
አዲስ አበባ:- የሩሲያ ቀዳሚ ዓላማ “ዶንባስን ነጻ ማውጣት” ነው ሲሉ የጦር ባለሥልጣኖቿ ገለጹ።
“ኮሎኔል ጀኔራል ሰርጌ ሩድስኮይ አሁን የዩክሬን ወታደራዊ ኃይል ለሩሲያ ስጋት ሊሆን በሚችልበት ደረጃ ላይ ባለመሆኑ ሙሉ ትኩረታችን ዶንባስን ነጻ ለማውጣት አድርገናል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ጉዳዩን ሲከታተሉ የቆዩ ተንታኞች እንደሚሉት “የሁለቱ ሀገራት ጦርነት መጨረሻው ወዴት እንደሚያመራ ለማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም ሩሲያ ዶንባስን ነጻ ለማውጣት በሚል ያቀረባቸው የአሁኑ እቅድ ግን የቀደመ ሽንፈቷን ለመሸፈንና ኃይሏን በድጋሚ ለማደራጀት ነው”።
የአሜሪካ እና የሌሎች ሀገራት የጦር መሳሪያዎች እና ወታደራዊ ቁሳቁስ ወደ ዩክሬን እየገቡ መሆናቸውን ተከትሎ የሩሲያ ወታደራዊ ኃይል ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንደገባ ተነግሯል።
በአንዳንድ አካባቢዎች የዩክሬን ወታደራዊ ኃይል ከመከላከል ወደ ማጥቃት መሸጋገሩን የሚያሳይ ማስረጃ እንዳለም የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጠቁመዋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይም የዩክሬን ወታደራዊ ኃይል በጥቁር ባህር ዳርቻ አካባቢ ትልቅ የሩሲያ መርከብ መምታታቸው ተነግሯል።
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ለመደራደርና በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ ፍላጎት እንዳላቸው ቢገልጹም፣ ዩክሬን ለሠላም ብላ ግን የምትሰጠው አንዳች መሬት እንደሌለ ማስገንዘባቸውን አልጀዚራ ዘግቧል።
“የዩክሬንን ሉዓላዊነት ከህዝባችን ጋር በመሆን አናስደፍርም” ሲሉም ነው ምሽት ላይ ለህዝባቸው ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ያስታወቁት።
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2014 ዓ.ም