ከአንድ አፍሪካዊ ቢሊየነር የገንዘብ ድጋፍ ስለማግኘታቸው ዋሽተዋል የተባሉ የአሜሪካ ምክር ቤት አባል ከእንደራሴነታቸው ሊባረሩ እንደሚችሉ ተነገረ።
ጄፍ ፎርተንቤሪ የተባሉት የኔብራስከካ ግዛት የሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካይ፣ ከስኬታማው ናይጄሪያዊ የንግድ ሰው ጊልበርት ቻጉሪ ሕገወጥ የገንዘብ ድጋፍ ስለመቀበላቸው ለአገር ውስጥ የምርመራ ተቋም ኤፍቢአይ መዋሸታቸውን የፌደራል ዳኞች ደርሰውበታል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በሦስት ጥፋቶች እስከ 15 ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት ሊፈረድባቸው ይችላል። ይህ ጉዳይም የውጭ ተጽእኖ ፈጣሪዎች በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ሊያሳድሩ የሚችሉትን ጫና በተመለከተ ከዚህ በፊት የነበረውን ክርክር መልሶ ቀስቅሶታል።
ምንም እንኳን የውጭ ዜጎች ለፖለቲካ ጉዳዮች የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ባይፈቀድላቸውም የ75 ዓመቱ ናይጄሪያዊ ቢሊየነር በርካታ የገንዘብ ስጦታዎችን ማበርከታቸው ይነገራል። በዚህም ከአራት ዓመት በፊት ጊልበርት ቻጉሪ የ1.8 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት በአሜሪካ መንግሥት የተጣለባቸው ሲሆን፣ የገንዘብ ስጦታውን የተቀበሉ አንዳንድ ሰዎች ላይም ምርመራ ተደርጎባቸዋል።
ግለሰቡ እንደ አውሮፓውያኑ በ2016 አሁን ጥፋተኛ ሆነው ለተገኙት የምክር ቤት አባል ጄፍ ፎርተንቤሪ በአንድ ዝግጅት ላይ በሌሎች ለጋሾች በኩል በሕገወጥ መንገድ የ30,000 ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ሰጥተዋል ተብሏል።
መቀመጫቸውን ፈረንሳይ ፓሪስ ያደረጉት የኢንደስትሪዎች ባለቤት የሆኑት ናይጄሪያዊው ባለሀብት ከፍ ያለ ዝና አላቸው። በአንድ ወቅት ከእስላማዊው ታጣቂ ቡድን ሔዝቦላህ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው አሜሪካ እንዳይገቡ ቪዛ ተከልክለው ነበር።
ባለሀብቱ በ1990ዎቹ የናይጄሪያ ወታደራዊ መሪ የነበሩትና በኋላም በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ከአገሪቱ ካዝና ዘርፈዋል የሚባሉት የጄነራል ሳኒ አባቻ ዋነኛ አማካሪ ነበሩ። ጊልበርት ቻጉሪ ለምን እንደራሴ ጄፍ ፎርተንቤሪን ኢላማ እንዳደረጉ የታወቀ ነገር ባይኖርም የምርመራ ሰነዱ ባለሀብቱ “ብዙም ትኩረት ከማያገኙ ግዛቶች ለሚመጡ ፖለቲከኞች የገንዘብ ድጋፍ እንዲሰጡ” መመከራቸውን ያመለከተ ሲሆን ምክንያቱም ድጋፉ “ትኩረት ያገኛል” የሚል ነው።
እንደራሴው 30,000 ዶላር የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያገኙ የሚገልጽ የተቀረጸ የስልክ ውይይት የተገኘ ቢሆንም፣ ለኤፍቢአይ መርማሪዎች ግን ስለገንዘቡ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ክደዋል። ዐቃቤ ሕግ ክሱን ባስረዳበት ጊዜ የምክር ቤት አባሉ “ሥራቸውን፣ ዝናቸውንና የቅርብ አጋሮቻቸውን ለመከላከል ሲሉ በተደጋጋሚ” ስለገንዘብ ስጦታው ደብቀዋል ብሏል።
ሐሙስ እለት ሎስ አንጀለስ ውስጥ ለሁለት ሰዓታት ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኞች፣ ጄፍ ፎርተንቤሪን ሐሰተኛ ቃል በመስጠትና እውነትን ከፌደራል መርማሪዎች በመደበቅ ጥፋተኛ ብለዋቸዋል።
የምክር ቤት አባሉ ላይ የቅጣት ውሳኔ የሚሰጠው ከወራት በኋላ ሰኔ ላይ ሲሆን፣ እስከዚያው ድረስ ግን እንደራሴው በውሳኔው ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል። ይህንን ተከትሎ በአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራቲክና የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት እንደራሴው በፈቃዳቸው ሥራቸውን እንዲለቁ ጥሪ አቅርበዋል።
ነገር ግን ጄፍ ፎርተንቤሪን በፈቃዳቸው ከምክር ቤቱ አባልነታቸው የማይለቁ ከሆነ ከእሳቸው በፊት ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ የምክር ቤቱ አባላት እንዳጋጠማቸው ከኮንግረሱ ሊባረሩ ይችላሉ ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2014