ዛሬ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበት 11ኛ ዓመት ነው። ቀኑን ለየት የሚያደርገው ደግሞ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበት ዕለት ልክ እንደ ዛሬው ቅዳሜ ነበር። ሌላ ለየት የሚያደርገው ደግሞ በዚህ ዓመት የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን ቀን የምናከብረው ኃይል የማመንጨት ሥራውን በጀመረበት ዓመት መሆኑ ነው።
ስለ ዓባይ በሰፋፊና ጥልቅ ትንታኔዎች፣ በቃለ መጠይቆች፣ በዜናዎች በብዙ ተብሏል። እስኪ በዚህ ዓምድ ደግሞ ከጠንካራ ሀሳቦች (Hard Issue) ወጣ እንበልና ዓባይን ምናባዊ ቃለ መጠይቅ እናድርግለት።
ግድቡ በተገባደደበትና በዚህ ኃይል ማመንጨት በጀመረበት ዓመት ዓባይ ከሰው ጋር ቢያወራ ምን ይል ይሆን? ብለን አሰብን። ምናባዊ ቃለ ምልልስ እናድርግለት። የህዳሴው ግድብ የሚገነባበትን ቦታ ታሳቢ በማድረግ የዚህ ምናባዊ ቃለ ምልልስ አድራጊ ጋዜጣ ጉባ ተብሎ ተሰይሟል። የጉባ ጋዜጣ ጋዜጠኛ ዓባይነህ ከዓባይ ጋር ቆይታ አድርጓል፤ መልካም ንባብ።
ጉባ፡- እስኪ በመጀመሪያ ራስህን አስተዋውቅ?
ዓባይ፡- ዓባይ እባላለሁ።
ጉባ፡- ሰፋ አድርገህ አስተዋውቅ፤ ዓባይ የሚባል እኮ ብዙ ሰው አለ፤ ሰው ብቻ ሳይሆን ዓባይ እየተባለ የተሰየመ ስንትና ስንት ነገር አለ። የትኛው ዓባይ ነህ?
ዓባይ፡- አሁንማ በቃ ተደፋፈርከኝ አይደል? እኔ ዓባይ ወንዙ ነኝ ብዬ ልንገርህ? መቼም አታፍርም ዓባይ ማለት ወንዝ መሆኑን የማያውቅ ይኖራል ትለኝ ይሆናል እኮ።
ጉባ፡- ይሄ ትውልድ የአገር ፍቅር የለውም፣ ታሪኩን የዘነጋ ነው እየተባለ ይታማል፤ ታዲያ ይሄ ትውልድ የተምታታበት ከሆነ ዓባይ ወንዝ መሆኑን የማያውቅ ይኖራል ብዬ ብሰጋ ምን ችግር አለው?
ዓባይ፡- የተምታታብህ ራስህ ነህ ባክህ! ይሄ ትውልድ የአገር ፍቅር የሌለው ሳይሆን ያለው ነው። ለዘመናት በአይነኬነት ስመለክ የኖርኩትን አግዶ ያስቀረኝ ታዲያ ይሄ ትውልድ ነው እንጂ ሌላ ማነው?
ጉባ፡- ስለዚህ የዚህ ትውልድ አድናቂ ነህ ማለት ነው?
ዓባይ፡- አንተ ማድነቅ አለብህ ማለቴ ነው እንጂ፤ እኔማ ምኑን አደንቀዋለሁ። ስንት ሺ ዘመን ተፈርቼና ተከብሬ፣ አገር ምድሩን አቋርጬ እስከ ሜዲትራኒያን ባህር ድረስ እንዳላጓራሁበት ሁሉ አንድ ቦታ አግዶ ሲያስቀረኝ እንዴት ላደንቀው እችላለሁ? በእርግጥ ድፍረቱን አደንቃለሁ!
ጉባ፡- አግዶ እንዳስቀረህ አመንክ ማለት እኮ ያው አደነቅከው ማለት ነው። ለመሆኑ የድሮ ጀግንነትህ ምን ነበር?
ዓባይ፡- ወይ! መደፋፈር፤ እውነት አሁን የድሮ ዝናዬን ስተኸው ነው? እንደተገደብኩ አይተህ ነው እንጂ አንተስ ካጠገቤ ዝር ትል ነበር? አላውቅህም እንዴ አፋፍ ላይ ቆመህ ‹‹ዓባይ ጉደል ብለው አለኝ በታህሳስ፤ የማን ሆድ ይቆያል እስከዚያ ድረስ›› እያልክ ትዘፍን እንደነበር።
ጉባ፡- ኧረ ዓባይ ወደ ዋናው ቃለ ምልልስ ከመግባታችን በፊት ስለውልደትህና አስተዳደግህ ትንሽ እናውራ።
ዓባይ፡- ጄምስ ብሩስን ጠይቀው፤ ከአጠገብህ ተነስቼ የዓለም አገራትን አቆራርጬ ስጓዝ የዓለም ተመራማሪዎች ስለእኔ ብዙ ሲጽፉ የት ነበርክ? ጭራሽ የት ተወለድክ ትለኛለህ እንዴ?
ጉባ፡- ስለሽ ደምሴ(ጋሼ አበራ ሞላ) እንደዘፈነው ከሆነ አባትህ ደጄን እናትህ ጣና ናቸው ማለት ነው?
ዓባይ፡- ሂድና ራሱን ጠይቀው።
ጉባ፡- ቆይ ግን ምንድነው እንዲህ የሚያነጫንጭህ? ዛሬም እንደ ድሮው የምፈራህ መሰለህ እንዴ! ከፈለክ አሁንም ሌላ ቦታ እንዳልገድብህ።
ዓባይ፡- ሆሆሆሆሆ! ወደው አይስቁ አሉ። እሱማ እኮ የጀግኖች ነው። ምንህ እንዳሳቀኝ ታውቃለህ? አንተ ለአንባቢዎችህም ብለህ ይሆናል፤ ግን እኔን የት ተወለድክ? የት አደክ? ብለህ ስጠይቅ አንባቢም ይስቅብሃል። ከዚያ አልፈህ ደግሞ እገድብሃለሁ ትላለህ። እኔን የገደቡ እኮ ስለማንነቴ አንጠርጥረው የሚያውቁ፤ ከየት ተነስቼ የት እንደምሄድ የገባቸው ናቸው። ዝም ብለህ ምንም ሳታውቅ አፍህ እንዳመጣ እገድብሃለሁ እያልክ አታስፈራራ። ደግሞ ከአሁን በኋላ የምፈራ እንዳይመስልህ! ሜዲትራኒያ ማደሪያዬ እንደነበር ሁሉ ጉባም ማደሪያዬ ይሆናል።
ጉባ፡- ግንድ ይዘህ ከመዞር በስተቀር ማደሪያ የለህም አልተባለም ነበር እንዴ?
ዓባይ፡- እሱማ ተረት ሆነ እኮ። አሁን ግንድ ይዘህ የምትዞር ራስህ ነህ።
ጉባ፡- ደግሞ እኔ የምን ግንድ ነው ይዤ የምዞር?
ዓባይ፡- ብትፈልግ የዋርካ፣ ብትፈልግ የዋንዛ(ሃሃሃሃሃ) ያው መቼም መብራት ለማስገባት በየገጠሩ እየዞራችሁ የመብራት እንጨት መትከላችሁ አይቀርም ብዬ ነዋ!
ጉባ፡- እስኪ ለሰዎች ጥቅም መስጠትህን ካነሳኸው አይቀር ከጥንት እስከ ዛሬ ምን ጥቅም ሰጥቻለሁ ብለህ ታስባለህ?
ዓባይ፡- በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። እንግዲህ እስከዛሬ የሰጠሁትን ጥቅም በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን።
ጉባ፡- ደግሞ አንተም እንደ ምሁራን ‹‹በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን›› እያልክ ማብራራት ጀመርክ? እስኪ ምን ምን ናቸው?
ዓባይ፡- ደግሞ አትዘባርቅ! ዝም ብለህ አዳምጠኝ። በሁለት መከፈል ያለበት ነገር ካለ ይከፈላል። ለምሳሌ እኔ በሁለት ይከፈላል ያልኩህ ድሮ የምሰጠውን ጥቅምና አሁን የምሰጠውን ጥቅም ነው።
ጉባ፡- እስኪ ድሮ ምን ነበር? አሁንስ ምንድነው?
ዓባይ፡- ድሮ ድሮ ጥቅም የምሰጠው ለቅኔ፣ ለፉከራና ለቀረርቶ ነበር። ብዙነትን፣ ኃይለኝነትን፣ ተጓዥነትን… ለመግለጽ፣ በሌላ በኩል የአባባሎች ምንጭ ነበርኩ። በየጎራው እየወጣህ ‹‹እንዴት አምሮበታል ጭስ ዓባይ ዘንድሮ›› እያልክ ታቅራራብኝ ነበር። እኔ አትገናኙ ያልኩ ይመስል ‹‹ከዓባይ ማዶ ሆነሽብኝ›› እያለ እየየውን ያንጎራጉርብኛል።
ጉባ፡- ዓባይ እዚህ ላይ ላቋርጥህና እኔ አትገናኙ ያልኩ ይመስል ያልካት ነገር አልተዋጠችልኝም። ለምሳሌ ድልድይ ከመኖሩ በፊት ከአንተ ማዶና ማዶ ያሉ ተፋቃሪዎች እንዴት ይገናኙ ነበር? የበጋ ወቅትን ጠብቀህ ጎደል ስትል ዘመድ አዝማድ ይጠያየቃል። በዚያው ደግሞ ከአንተ ማዶ ፍቅር ይዞት ይመጣል። ግራ ቢገባው እኮ ነው ‹‹አንቺ ወዲያ ማዶ እኔ ወዲህ ማዶ፤ አንገናኝም ወይ ተራራው ተንዶ!›› ብሎ የዘፈነው።
ዓባይ፡- ሃሃሃሃሃ! አንዳንድ ዘፈኖቻችሁ ደግሞ ያስቁኛል። ተራራ ነው እንዴ ያለያየው እኔ ነኝ እንጂ። እስኪ አሁን ማን ይሙት የውሃ መጉደልን ከተራራ መናድ ጋር ምን አገናኘው?
ጉባ፡- ዓባይ ስለቅኔ እናውራ ከተባለ ከባድ ነው። ይህኔ እኮ ተራራ የተባለው ነገር አንተ ልትሆን ትችላለህ። ተራራው ይናድ የተባለው አንተን ጉደል እንደማለት ሊሆን ይችላል። ግጥም ደግሞ ብቻውን እንደማይፈታ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ቆይ ግን ድሮ ለቅኔና ለቀረርቶ ይጠቀሙብኝ ነበር አልክ። አሁን በአንተ ላይ መቀኘትና ማቅራራት አይቻልም እንዴ?
ዓባይ፡- አይ! እንደ ድሮው አይደለም። በዚያ ላይ ደግሞ የአሁኑና የድሮው በጣም የተለያየ ነው። ድሮ አይነኬው፣ ጀግናው….. የሚሉ ነገሮች ናቸው የሚበዙት። አሁን ግን ቅኔውም ፉከራውም እኔን ስለማሸነፍ ነው።
ጉባ፡- ቆይ አንተ ግን አሥር ጊዜ ተሸነፍኩ ተሸነፍኩ የምትል ምን ጎድሎብህ ነው? ሜዲትራኒያም ገባህ፣ ጉባም ታገድክ ለአንተ ምን ልዩነት አለው?
ዓባይ፡- ኧረ እባክህ! እዚያ ስሄድ እኮ የዓለም አገራትን እያቆራረጥኩ ነው። ለም አፈርን እየጠራረኩ እየበላሁ ነው። መታገዴ ሳያንስ አሁን ደግሞ ግድቡ በደለል እንዳይሞላ በማለት አፈርም እንዳላገኝ አደረጋችሁኝ። ታዲያ ለምን ተደፈርኩ አልል ጉባ?
ጉባ፡- ነገርህ ሁሉ ዓባይን በጭልፋ እየሆነብኝ ነው።
ዓባይ፡- እንዴት?
ጉባ፡- ስለአንተ ብዙ ነገር ማውራት ይቻላል። ግን ከምን ጀምሬ በምን እንደምጨርሰው ግራ ገባኝ። እንግዲህ ልንሰነባበት ነውና ዝም ብዬ ዕድል ልስጥህ። እስኪ በመጨረሻ ምን ታስተላልፋለህ?
ዓባይ፡- በመጨረሻ የማስተላልፈው ኤሌክትሪክ ነው።
ጉባ፡- ሃሃሃሃሃ! በእውነት ይህን ቀልድ ልጅ ያሬድ ከቀለደው በላይ ያሳቀኝ ዛሬ ነው። በዚህ ቀልድህ ላይ ምንም ነገር ሳልደርብበት ሰላም ሁን! መልካም ኤሌክትሪክ ማስተላለፍ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2014