የባህል ሳምንት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ብዝሐ ባህል ላለባቸው አገራት ፋይዳው ከፍ ያለ ነው ። ከተለያዩ የባህል ዳራዎች እና ልምዶች ካሉባቸው አካባቢዎች የሚሰባሰቡ ዜጎች እርስ በእርሳቸው እንዲማማሩና ባህሎቻቸውን እንዲጋሩ እድል ይፈጥራል ። ሳምንቱ አንዱ አንዱን እንዲያውቅ እና እንዲማር እድል ስለሚፈጥር ፤ የተለየ ባህል ያለውን እንደ ባዕድ ከማየት ይልቅ ለማወቅ እንዲጓጉ ያደርጋል ። ይህም ማኅበረሰቡን በማስተሳሰር በሕብረ ባህል የደመቀ አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ለሚደረገው ጥረት ከፍ ያለ ፋይዳ አለው ።
ካለፈው ዓመት ጀምሮ ኢትዮጵያ የባህል ሳምንት ማክበር የጀመረች ሲሆን፤ ከግንቦት 10 እስከ 16/2013 ዓ.ም ድረስ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የባህል ሳምንት በወዳጅነት አደባባይ ተከብሮ ነበር ። ከሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የተወጣጡ ልዑካን ወካይ ቅርሶችን እና የባህል ጭፈራዎቻቸውን ይዘው በመገኘት ያሳዩበት ነበር ። መድረኩ ኢትዮጵያውያን አብሮነታቸው እና ወንድማማችነት የጎላበትም ነበር።
ዘንድሮ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ አርሲ ዞን በሻሸመኔ ከተማ “ባህላችን ለቱሪዝም ዕድገት” በሚል መሪ ሀሳብ የኦሮሚያ ባህል ሳምንት ተካሂዷል ። በባህል ሳምንቱ ላይ ሁሉም የኦሮሚያ ክልል ዞኖች የባህል ቡድኖች የተሳተፉበት ሲሆን በጎዳና ላይ ትርዒት፣ የባህል ኢንዱስትሪ ምርቶች አውደርዕይ፣ በተለያዩ ሙዚቃ ባንዶች መካከል ውድድር ቀርቦበታል ።
በባህል ሳምንቱ የሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የባህል ልዑካን ቡድኖች የየራሳቸውን አለባበስ እና አጨፋፈርም አሳይተዋል ። ከሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የተለያዩ ብሔሮችን ወክለው የመጡ ቡድኖች ጭፈራዎቻቸውን ለታዳሚው አሳይተዋል ። ከኦሮሚያ ከተለያዩ ዞኖች የመጡ ተወካዮች ደግሞ ከጭፈራ ባሻገር ፣ ባህላዊ ምግቦችን ፣ አልባሳትን ፣ መጠጦችን ለሕዝቡ አስጎብኝተዋል ። የባህላዊ ምግቦቹ እና መጠጦቹ አዘገጃጀት ፣ መቼ እንደሚዘጋጅ ፣ ለማን እንደሚዘጋጅ እንዲሁም ከምን እንደሚዘጋጅ የብሔሩ ተወላጆች ማብራሪያ ሰጥተዋል ።
ከዚያ ጎን ለጎን ሁሉም የክልሉ ዞኖች የተውጣጡ ልዑካን ቡድኖች በአካባቢያቸው የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችን ወካይ ምስሎችን በማዘጋጀት የማስተዋወቅ ሥራዎችን ሠርተዋል። የቱሪዝም እምቅ ሀብቶችን አሳይተዋል ። በተለያዩ ዘርፎች የመሳተፍ ፍላጎቱ ያላቸው ኢንቨስተሮች መረጃ እንዲያገኙ እድል የፈጠረ ነው ።
የባህል ሳምንቱ የተከበረባት ሻሸመኔ አሳዛኙን ክስተት ካስተናገደች ሁለት ዓመት እንኳ ሳይሞላት አገግማ እንዲህ አይነት ትልቅ መርሐ ግብር ለማስተናገድ መቻሏ በብዙዎች ዘንድ ግርምትን ፈጥሯል ። በወቅቱ የደረሰውን ውድመት ያዩ ሰዎች ከተማዋ ዳግም ለመነቃቃት በርካታ አስርተ ዓመታት ሊፈጅባት እንደሚችል ሲገለጹም ነበር። ሻሸመኔ ግን ከጉዳቷ ለማገገም ብዙ ጊዜ አልፈጀባትም ። ከተማዋ ፍፁም ሰላም ፣ የተነቃቃች እና ጥሩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚታይባት ሆናለች ። አምራ ደምቃ በአምስቱም በሮቿ እንግዶቿን እያስተናገደች ትገኛለች።
የባህሉ ተሳታፊ የሆኑት እንደተናገሩት ሳምንቱ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን የተለያዩ ባህሎችን በአንድ ቦታ ላይ አቅርበው የሚያሳዩበት እድል መፈጠሩ ብዙ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል ። አንዱ የአንዱን እንዲያውቅ እድል የፈጠረ ከመሆኑም ባሻገር ቱሪዝም እና ኢንቨስትመንት ለመሳብም የራሱ ድርሻ ይኖረዋል።
ወይዘሮ ሰላማዊት ሙላቱ፤ ከቢሾፍቱ ባህልና ቱሪዝም የቱለማ ባህላዊ አልባሳት፣ አጨፋፈር፣ አመጋገብ ለማሳየት በቦታው የተገኙ ናቸው። ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን የሸዋ ቱባ ባህልን ማስተዋወቅ መቻላቸውን ጠቁመዋል።
የባህል ሳምንቱ የማኅበረሰቦቹ እሴቶች እንዳይረሱ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ። መንግሥት መሰል ትርኢቶች የሚቀርቡበትን መድረኮችን ማዘጋጀቱን መቀጠል አለበት። ለቱሪስት ፍሰት እድል ስለሚፈጥር የኢኮኖሚ እድል የመፍጠር አቅም ስለሚኖረው ትኩረት መድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል ። ትርዒቶቹን አሳይቶ ወደ ቤት መሄድ ብቻ ሳይሆን ወደ ገንዘብ መቀየር የሚቻልበትን ሁኔታ መንግሥት በጥናት ላይ ተመርኩዞ ሊሠራበት ይገባል ብለዋል ።
በነዚህ መድረኮች ላይ የታዩ አጨፋፈሮች ፣ አለባበሶች ፣ ምግቦች ፣ መጠጦች የየራሳቸው መገለጫዎችን ቢኖሩም የሚያቀራርባቸው ነገሮችም አሉ ። ይህም የኢትዮጵያውያን በዘመናት አብሮነት ሂደት የገነቡትን ትስስር አመላካች ነው ። በመድረኩ ሲዳማን ወክሎ የተሳተፈው አስናቀ አየለ እንደሚለው፤ የአንዳንድ ብሔሮች ባህላዊ ምግብ መመገቢያ ቁሶች የሚታየው መመሳሰል የሕዝቦችን ትስስር የሚያመላክት ነው ።
እንደ አቶ አስናቀ ማብራሪያ ፤ በባህል ሳምንቱ የቀረበውን የተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦችን መገለጫዎችን ለማየት እድል የፈጠረለት እንደመሆኑ ሙሉ ኢትዮጵያን በአንድ ቦታ የማየት እና ስለ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ከዚህ በፊት ከሚያውቀው የበለጠ የማወቅ እድል አግኝቷል። ሲዳማ ሆኖ የመላውን ኢትዮጵያውያንን አመጋገብ፣ አለባበስ፣ አጨፋፈር እና ሌሎች መገለጫዎች ማወቅ መቻሉ በየትኛውም አካባቢ ቢሄድ እንግድነት እንዳይሰመው እንደሚያደርገው ያነሳል ።
በተመሳሳይ መልኩ ከሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች በባህል ሳምንቱ ላይ የተገኙ ሲዳማ ክልልን የማያውቁ ኢትዮጵያውያን ሲዳማ ሳይሄዱ በሻሸመኔ ሆነው ስለ ሲዳማ እንዲያውቁ እድል መፍጠሩን ተናግሯል ። በቀጣይ በርካቶች ሲዳማ ሄደው ለመጎብኘት ጉጉት እንዲያድርባቸው የሚያደርጉ እሴቶች መታየታቸውን ጠቁሟል።
የብሔረሰቦችን ባህሎችን ከማወቅ ባሻገር ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከተገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር በግል የመተዋወቅ እድል እንደተፈጠረለት የሚናገረው አስናቀ ፤ ከተለያዩ አካባቢዎች ከመጡ ኢትዮጵያውያን ጋር ጓደኝነት ለመፍጠር እንዳስቻለው አብራርቷል ። ይህም ለወደፊት ሕይወቱ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ያነሳል ። በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ ቢሄድ ብቸኝነት እንደማይሰማው የሚያደርግ መሆኑን አንስቷል ።
አገር ለማልማትና ሰላምን እውን ለማድረግ መተዋወቅ እና መቀራረብ ወሳኝነት አለው። አንዱ ሕዝብ የሌላውን ቋንቋ ፣ ባህል እና ሌሎች መገለጫዎችን እንዲያውቅ እድል ይፈጥራል። ማኅበረሰቡ የሚታወቅበትን ተቻችሎ የመኖር ባህሉን እንዲያጠናክር ስንቅ በመሆንም ያገለግላል። ይሄ እንደ ቀላል መርሐ ግብር የሚታይ አይደለም ።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ መረጃዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት ተዋደው በኖሩ በብሔር ብሔረሰቦች መካከል አብሮነትና መቀራረብን ሳይሆን ልዩነትን፤ ጥላቻን የሚሰብኩ እየሆኑ መምጣታቸውን የሚያነሳው አቶ አስናቀ ፤ ኢትዮጵያውያን በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ በሚናፈሰው አፍራሽ ወሬዎች እንዳይወሰዱ የባህል ሳምንትን የመሳሳሉ መርሐ ግብሮች ከፍ ያለ ጥቅም እንዳላቸው ያብራራል ።
የባህል ሳምንቱ ከምስራቅ ፣ ምዕራብ፣ ከደቡብ ሰሜን ጫፍ የሚመጡ ሕዝቦች መገለጫዎቻችን የሚያሳዩበት በመሆኑ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በአገሪቱ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች አንዱ አንዱን እንዲጠላ እንዲጠራጠር፣ እንዲሸሽ የሚገፋፉ እኩይ ዓላማ ያላቸው ሰዎች የሚያናፍሱትን አደገኛ ትርክት ለማክሸፍ ትልቅ መድረክ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ነው ። ይህም ኢትዮጵያዊነት እየጠነከረ እና አንዱ አንዱን የመረዳት እድል እየሰፋ እንዲሄድ የሚያስችል ነው ።
ኢትዮጵያውያን የሚገናኙበት የባህል ሳምንታት በተደጋጋሚ ቢዘጋጁ ኢትዮጵያውያን እንዲተዋወቁ እና እንዲቀራረቡ እንዲሁም አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ እድል የሚፈጥር እንደመሆኑ በቀጣይነት በአገር አቀፍ እና በክልሎች ደረጃ ቢዘጋጁ ከፍ ያለ ፋይዳ እንደሚኖረውም ተናግሯል ።
የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሰዓዳ ኡስማን እንደተናገሩት ፤ ከዚህ ቀደም የኦሮሚያ ባህል ሳምንት የክልሉን ዞኖች ብቻ ባሳተፈ መልኩ ይከበር ነበር። በዚህ ዓመት ግን ሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦችን ባሳተፈ ሁኔታ የሁሉም ክልሎች ባህል ቡድኖች በተገኙበት እንዲሁም የሁሉም ክልሎች ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎች በተገኙበት መከበሩ ለበዓሉ ውበትና ድምቀት ጨምሯል ። የዘንድሮ የባህል ሳምንት ኢትዮጵያውያን ብዙ ሆነው እንደ አንድ የታዩበት ነው ።
ሻሸመኔን እና የአርሲን ሕዝብ በማይገልጽ መልኩ ከባድ ጉዳት አስተናግዳ የነበረችበት ነው ። ከተማዋ ግን በሕዝቦቿ እና በመንግሥት ጥረት ሁለት ዓመት ሳይሞላት የወደመውን ጠግና ፣ የፈረሰውን መልሳ ገንብታ መገኘቷ የሚያስመሰግናት ነው ። ዳግም ወደ ነበረችበት ለመመለስ እስከ 50 ዓመት ሊፈጅባት ይችላል የተባለችው ሻሸመኔ በሁለት ዓመት ውስጥ ማገገም መቻሏ ሕዝብና መንግሥት እጅ ለእጅ ተያይዘው ከተንቀሳቀሱ የማያሳኩት ነገር እንደማይኖር የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የባህል ሳምንት መዘጋጀቱ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም እንዳለው የጠቆሙት ወይዘሮ ሰዓዳ የውጭ እና የአገር ውስጥ ቱሪስቶችን ለመሳብ እንዲሁም ኢንቨስትመንቶችን ለማስፋት እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል ። እምቅ አቅም የታየበት እንደመሆኑ የውጭ እና የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ወደ አገር ውስጥ እንዲሳቡ ያደርጋል ። ያልታዩ የባህል ሀብቶችና ጸጋዎች የታዩበት እንደመሆኑ ባህልን ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ከሚኖረው ፋይዳ ባሻገር ኢንቨስትመንት እድገት ከፍተኛ ሚና ይኖዋል።
የኢፌዲሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው ፤ “ባህል ሰፊና ትልቅ ትርጉም ያለው የአንድ የኅብረተሰብ ማንነት የሚገለጽበት ምሰሶ ነው” ሲሉ የገለጹ ሲሆን ባህልን መጠበቅ ፣ መንከባከብ እና ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው።
ኢትዮጵያ ህብር ባህል ያለባት አገር እንደመሆኗ ባህሎችን ማስተዋወቅ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ የሚገባው ቢሆንም እስካሁን ድረስ በሚገባው ልክ አልተሠራም ብለዋል ። ባለፈው ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የባህል ሳምንት አከባበር መልካም ጅምር የታየበት ነበር ብለዋል ።
የባህል ሳምንቱን በክልሎች እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ማክበር ፋይዳው የጎላ መሆኑ ስለታመነበት በቀጣይ የባህል ሳምንቶች እንዲከበሩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል ። የባህል ሳምንቱን በኢትዮጵያ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካ ደረጃም ማክበር የቀጣናውን ህዝቦች አብሮነት ለማጠናከር ስለሚረዳ ፤ በዚህ ወር መጨረሻ በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ በአዲስ አበባ የባህል ሳምንት ለማክበር ቀጠሮ እንደተያዘለት ነው የጠቆሙት።
በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ የሚካሄደው የባህል ሳምንት በዓይነቱ ልዩ የሆነ የምስራቅ አፍሪካ የባህልና ኪነጥበብ ሲምፖዚየም ከመላው አፍሪካ የተውጣጡ የባህል ዘርፍ ያሉ ሚኒስትሮች፣ የታወቁ የአፍሪካ ዩኒቨርስቲዎች፣ ከምስራቅ አፍሪካ የተውጣጡ የባህል ቡድኖች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚሳተፉበትም አቶ ቀጄላ ገልጸዋል።
የበዓሉ አከባበር ሥነ-ሥርዓት ላይ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎች፣ የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች በፌስቲቫሉ ታድመዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን መጋቢት 25 ቀን 2014 ዓ.ም