
በሰሜናዊቷ አፍሪካ አገር አልጄሪያ የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ሲሆን ለዚህም የአንበሳ ድርሻውን የያዘው በአገሪቱ የተከሰተው የዘይት እጥረት ነው።
በገበያ ውስጥ ያለው ዘይትና እና ወተት ምርቶች በጣም አናሳ በመሆኑ ምክንያት ሸማቾች በመደብሮች ውስጥ በሚገበዩበት ወቅት ነጋዴዎችን መለማመጥ እንዲሁም ማሞካሸት ይጠበቅባቸዋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት ተጥለው የነበሩ መመሪያዎች እንዲሁም በቅርቡ የተከሰተው የዩክሬን ጦርነት ተደማምሮ እጥረቱን ያባባሰው ሲሆን ለሸማቾችም ሕይወትን ፈታኝ አድርጓታል።
“መድኃኒት የመግዛት አይነት ስሜት አለው” ትላለች የ31 ዓመቷ ሳሚሃ ሳመር በንዴትና በምጸት በተቀላቀለው ድምጸት።
ለቤተሰቦቿና ጓደኞቿ ኬክ መሥራት ትወድ የነበረችው ሳሚሃ በዚህም ገቢም ታገኝ ነበር በአሁኑ ወቅት ግን ለኬክ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ማግኘት አልቻለችም።
“ከየትኛውም መደብር ዘይት ለመግዛት የሱቁ ባለቤት ጋር ወዳጅነት ወይም ትውውቅ መኖር አለበት” በማለት ሁኔታውን ታስረዳለች።
የግብይይት ሁኔታውም የሚከናወነው ሚስጢራዊ በሆነ ሁኔታ ነው። ዘይት እንደማንኛውም እቃ መደብሩ መደርደሪያ ፊት ለፊት ላይ አይታይም፤ ሻጮች መደብሮች ውስጥ ደብቀው ነው የሚያስቀምጡት።
እንደ በርካታ አልጄሪያውያን የኮሮና ቫይረስ መመሪያዎች ከፍተኛ ጫና ሲያደርሱና በርካታ ነገሮችን ሲቀይሩ የተመለከተችው ባለፈው ዓመት ነበር።
የሙስሊሞች ረመዳን ፆም ሊጀምር በተቃረበበት በአሁኑ ወቅትና ቅዱስ ወር ተብሎ በሚጠራው በዚህ ወር ለሚሠሩ የተለያዩ ዓይነት ምግቦች ግብዓት የሚሆነውን ዘይት ለመሸመት ነዋሪዎች ፍለጋቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።
ሳሚሃ አንዳንድ ጊዜ ፍራፍሬ እና አትክልቶችን ለመግዛትም ከምትኖርበት ከተማ ቢልዳ ረከስ ወዳለባትና ወደ አቅራቢያዋ ወደምትገኘው ኮሊያ ሄዳ መሸመት ይኖርባታል።
ሌሎች የምግብ ሸቀጦችም እንዲሁ ዋጋቸው ንሯል። ለምሳሌ ድንችን ብንወስድ ከጥቂት ወራት በፊት ከነበረው ከ30 በመቶ በበለጠ አሻቅቧል። ወተት ለመግዛት ነዋሪዎች ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት ወደ መደብሮች በማቅናት ረጅም ወረፋ መጠበቅ ይኖርባቸዋል።
“ወተት ለማግኘት የተሰለፉ ሰዎችን መግፋት አንዳንዴም መጣላት ስለሚያጋጥም አሁን አቁሜያለሁ” በማለት የአስተዳደሩ ጸሐፊ ይናገራሉ። “በጣም የሚያዋርድ ተግባር ነው “ የሚሉት ጸሐፊዋ እነዚህን ሰልፎች መራቅ ግን ዋጋ አስከፍሏቸዋል።
ከሕዝብ ጋር እየተገፋፉና ረጅም ወረፋ መጠበቅንም በመተው ከውጭ አገር ለሚገባ አንድ ኪሎ የዱቄት ወተት 2.90 ዶላር አካባቢ መክፈል ይጠበቅባቸዋል። በመንግሥት ድጎማ የሚደረግለት ወተት ዋጋ 17 ሳንቲም ዶላር ነው።
አልጄሪያ ወተት ብታመርትም ነገር ግን መጠኑ በጣም አናሳ ነው። ለዓመታትም ከፈረንሳይ፣ ከሌሎች የአውሮፓ ሕብረት አገራት እንዲሁም በቅርብ ጊዜ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሚመጣ ወተት ጥገኛ ናት። የሚገባው ወተት በዱቄት መልክ ሲሆን ለሸማቾች ከመድረሱ በፊት ፋብሪካዎች ወደ ፈሳሽነት ይቀይሩታል።
ወተት እጥረት ቢኖርም በርካታ አልጄሪያውያንን እያስጨነቀ ያለው የዘይት ዋጋ መናር ነው።
እንደ ወተት ዘይትም ቢሆን በመንግሥት ድጎማ ቢደረግለትም በቅርቡ ከተከሰተው ቀውስ በፊትም ቢሆን ውድ ነበር። በዚያን ጊዜም የአምስት ሊትር ዘይት ዋጋ 4.20 ዶላር ወይም 216 ብር ነበር።
የአልጄሪያውያን ወርሐዊ ደመወዝ በአማካይ በግሉ ዘርፍ 240 ዶላር እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኞች ደግሞ 410 ዶላር ሲሆን ባለስልጣናቱም በናረው የሸቀጥ ዋጋ ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ጫና ቢፈጠርባቸው ብዙም አያስገርምም።
በአገሪቷ ኢኮኖሚ ሳቢያ ምግብ ማከማቸት እንዲሁም ሙስና በከፍተኛ ሁኔታ ማንሰራራቱን የፓርላማው ኮሚቴ በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።
በፓርላማው የተመረጠው ኮሚቴ አባል የሆኑት ሂሻም ሳፋር ለቢቢሲ እንደተናገሩት የዘይት ነጋዴዎች ከመንግሥት ተጨማሪ ገንዘብን ለመጠየቅ በሚል ድጎማ የተደረገለት ዘይት ላይ ሰው ሰራሽ የሆነ የዋጋ ንረት እየፈጠሩ ይገኛሉ።
ባለፈው ዓመት ወደ 150 ሺህ የሚጠጉ ጥሰቶች ለባለስልጣናቱ ሪፖርት የተደረጉ ሲሆን አብዛኞች ፍርድ ቤት ቀርበዋል እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ የንግድ ፈቃዶች ተነጥቀዋል።
ከዚህም ጋር በተያያዘ በአገሪቷ ድጎማ የተደረገላቸው ሸቀጦች በደቡባዊ ድንበር አቋርጦ በጎረቤት አገራት በሕገወጥ መንገዶች እየተሸጡ ይገኛሉ። ይህም መጠነ ሰፊ እንደሆነ የፓርላማ ኮሚሽኑ መጠነ ሰፊ እንደሆነም አመልክቷል።
ምንም እንኳን ይፋ የሆነ አኃዝ ባይኖርም ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት 12 የሚሆን የጭነት መኪና ዘይት ወደ ማሊና ኒጀር በድብቅ ይወሰዳል።
ሕገወጥ ነጋዴዎቹ በመንግሥት ድጎማ የተደረገለትን ዘይት በመቸብቸብ በአንድ ጭነት መኪና እስከ 17 ሺህ 800 ዶላር ትርፍ እንደሚያገኙም ምንጮቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ፕሬዚዳንት አብደልማጂድ ቴቡኔ ከውጭ የመጡ ምርቶች ወይም ግብዓታቸው ከውጭ የመጣ እንደ ዘይት፣ ስኳር፣ ፓስታ፣ ሰሞሊና እና የስንዴ ምርቶች ወደ ውጭ እንዳይላኩ አግደዋል።
ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ፕሬዚዳንቱ መሰል ድርጊቶች ሆን ብሎ የአገሪቱ ምጣኔን ሆን ብሎ ለማደናቀፍ የተሸረበ ሴራ ስለሆነ ከፍተኛ ቅጣት እንዲጣልባቸው ይፈልጋሉ።
ነገር ግን በአልጄሪያ ለተነሳው ቀውስ ጥልቅ መንስኤዎችን ለማወቅ ወደ ኋላ መለስ ብሎ መመልከት እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ምንጭ ቢቢሲ
አዲስ ዘመን መጋቢት 21 /2014