በምንም ያልተበገረ፣ ለምንም ያልተንበረከከ ማንነት
ጦርነት፣ ስደትና መሰል ማህበራዊ ቀውሶች ሲፈጠሩ የበለጠ ተጎጂ ከሚሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሴቶች፣ አቅመ ደካሞች፣ ህጻናትና አካል ጉዳተኞች ቀዳሚዎች ናቸው።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በፈጠረው ፀረሰላም እንቅስቃሴ ንፁሃን ለህልፈት ተዳርገዋል፤ በርካቶች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ከእነዚህ ውስጥ የ11ኛ ክፍል አካል ጉዳተኛው ተማሪ ማስረሻ አያሌው አንዱ ነው።
ማስረሻ ገና በልጅነቱ በምች ምክንያት የዓይን ብርሃኑን ማጣቱን ይናገራል። ይባስ ብሎ ጦርነቱ በፈጠረው ጦስ ይኖርበት የነበረውን ቀዬ ትቶ እንዲወጣ ተገዷል። በሰሜን ወሎ ዞን፣ ዳውንት ወረዳ የነገ ተስፋውን ለማለምለም እየተጋ ነበር።
ሆኖም የመማር እድሉ ሕወሓት በፈጠረው አገራዊ ቀውስ ተቋርጧል። እናም አሁን በጦርነቱ ምክንያት ከአካባቢው ተሰዶ አዲስ አበባ ይኖራል። ይህም ቢሆን ከጦርነት የማይተናነስ ሕይወት እንዲያሳልፍ እያደረገው ይገኛል። ይሁን እንጂ ትምህርቱን ከመማር አልተቆጠበም።
እዚህ አዲስ አበባ ከባድ የኑሮ ፈተናን እያሳለፈ የሚገኘው ተማሪ ማስረሻ፤ በተለይም የቤት ኪራይና ምግብ እጅግ ያሳስበዋል። ትራንስፖርትም ቢሆን ሰቆቃ ውስጥ ከሚከቱት የኑሮ ፈተናዎች መካከል ከሆነ ውሎ አድሯል። ለመማር ልዩ ጉጉት ስላለውም ነው ትምህርት ቤት የሚሄደው። በትራንስፖርት እጥረት ምክንያት ንብረቱ ሁሉ እየተዘረፈበት ትምህርት ቤት እንደሚገባ አጫውቶናል።
እኛ ስናገኘውም ዩኒፎርሙን ወስደውበት ነበር። አዲስ አበባን አይደለም አይነስውር ሆኖ አይናማም ሆኖ እንኳን ቶሎ ለመልመድ ያስቸግራል። በዚያ ላይ የቤት ኪራዩ አንገብጋቢ ነው። ትራንስፖርትም ቢሆን በቀላሉ ማግኘት አዳጋች እንደሆነ ሁሉም ያውቀዋል።
ይሁን እንጂ አላማን ከግብ ለማድረስ መሰዋዕትነት መክፈል ግድ ነውና እርሱም ይህንን እያደረገ አለ። ማደሪያ እንዳይቸግረውም በተለምዶ “ኬሻ በጠረባ” እየተባለ በሚጠራው ቤት አውቶቡስ ተራ፣ ጨው በረንዳ፣ ጉልት አካባቢ በቀን 20 ብር እየከፈለ ያድራል።
ይህ ደግሞ በወር ሲደመር ስድስት መቶ ብር ይደርሳል። ከአይነስውራን ማህበር የሚሰጠው አምስት መቶ ብር ብቻ ነው።
እናም ሌላውን ሰዎች ከሚያደርጉለት እርዳታ ያሟላዋል። ተማሪ ማስረሻ አያሌው ብዙ ጊዜ እሚማርበት ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመድረስ የሚያስችለው ገንዘብ አይኖረውም። የዚህን ጊዜ እጅጉን ያዝናል፤ ይበሳጫልም። ነገር ግን ምንም ማድረግ ስለማይችል በቻለው ሁሉ ትምህርት ቤት ለመድረስ ይሞክራል። እየወደቀና እየተነሳም ጭምር በእግሩ የሚመጣባቸው ጊዜያትም አሉ።
ቀን እስኪያልፍ ያለፋል አይደል ነገሩ። የማስረሻ ማደሪያ ቦታ ለማደርም ሆነ ለማንበብ ምቹ አይደለም። ምክንያቱም ቤቱ በረብሻ የተዋጠ ነው፣ የሚያነብለትም የለም። በዚያ ላይ እንቅልፍ እንኳን ለመተኛት አዳጋች ነው። ስለዚህም አዳሩ ውጥንቅጥ ውስጥ ይገባል። በመሆኑም ትምህርቱን የሚሸፍነው ክፍል ውስጥ በተማረው ብቻ ነው። ይህም ቢሆን በብዙ መንገድ እየተፈተነበት ይገኛል። የመጀመሪያው ቶሎ ባለመድረሱ የሚያመልጠው ትምህርት መኖሩ ሲሆን፤ ሁለተኛው በረሃብ ምክንያት በሙሉ ልብ አለመከታተሉ ነው። ክፍል ውስጥ የተማረውን ዳግመኛ እንዳያዳምጥ ደግሞ ብዙ ያልተሟሉለት የትምህርት ቁሳቁሶች አሉ።
ለምሳሌ፡- መቅረጸ ድምጽና የመሳሰሉት የመሰሉት አልተሟሉለትም። መዋያም ቢሆን የለውም። አንዳንዴ የሚያነቡለት ሰዎች ካገኘ ቤተመጻሕፍት ይገባል። ከሌለ ደግሞ ቶሎ ሄዶ የሚያርፍበት ስለማይኖር ዝም ብሎ በዚያው ይቆያል። ማስረሻ ቀደም ሲል በሚኖርበት አካባቢ ራሱን ለማቋቋምና ለማኖር የቻለውን ሥራ ሁሉ ይሠራ ነበር። ከእነዚህ መካከል ቅስና ስለነበረው በአካባቢው እያገለገለ የራሱን ገቢ የሚያገኝበት አንዱ ነበር። ከዚያ ያለፈውን ወንድሙ ይሞላለታል።
እንደውም አካል ጉዳቱ ጭምር ሳይታሰበው እንዲኖር ሆኖ ነበር። አሁን የገጠመውን አይነት ከባድ ስቃይ ገጥሞት አያውቀውም። የደረሰበት የአካል ጉዳት እንደማንኛውም ሰው ሊደርስ የሚችል አጋጣሚ እንደሆነ ቢያምንም ምን እንደሚያደርግ ግን ግራ ተጋብቷል።
መሸሺያና ማምለጫን ጭምር የማያውቅ አይነስውር ምግብና ቤት ተጨማሪ ችግሮች ሲሆኑበት ሁሉ ነገሩ ይዛባል። ተፈናቃይ ተብለው ሲመጡም ቢሆን እኩል ድጋፍ አለማግኘታቸው በራሱ ህመም ነው። እንኳን ሌላው መውጣትና መግባትም ያዳግታል። በመሆኑም ተዘዋውሮ የእለት ጉርሱን መሙላት አልቻለም።
ቤተሰቡ እየላከ እንዳይደጉመውም አባቱ አዛውንትና በወንድሙ ጥገኝነት ውስጥ ያሉና በኑሯቸው እጅግ የደከሙ ናቸው። እናቱንም ቢሆኑ ዘጠነኛ ክፍል እያለ በሞት ተነጥቋል።
ስለዚህም ወንድሙ ብቻ ነው ያለው። እርሱም ቢሆን በጦርነቱ ብዙ ነገር ስላጣ ቤተሰቡን እንኳን ማስተዳደር አልቻለም። ስለዚህም ማስረሻ ኑሮውን በሰው እጅ (እርዳታ) ላይ አድርጎ ይገኛል። ማስረሻ ሌላም ፈተና አለበት። የምግብ ጉዳይ። እስከ ዘጠኝ ሰዓት ተኩል በትምህርት ቤት ሲቆይ ምግብ ሳይበላ የሚውልባቸው ቀናት ብዙ ናቸው። ሳይበሉ መማር ደግሞ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በአንድ ቀን ጾማችን ብቻ መለካት እንችላለን።
በዚያ ላይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በብዙ ታዳጊና ደሀ አገሮች አካል ጉዳተኝነት እንደ አንድ የጤና እክል ሳይሆን እንደ የግለሰብ አሳዛኝ ገጠመኝ ወይም ድርጊት ተደርጎ ይወሰዳል። ይህ ደግሞ ለእንደ ማስረሻ አይነት አካል ጉዳተኞች ሕይወትን ከባድ እንደሚያደርግ ማንም ይረዳዋል። ማስረሻም ዳውንት ወረዳ ላይ እያለ የ”ልዩ ፍላጎት” ትምህርት ባይማር ኖሮ ብዙ ነገሮችን ማለፍ አይችልም ነበር። በተለይም በብሬል መፃፍና ማንበብን በተመለከተ የወሰደው ትምህርት ለዛሬ ትልቅ መሰረት ሆኖለት እንጂ በቀላሉ የሚወጣው አልነበረም።
ነገር ግን ሁሉ ነገር በጊዜ ሂደት ያልፋል ብሎ ያምናልና የማይሞክረው ነገር እንደሌለም ይናገራል። የመማር ጉጉቱን ከስኬት ለማድረስ ሰርቶ መኖር ግዴታው እንደሆነ ያውቃል። ነገር ግን በማያውቀው አካባቢ እንዴት አድርጎ ይህንን ያድርግ። ገና ዓመት እንኳን ላልሞላው ተፈናቃይና አይነስውር ይህንን ነገር ለማድረግ ብዙ ነገር ያስፈልገዋል። ነገር ግን አሁንም መፍትሄ ከማፈላለግ አልቦዘነም። እንደውም በቅርቡ በምትኖረው ሰዓት ማስክን የመሳሰሉ ነገሮች ሸጦ ገቢ ለማግኘት አስቧል።
ጦርነት አይደለም ለአይነስውር ለዓይናማውም እጅግ ፈታኝና ስቆቃን የሚያበዛ ነው። ምክንያቱም መሸሸጊያን ያሳጣል፤ መብላትን መጠጣትንም ይገድባል፤ የመኖር መብትን ጭምር ይነፍጋል፤ ከሁሉም በላይ ሕይወትን ያሳጣል። እንደውም የአካል ጉዳተኝነትን የሚፈለፍልም ነው። እናም ይህንን ስቃይ ማለፍና ከዚያ መውጣቱ አንዱ ሆኖ ሳለ ከዚያ በኋላ የሚመጣው መከራ ግን ይብሳል። መኖርን ጭምር የሚያስመኝ አይሆንም።
ከተመቻቸና ኑሮን ከተላመደ ቦታ ላይ ተነቅሎ መውጣትና አዲስ ቦታን መልመድ በራሱ ቀላል አይደለም። በዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እገዛ የ11ኛ ክፍል ትምህርቱን የጀመረው ማስረሻ፤ ተፈናቅሎ መምጣቱ ትልቅ የስነልቦና ችግር ፈጥሮበት ነበር። ሆኖም በትምህርት ቤቱ እገዛ ነገሮች ተስተካክለውለታል።
ካሉት ተማሪዎች እኩል ይሆን ዘንድም የደንብ ልብስና አንዳንድ የትምህርት ቁሳቁስ ተሟልቶለታል (በሚኖርበት አካባቢ እየወሰዱበት ቢያስቸግሩትም) እስካሁን ምንም ባያገኝም ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ቢያንስ ምግብና የትራንስፖርት እንዲያገኝ እየተሰራለት ነው።
የዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የልዩ ፍላጎት መምህሯና ምክትል ርዕሰ መምህሩ እንደሚሉት ከሆነ፣ ትምህርት ቤቱ ብዙ ተማሪዎችን ስለሚያስተናግድ በቂ ነገር ለማሟላት ይከብደዋል።
አጋዥ አካላትም ሁሉንም ሊያሟሉ አይችሉም። ለመማር የሚመጡትን ሁሉ እንደ ጉዳታቸው መጠን ተለይተው ነው ድጋፉ የሚሰጣቸው። ይህም ቢሆን በሚፈለገው መልኩ አይደለም። መሰረታዊ ፍላጎት የሚባሉትን ሁሉ ማሟላት የማይቻልበት ሁኔታ አለ።
የተፈናቀሉት ደግሞ ድንገተኛ የመጡ በመሆናቸው ብዙ ነገሮች ያገኛሉ ተብሎ አይታመንም። እናም ማስረሻን የሚደግፉ አካላት ቢኖሩ መልካም ነው። ማስረሻና መሰሎቹ፣ በተለይም ከመጠለያና ከምግብ አንጻር፣ በጣም ፈተና ውስጥ ናቸው።
ራቅ ብለው በመከራየትና ከማይመስላቸው ጋር አብረው በመኖር የሚያሳልፉት ችግር በቃላት የሚገለጽም አይደለም። እንደውም በትምህርት ቤት ደረጃ ከሆለታና ከሰበታ ድረስ መጥተው የሚማሩ ተማሪዎች ጭምር አሉን። ስለሆነም ችግሮቹን ከበጎ አድራጊ ድርጅቶችም ባለፈ መንግስት ቢደግፈው ብዙ ነገሮች መፍትሄ ያገኛሉ ብለውናል።
በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ የአካል ጉዳተኞች ብቻ ሳይሆኑ አካል ጉዳት የሌለባቸው ጭምር ምግብ የሚያገኙበት አማራጭ አለ። ጥሩ እድልም የሰጠ እንደሆነ ማንም ያውቀዋል። ነገር ግን በዚያ መልኩ የቆዩ ተማሪዎች ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ሁሉም ነገር ይቋረጥባቸዋል። በዚህም ስኬትን በችግር ውስጥ ሆነው እንዲፈልጉ ይገደዳሉ።
ያልገጠማቸውን አዲስ ሕይወትም እንዲኖሩ ይፈረድባቸዋል። ይህ ደግሞ ትምህርት እስከ ማቋረጥ ደረጃ ያደርሳቸዋል። ባስ ሲልም ሱሰኛና አጥፊ ሊሆኑ ይችላሉ። ሰዎች አካል ጉዳተኞች ሲሆኑ ሰማይ ሁሉ ይደፋባቸዋል። እናም የስኬት ማማ ላይ ሲደርሱ ትምህርታቸውን ሁሉ ሊተውት ይችላሉ። ይህ ደግሞ አይገባም።
ይልቁንም ትልቅ እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል። አሁን እየሆነ ያለው ምግብን አሳይቶ ከመንሳት አይተናነስምና መንግስት ሊያየውና ሊወስንበት እንደሚገባም ይመክራሉ። ለስኬት የቀረቡና ብዙ ትግልን የተጋፈጡ ተማሪዎች በብዙ መልኩ መደገፍ ይኖርባቸዋልም ነው ያሉን። ሁሉም ባይሆን እንኳን አካል ጉዳተኞችን በምግብና በትራንስፖርት እንዲሁም በቤት ኪራይ ማገዝ ቢቻል ብዙ ጉዳትን ቀንሶ ብዙ ስኬትን ማምጣትም ይቻላል ባይ ናቸው።
እንደ ማስረሻ አይነት ተማሪዎች የሚያግዛቸው ቤተሰብ፣ እንደልባቸው ተራሩጠው የሚሰሩት ነገር የለም፤ ለመመገብም እንዲሁ አጋዥ ሰውን ይሻሉ። የምግብ እድል የሰጣቸው አካልም አላገኙም። በዚያ ላይ ቤት የሌላቸውና በትራንስፖርት ጭምር የሚሰቃዩ ናቸው።
ሥራ ለመሥራት የሚያስችላቸው ጊዜም እንዲሁ ብዙ አይደለም። ምክንያቱም የሚማሩት እስከ 10 ሰዓት ነው። ከዚያ በኋላ አይደለም አይነስውር ሆኖ ዓይናማም ሆኖ ያለውን ፈተና ማንም ይረዳዋል። ትራንስፖርቱ፣ ምግብና ማደሪያም ማግኘቱ እንዲሁ መከራ ነው።
ነገር ግን የትምህርት ጉጉታቸው ብቻ እያኖራቸው መከራውን ሁሉ አሜን ብለው ተቀብለዋልና መጀመሪያ መንግስት፤ ከዚያም አጋር አካላት እጃቸውን እንዲዘረጉላቸው ይማጸናሉ። የችግራቸው መንስኤ ሁሉም እንደሚያውቀው ከአመለካከት ይጀምራል። አካባቢያዊ፣ ተቋማዊ እና የሕግ መሰናክሎች ብዙ ፈተና የሚጥሉባቸው ናቸው።
እናም እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ከማብቃት አንጻር ከአመለካከት ጀምሮ ያሉ ችግሮች ሊፈቱ ይገባል። ከእነዚህ ሁሉ ችግሮች አኳያም አይነስውራንንም ሆነ ሌሎች አካል ጉዳተኞችን ቢያንስ ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ ማገዝ ለነብስም ለስጋም እርካታ ነውና አቅሙ የፈቀደ ሁሉ ሊረባረብ ይገባል። እንደ አገር እነዚህን ችግሮች መፍታትና መደጋገፍ ካልተቻለ የእነዚህ ወገኖች የመማርና ሰው የደረሰበት የመድረስ ህልም ይጨልማል።
በእስካሁኑም ቢሆን የትምህርት ሚኒስቴር ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ ከአምስት በመቶ በታች የሆኑ አካል ጉዳተኞች ብቻ ናቸው የትምህርት እድል ያገኙት። ስለዚህ እነዚህን ወገኖች መደገፍና ማብቃት የማስፈለጉ ጉዳይ አጠያያቂ አይደለም።
እንዲህ ሆነው ተምረው ሥራ ሲፈልጉም የሚቀጥር እንደሌለ ብዙዎቻችን እናውቃለን። እየሰሩ ለመማር እንኳን ቢፈልጉ የሚሰጣቸው እድልም ስለመኖሩ አፍ ሞልቶ መናገር አይቻልም። አሁንም ከሥራ እድል አንጻር ሲነሳ 98 በመቶ የሚሆኑት የአካል ጉዳተኞች በመስሪያ የዕድሜ ክልል ውስጥ ቢገኙም ሥራ የላቸውም።
ስለሆነም እንደ ማስረሻ አይነት ተማሪዎች ቢያንስ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የምግብና የመጠለያ ጉዳይ አሳስቧቸው ይገኛሉና ከዚህ ፈተና እና ስቃይ እንታደጋቸው፤ በምንም ያልተበገረው፣ ለምንም ያልተንበረከከው የተማሪ ማስረሻ ማንነትም ወደ ኋላ እንዳይቀለበስ አቅማችን በፈቀደ መጠን ሁሉ እንደርስለት ዘንድ ጥሪ እያቀረብን የዛሬውን ሀሳባችን ቋጨን። ሰላም!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መጋቢት 17 /2014