት አገር ናት። የመሬት አቀማመጧም በጣም አስፈላጊ ነው። ስለዚህ አሜሪካ ወደደችም ጠላችም ከኢትዮጵያ ጋር መሥራት ግዴታዋ ነው። ባለፈው ታሪክም ለኢትዮጵያ ወሳኝ በሆኑ ጊዜያት ማለትም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት እና በዚያድባሬ ወረራ እንዲሁም በሌሎች አስቸጋሪ ጊዜያት ላይ ሲታይ አሜሪካ እና ምዕራባውያን ከጎናችን ነበሩ ማለት አይቻልም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው ሲባል አንደኛው ታሪካቸው ነው። ኢትዮጵያ በነፃነት የኖረች አገር ናት። በ(neocolonialism) አስተሳሰብ ውስጥ ያሉ አገራት በተለይ ምዕራቡ ይህንን አይወዱትም። ይህ ተምሳሌትነት በምዕራባውያን ነው ተምሳሌትነት ነው የሚታየው።
ስለዚህ እነዚህ ምዕራባውያን የሚፈልጉት ይህችን አገር ማዳከም፤ መከፋፈል ዋና አጀንዳቸው ነው። ነገር ግን ይህንን አጀንዳቸውን ለማስፈጸም በተለያየ ዘዴ ቀባብተው ነው የሚያመጡት። በቀጥታ ኢትዮጵያን ልናፈርስ ነው አይሉም። ኢትዮጵያን እንወዳታለን ብለው የሚፈልጉትን ተቃራኒ ተግባር ለመፈፀም ጥረት ያደርጋሉ።
ይህን ለማድረግ በዋናነት እንደመሣሪያ የሚጠቀሙት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውን ነው። የውጭ ፖሊሲያቸውን የሚፈፅሙባቸውም የተለያዩ መንገዶች አሉ። የመጀመሪያው እና ዋነኛው መንገድ ደግሞ ዲፕሎማሲ ነው። ዲፕሎማሲ ሰላማዊ ግንኙነትን መሠረት ያደረገ እና በመነጋገር ችግሮችን የሚፈቱበት ዓይነተኛ መሣሪያ ነው። ሁለተኛው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ መሣሪያ ደግሞ ስለላ ነው። ከስለላ ባለፈ ሌላኛው የውጭ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ መሣሪያቸው ደግሞ ፕሮፖጋንዳ ነው። ከእነዚህ አመራጮች በተጨማሪ አንዳንድ ጊዜ ነገሮችን ለመቆጣጠር እና የብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ኃይል መጠቀምም ሊኖር ይችላል። ለዚህ ደግሞ ራሺያ ዩክሬን ላይ እያደረገች ያለችው ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ ነው።
ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት በጥንቃቄ መያዝ ያለበት ነው። አሜሪካ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውም በሌላውም ትልቅ አገር ናት። ስለሆነም ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር የምታደርገው ግንኙነት ለኢትዮጵያ አስፈላጊ ነው። እስካሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ታማኝ ናት። አሁንም ቢሆን ከአሜሪካ ፍላጎት ጋር የሚጋጭ ነገር አድርጋ አታውቅም። በጣም አስቸጋሪ በነበረው በደርግ ሰዓት እንኳን እነሱ ናቸው ኢትዮጵያን የገፉት እንጂ ኢትዮጵያ እነሱን አልገፋችም። በወቅቱ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር ኢትዮጵያ ከአሜሪካ የገዛችውን መሣሪያ ጭምር ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ነው የከለከሉት። ይህ ማለት አሜሪካ የሶማሊያውን አምባገነን መንግሥት ዚአድባሬ በመርዳት ኢትዮጵያ በሶማሊያ እንድንወረር አድርገዋል።
በኢትዮጵያ አሻንጉሊት የሆነ ታዛዥ መንግሥት ለመመስረት አለፍ ሲልም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ባለፉት 30 እና 40 ዓመታት አሜሪካኖች እና ምዕራባውያን የቀረጹት ስልት ኢትዮጵያን በቀጥታ መዋጋት ወይም መጋጠም አይደለም። ምክንያቱም ሕዝቡ ንቁ ስለሆነ ይህን መሞከር አይፈልጉም። ኢትዮጵያውያን የትም ይኑሩ የት ለሉዓላዊነታቸው ቦታ የሚሰጡ ሕዝቦች ናቸው። ይህን ሁሉ ግንዛቤ ውስጥ ያስገቡት ምዕራባውያን በኢትዮጵያ አሻንጉሊት መንግሥት ለመፍጠር አለፍ ሲልም አገሪቱን ለመበታተን የተጠቀሙት የኒዎኮሎኒያሊዝም ፖሊሲን ነው። በዚህ ፖሊሲአቸው በቀጥታ አንድን አገር አይዙም። ፖሊሲ ያወጣሉ በዚህ በፖሊሲ አንድን አገር ለመጉዳት እና ለመጥቀም የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ።
በዚህ ስውር እና ያልተጻፈው ፖሊሲያቸው ምዕራባውያን እኛን እርስ በራሳችን ማጋጨት ነው የሚፈልጉት። ለዚህ ደግሞ የታጠቀ ቡድን ያስፈልጋቸው ነበር። ይህን ተከትሎ ለዓላማቸው መሳካት የሚመቸውን የሕወሓት ቡድን በራሳቸው ወርድ እና ቁመት ልክ አዘጋጁ። ሕወሓት ደግሞ ትዕቢት እንዳይኖርበት እና አልታዘዝም ብሎ እንዳያስቸግራቸው ወዲያውኑ በሽብርተኝነት መዘገቡት።
ሲመሠረት ጀምሮ እስከ አሁን ሕወሓትን የሽብርተኝነት መዝገብ ውስጥ እንዳስቀመጡት ነው። አሁን ድረስ አልሰረዙለትም። ትናንትና የተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ብሎ ሕወሓትን ሲያወግዝ እና በሽብርተኝነት መዝገብ ውስጥ እንዲካተት ሲያደርግ ኢትዮጵያውያን ሲገረሙ ተመልክተናል።
ሕወሓት ወደ መንግሥትነት ሲመጣ ሰላማዊ አልነበረም። የሽብር ሥራ እየሠራ ነው የመጣው። የትግራይ አካባቢን ማህበረሰብ ሳይቀር እያገተ እና በርሃብ እየቀጣ ወደ ስልጣን የመጣ ድርጅት ነው። ይህንን እንዲሆን ያደረጉት ምዕራባውያን ናቸው። በሕወሓት አቅም ኢትዮጵያን መቆጣጠር አይችልም ነበር። የፈለገ ግራ እና ቀኝ ቢተነተን በሕወሓት አቅም ኢትዮጵያን መቆጣጠር አይችልም። ምዕራባውያን ግን ገንዘብ ሰጥው፤ አቅጣጫ ቀይሰው፤ ደጋፍ ሰጥተው፤ በፕሮፓጋንዳ እያጀቡ አዲስ አበባ አምጥተው ቁጭ አደረጉት።
አሜሪካ እና ምዕራባውያን ሕወሓትን አዲስ አበባ ቁጭ ካደረጉት በኋላ የራሳቸው መጠቀሚያ መሣሪያ አድርገው አስቀመጡት። ኢትዮጵያውያን ሕወሓትን ሲመለከቱ ኢትዮጵያዊ ሊመስላቸው ይችላል። ምክንያቱም የሚናገረው አማርኛ፣ ትግርኛ፣ ኦሮምኛ ወይም ሌላ ሊሆን ይችላል። የሚሠራው ግን ኢትዮጵያዊ አይደለም። ሕወሓት ስልጣን ላይ እንደወጣ ወዲያውኑ የጀመረው ኢትዮጵያን የማፍረስ ተልዕኮውን ነው።
በተማሪዎች እንቅስቃሴ ጊዜም ያስፈጽሙ የነበረው የአሜሪካ እና የምዕራባውያንን ፍላጎት ነበር ። በዚያን ጊዜ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ የማይመለከታትን ሥራ እንድትሠራ ያደረጓት ነበር ።
ኢትዮጵያ በታሪኳ በብሔረሰቦቿ መካከል ያለውን ልዩነቷን ፈር ማሲያዝ አቅቷት አያውቅም። ፈዴራሊዝም ከመጀመሪያ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ይታወቃል። በሕገ መንግሥት ቅቡልነት ባይሰጠውም እንኳን የሸዋ፣ የጎንደር፣ የባሌ፣ ወለጋ ፣ ጅማ ፣ ወላይታ ወዘተ መደበኛ ባልሆነ መንገድ (ኢንፎርማሊ) በአገራችን ሲተገበር የኖረ ነው። በሕወሓት ዘመን ምዕራባውያን ይህን መልክ ማሲያዝ በሚል ሂሳብ መጥቷል።
የአንድ አገር ሕገ መንግሥት መቼም የፍችውን እና የጋብቻውን ውል በአንድ ወረቀት ላይ አይጽፍም። ሕወሓት የአሜሪካ እና የምዕራባውያንን ተልዕኮ ለማስፈጸም በአሜሪካ እና ምዕራባውያን ወርድ እና ቁመት ልክ ቀዶ የሰፋው ሕገ መንግሥት ግን ፍች እና ጋብቻውን በአንድ ወረቀት አጣምሮ የያዘ ነው። በመሆኑም ይህ ሕገ መንግሥት በዓለም ላይ በዓይነቱ ልዩ ያደርገዋል።
ሕገ መንግሥቱ ፍችውን እና ጋብቻውን የያዘ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ላለፉት 30 ዓመታት በዓለም ሕዝብ ፊት እንዲዋረዱ ሲያደርግ ኖሯል። ኢትዮጵያውያን በዘር፣ በሃይማኖት ወዘተ በማይመለከታቸው ነገር እንዲከፋፈሉ አድርጓል። በአገሪቱ ምንም ሰላም እንዳይኖር በማድረግ ኢትዮጵያንም ለማዋረድ ይህን ያደረገችው ለሕወሓት በገፍ ገንዘብ የምትሰጠው አሜሪካ ናት። አሜሪካ ሕወሓትን ተጠቅማ በኢትዮጵያ ላይ የሠራቸው ግፍ በዓለም ላይ በዓይነቱ በጣም የተለየ ነው።
ዲፕሎማሲ ማለት ምን ማለት ነው? አገርን ነው የሚወክለው የሆነ ፓርቲን ወይም መንግሥትን አይደለም። መንግሥት ማሽን ነው። መንግሥት ይመጣል፤ መንግሥት ይሄዳል። ከለውጡ በፊት የነበሩ ዲፕሎማቶቻችን እውነት ኢትዮጵያን ይወክሉ ነበር? ብለን ከጠየቅን በግሌ ኢትዮጵያን ይወክላሉ ብዬ አላስብም። ምክንያቱም በሚጽፉት ጽሑፍ እራሱ ኢትዮጵያን በትልቅነት ለማንሳት ይቸገራሉ። ገናና ታሪኮቿን እና ታላቅነቷን ማንሳት ይቸገራሉ። አንድም ቀን ታላቅነቷን ሲያነሱ አይተን አናውቅም።
በኢህአዴግ የነበረውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ልክ እንደ ሕገ መንግሥቱ ነበር። የኢትዮጵያን የውጭ ፖሊሲ የሚመለከት ማንም ሰው መቼም አንድ እውነተኛ የሆነ ኢትዮጵያዊ ፈጽሞ ሊያደርገው እንደማይችል ይመለከታል።
በዘመነ ኢህአዴግ ሁሉ ነገር በዘር የተከፋፈለ ስለነበር ኢትዮጵያውያን በፓርቲውን እምነታቸው እየቀነሰ በመምጣቱ የፓርቲው ህልውን በአጭሩ ተቀጨ። ፓርቲውን ለማስወገድ የነበረው ትግል በአገሪቱ ብጥብጥን አመጣ። ኢትዮጵያውያን ግን አብሮ የመኖር የሺህ ዓመታት ልምድ ስለነበራቸው ይህን በትልቅ አገራት የሚመራ ለጥፋት የተደራጀ ቡድን በብልሃት እና በጥበብ እንዲሁም በትዕግስት እስከወዲያኛው ሸኙት። ሕወሓትን ከስልጣን ለማባረር በነበረው ትግል ውስጥ ሕዝብ በከፍተኛ ደረጃ ባይሳተፍበት ኖሮ በታላላቅ አገራት በሁለንተናዊ መልኩ የሚረዳን ቡድን ማሸነፍ ፈጽሞ የማይታሰብ ነበር። እጅጉን ከባድ ነበር።
ለሕወሓት መውደቅ የሕዝብ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ለመረዳት የተለያዩ ነገሮችን ሂደት እና ውጤት መመልከት ይቻላል። ለምሳሌ ወታደር በፈረሰበት፣ የደህነነት እና የስለላ ተቋማቱ በደከሙበት ሰዓት እንኳን በ15 ቀናት ውስጥ ነው ወያኔን ለግባተ መሬቱ ያበቁት። ይህን አምኖ መቀበል ያቃታቸው አሜሪካ እና ምዕራባውያን የወያኔ ውድቀት እንዴት በ15 ቀናት ሊሆን ይችላል? በማለት ተናደዱ። እንዴት ተበለጥን? የሚለው ደግሞ እጅጉን አንገበገባቸው። ምክንያቱም ስንት አመት ኢንቨስት ያደረጉበት ሕወሓት በ15 ቀናቶች እንደዚህ ይሆናል ብለው አልገመቱም ነበር ።
አሜሪካ እና ምዕራባውያን ሕወሓት የፈረሰ ቀን ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ብለው አቅደው ይሠሩ ስለነበር ነው። ስለዚህ አሜሪካ እና ምዕራባውያን ኢትዮጵያን የማጥፋት ፕላን በሌላ ባልተገመተ ፕላን እና እውቀት ተመትቶ ከጥቅም ውጭ ሆነ። በእውነቱ አሜሪካ እና ምዕራባውያን ስንት አመት የደከሙበት ፕሮጀክት ውሃ ሲበላው በጣም መናደድ ነበረባቸው። ምክንያቱም ኢትዮጵያን ለማጥፋት ለጥፋት ቡድኑ በከፍተኛ ደረጃ ኢንቨስት ያደረጉበት ስለነበር ነው። ኢትዮጵያ ከዚህ ጥፋት መትረፏ አሜሪካ እና ምዕራባውያን ሊዋጥላቸው አልቻለም።
አሜሪካ እውነተኛ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ውስጥ አላት ብዬ አላምንም። የቻይናን ኢንቨስትመንት ስንመለከት ግን መንገዶችን፣ ፋብሪካዎችን፣ ሞሎቹን ወዘተ እንመለከታለን። እውነተኛ የአሜሪካ ኢንቨስትመንት ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ምንድን ነው? ቢባል መልሱ ምንም የለም ነው።
ዩ ኤስ ኤድ የሚባል ድርጅት አለ። እሱ ደግሞ ዋና ሥራው መረጃ መሰብሰብ ነው። ይህ ድርጅት መረጃ ለመሰብሰብ ነው እንጂ ገንዘብ የሚያወጣው እኛ ኢትዮጵያውያንን ለመደገፍ አስቦ አይደለም። አሁን በሰሜኑ ጦርነት ያደረገውን እንኳን እናውቃለን። አጠገቡ ለሚገኙ በጣም ለተራቡ ኢትዮጵያውያን እህቶቻችን እና ወንድሞቻችን ለችግራቸው አልደረሰላቸውም። ከዚያ በፊትም አካባቢ በተለያዩ ነገሮች መጎዳቱ ይታወቃል። ወረራው የተቀጣው ደግሞ ታስቦበት ፕላን ተቀርጾለት ነው።
በዲፕሎማሲ love and hate የሚባል አካሄድ አለ። እየሳሙ መንከስ እንደማለት ነው። ይህ በዲፕሎማሲያዊ ሂደት የታወቀ ነው። አሜሪካኖች ይህንን ስልት በከፍተኛ ደረጃ ይጠቀሙታል። በኢትዮጵያም ሲያደርጉት የኖሩት ይህንን ነው።
አሜሪካኖችን ያበሳጫቸው ያ ለረጅም ጊዜ ያሰቡት አፍሪካውያንን ጭምር በማስፈራራት ኒዎኮሎኒያሊዝምን ለመተግበር የሄዱበት እርቀት የተደናቀፈበት አጋጣሚን የፈጠረ በመሆኑ ነው። በዚህም በንዴት በጣም ተወራጩ። በዚህም አበቃለት የተባለውን ወያኔ በመረጃ እና ደህንነት እያገዙ፣ እርዳታ እየሰጡ ወዘተ ወያኔ ከሞተበት በማንሳት እንደገና እንዲያገግም አደረጉ። ያ ብቻ አይደለም አሁን ላይም የሞተውን ወያኔ ወደ ስልጣን ለማምጣት እና የኢትዮጵያን ሕዝብ ትግል ለማደናቀፍ የተለያዩ ፖሊሲዎችን እያወጡ ነው።
አዲስ ዘመን፡-ሰሞኑን ለአሜሪካ ኮንግረስ የተመሩት ኤችአር 6600 እና ኤስ 3199 የተሰኙ ረቂቅ ሕጎች መነሻንስ እንዴት ያዩታል፤ እነዚህ ሕጎች በኮሚቴ ተቀባይነት ያገኙት ኢትዮጵያ በርካታ ማሻሻያዎችን እያደረገች ባለችበት ሁኔታ ውስጥ መሆኑስ ምን ያሳያል፤ለምሳሌ ኢትዮጵያ ግጭት ማቆሟን ባሳወቀችበት እና ሰብአዊ ርዳታ ለማስገባት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እያለች ባለችበት ወቅት መወሰኑ ምን ያሳያል?
አቶ እንዳለ፡- እንግዲህ ለውጡን ማየት ያስፈልጋል። እነሱ ጁንታውን አምጥተው ዲዛይን ያደረጉት ኢትዮጵያውያንን እንዲከፋፍል አስበው ነው። ይህን ተከትሎ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ባለፉት 30 አመታት በራሳቸው ኤምባሲ ፊት የራሳቸውን አገር ሲቃወሙ በተደጋጋሚ ተመልክተናል። እብድ ሆነው እኮ አይደለም። ያ በዘመነ ሕወሓት ኢትዮጵያ ትከተለው የነበረው ዲፕሎማሲያዊ አሠራር የሌላ አገር ማስፈጻሚያ ስለሆነ ነው። የአንድ ቡድን ማስፈጸሚያ ስለነበር እና ያ ቡድን ደግሞ የሌላ አገር ተላላኪ ነው። ያውም ደብል ተላላኪ። አንደኛ ለአሜሪካ ይላላካል። በሌላ መልኩ ደግሞ ለግብጽ ይላላካል። የሁለቱ ፍላጎት ኢትዮጵያን ማጥፋት ነው።
በተለይ የግብጽ ፍላጎት አሁን ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ባላት ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይታረቃል ተብሎ አይታሰብም። ምክንያቱም በሕገ መንግሥት የተደገፈ ነው። የግብጾችን ሕገ መንግሥት ብንመለከት ከአንቀጽ 44 ላይ ከዚህ በፊት እና በኋላ ያሉ አንቀጾች ቢነበቡ ምንድን ነው የሚሉት ዓባይ የግብጽ ታሪካዊ ሀብት ነው የሚል ነው። ለዓባይ ውሃ ዜሮ በመቶ የማያመነጭ አገር በሕገ መንግሥቱ ዓባይ የእኔ ነው ብሎ ነው የጻፈው። ስለዚህ ምንም የዲፕሎማሲውን ሂደት ጠብቀን ስንወያይ ብንውል ግብጻዊያን በሕገ መንግሥታቸው ላይ የተቀመጠ ስለሆነ የእነሱ ሕገ መንግሥት ካልተቀየረ ወይም ካልተሻሻለ በስተቀር መግባባት ላይ ልንደርስ አንችልም።
የቱንም ያህል ኢትዮጵያውያን ከግብጽ ጋር ሲወያዩ ቢውሉ ሕገ መንግሥቱ ላይ ያለውን ነገር አልሲሲ ሊቀይረው አይችልም። ሕገ መንግሥቱ መሻሻል አለበት። ሕወሓት የዚህ ጽንፈኛ ቡድን ዋነኛ ተላላኪ ነው፤ የዚህ ቡድንም ገንዘብ ተቀባይ ነው። አሁን ላይ ኢትዮጵያውያን ያከሸፉት ያንን ምዕራባውያን እና አሜሪካውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ለዘመናት ሲሠሩባቸው የቆየቱን የጥፋት ድግስ ነው። ይሄ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም የሚጠቅም ነው። ስለዚህ ለውጡ ሲመጣ ማስተንፈሻው መንገድ ምን ነበረ? ሕወሓትን ተጠቅመው የአገርን ሰላም ማወክ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናሁ።
አቶ እንዳለ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2014