
የሶሪያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት አህመድ አል-ሻራ እስራኤል በሶሪያ ላይ የፈጸመችውን ጥቃት አውግዘዋል፤ እስራኤል አዲሷ ሶሪያ እንዳትረጋጋ እያደረገች እንደሆነና ጣልቃ ገብነቷን እንድታቆምም አሳስበዋል።
ሰሞኑን ከደማስቆ ደቡባዊ አቅጣጫ በምትገኘው ሱዌይዳ ከተማ ውስጥ በድሩዝ እና ቤዱዊን ጎሳዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሶሪያ መንግሥት ኃይሎች በድሩዝ ማህበረሰብ አባላት ላይ ጥቃት ፈጽመዋል ያለችው እስራኤል፤ በሶሪያ ላይ ጥቃቶችን ፈጽማለች። ከጥቃቶቹ መካከል አንዱ በደማስቆ ከፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥቱ አቅራቢያ በሚገኙ ስፍራዎችና በሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር ሕንጻ ላይ የተፈጸመው ነው። በእዚህ ጥቃት ሦስት ሰዎች መገደላቸውንና ከ35 በላይ የሚሆኑ ደግሞ መቁሰላቸውን የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ ‹‹የሀገሪቱ ኃይሎች ድሩዝ ወንድሞቻችንን ለማዳን እና የሥርዓቱን ወንበዴዎች ለማስወገድ እየሠሩ ነው›› ያሉ ሲሆን፤ የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ‹‹እስራኤል የክህደት ጥቃት ፈጽማለች›› ሲል ከሷል።
ከእዚህኛው ጥቃት አንድ ቀን ቀደም ብሎ ደግሞ እስራኤል ወደ ሱዌይዳ ከተማ እየገቡ የነበሩ የሶሪያ መንግሥት ወታደሮችን በቦምብ ደብድባለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ፤ በሱዌይዳ አካባቢ በሚገኙ የሶሪያ ኃይሎችና የጦር መሣሪያዎች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ትዕዛዝ የሰጡት ‹‹የሶሪያ መንግሥት በድሩዞች ላይ ሊጠቀምባቸው ስላሰቡ ነው›› ብለዋል።
ሰሞኑን በድሩዝ ሚሊሻዎች እና በቤዱዊን ጎሳ ታጣቂዎች መካከል በተቀሰቀሰው ውጊያ ከ360 በላይ ሰዎች መገደላቸውን መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው ‹‹የሶሪያ የሰብዓዊ መብቶች ታዛቢ›› (Syrian Observatory For Human Rights) የተሰኘው ቡድን ባወጣው ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
ፕሬዚዳንት አህመድ አል-ሻራ የሀገሪቱ መንግሥት የድሩዝ ማህበረሰቦችን ከጥቃት እንደሚጠብቅና መብታቸውንም እንደሚያስከብር ተናግረዋል። ‹‹በድሩዝ ማህበረሰቦቻችን ላይ ጥቃትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙትን ሁሉ ተጠያቂ እናደርጋለን። የድሩዝ ማህበረሰቦች በሶሪያ ጥበቃና ኃላፊነት ስር ናቸው። ድሩዞች የሶሪያ ሀገረ መንግሥት አካል ናቸው። መብቶቻቸውንና ነጻነታቸውን መጠበቅ ቀዳሚ አጀንዳችን ነው። በመካከላችን ክፍፍል ለመፍጠር የሚሞክሩትን የውጭና የውስጥ ኃይሎች ሁሉ አንቀበልም›› ብለዋል።
በሶሪያ መንግሥትና በድሩዝ ማህበረሰብ መካከል በተደረገ ስምምነት፤ የመንግሥት ኃይሎች ከሱዌይዳ እንዲወጡ ተደርገዋል። የድሩዝ ማህበረሰብ መሪ ሸህ ሱፍ ጃርቡ የተኩስ አቁም ስምምነት መደረሱን ገልጸው፤ የመንግሥት ወታደሮች ከሱዌይዳ መውጣታቸውን ተናግረዋል።
ከእዚህ በተቃራኒው ሌላኛው ድሩዝ መሪ ሸህ ሂክማት አል-ሃጃሪ የተኩስ አቁሙን ውድቅ አድርገዋል፤ሱዌይዳ ሙሉ በሙሉ ነጻ እስከምትሆን ድረስ መዋጋታቸውን እንደሚቀጥሉም ዝተዋል። የድሩዝ ተዋጊዎች የአል-ሃጃሪን ጥሪ ተቀብለው ውጊያ እንደሚቀጥሉ የታወቀ ነገር የለም።
በሌላ በኩል እስራኤል በሶሪያ የምትፈጽማቸውን ጥቃቶች ለማቆም መስማማቷን አሜሪካ ገልጻለች። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፤ በደቡብ ሱዌዳ ግዛት በተከሰተው ግጭት እጅጉን መጨነቃቸውን የገለጹ ቢሆንም፤ ሁኔታው በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ያበቃል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ሩቢዮ፤ ‹‹ይህንን አሳሳቢ እና አስፈሪ ሁኔታ ዛሬውኑ ለማቆም በሚያስችሉ የተለያዩ ርምጃዎች ላይ ተስማምተናል›› ሲሉ በ‹ኤክስ› ገጻቸው ጽፈዋል።
‹‹የስድስቱ ቀናት ጦርነት›› በመባል ከሚታወቀው ከሁለተኛው የአረብ-እስራኤል ጦርነት (እ.አ.አ 1967) በኋላ እስራኤል ከጎላን ተራሮች ተጨማሪ ስፍራዎችን መቆጣጠሯን ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እስከ ዛሬም ድረስ እንደሻከረ ዘልቋል። ለሩብ ክፍለ ዘመን ያህል በሥልጣን ላይ የቆየው የበሺር አል-አሳድ መንግሥት ከተወገደ ወዲህ ደግሞ እስራኤል በሶሪያ ላይ የምትፈጽማቸውን ጥቃቶች አጠናክራ ቀጥላለች።
በጥቃቶቹም አብዛኛዎቹን የሶሪያን ጦር መሣሪያዎች ከጥቅም ውጪ አድርጋቸዋለች። የሶሪያ የሰብዓዊ መብቶች ታዛቢ ተቋም ይፋ ባደረገው መረጃ፣ እስራኤል የበሺር አል-አሳድ መንግሥት ከተወገደበት ጊዜ ጀምሮ እስካለፈው ወር ድረስ፣ በአምስት ወራት ውስጥ፣ በሶሪያ ላይ 61 ጥቃቶችን የፈጸመች ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል 51 የሚሆኑት የአየር ጥቃቶች እንደሆኑ ታውቋል።
እስራኤል ለምትፈጽማቸው ጥቃቶች ከምትሰጣቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ፣ ሶሪያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የነበረው የጦር መሣሪያ ለደህንነቷ ስጋት ይሆናሉ ባለቻቸው ታጣቂዎች እጅ እንዳይገባ የሚል ነው። ሌላው ምክንያቷ ደግሞ የሶሪያ መንግሥት ኃይሎችና ተባባሪዎቻቸው በደቡባዊ ምዕራብ ሶሪያ በሚኖሩት የድሩዝ ማህበረሰብ አባላት ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት ለመበቀልና ለማስቆም የሚል ነው።
የድሩዝ ማህበረሰብ አባላት የሺአ እስልምና ተከታዮች ሲሆኑ፤ በሶሪያ፣ በእስራኤልና በሊባኖስ ይኖራሉ። እስራኤል የማህበረሰቡን አባላት እንደአጋሯ የምትቆጥራቸው ሲሆን፤ ብዙ ድሩዞች የእስራኤል ጦር አባላት ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ድሩዞች ከመንግሥት ኃይሎች ጋር በተጋጩባቸው አጋጣሚዎች እስራኤል በሶሪያ ጥቃቶችን ፈጽማለች።
ለአብነት ያህልም ባለፈው ሚያዝያ ወር በሶሪያ ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ ከባድ የአየር ጥቃት መፈጸሟ ይታወሳል። ድሩዞች በብዛት የሚኖሩበት የሶሪያ ክፍል ሶሪያ ከእስራኤል ጋር የምትዋሰንበት አካባቢ ነው። በሌላ በኩል እስራኤል የበሺር አል-አሳድን መንግሥት የገለበጡትን ኃይሎች ያሰባሰበውን የሶሪያን የሽግግር መንግሥት በበጎ አትመለከተውም። በአህመድ አል-ሻራ የሚመራውን የሶሪያን የሽግግር መንግሥት ‹‹ከኢድሊብ ተነስቶ ደማስቆን በኃይል የተቆጣጠረው የሽብር ቡድን›› ብላ ሰይማዋለች።
እስራኤል አንድ ጊዜ ሶሪያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የተከማቸው የጦር መሣሪያ ለደህንነቴ ስጋት በሆኑ ታጣቂዎች እጅ እንዳይገባ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሶሪያ መንግሥት አጋሮቼ የሆኑትን የድሩዝ ማህበረሰብ አባላትን ከጥቃት ሊታደግ አልቻለም በሚሉ ሰበቦች ሶሪያ ውስጥ በተከታታይ የምትፈጽማቸው ጥቃቶች፣ ዓይነተ ብዙ ፍላጎት ባላቸው የውስጥና የውጭ ኃይሎች ሽኩቻ ምክንያት አስተማማኝ መሆን ለተሳነው የሶሪያ ሰላምና ጸጥታዋ ሌላ ስጋት እንዳይሆን የብዙዎች ስጋት እንደሆነ ተገልጿል።
በአንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 11 ቀን 2017 ዓ.ም