የዛሬው የዘመን እንግዳችን በጉራጌ ዞን ቆለኖረና ቀበሌ ገበሬ ማህበር ልዩ ስሙ ጫንጮ ቅዱስ ቂርቆስ ደብር በሚባል አካባቢ በ1928 ዓ.ም ነው የተወለዱት።
እንደማንኛውም የገጠር ልጅ የወላጆቻቸውን ከብቶች እየጠበቁ ነው ያደጉት። በእድሜ ሲጎረምሱ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ጉለሌ አካባቢ በሚገኘው የሲዊዲን ሚሽን ትምህርት ቤት እስከ አራተኛ ክፍል ተማሩ። በመቀጠልም አርበኞች ትምህርት ቤት ገብተው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ። በኮከበ-ፅባህ ትምህርት ቤት ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሰልጥነው ዲፕሎማቸውን አግኝተዋል። ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ለአንድ ዓመት ያህል በሶዶ ሊጋባ በየነ ትምህርት ቤት በመምህርነት ሰሩ።
ይሁንና በወቅቱ የትምህርት ተቋማት ዳይሬክተሮች እጥረት ስለነበር በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶችና ትምህርት ቢሮዎች በዳይሬክተርነት፤ በተቆጣጣሪነትና በከፍተኛ አመራርነት ለ28 ዓመታት አገልግለዋል። በዳይሬክተርነትና በተቆጣጣሪነት ካገለገሉባቸው የትምህርት ተቋማት መካከልም ቦዲቲ ፣ ሃዋሳ ታቦር እና አርባ ምንጭ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተጠቃሽ ናቸው።
እንዲሁም በትምህርት ሚኒስቴር የጥናትና ምርምር ኃላፊ ሆነው እንዲሁም በህገመንግሥት አርቃቂ ኮምሽን ሰርተዋል። በትምህርት ዘርፉ እድገት ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በሶስቱም መንግሥታት እውቅና የተቸራቸው እኚሁ ሰው በተለይም በደርግ ዘመነ መንግሥት በአርባ ምንጭ ተከስቶ የነበረውን የተማሪዎች ረብሻ ለማረጋጋት ባከናወኑት ሥራ ሥማቸው ጎልቶ ይነሳል።
ከመማር ማስተማር ሥራው ባሻገርም የዶሮ ጫጩት መፈልፈያ ማሽን ዲዛይን ጥናትና ምርምር አካሂደዋል።
የመጀመሪያውን የክስታኔ ጉራጌ ቋንቋ መዝገበ ቃላት ያዘጋጁት እንግዳችን ‹‹የጉራጌ ማህበረሰብ ማንነት በኢትዮጵያ አንድነትና ነፃነት እቅፍ ውስጥ›› የተሰኘ የጉራጌ ማህበረሰብን በሰፊው የሚያስተዋውቅና ለሀገር አንድነት ያበረከቱትን አስተዋፅኦ የሚያትት መጽሐፍ ለንባብ አብቅተዋል።
በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስን አራት ወንጌሎች በክስታንኛ ቋንቋ የተረጎሙ ሲሆን ከኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ጋር በመተባበር ለማሳተም በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን ጋዜጣም መምህርና ደራሲ አቶ ታምርአየሁ ሲማን የዛሬው የዘመን እንግዳ አድርጓቸዋል። በሕይወት ተሞክሯቸውና በተለያዩ ሃገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- መምህርነት ለእርሶ ምን ማለት እንደሆነ ያስረዱንና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ ታምርአየሁ፡- ለእኔ መምህርነት ከልጅነቴ ጀምሮ የምመኛውና የምወደው ሙያ ነው። ትውልድን ከፈጣሪ ቀጥሎ ሰው አድርጎ የሚፈጥር መሆኑ ከምንም በላይ የሚከበር የሥራ መስክ ነው። እንዳልኩሽ መምህርነት ሙያን ከልቤ እወደው ስለነበር እድሜ ዘመኔን በዛው ሙያ መቀጠል ነበር የምፈልገው።
ይሁንና በወቅቱ የአመራር እጥረት ስለነበር ሳልወድ በግዴ በዳይሬክተርነትና በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ እንድሰራ ተደረኩኝ። የሚገርምሽ የኃላፊነት ሥራ አልፈልግም ብዬ የአውራጃ ገዢው ጋር በተደጋጋሚ አቤቱታ አቅርቤ ነበር።
ነገር ግን አቤቱታዬ ተቀባይነት አላገኘም። እንደእውነቱ ከሆነ በተለይ በወጣትነት ጊዜዬ በሙያዬ ለሃገርና ለወገን ለመስራት ፅኑ ፍላጎት ነበረኝ። ግን የማስተማር ሕይወቴ ለአንድ ዓመት ብቻ ነው የዘለቀው።
ያም ቢሆን በተመደብኩበት ሥራ በጣም ውጤታማ ሥራ አከናውኛለሁ፤ በዚህም ህብረተሰቡን የጠቀምኩ ይመስለኛል። እንዲያውም በቀዳማዊ ኃይለስላሴ የሽልማት ድርጅት ለሽልማት ታጭቼ ነበር። ይሁንና በ1966ዓ.ም ዓብዮት በመከሰቱ ሽልማቱ ተጨናገፈ።
ባለመሸለሜ ግን ብዙም ቅር አልተሰኘሁም፤ ምክንያቱም እኔ ከመጀመሪያውም ጀምሮ እሸለማለሁ፤ እሾማለሁ ብዬ ሰርቼ አላውቅም። በመሰረቱ ያንን የማስብ ቢሆን ኖሮ በንጉሱም ሆነ ደርግም ጊዜ ወደ ስልጣን የመምጣት እድሉ ነበረኝ። ሽልማትና ስልጣን ሲያድኑ የሞቱ፤ የጠፉ ሰዎች አሉና እኔ በሕይወት በመቆየቴ በእውነት ደስተኛ ነኝ።
በተለይ በደርግ ጊዜ ‹‹እበላለሁ›› ብለው ካድሬ ሆነው ብዙ ችግር የደረሰባቸው ሰዎች አሉ። በነገራችን ላይ እኔም ብሆን ሃገሪቱ በተማሩ ሰዎች መመራት አለባት ተብሎ ከ1ሺ800 ከሚሆኑ አመራሮች ጋር ለ15 ቀናት ስልጠና እንድወስድ ተደርጌ ነበር። ግን የፖለቲካ ሹመኛ መሆኑን ፈፅሞ ስላልፈለኩት ፈጣሪዬን ለመንኩት፤ በመጨረሻም ዘዴ ፈጥሬ በሙያዬ ለመመደብ ችያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ይህን ሲሉ ምን ማለቶ ነው?
አቶ ታምርአየሁ፡- በወቅቱ በተመደቡበት ኃላፊነት አልሰራም ማለት ፈፅሞ የማይቻል ነበር። እኔ ግን የዶሮ መፈልፈያ(ኢንኪዩቤተር)በሃገር ውስጥ መስራት እንደሚቻል ጥናት አድርጌ ስለነበር ከፖለቲካው ሹመት ይልቅ ያንን ማሽን ብሰራው የበለጠ ሃገሬን እንደምጠቅም በማሳመን ከፖለቲካው በዘዴ ዞር ማለት ቻልኩኝ።
ይህንን ከውጭ የሚመጣውን የዶሮ መፈልፈያ መሳሪያ በማስቀረት በሃገር ውስጥ በማምረት እያንዳንዱ ገበሬ ቤት ማድረስ የሚያስችል ዲዛይን ሰርቼ ነበር። በዚያ ምክንያት ተፈቀደልኝና ወደ ትምህርት ሚኒስቴር ተመለስኩኝ።
በነገራችን ላይ እኔ በሕይወቴ የትኛውም ፖለቲካ ድርጅት አባል ሆኜ አላውቅም። ምክንያቱም ርዕዮተ ዓላማቸው ራሱ የፈጣሪን መኖር የማያምን በመሆኑ ከእኔ እምነት ጋር ይጋጫል። ይህም ሆኖ ግን ተገደን የውይይት ክበብ ውስጥ እንሳተፍ ነበር። ካድሬዎቹ እንድንናገር ያጣድፉን ነበር።
በዚህ መድረክ ላይ በማደርገው ተሳትፎ አርባ ምንጭ የክፍለሃገር ትምህርት ቤቶች ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆኜ ለሶስት ዓመት ተኩል ሰርቻለሁ። ይሁንና ወቅቱ በጣም የተበላሸ ጊዜ ስለነበር ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ነበሩ። ሁሉም ግራ እጁን እያወጣ ‹‹አድሃሪያን ይውደሙ፤ ቢሮክራቶች ይውደቁ›› የሚልበት ጊዜ ነበር።
ቤተክርስቲያን መሄድ አይቻልም ነበር። እኔ ግን ሄጄ አስቀድስ ነበር። ይህም የደርግ ሰዎች ጥርስ ውስጥ አስገብቶኝ ነበር። ግን በፈጣሪ ጥበቃ አንድም ቀን ታስሬ አላውቅም ነበር። በሥራዬም ደግሞ ፈርቼ ላደርገው የሚገባኝን ነገር ሳላደርግ የቀረሁበት፤ ማድረግ የሌለብኝን ነገር ያደረኩበት ነገር የለም።
ትምህርት ሚኒስቴር በነበርኩበት ወቅት እንዳውም ምስጉን ባለሙያ ተብዬ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተሸልሜበታለሁ። በኢህአዴግ ዘመን ጡረታ ከወጣሁ በኋላም ቅጥሩ እንዲቀጥልልኝ ጠይቅ ቢሉኝም እኔ ግን አሻፈረኝ አልኳቸው። እኔ ደርግንም ሆነ ተተኪዎቹን አልወደድኳቸውም።
በተለይ የህወሓት ሰዎች ይዘውት የመጡት ህገ-መንግሥት እስከመገንጠል ድረስ የሚፈቅድ በመሆኑ በዚህ ምክንያት አልወደድኳቸውም ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ጋር ተያይዞ የኢህዴግ አመራሮች ጋር ያልተግባቡት ነገር እንደነበር ሰምተ ናል፤ እስቲ ምክንያቱ ምን እንደነበር ያስረዱን?
አቶ ታምርአየሁ፡- አንድ ወቅት ላይ የኢህአዴግ አመራሮች መላውን የትምህርት ማህበረሰብ ምኒሊክ ትምህርት ቤት አዳራሽ ውስጥ ሰብስበውን እስከመገንጠል የሚለውን ሃሳብ እንድንቀበል ለማሳመን ጥረት አድርገው ነበር። ስለኤርትራ መገንጠል ህጋዊነት ነገሩን። በወቅቱ እኔ በጉዳዩ ላይ ሃሳብ ለመስጠት አልፈለኩም ነበር።
ሆዴ ግን ታሞ ነበር። ባንዲራ ጨርቅ ነው እና ነጻነት እስከመገንጠል የሚለው ነገር ህመም ፈጥሮብኝ ነበር። ያን ቀን ግን ዝም ማለት አቃተኝ። በተለይ የደርግ አባል ሆነው ህዝቡን ሲያምሱና ሲያተራምሱ የነበሩ ሰዎች ወደ ህወሓቶቹ ተገልብጠው ሲያወድሷቸውና ሲያንቆለጳጵሷቸው ስመለከት በጣም ነደደኝ።
እጄን አውጥቼ እስኪበቃኝ ድረስ ተናገርኩኝ። ልክ እንደ አበደ ሰው እሳት ጨብጬ አጠቃላይ ፖሊሲያቸው ምን ያህል ሃገር አፍራሽ እንደሆነ ተናርኩኝ። በዓለም ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የኤርትራን መገንጠል መፍቀዳቸው ትክክል እንዳልሆነ አስረዳሁ።
እንዳውም ይህ ሃሳብ የአረቦች እጅ እንዳለበት አነሳሁኝ። ራሴን መቆጣጠር አቃተኝና አለቃቸው መለስ ዜናዊ ባንዲራ ጨርቅ ነው ማለቱ በጣም አሳፋሪ መሆኑን በድፍረት ተናገርኩኝ። ጨርቅ ማለት እዳፊ ቆሻሻ መጥረጊያ ነው። ባንዲራ ግን ከዚያ የተለየ ትርጉም ያለው መሆኑን ገለፅኩኝ። በተለይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ አሉላ በዶጋሊ፤ ኃይለስላሴ በማይጨው፤ ምኒልክ በአድዋ ደማቸውን ያፈሰሱለት፤ አጥንታቸውን የከሰከሱለት ነው አልኳቸው።
ያን ጊዜ ፈርቶ ዝም ብሎ ተቀምጦ የነበረው ተሳታፊ ሁሉ የልቡን ስለተናገርኩለት በደስታ ብዛት ያጨበጭብና በሁካታ አደራሹን ያሸብሩት ጀመር። ሰብሳቢው የሚያደርገው ጠፋው፤ ሰብሳቢውን የሚሰማው አጣ። ግማሹ ሰው ይስመኝና ይጨብጠኝም ነበር።
ለካ ሰው የሚተነፍስበት አጥቶ ነው እንጂ ታሞ ከርሞ ነበር ብዬ አሰብኩ። ከዚያ ጊዜ በኋላ አልሰራም ብዬ ወጣሁኝ። በወቅቱ የሚገርምሽ ባለቤቴ ሥራ አልነበራትም፤ ልጆቼም ለሥራ አልደረሱም ነበር፤ ግን ወኔ ብቻ ይዤ ነው የለቀቅኩት።
አዲስ ዘመን፡- ከትምህርቱ ባሻገር የተለያዩ መጽሐፍት ፅፈዋል፤ እዚህ ስለመጽሐፎቹ ይዘት በጥቂቱ ይንገሩን?
አቶ ታምርአየሁ፡- እንደነገርኩሽ እኔ የኖርኩት ከመጽሐፍት ጋር ነው። ብዙ እውቀት ያጎለበትኩም ከማንበብ ነው። ማንበብ እወድ ስለነበር እዚያ ውስጥ የማገኛቸው ቁምነገሮች ብዙ አሉ። ያነበብኩትንና ያገኘሁትን እውቀት ለህዝብ ማካፈል አለብኝ ብዬ አምን ነበር። በየጊዜው ከምፅፋቸው አጫጭር መጣጥፎች ፤ ግጥሞችና የጥናት ሥራዎች ባሻገር የክስታኔ ጉራጌ መዝገበ ቃላትና የጉራጌ ማህበረሰብ ማንነትና ለሃገር አንድነት ያበረከተውን አስተዋፅኦ የሚተነትን መጽሐፍት ለህትመት በቅተውልኛል።
ከዚህም በተጨማሪ በክስታንኛ ቋንቋ የመጽሐፍ ቅዱስን አራት ወንጌሎች ተርጉሜ አጠናቅቄያለሁ። አሁን የመጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ለማሳተም ወስዶታል። በነገራችን ላይ እኔ ስለጉራጌ ማህበረሰብ ብፅፍም ለሁሉም ህዝብ የሚጠቅም ሃሳብ ነው በመጽሐፎቼ ያሰፈርኩት።
በመሰረቱ እኔ በኢትዮጵያዊነቴ የማምንና ኮርቼ የምናገር ሰው ነኝ። ሌላውም ሰው ሃገሩን እንዲወድ እፈልጋለሁ። ከዚህ አንፃር በጉራጊኛ ቋንቋ ላይ ለመፃፍ የተነሳሁበት ምክንያት ቋንቋውን ለትውልድ ማስተላለፍ አለብኝ ከሚል መነሻ ነው።
ብዙ ቋንቋዎች ተናጋሪ አጥተው ጠፍተዋል። ለምሳሌ ጋፋት የሚባለው ቋንቋ ከመካከለኛው ሸዋ ተገፍቶ በኃይለኛ ወራሪዎች ወደ ወለጋ ሄደ፤ ከዚያ ወደ ጎጃም፤ በመቀጠልም ወደ ጎንደር በጌ ምድር ተሰደደ። ከጊዜ ጊዜ እየተበተነ ሄዶ ቋንቋው አሁን ላይ ጠፍቷል።
ልክ እንደክስታንኛ ቋንቋ ቅርብ የሆነ ቋንቋ ነበር። መጽሐፉ ላይ እንደጠቀስኩትም አንዳንድ ቃላት ከክስታንኛ ጋር ተመሳሳይነት አላቸው። ለምሳሌ ‹‹ ሸንጎበት›› ማለት ጢም ማለት ነው። ይህ ቃል በክስታንኛም ሆነ በጋፋትኛ ተመሳሳይ ትርጓሜ ነው ያለው። አሁን ላይ ጎጃም አካባቢ ይህንን ቃል ይጠቀሙበታል።
ሌላ ምሳሌ ልጨምርልሽ ‹‹ ኩማ›› በክስታንኛ ተረከዝ ነው። ጎጃምም እንዲሁ ተመሳሳይ ትርጓሜ ነው ያለው። ‹‹ቡላል›› ማለት ደግሞ እርግብ ናት፤ጎጃም ብትሄጂ እነሱም እርግብን ‹‹ቡላል›› እያሉ ነው የሚጠሯት። የእኔ አቅም አልቻለውም እንጂ ትንሽ ምርምር ቢደረግበት ብዙ ነገር ማወቅ ይቻል ነበር። ለዚህ ነው የእኔ መጽሐፍ አንድ ቋንቋ ላይ ብቻ አያጠነጥንም ያልኩሽ።
ሁለተኛው መጽሐፌን ስፅፍ ብቻዬን አላዘጋጀሁትም፤ አንዳንድ ሰዎች አግዘውኛል። በተለይ ሰነዶችን በመስጠት ድጋፍ ያደረጉልኝ የውጭ ዜጎች አሉ። የፃፍኩት ስለጉራጌ ማህበረሰብ ቢሆንም ከሌላው ህዝብ ጋር ያለውን መስተጋብር ያንፀባርቃል።
ጉራጌ ሰራተኛ ነው፤ የፍቅር ህዝብ ነው። ለሌሎችም ምሳሌ መሆን የሚችል ማህበረሰብ ነው። በጦርሜዳም ቢሆን ጀግና መሆኑን በማይጨውና በአድዋ ጦርነቶች አስመስክሯል። አርበኛም ነው።
አዲስ ዘመን፡- ግን ስለጉራጌ አርበኞችና ጀግኖች ብዙም ሲወራ አይሰማም፤ በታሪክ ብዙ ስማቸው ሲጠቀስ አናይም። ለመሆኑ የሆነበት ምክንያት ምንድንነው ይላሉ?
አቶ ታምርአየሁ፡- የጉራጌ ህዝብ በተለይ በአድዋ ጦርነት ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ተሳትፎ ሃገሩን ከጠላት እንደታደገ ይታወቃል። ድሉም የሁሉም ነው። እኔ ብቻ ነው የተፋለምኩ የሚል ሰው ውሸታም ነው ባይነኝ። ምኒልክ ያወጁትን አዋጅ ሁሉም ተቀብሎ መዝመቱን ታሪክ ያሳያል።
ጉራጌም ልክ እንደሌላው ዘምቶ ደሙን አፍስሷል፤ አጥንቱን ከስክሷል። በ1928 ዓ.ም በማይጨው ጦርነት ላይም ተመሳሳይ አስተዋፅኦ ነበረው። ከዚሁ ጎን ለጎንም መንገድ በመገንባት ረገድ ‹‹ጀፎረ›› የሚባለውና የጉራጌ ማህበረሰብ ያቋቋመው የኮንስትራክሽን ድርጅት 1ሺ 500 የጉራጌ ተወላጆች ተመልምለው ከመቀሌ እስከ አሸንጌ ሃይቅ ድረስ ቦንብ ከሰማይ እየወረደባቸው ገንብተው አጠናቀዋል።
ለአብነት ያህል ብጠቅስልሽ እነደጃዝማች በቀለ ወያ፣ እነ ቀኝአዝማች ሃብተማርያም ጎቤ፣ ፊታውራሪ ታደሰ ማርቆስ የተባሉ ጀግኖች ጣሊያንን ሲያርበደብዱ እንደነበር ይታወቃል። ከማንም ባልተናነሰ ሁኔታ የጉራጌ ህዝብ ለኢትዮጵያ አንድነትና ነፃነት ታግሏል።
ስለሆነም ነው የዚህን መጽሐፍ ርዕስ‹‹ የጉራጌ ህዝብ ማንነት፤ በኢትዮጵያ አንድነትና ነፃነት እቅፍ ውስጥ›› ብዬ የሰየምኩት። ይህንን ሁሉ ታሪክ ያለው ህዝብ ግን ስለጀግንነቱ እምብዛም ያልተነገረለት ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ።
እንደሚታወቀው ይህ ማህበረሰብ በአብዛኛው ንግዱና ሥራው ላይ ከማተኮር ባለፈ ታሪክና አውቆ ለትውልድ ለማስተዋወቅ ሲጥር አይታይም። እርግጥ ነው ጥቂትም ቢሆኑ ታሪኩን የፃፉ ሰዎች አሉ። ለምሳሌ ተስፋ ገብረየስ፣ ሰይፉ ድባቤና አለሙ ድንበሩ የፃፏቸው ድንቅ መጽሐፍት አሉ።
ግን በተሟላ መልኩ አልተፃፈም። ምክንያቱም አብዛኛው ጉራጌ ለሥራ ይጣደፋል እንጂ ታሪክንም አይሻማም፤ ታሪክ ሰርቻለሁና ልሾም ልሸለም ብሎ የሚስገበገብ ማህበረሰብ አይደለም። በአጠቃላይ ጉራጌ ታሪካዊና ትውልዳዊ ማንነቱ ሴሜቲክ ነው፤ ብዙ ግፊት ተደርጎበታል፤ በወራሪዎች በየጊዜው ከመሬቱ ተፈናቅሏል።
አሁን እዚህና እዚያ ቦታ ነበር ማለቱ አይጠቅምም። ምክንያቱም ያለፈ ጊዜ ለዛሬ መፍትሔ ሊሆን አይችልም። ዛሬን ነው መጠቀም ያለብን።
አዲስ ዘመን፡- ክስታንኛ ቋንቋ ልክ እንደጋፋትኛ የመጥፋት አደጋ ያሰጋዋል ብለው ያምናሉ?
አቶ ታምርአየሁ፡- ክስታንኛ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ጉራግኛ ቋንቋ በተወሰነ ደረጃ የመጥፋት አደጋ ያሰጋዋል። በሌሎች ቋንቋዎች እየተዋጠ ፤ እየተደባለቀ ነው ያለው።
በተለይ አሁን ያለው ትውልድ ግራ ተጋብቷል። አለማየሁ ነሪ ‹‹እሰት›› በሚለው መጽሐፉ ላይም ይህንን ስጋቱን አንስቷል። ጉራግኛ ከሌሎች ቋንቋ እየተደባለቀና እየተዋጣ በመሆኑ እንዳይጠፋ የሚያሰጋ መሆኑን በዝርዝር አትቷል።
ለምሳሌ በክስታንኛ ቋንቋ ‹‹ ምካት የለም›› የሚል ቃል አለ፤ ይህንን ቃል ወጣቱ አይጠቀመው፤ በምትኩም ‹‹ችግር የለም›› እያለ ይመልሳል። ቋንቋውን በማዳቀል ስንጠቀም ደግሞ በሂደት እየጠፋና እየተዋጠ ይመጣል። ይሄ ችግር በጉራግኛ ወይም በክስታንኛ ቋንቋ ላይ ብቻ የተጋረጠ አይደለም። በየትኛውም ቋንቋ ላይ የሚከሰት ነው። አንድ ቋንቋ አይሎ ሌላውን ሊውጠው ይችላል።
ለምሳሌ ጉራግኛ ቃላት በኦሮምኛ ቋንቋ ውስጥ አለ፤ ኦሮምኛም በጉራግኛ ቋንቋ ውስጥ አለ። መወራረስ ያለ ነው። ግን በወረራ የሚደረግ የቋንቋ መወራረስ ሁኔታ አንድን ማህበረሰብ ጭራሹን እስከነባህሉና ማንነቱ ጭምር ሊያጠፋው ይችላል። በሌላ በኩል ግን ባህሉንና ቋንቋውን ከመታደግፍ ባለፈ ከሁሉም ብሔረሰቦች ጋር በሰላምና በፍቅር መኖር ወሳኝ ጉዳይ ነው።
በአንድ አንድ ፖለቲከኞች ‹‹እኔ አውቅልሃለሁ›› በሚል ህዝቦችን ለማጣለት የሚደረገው ጥረት አልደግፈውም። ‹‹ነፃ አውጪ ነኝ›› እየተባለ የሚደረገውን ሃገር የማተራመስ እንቅስቃሴን ፈፅሞ የማልቀበለው ነው። በመሰረቱ ማንን? ከማን? ማን? ነፃ የሚያወጣው?። ምንአልባት ከችግር ነፃ መውጣት ሊያስፈልገን ይችላል፤ ግን ምን በሌለበት አንድ ከሆነ ህዝብ ተነጥሎ ነጻ እወጣለሁ ማለት ትርጉም አልባ ነው የሚመስለኝ።
በተለይ አሁን የሚያዋጣን አንድነታችንን እና ህብረታችንን ማጠናከር ነው። ተስማምተን፤ ልዩነታችንን አቻችለን በአንድነት ፤በነጻነት መኖር ነው የሚያዋጣን።
አዲስ ዘመን፡- የጉራጌ ዞን ሁሉም የብሔረሰቡ ተወላጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ የጀመረውን ጥረት እንዴት ያዩታል? በተለይ ቋንቋውን ከመታደግ አኳያ ምን ፋይዳ ይኖረዋል?
አቶ ታምርአየሁ፡– ከዚያ በፊት አንድ ነገር መናገር እፈልጋለሁ። አማርኛ ቋንቋ መኖሩ ለሁሉም ማህበረሰብ ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም መነጋገሪያችን እርስ በርስ መግባቢያ ቋንቋችን ነው።
ትልቅና በዘመናት የዳበረ ቋንቋ ነው። ታሪክ ተፅፎበታል፤ የሃይማኖት መጽሐፍ ተፅፎበታል፤ የብዙ ብሔረሰቦች መገናኛ ሆኗል። ለጉራጌም አስፈላጊ ነው። በመጽሐፌም ላይ ይህንኑ ብያለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ የራሱ ማንነት የሚከበርበት፤ ማንነቱ የሚታወቅበት አንዱ ትልቁ ቋንቋው ነው። በቋንቋው ፀሎት ያደርጋል፤ በቋንቋው የሸንጎ ስርዓትን ያከናውናል፤ ስለዚህ ትውልዱ በአፍ መፍቻ ቋንቋው መማሩ ያለው ጠቀሜታ ምንም አያወላዳም። የሚዳብርበት አንዱ መንገድ ይህ ነው።
ዩኒስኮም ቢሆን ህፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ያዛል። እዚህም መጽሐፌ ላይ ምክረ ሃሳቤን ጽፌአለሁ። በመዘገበ ቃላቱ ውስጥ የተረሱ ቃላትን ለማካተት ሞክሪያለሁ። ይህንን ፈር ማስያዝ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- የትምህርት ተቋማት በየስርዓቱ የአብዮት መነሻ፤ የነውጥ መቀስቀሻ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ፤ ይህ የሚሆንበት ምክንያት ምንድነው ይላሉ? አቶ ታምርአየሁ፡- ይሄ ነገር እኮ ዛሬ የተጀመረ አይደለም። በንጉሱ ጊዜም እኮ የትምህርት ተቋማትን በመጠቀም አብዬት የማስነሳት ጥረት ተደርጎ ነበር። ጥላሁን ግዛው ሲገደል ጀምሮ እንቅስቃሴው ነበር። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ነውጥ ያስነሱ ነበር። ያ እንቅስቃሴ ግን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ብቻ የመነጨ አይመስለኝም። የውጭ ኃይሎች እጅ አለበት።
በተለይ የኢትዮጵያን ከፍታን ማየት የማይፈልጉ ኃይሎች እንዲሁም የምዕራባውያንም እጅ ይኖርበታል። ኢትዮጵያ አድጋ፤ ከፍ ብላ በምስራቅ አፍሪካ እንዳትታይ የሚደርጉ በተለይም የምዕራባውያን መጥፎ ምሳሌ ሆናለች ፤ ብለው በማመን ነው ጫና እያደረሱባት ያለው።
በእኔ እምነት ግን ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ ሃገራትም ሆነ ለጭቁን ህዝቦች መልካም ምሳሌ ሆነ የቀጠለች ሃገር መሆንዋን ነው። ኢትዮጵያን በማየት ነው ብዙዎቹ ነፃ የወጡት። ለአፍሪካ ነፃነት ተሟግታለች።
ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ዚምባብዌ ከእንግሊዝ ቀኝ ግዛት እንዲላቀቁ የእኛ ሃገር መንግሥታት ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። ለአፍሪካ አንድነት መጠናከርም ብዙ ሰርታለች። ግን ደግሞ ይህ እንዳይሆን የሚፈልጉ ምዕራባውያን ሃገራት አሉ።
እነሱ ጥቅማቸውን ብቻ ስለሆነ የሚፈልጉት ይህንን ለማስጠበቅ ሲሉ ብቻ በሃገራችን ውስጥ ገብተው እርስበርስ እንድንበጣበጥ ያደርጉናል። ለዚህ ደግሞ ተማሪዎችን መጠቀሚያ ያደርጋሉ። ትንሽ ገንዘብ ሰጥተው በመደለል ነውጥ እንዲነሳ ያደርጋሉ። እኔ በዘመኔም ያንን ነገር በግልፅ አይቻለሁ። ግን ይህንን ያክል በጣም የተስፋፋ አልነበረም።
በኋላ ደርግ የመደብ ትግል ብሎ ተማሪና ተማሪን ያጋጭ ጀመር፤ ከፊሉ ተማሪ ተራማጅ ሆነ፤ ሌላው ተቃዋሚ ሆነ። ህወሓት ደግሞ በዘመኑ ያንን የተማሪ እንቅስቃሴ በማክረር ሙሉ ለሙሉ የፖለቲካው መጠቀሚያ አደረገው።
አንጃ እንዲፈጠር ተማሪዎች በብሔርና በእምነት ሳይቀር ተከፋፍለው እንዲጣሉ ሲያደርግ ቆይተዋል። ባለፉት ዓመታት ተማሪዎች እርስበርሳቸው ጩቤ መማዘዝ እንደመፃፍ እንደመማዘዝ ቀላል ሆኖባቸዋል።
እስከመጋደል ደርሰዋል። ያኔ በተዘራው ልዩነት ምክንያት አሁንም ድረስ የትምህርት ተቋማት የፖለቲካ መሳሪያ ሆኗል። የትምህርት ስርዓት ከፖለቲካ ነፃ መሆን አለበት፤ ሰላማዊ መሆን አለበት። ሰላማዊና አመቺ ምህዳር የሌለው የትምህርት ተቋም መቼም ቢሆን ተልኮውን ሊያሳካ አይችልም።
ጥይት እየተተኮሰበት ፤ እርስ በርሱ እየተባላ ቀጣይነት ሊኖረው አይችልም፤ ትውልድንም ሊያሻገር አይችልም። መማር የሚቻለው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ነው።
መንግሥታት ደግሞ በተማሪው ላይ ካርታ መጫወት የለባቸውም።ስርዓተ ትምህርቱ አሳታፊ ይሆናል ይባላል ግን በተግባር እንዲውል አይፈለግም። ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ያጋጠመኝን ነገር ላጫውትሽ፤ እኔ በትምህርት ዓለም አርባምንጭ በነበርኩበት ጊዜ አርባ ምንጭ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠርቼ ሄድኩኝ።
ተማሪዎች በሁለት ተከፍለው እርስ በርስ በመጋጨታቸው፤ የውጭ መምህራን ሳይቀሩ ፈርተው ቢሮ ውስጥ መደበቃቸውን ሰማሁኝ። የቀበሌውና የወረዳው አመራሮች ቀስቃሽነት ብጥብጡ መጀመሩን ተረዳሁ። ተማሪ ትምህርቱን ትቶ ፖለቲካ ውስጥ እንዲገባና የነውጥ አካል እንዲሆን አድርገውት ነበር። ፈርተሽ ሃላፊነትን መሸሽ አትቺይም። ሃላፊነት በሸሸ ቁጥር ይከተልሻል።
የፖሊስ ኃይል በአካባቢው እንዲገኝ ጠየኩና ተማሪዎቹን ለማናገር ሄድን። እንደተባለውም ተማሪው ጠራራ ፀሐይ ሳይበገር ወጥቶ እየጮኸና መፈክር እያሰማ ነበር። ግራ እጃቸውን እያወጡ ‹‹ እየተማርን እንታገላለን፤ እየታገልን እንማራለን›› ይሉም ነበር። እኔን ሲያዩም ‹‹ በዥባዦች እና ፊውዳሎች ይውደሙ›› በማለት ጮሁ።
የሚገርመው ሽጉጥ የታጠቁ ተማሪዎች ሁሉ ነበሩ።በዚህ ምክንያት መምህራኑና ዳይሬክተሩ ሁሉ ተማሪዎችን ቀርበው ለማናገር ፈሩ። እኔ ግን ኃላፊነት ስለነበረብኝ ሰልፉ ላይ ታደምኩኝ። እነሱ የሚያነሷቸውን መፈክሮች እኔም ከእነሱ ጋር እያልኩኝ ድጋፌን አሳየኋቸው።
ይህንን ጊዜ ትኩረታቸው ተሳበ። ይህንን ያደረኩት መምህርና ዳይሬክተር ሆኜ ብዙ ስለሰራሁ የተማሪን ባህሪ ጠንቅቄ አውቃለሁ። ከእነሱ ጋር ተሰልፌ መፈክራቸውን ሳሰማ ግራ ተጋቡ። ትኩረትም ሲሰጡኝ ሃሳባቸውና ጥረታቸው ጥሩ እንደሆነ ነገርኳቸው። በተለይ እየተማርን እንታገላለን ያሉት ሃሳብ ጥሩና ወቅታዊ እንደሆነ ገለፅኩላቸው። ግን እንደሚሉት እየተማሩ ትግሉን እያካሄዱ አለመሆኑን ነገርኳቸው።
የምንከተለው ሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም ደግሞ በዲሲፕሊን የሚመራ ነው። አሁን እናንተ እየበጠበጣችሁ ነው እንጂ እየተማራችሁ አይደለም አልኳቸው። እነሱም ይህንን በምላቸው ጊዜ በረድ እያሉ መጡ።
ያን ጊዜ ተረጋግተው ችግራቸውን ያስረዱ ጀመር። ግን የሚያነሱት ጥያቄ ለነውጥ የሚያበቃ አልነበረም። ይሁንና በጥያቄአቸው መሰረት ያነሱትን ችግር ይዤ የትም ህርት ተቋሙን አመራሮችና መምህራን አነጋገርኳቸው። ችግሩን እንዲፈታ አደረኩኝ።
አዲስ ዘመን፡-ሌላው አሁን ያለው ትውልድ ሃገር ወዳድ ላለመሆኑ ታሪክ እንዳያውቅ መደረጉና ከትምህርት ስርዓቱ ጀምሮ ሀገር ጠል የሆነ ብልሹ አሰራር መዘርጋቱ እንደሆነ ይጠቀ ሳል። ይህ ምን ያህል አሳማኝ ነው ይላሉ?
አቶ ታምርአየሁ፡- እኔም ይህንን ሃሳብ ከሚደግፉ ሰዎች አንዱ ነኝ። የታሪክ ትምህርት ከትምህርት ስርዓቱ እንዲጠፋ በመደረጉ እጅግ ያሳዝነኛል። ታሪክ የሌለው ህዝብ፤ ሃገርም በዓለም ታይቶ አይታወቅም።
ለአንድ ህዝብ ታሪኩ ማንነቱን የሚገልፅበት፤ የወደፊቱን የሚቃኝበት እጅግ አስፈላጊ ሃብቱ ነው። መንግሥት በተለወጠ ቁጥር ኢትዮጵያ ውስጥ ስርዓተ ትምህርቱም ይለወጣል። መንግሥታቱ ይህንን የሚደርጉት እነሱን እንዲመስል ነው።
የንጉሱ ስርዓተ ትምህርት እኔ የተማርኩበት ነው፤ አሳታፊ ነበር፤ ዘር፤ ጎሳ፤ ሃይማኖት ልዩነት የሌለበት ነበር። ኢትዮጵያውያን ሁሉ አንድና ወጥ የዜጋ ትምህርት እንዲያገኙ ነበር የሚደረገው። ደርግ ደግሞ የመደብ ስርዓተ ትምህርት ያስፈልገናል አለ። ይህም በርዕዮተ ዓለም እና በቁሳዊ አመለካከት የተቃኘ ነበር።
‹‹ሁሉ ነገር ቁስ ነው፤ ፈጣሪ የለም›› እያለ ያስተምር ነበር። ይህ አስተምህሮ ጠባሳውን ጥሎ ነው የሄደው። እንደዚያም ሆኖ ታሪክ ግን አልጠፋም። ልክ እንዳሁኑ አልተሰደደም። ግን ደግሞ እድሜውን ሙሉ ጦርነት ውስጥ ነው ያሳለፈው፤ ማንኛው ነገር በጥይት የሚመለስ መስሎት ጥይት ሲያዘንብ ነው የኖረው። በእርግጥ ሃገር ወዳድ ነበር።
የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ ታግሏል። ሃገር ወዳድነቱ ታሪኩ ነው። በወቅቱ የኢትዮጵያን ህዝብ አንድ አድርጎ ከሱማሌ ወረራ ህዝቡን ታድጓል።
ህወሓትም ቢሆን ያደረገው ይህንኑ ነው። እንዳውም የሃገሪቱ ታሪክ እስከነአካቴው እንዲጠፋ በማለም የታሪክ ትምህርት ክፍልን ዘጋ። የኢትዮጵያ ታሪክ ውሸት ነው አለ። ዛሬም ኢትዮጵያ ታሪክ የላትም ለማለት የሚዳዳቸው አሉ። በመሰረቱ ታሪክ የሌለው ሰውም ሆነ ሃገር የለም።
የኢትዮጵያ ታሪክ እንዳውም የጎላ ነው። ብዙ ጊዜዋን ያሳለፈችው በጦርነት ነው። ከውጭና ከውስጥ ጠላቶቿን ተፋልማ አንድነቷን ያስጠበቀች ድንቅና ወርቃማ የድል ታሪክ ያላት ሃገር ናት። በቀደሙት መንግሥታት ግን ከህዝብ መዝሙር ሳይቀር ትወልዱ የሃገሩን ታሪክ እንዲያውቅና ሃገሩን እንዲወድ ተደርጎ የሚቀረፅበት ሁኔታ ነበር።
አርበኝነትን፤ የሃገርን ፍቅር የሚሰብኩ ነበሩ። መንግሥታት በተለዋወጡ ቁጥር የፈለገውን ፖለቲካ የሚጭንበት የኢትዮጵያ ህዝብ ከሚሸከመው በላይ ችግሩ እንዲከፋበት አድርገውታል።
በተለይ ህወሓት በጎሳ ከፋፍሎን እርስበርስ ሲያባላን መኖሩ አልበቃ ብሎ ሁሉም የራሱን ሃገር እንዲመሰርት የሚፈቅድ ህገ-መንግሥት ተክሎብን መሄዱ ሃገር ወዳድ ትውልድ እንዳይፈጠር፤ ሃገርም ህብረቷን አስጠብቃ እንዳትቆይ አድርጓታል ባይ ነው።
በመሆኑም አሁን ያለው መንግሥት በየቦታው የሚታየውን ግጭት ማስቆም የሚችለው ትውልዱ በትክክለኛው መስመር እንዲቀረፅ በማድረግ ብቻ ነው። ፓርቲዎቹና የትምህርት ተቋማትም ቢሆኑ ወጣቶች ትክክለኛውን የሃገራቸውን ታሪክ እንዲያውቁ የየራሳቸውን ጥረት ማድረግ መቻል አለባቸው።
የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል። ኃላፊነት የሚሰማቸውን ስነ-ምግባር ያለው ዜጋ እንዲፈጠር ወላጆችም ልጆቻቸውን ኮትኩተው ማሳደግ ይኖርባቸዋል። ፈሪሃ እግዚአብሄርን ማስተማር አለብን፤ ምክንያቱም ፈሪሃ እግዚአብሄር ያለው ትውልድ አያስቸግርም።
አዲስ ዘመን ፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ታምርአየሁ፡- እኔም እዚህ ድረስ መጥታችሁ ሃሳቤን እንድገልፅ እድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን መጋቢት 17 /2014