
ሩሲያ ወደ ውጭ አገራት ለምትልካቸው የነዳጅ ዘይትና ጋዝ ምርቶች ክፍያዎችን በቢትኮይን ለመቀበል እያሰበች መሆኑን አንድ የአገሪቱ ከፍተኛ የሕግ አውጪ ምክር ቤት አባል ገለጹ።
ፓቬል ዛቫልኒይ እንዳሉት የሩሲያን የኃይል ምርቶች የሚገዙ “ወዳጅ” አገራት ክፍያቸውን በክሪፕቶከተንሲ ወይም በራሳቸው የመገበያያ ገንዘብ እንዲከፍሉ ሊፈቀድላቸው ይችላል። በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን “ወዳጅ ያለሆኑ” አገራት የአገራቸውን የጋዝ ምርት ሲገዙ በሩሲያ ገንዘብ (ሩብል) እንዲከፍሉ ለማድረግ እንደሚፈልጉ ገልጸው ነበር።
ይህ እርምጃቸውም በዚህ የፈረንጆች ዓመት ብቻ ከ20 በመቶ በላይ ዋጋውን ያጣውን ሩብል ጥንካሬ ለመመለስ እንደሆነ ተገምቷል። በዚህም ሩብል በከፍተኛ ሁኔታ ማንሰራራት አሳይቷል። ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ሕብረት የተጣሉባት ማዕቀቦች በአገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ ላይ ጫናን የፈጠረ ሲሆን የኑሮ ውድነትንም አንሮታል።
ነገር ግን አሁንም ቢሆን ሩሲያ ለዓለም ገበያ ከፍተኛ መጠን ያለው የተፈጥሮ ጋዝን በማቅረብ ቀዳሚ ስትሆን በነዳጅ ዘይትም ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በሩሲያ ምክር ቤት ዱማ ውስጥ የኢነርጂ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ፓቬል ዛቫልኒይ እንዳሉት፣ አገራቸው ወደ ውጭ ለምትልካቸው የነዳጅና የጋዝ ምርቶች መገበያያ አማራጭ የክፍያ መንገዶችን እያፈላለገች እንደሆነ አመልክተዋል።
ጨምረውም ቻይናና ቱርክ በሩሲያ ላይ እየተደረገ ባለው “የማዕቀቦች ጫና ውስጥ ያልተሳተፉ ወዳጅ” አገራት ናቸው በማለት ጠቅሰዋል። “ለረጅም ጊዜ ከቻይና ጋር የሚደረገውን የንግድ ልውውጥ በየአገሮቻችን መገበያያ ገንዘብ በሩብል እና በዩዋን እንድናደርገው ሃሳብ ስናቀርብ ቆይተናል” ያሉት ዛቫልኒይ “ከቱርክ ጋር በሊራ የምንገበያይ ይሆናል” ብለዋል።
ባለሥልጣኑ ጨምረውም ከአገራቱ የመገበያያ ገንዘብ በተጨማሪ “በቢትኮይንም መገበያየት ይቻላል” ብለዋል። ተንታኞች እንደሚሉት ግን አደጋዎች ሊኖሩት ቢችሉም ሩሲያ በታዋቂ ክሪፕቶከረንሲዎች መገበያየት ከጀመረች ተጠቃሚ ልትሆን ትችላለች።
ነገር ግን ከተለመዱት የግብይት ገንዘቦች በተቃራኒ የቢትኮይን ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ተለዋዋጭ በመሆኑ የራሱ የሆነ አደጋን ሊያስከትል እንደሚችል በኢነርጂው ዘርፍ ባለሙያ የሆኑት ዴቪድ ብሮድስቶክ ይናገራሉ።
የሩሲያ ከበርቴዎች በምዕራባውያን የሚጣሉ ማዕቀቦችን ለማምለጥ ሲሉ እነዚህ ክሪፕቶከረንሲዎች ሊጠቀሙ ይችላሉ በሚል የዩክሬን፣ የአሜሪካና የአውሮፓ ፖለቲከኞች የክሪፕቶከረንሲ የመገበያያ መድረኮች የሩሲያ ተጠቃሚዎችን እንዲያግዱ ጠይቀዋል። ነገር ግን አብዛኞቹ ይህንን ጥያቄ ውድቅ አድርገውታል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መጋቢት 17 /2014