የፋሽን ኢንዱስትሪ መዘመን አንዱ ማሳያ ነው አዲስነት:: የነበረን ቀድሞ የተለመደን በአዲስ ቅርፅና ዲዛይን ተመራጭና ተፈላጊ አድርጎ አበጅቶ ለገበያ ማቅረብ:: በፋሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ የፈጠራ አቅምን እየተጠቀሙ በፊት የነበሩና በብዛት ማሕበረሰቡ የሚጠቀምባቸው ቁሶች አልያም አልባሳት በአዲስ ዲዛይንና አዲስ በሆነ መንገድ ሰርቶ ለገበያ በማቅረብ ላይ የሚገኝ አንድ ተቋም የዛሬ የፋሽን አምዳችን ትኩረት ሆኗል::
ቀድማ አገርዋን ለማስተዋወቅ ኢትዮጵያን በሌላው ዓለም ለማሳየት ብዙ ጥራለች:: ከልጅነቷ ጀምሮ ለፋሽን ዲዛይን የነበራት ልዩ ፍላጎት እያደገችና አቅም እያደረጀች ስትሄድ ሙያውን አውቃና ለይታው ሰፈሯ ላሉ ሰዎች በአብዛኛው ወጣቶች በራሷ ዲዛይን እየሰራች እንዲለብሱላት ትጋብዝ ነበር::
ይህንን አሳድጋ በሌሎች አገሮችም ኢትዮጵያዊ ባህልን የሚያንፀባርቁ አልባሳት በልዩ ልዩ ፋሽን ሾው መድረኮች ላይ አቅርባለች::
ነገር ግን በስፋት ስትሰራው የነበረው ባህልን የማስተዋወቅና አዳዲስ የፋሽን ዲዛይን ስራዎቿ በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደፊት ሊራመድላት አልቻለም:: ወደ አገር ተመልሳ አንድ ነገር ሞከረችና በፊት የነበረው ፍላጎት ውስጣዊ መሻትና ልታሳካው የምትፈልገው ዓላማ የአገር ባህል አልባሳት በሌላ ገፅታ ሰፍታና አዘጋጅታ በመሸጥ እንደገና እንደ አዲስ ማስተዋወቅና ለገበያ ማቅረብ ጀመረች:: ይሄኛው ጉዞና ጥረቷ ሰመረና ዛሬ ላይ ሰዋሰው ዲዛይን የተሰኘ የፋሽን አልባሳት በአዳዲስ ዲዛይኖች እየሰራ የሚሸጥ ለሌሎችም የሥራ እድል የፈጠረ ድርጅት መስርታ በቀና ጎዳና ላይ ትገኛለች፤ ዲዛይነር ሰዋሰው ኃይሉ::
ኮሮና የፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ጫና በሰዋሰው ዲዛይን ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ አልቀረም ነበርና እቤት ተሁኖ የተለያዩ ስፌትና ዲዛይኖችን ማሰቡ ለወቅቱ የሚያስፈልጉ የአፍ መሸፈኛዎችን እያዘጋጁ ማቅረቡን ተያያዙት:: በሂደትም የሰዋሰው ዲዛይን መስራች የሆነች ሰዋሰው ኃይሉ ከልጇ አብለኔ ዳዊት ጋር በመሆን አዲስ የሆነ ዲዛይን ይዘው ብቅ አሉ::
የኢትጵያን የተለያዩ የሽመና ጨርቆችን እና የሸማ ልብስ በመጠቀም በአዲስ ዲዛይንና ለሰዎች አይነግቡ በሆነ መልኩ አልባሳትን ሰፍተው ማቅረብ ጀመሩ:: በአዲስ መልክ የተጀመረው ዲዛይን በብዙዎች መወደድ ጀመረ:: በዚህም መልካም እድል ተፈጥሮ ሥራው እየሰፋ ሄደ::
በአሁን ሰዓት ከባህላዊ አልባሳት ጨርቆች የተሰሩ ልዩ ልዩ አልባሳት ጃኬት(ኮት)፣ ሹራብ የአንገት ጥምጣምና ሌሎች አልባሳ በጥራት እና በብዛት በማምረት ለገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ:: ቀድሞ ይሰራው የነበረ የግል ሥራ በመተው ከእናቱ ጋር ሰዋሰው ዲዛይን በመቀላቀል ለሰዋሰው ዲዛይን የራሱን በጎ ሚና በመወጣት ላይ የሚገኘው አብለኔ የድርጅቱ ዋንኛ ዓላማ አገራዊ ምርት ማስተዋወቅ፣ ባህልን የተላበሱ አዳዲስ ዲዛይኖችን ወደ ገበያው ማቅረብና ማሕበረሰቡ ምቹና አዳዲስ በሆኑ ዲዛይኖች አምሮ እና ተውቦ ባህሉን ሳይለቅ የሚታይባቸው አልባሳት ማቅረብ መሆኑን ይናገራል:: ሰዋሰው ዲዛይን ዛሬ ላይ ሥራውን አጠናክሮ ደንበኞቹ ጋር መድረስ ችሏል::
በዚህም ከ19 ሰው በላይ የሥራ አድል መፍጠር የቻለ ሲሆን በተለይ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች በሥራ እድሉ ተጠቃሚ ማድረጉ የሚበረታታ ተግባሩ ነው:: ወደፊት ሥራውን በተጠናከረ መልኩ በመስራት ለሴቶችና ለአካል ጉዳተኞች ተጨማሪ የሥራ እድል ለመፍጠር እቅድ እንዳላቸው አብለኔ ያስረዳል::
በሰዋሰው ዲዛይን የሚዘጋጁ ባህል ነክ አልባሳት በሰዎች ዘንድ ተመርጠው የሚለበሱና ምቾት የሚፈጥሩ መሆናቸውን የሚናገረው አብለኔ ለዚህም ከጊዜ ወደ ጊዜ የደንበኞቻቸው ቁጥር መጨመሩን እንደ ማሳያ ያነሳል::
አልባሳቱ ከሌሎች ባህላዊ አልባሳት የሚለዩት በማንኛውም ሁኔታ በየትኛው ጊዜ ሊለበሱ መቻላቸው ሲሆን በሽመና የሚዘጋጁ ኦርጅናል ጨርቆችን ከሌሎች የጋርመንት ጨርቆች ጋር በማድረግ ዘመነኛውን ያስውባሉ::
በባህላዊ መንገድ በሽመና የሚዘጋጁ ኦርጅናል ጨርቆች ፈትል ጋቢ ድንጉዛ የጉጂ ጨርቅ ድንጉዛ የመሳሰሉ እዚሁ እኛው አገር በሰው የሚዘጋጁ ጨርቆች ደግሞ የሰዋሰው ዲዛይን ለሚሰራቸው አዳዲስና ተመራጭ ዲዛይን አልባሳት መስሪያ ግብዓቶቹ ናቸው::
በተቋሙ ውስጥ ውስን የሸማ ሥራ የሚሰሩ ቢኖሩም በአብዛኛው ግን ከከደቡብ ኢትዮጵያ እያስመጡ እንደሚጠቀሙ አብለኔ ይገልፃል::
‹‹የአልባሳት ተመራጭነት ምክንያት በዲዛይን አዲስና ለመልበስ ምቹ መሆን እንዲሁም የጋርመንት ጨርቆች ከባህላዊ አልባሳት ጋር በማድረግ መዘጋጀታቸው ነው›› የሚለው አብለኔ፤ ማሕበረሰቡም ባህሉን መውደዱና በአልባሳቱ እሱነቱን ማንፀባረቅ መውደዱ ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ ያስረዳል:: ሰዋሰው የባህል አምባሳደር በመሆን በሚያዘጋጃቸው አልባሳት ለትውልድ ባህሉን ሳይረሳ ከጊዜው ጋር የሚሄዱ አልባሳት እንዲለብስ እንዲከተል የማድረግ ሥራን መስራቱን ቀጥሏል:: ደንበኞቻቸውን በአብዛኛው የሚያገኙት የሰሩትን ሥራዎች በሚያስተዋውቁበት በተለያዩ ማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲሆን በቴሌግራም፣ ቲዊተር፣ፌስቡክና ዌብ ሳይት የመገናኛ መንገድ በመሆን ትዕዛዛት ተቀብለው ደንበኞች ባሉበት ቦታ ያደርሳሉ::
ሰዋሰው ዲዛይን ሥራዎችን በይበልጥ ሰርቶ ለማቅረብ ውጥን እንዳለው የሚገልጸው አብለኔ ነገር ግን በአቅርቦት በኩል ያው የዋጋ መለዋወጥና የሚፈለጉ መስሪያ ግብዓቶች ገበያ ላይ በብዛት አለመኖር እንደ ችግር የሚያነሳው ጉዳይ ነው:: በተለይ በአገር ውስጥ የሚዘጋጁ የባህላዊ አልባሳት ጨርቆች የዋጋ መለዋወጥና የጥራት ችግር በገበያው ላይ ተፅዕኖ አሳዳሪ ምክንያቶች ናቸው::
የፋሽን ገበያው ሰፊና ገና ብዙ መስራት የሚቻልበት እንደሆነ የሚናገረው ወጣት አብለኔ ለዘር ትኩረት ከተሰጠውና የግብዓት ችግሩ መቅርፍ ከተቻለ ሰፊ የሥራ እድል ከመፈጠሩም ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውም ሃያል ነው::
በተለይ ብዙ ሰዎችን ማሳተፍ የሚያስችለውና የሥራ እድል ማስገኘት የሚችለው የሽመና ሙያ ትኩረት ቢሰጠው አገራዊ ምርትን ከማሳደግ ባለፈ ባህል በማስተዋወቅ ለሌሎችም ምርቱን በመሸጥ ከፍ ያለ እድገት ማስመዝገብ ይቻላል::
በሌላው ዓለም ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚፈስበት የፋሽን ዘርፍ የሚያስገኘው ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አገራችንም ማግኘት እንድትችል ሙያተኞች ማበረታታት ምቹ ሁኔታ መፍጠርና ገና ታዳጊ የሆነውን የፋሽን ኢንዱስትሪ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ወሳኝ መሆኑንም ያስረዳል::
ሰዋሰው ዲዛይን ባህላዊ አልባሳት በሌላ አዲስ መልክ በማቅረብ አገራዊ ባህልን ከማስተዋወቅ ባለፈ በራስ መንገድና አዲስ ዲዛይን ለመልበስ ምቹ፤ ለመዘነጥ ተመራጭ አድርጎ አቅቧልና ለዘርፉ እድገት ትልቅ አቅም ፈጣሪ በመሆኑ ተግባራችሁ ይቀጥል እንላለን::
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 /2014