
ናይጄሪያ በ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ያስገነባችውን በአፍሪካ ትልቁን የማዳበሪያ ፋብሪካ በይፋ ስራ አስጀመረች።
የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃመድ ቡሃሪ በመክ ፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት በተፈጠረው የዋጋ ንረት የዓለም ማህበረሰብ ተፅዕኖ ውስጥ እንዳይወድቅ ናይጄሪያ በሰብል ማዳበሪያ አቅርቦት ረገድ የራሷን ሚና ትወጣለች ብለዋል፡፡
የንግድ ከተማ በሆነችው ሌጎስ የተገነባው የዳንጎቴ ማዳበሪያ ፋብሪካ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር አገሪቱ ወደ ውጭ በምትልከው የማዳበሪያ ምርት ከፍተኛ ገቢ ታገኛለች ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡
ፋብሪካው በዓመት 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሰብል ማዳበሪያ የማምረት አቅም እንዳለውም ነው የተናገሩት።
የናይጄሪያ ማዕከላዊ ባንክ ገዥ ጎድዊን ኢምፊሌ በበኩላቸው የፋብሪካው መከፈት የናይጄሪያን የማደበሪያ አቅርቦት ችግር በዘላቂነት እንደሚፈታ እምነታቸውን ገልጸዋል።
ግብርና ለናይጄሪያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሲሆን ሀገሪቱ በ2021 ከ173 ቢሊዮን ዶላር ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ውስጥ 25 ነጥብ 8 በመቶውን የግብርና ምርት ይሸፍናል።
ሆኖም የናይጄሪያ ገበሬዎች አልፎ አልፎ ማዳበሪያ እና የተሻሻሉ ችግኞች አቅርቦት ችግር ያጋጥማቸው እንደነበር አፍሪካ ኒውስ በዘገባው አመላክቷል፡፡
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 16 ቀን 2014 ዓ.ም