የሸዋ ንጉሥ የነበሩት የንጉሥ ሣህለሥላሴ የልጅ ልጅ ናቸው። የንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የአክስት ልጅ ናቸው። እኚህ ሰው የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አባት ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል።
ራስ መኮንን ወልደሚካኤል በዚህ ሳምንት ይታወሳሉ። ያረፉት ከ116 ዓመታት በፊት መጋቢት 13 ቀን 1898 ዓ.ም ነው። ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል የተወለዱት ግንቦት 1 ቀን 1844 ዓ.ም በሸዋ ግዛተ አፄ፣ ጎላ ወረዳ፣ ደረፎ ማርያም በሚባል ሥፍራ ነው።
ገና በወጣትነታቸው ወደ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ሄደው ከአጎታቸው ልጅ ከንጉሥ ምኒልክ (በኋላ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ) ጋር ተዋውቀው ቤተሰባዊና ዝምድናቸውን አጸኑ።
በፀባያቸው ታጋሽና አስተዋይ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ልዑል ራስ መኮንን ከንጉሥ ምኒልክ ጋር ጠንካራ ወዳጆች በመሆን እንደ አባትና ልጅ ይተያዩ ጀመር። የሐረርጌን ግዛት በሚገባ በማስተዳደር ለንጉሥ ምኒልክ አገር የማቅናት ተግባር ብርቱ አጋዥ ሆኑ። ከቤተ መንግሥት ባለሟልነት ተነስተው በዘመኑ ከንጉሥ በመቀጠል ከፍተኛ ለሆነው የ‹‹ራስ›› ማዕረግም በቁ።
ልዑል ራስ መኮንን የአፄ ምኒልክ ተወካይ በመሆን ሁለት ጊዜ ወደ አውሮፓ አገራት ተጉዘዋል። ወደ ኢጣሊያ በሄዱ ጊዜም የኢጣሊያ ጋዜጦች የውጫሌ ውልን ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ መንግሥት ጥገኝነት ስር እንዳለች አድርገው የሚጽፉትን ጽሑፍ በመመልከታቸው ራስ መኮንን ተቃውሟቸውን ለኢጣሊያ መንግሥት ከነገሩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የውሉን መበላሸት ለአፄ ምኒልክም አሳውቀዋል።
የውጫሌ ውል ያስከተለው የትርጉም ለውጥ መፍትሄው ጦርነት ሲሆንም ልዑል ራስ መኮንን ሰራዊታቸውን ይዘው ከአምባላጌ እስከ እስከ ዓድዋ በተደረጉት ውጊያዎች ላይ በመሳተፍ ታሪክ የማይዘነጋው ታላቅ ጀግንነታቸውን አስመስክረዋል። ልዑል ራስ መኮንን ከቤተ መንግሥት ባለሟልነት ጀምረው በወታደርነት፣ በጦር መሪነት፣ በግዛት አስተዳዳሪነትና በዲፕሎማትነት በፈጸሟቸው አኩሪ ተግባራት ምክንያት ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የዙፋናቸው ወራሽ እንደሚያደርጓቸውም ይወራ ነበር።
ነገር ግን ምኒልክ ያሰቡት ሳይሆን ቀረና ልዑል ራስ መኮንን መጋቢት 13 ቀን 1898 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ሞታቸው በንጉሰ ነገሥቱ ቤተ መንግሥት (አዲስ አበባ) በተሰማ ጊዜም ከፍተኛ ሀዘን ሆነ። ንጉሥ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክም አምርረው አለቀሱ። በወቅቱም ይህንን የተመለከቱ ሰዎች እንዲህ ብለው ገጠሙ …
”ዋ አፄ ምኒልክ እግዚአብሔር ያጥናዎ፣
በየበሩ ቋሚ ከላካይ ሞተብዎ።
ሲታሰር አየነው ብረቱ ሲመታ፣
ምን ዋስ አገኘና ሐረርጌ ተፈታ።
ጃንሆይ ምኒልክ ፀጉራቸው ሳሳና በራ ገለጣቸው፣
እንግዲህ ንጉሡ ምን ራስ አላቸው።››
ከአልቃሾቹ መካከል አንደኛው ደግሞ የልዑል ራስ መኮንንን ደግነት ለማስታወስ እንዲህ ብሎ ሙሾ አወረደ …
«ስልከኛው ሲያረዳ ነገር ተሳሳተው፣
መኮንን አይደለም ድሀ ነው የሞተው።»
ተብሎላቸዋል።
ዋለልኝ አየለ
በአጼ ቴዎድሮስ የተፈሩት ራስ ዳርጌ
የንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ አጎት የሆኑትና በጀግንነታቸው ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስን ጭምር ያስጨነቁትና ያስደነቁት ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ ያረፉት ከ122 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 15 ቀን 1892 ዓ.ም ነበር።
ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ የሸዋው ንጉሥ የንጉሥ ሳህለሥላሴ ወሰን ሰገድ ልጅ ናቸው። ራስ ዳርጌ የደጃዝማች አስፋው፣ የደጃዝማች ደስታ፣ የፊታውራሪ ሸዋረገድ፣ የወይዘሮ ትሰሜ፣ የወይዘሮ አስካለ፣ የወይዘሮ ፀሐየወርቅ እና የልጅ ጉግሳ አባት ናቸው። ወይዘሮ ትሰሜ ዳርጌ የልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ እናት ናቸው።
ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ የንጉሥ ኃይለመለኮት ሳህለሥላሴ (የንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ አባት ማለት ነው) ወንድም ናቸው። በ1822 ዓ.ም ሸዋ ውስጥ የተወለዱት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ፣ የልጅነት ጊዜያቸውን በአንኮበርና በአንጎለላ አሳልፈው ወደ ጎንደር ተጉዘው በነበሩበት ወቅት በሰላይነት ተጠርጥረው ታስረው ነበር።
ይሁን እንጂ ራስ ዳርጌ ንፁህነታቸው ታውቆ ነፃ ከወጡ በኋላ በመልካም ጠባያቸውና በጦር ሜዳ ጀግንነታቸው በንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ዘንድ ተወዳጅነትን አተረፉ። በዚህም ምክንያት ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ራስ ዳርጌን ‹‹ዳሩ››፣ ‹‹ዳርዬ›› እያሉ ይጠሯቸው ነበር።
የርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ ጀግንነት ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስን ጭምር ያስጨነቀ ነበር። በንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ጊዜ ሸዋን ይገዙ የነበሩት መርዕድ አዝማች ኃይሌ ንጉሰ ነገሥቱን በመክዳት ተጠርጥረው ታስረው ነበር።
ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስም አቤቶ ዳርጌን የሸዋ ገዢ አድርገው እንደሾሙ ተናገሩ፤ ነገር ግን ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የራስ ዳርጌን የጦር ሰፈር ሲመለከቱት በጣም የደመቀና የተደራጀ ስለነበር በጣም ተጨነቁ። ንጉሰ ነገሥቱም አቤቶ ዳርጌን አስጠርተው ‹‹ዳሩዬ ፈራሁህ! በጥንድ ጦር የሚስተውን ኃይሌን ሽሬ በነጠላ ጦር ደርበህ ሁለት ሰው የምትገለውን አንተን በሸዋ ላይ አልሾምም›› ብለው በግልጽ ነገሯቸው። ራስ ዳርጌም የመከፋትና የቅሬታ ምልክት ሳያሳዩና ሳይከፉ ‹‹እሺ›› ብለው ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስን በትህትና እጅ ነሱ።
ልጅ ምኒልክ (በኋላ ንጉሥ ምኒልክ፣ ከዚያም ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ) ከመቅደላ አምልጠው ሸዋ በገቡና በአባታቸው ዙፋን በተቀመጡ ጊዜም፣ ራስ ዳርጌ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ወደ ሸዋ ተመልሰው ከምኒልክ ጋር ተገናኙ። ምኒልክም ሸዋ ገብተው በአባቶቻቸው አልጋ ተተክተው የሸዋ ንጉሥ ሆነው ነበርና ራስ ዳርጌ እንደመጡ ‹‹እርስዎ ቀጥታ የንጉሥ ሳህለሥላሴ ልጅ ስለሆኑ ንጉሥነቴን ልተውልዎ›› ብለው ጠየቋቸው።
ራስ ዳርጌም ‹‹አይሆንም! አባታችን ሳህለሥላሴ አልጋቸውን አውርሰው የሞቱት በቀጥታ ለአንተ አባት ለንጉሥ ኃይለመለኮት ነው፤ አሁንም የነጋሲነት መስመሩ በዚያው ባንተ በኩል ነው መቀጠል ያለበት››
ብለው ንግሥናውን እንደማይፈልጉ ተናገሩ። ከዚያ በኋላም ራስ ዳርጌና ንጉሰ ነገሥት ምኒልክ እንደ አባትና ልጅ ሆነው ከ30 ዓመታት በላይ ዓመታት ኖሩ።
ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ የተለያዩ አካባቢዎችን በማቅናትና በማስተዳደር ስራ ውስጥ የላቀ ድርሻ ነበራቸው። ከነዚህ አካባቢዎች መካከል አርሲ እና ሰላሌና አካባቢው ይጠቀሳሉ። ንጉሰ ነገሥት አፄ ዮሐንስ 4ኛ እና ንጉሥ ምኒልክ በተቀያየሙ ጊዜም አስታራቂ ሽማግሌ ሆነው ያገለገሉት ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ ነበሩ። ንጉሰ ነገሥት አፄ ዮሐንስ 4ኛ እና ንጉሥ ምኒልክ ደብዳቤ የሚፃፃፉት በርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ በኩል ነበር። ደጃዝማች መሸሻ ሰይፉ በሸፈቱ ጊዜም ተቆጭው፣ አስማሚውና መካሪው ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ ነበሩ።
በዓድዋ ጦርነት ወቅትም ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ለጦርነቱ ወደ ዓድዋ በተጓዙበት ወቅት የንጉሰ ነገሥቱን ቦታ ተክተው ዙፋን የጠበቁትና አገር ያስተዳደሩት ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ ነበሩ።
በመልካም ጠባያቸው፣ በታማኝነታቸው፣ በበጎ አሳቢነታቸውና በጦር ጀግንነታቸው የሚታወቁት ርዕሰ መኳንንት ራስ ዳርጌ ሳህለሥላሴ መጋቢት 15 ቀን 1892 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው ስርዓተ ቀብራቸውም በደብረሊባኖስ ገዳም ተፈጽሟል።
ከላይ ያየናቸው ሁለቱ ራሶች (ራስ መኮንን እና ራስ ዳርጌ) ሁለቱም የዚህ ሳምንት ተዘካሪ ናቸው። እንደመገጣጠም ሆኖ ሁለቱም የንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ቤተሰቦች ናቸው። ሁለቱም በአንድ ወር ውስጥ ለዚያውም በአንድ ሳምንት ውስጥ ነው ያረፉት።
ለመረጃዎቹ Marcus, Menelik II, መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ፣ ዕለታዊ የታሪክ ድርጊት እና የ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ መጻሕፍትን እንዲሁም የተለያዩ ድረ ገጾችን በዋቢነት ተጠቅመናል።
የዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሊቀመንበር ሆኖ መሾም
የዚህ ሳምንት መጨረሻ ሌላኛው ክስተት ከአራት ዓመት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም ዕለተ ማክሰኞ ምሽት ወደ ሌሊት በተጠጋ ሰዓት የተሰማው ዜና የዶክተር ዐቢይ አሕመድ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆኖ መመረጥ ነበር።
መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም ስብሰባውን ያጠናቀቀው የኢህአዴግ ምክር ቤት ቀደም ሲል የኦህዴድ ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡትን ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡ መግለፁ ይታወሳል።
ዶክተር ዐቢይ ቀጣዩ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑም ተጠብቆ ቆይቷል። ምክር ቤቱ የግንባሩ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው የቆዩት አቶ ደመቀ መኮንን በያዙት ኃላፊነት እንዲቀጥሉ መርጦም ነበር።
በወቅቱ በተነገረው ግለ ታሪካቸው፤ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በጅማ አጋሮ በሻሻ የተወለዱ ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ አግኝተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ሰርተዋል።
በግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ እና በሊደርሺፕ ተቋም ደግሞ የሥራ አመራር ሳይንስ አጥንተዋል። እንዲሁም አሽላንድ ዩኒቨርሲቲ በንግድ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪ ያገኙ ሲሆን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰላም እና ደህንነት ጥናት ፒ ኤች ዲ አላቸው።
በወቅቱ የ42 ዓመት ጎልማሳ የነበሩት ዶክተር ዐቢይ ኦህዴድን የተቀላቀሉት በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ መሆኑን ተገልጾም ነበር። ከፖለቲካ ተሳትፏቸው በተጨማሪ በወታደራዊ ጉዳዮች ሰፊ ተሳትፎ የነበራቸው ሲሆን የሌተናል ኮሎኔል ማዕረግ አላቸው። በተባበሩት መንግሥታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮን ለማስፈጸም ሩዋንዳ ዘምተዋል።
ከ2000 እሰከ 2003 የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ መስራች እና ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል። ከዚያም የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚንስትር በመሆን አገልግለዋል።
ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2014