ዓለም አቀፉ የፋሽን ማሰልጠኛ በአዲስ አበባ

በኢትዮጵያን የፋሽን ዘርፍ ውስጥ የራሱን ዐሻራ ያሳርፋል የተባለለት ዓለም አቀፍ የፋሽንና ሞዴሊንግ ማሰልጠኛ ተቋም ሰሞኑን በአዲስ አበባ በይፋ ሥራ ጀምሯል።

ዳማሪዮስ የተሰኘው ይህ ማሰልጠኛ ተቋም በዓለም አቀፍ ደረጃ በፋሽን፣ በሥነ ውበት (ሜካፕ)፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ሴኩሪቲ እና በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ባለሙያዎችን እንደሚያሰለጥን ተጠቁሟል። በዚህም ባለሙያዎችን ከማፍራት ባሻገር ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ አስተምሮ የሥራ ዕድልን በማመቻቸት የበኩሉን ለመወጣት ዝግጅቱን አጠናቆ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ ተገልጿል።

ማሰልጠኛ ተቋሙ ተግባር ተኮር የሆኑ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጥ የተቋሙ መሥራች የክብር ዶክተር ሞዴልና ዲዛይነር ሰናይት ማሪዮ (ዶ/ር) የገለፀች ሲሆን፣ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ የሥራ ዕድልን ለሰልጣኞቹ እንደሚያመቻች አስረድታለች። ከመጪው መስከረም ጀምሮ ከደረጃ ሁለት ጀምሮ ዓለም አቀፍ በሆኑ ባለሙያዎች ሥልጠናዎች እንደሚሰጥ የተገለጸ ሲሆን፣ ሰልጣኞች ሥልጠናውን ካጠናቀቁ በኋላ በሙያው የራሳቸውን ሥራ እንዲፈጥሩ በተቋሙ አቅም መሠረት ከንብ ባንክ ጋር በመተባበር የፋይናንስ አገልግሎቶች ይመቻቻል ተብሏል። ሥልጠናዎችን ከሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ ከጣሊያን፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ናይጄሪያ፣ ጋና እና አሜሪካ የመጡ መምህራኖች እንደሚሰጡም ተገልጿል። በሜካፕ ትምህርት ክፍል ከማሪዮ ሜካፕ ድርጅት ጋር አብሮ ለመሥራት ውል መፈፀማቸው እና ከቆዳ ስፔሻሊስት ዶክተሮች ጋር በጥምረት አብሮ ለመሥራት መስማማታቸውም ነው የተገለጸው።

ማሰልጠኛ ተቋሙ ለሃያ ቋሚ ሠራተኞች የሥራ እድል የተፈጠረ ሲሆን፣ ከሮም ቢዝነስ ስኩል ጋር ለተማሪዎች የውጭ ሀገር የትምህርት እድል ለመስጠት ስምምነት አድርጓል። አቅም ለሌላቸው ሰልጣኞች ከዳሽን ባንክ ብድር እንዲያገኙ ስምምነት መፈፀሙም ተነግሯል። ዳማሪዮስ ፋሽን እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ቦሌ ብራስ የሚገኝ ሲሆን፣ በ1200 ካሬ ሜትር ላይ አርፏል። በቀጣይ አምስት ዓመታት ማሰልጠኛ ተቋሙን ወደ ዩኒቨርሲቲ ለማደግ እንደሚሠራም ተጠቁሟል።

ማሰልጠኛ ተቋሙ በዓለም አቀፍ ሞዴል እና ዲዛይነር ሰናይት ማሪዮ የተቋቋመ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ ግዙፉን የፋሽን እና ቴክኖሎጂ ተቋም ለመክፈት የማደራጀት ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን መሥራቿ ተናግራለች። ዓለም አቀፍ ሞዴል እና ዲዛይነር ሰናይት ማሪዮ ነዋሪነቷን ጣሊያን ሀገር ያደረገች ሲሆን፣ ለሠልጣኞች በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ የሥራ ዕድልን የማመቻቸት ሃሳብ አላት።

ከስድስት ዓመት በፊት የማሰልጠኛ ተቋሙ መሥራች የሆነችው ዓለም አቀፍ ሞዴል እና ዲዛይነር ሰናይት ማሪዮ የዓለም አቀፉ “Stay Up Aviation Institutes of Technology” የኢትዮጵያ ባሕል በዓለም እንዲታወቅ እያበረከተች ለሚገኘው አስተዋጽኦ የክብር ዶክትሬት ማበርከቱ ይታወቃል።

በተጨማሪም ሞዴል እና ዲዛይነር ሰናይት ማሪዮ በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፍ ፋሽን ኢንዱስትሪ ደረጃ ባሕልን በዘመናዊ ፋሽን እንዱስትሪ እንዲታወቅ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን ለመሥራት በመቻሏ በተደጋጋሚ የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ ሽልማቶች እንዲሁም እውቅና ያገኘች ጠንካራ ሴት መሆኗ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ የዘመናዊ ፋሽን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲተዋወቅ የተለያዩ ጥረቶችን የምታደርገው የዋን ፒስ መሥራቿ ሞዴልና ዲዛይነር ሰናይት ማሪዎ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትልም በትጋትና ጥረት የፋሽን ኢንዱስትሪው አንድ ርምጃ ወደፊት እንዲሄድ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተች እንደምትገኝ ለዘርፉ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ይናገራሉ። ዊን ፒስ የተሰኘውን ድርጅት በማቋቋም የኢትዮጵያን የባሕል አልባሳት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የማድረግ ራዕይ ሰንቃ በፋሽን ገበያ ላይ በመንቀሳቀስ ትታወቃለች። ሞዴልና ዲዛይነር ሰናይት እንዴት ወደዚህ ሙያ እንደገባች ስትናገርም “በአንድ ወቅት ጣሊያን ሀገር ነበርኩኝ፣ በዚያ ሰዓት ሙያውና እውቀቱ እንዳለኝ ባስብም በትንሹ ከመሞካከር ውጭ እዚህ ደረጃ ላይ ግን እደርሳለሁ ብዬ አንድም ቀን አስቤ አላውቅም ነበር። ታዲያ ሁልጊዜ በጣሊያን ጎዳናዎችና በሄድኩባቸው ቦታዎች ሁሉ አለባበሴን፣ ቁመቴን፣ እንዲሁም የሀበሻ መልኬን የተመለከቱ ሞዴል ነሽ?… ግን ለምን ሞዴል አትሆኚም?… የሚሉኝ ሰዎች በዙ። እኔም ያለኝን ነገር ትልቅ ደረጃ ላይ ማድረስ እንደምችል አመንኩ።” በማለት ትገልጻለች።

ገና ወደ ሥራው ሳትገባ በሰዎች ዘንድ ተቀባይነትና የሞዴልነትን ማዕረግ ያገኘችው ሰናይት፣ ጊዜዋን ሳታባክን ወዲያው ወደ ሞዴሊንግ ሙያ ገባች። ለተወሰኑ ዓመታትም ስኬታማ ሊባል በሚችል መልኩ በዚያው ሙያ ቆይታ ከዚያም ወደ ዘመናዊ የፋሽን ኢንዱስትሪ በዲዛይነርነት ተቀላቀለች። አሁን ደግሞ እንደ እሷ እውቅ የፋሽን ባለሙያዎችን በማፍራት ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ሙያውንም ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲያሻግሩ የማሰልጠኛ ተቋሙን እውን ማድረግ ችላለች።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You