የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በሚያደርጉት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችን ያስገኛሉ። የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በማቃለል በኩልም የውጭ ባለሀብቶች የማይናቅ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።
በአገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ከሚገኙ የውጭ ባለሀብቶች መካከልም ጆይ ቴክ ፒ ኤ ል ሲ ፋርም አንዱ ነው። ድርጅቱ የዛሬ 19 ዓመት አካባቢ ኢትዮጵያ የውጭ ባለሀብቶች በአገር ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ የሚያስችላቸውን ምቹ ሁኔተ ተጠቅሞ የገባ ሲሆን፤ በሆርቲ ካልቸር ዘርፍ ተሰማርቶ አበባና አትክልቶችን ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ የጣልያን ድርጅት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ያላትን ተፈጥሯዊ ሀብት እንዲሁም በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመጠቀም አበባና አትክልቶችን በማልማት ለውጭ ገበያ እያቀረቡ መሆኑን የገለጹት የጆይ ቴክ ፒ ኤል ሲ ፋርም ማናጀር አቶ ብስራት ኃይለስላሴ ናቸው፡፡ እንደሳቸው ገለጻ፤ ድርጅቱ በሰለጠኑና ልምድ ባላቸው ሠራተኞች የሚተዳደር የእርሻ ሥራ ነው፡፡ ከ40 ዓመታት በላይ በካበተ ልምድ እየተመራ ያለው የእርሻ ሥራ ትኩስ ለምግብነት የሚያገለግሉ እፅዋት፣ የአበባ ልማትና ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ እፅዋትን በማዳቀል ይሰራል፡፡
በዋናነት በአበባ ምርት እንቅስቃሴ እያደረገ ያለው ድርጅቱ በሆርቲ ካልቸር ዘርፍ ለመሰማራት ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ በአገሪቱ ያለውን ምቹ የተፈጥሮ ሀብት መነሻ በማድረግ እንደሆነ ያነሱት አቶ ብስራት፤ በሰው ኃይልም ተጠቃሚ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ድርጅቱ ወደ ሥራ ሲገባም ቢሾፍቱ አካባቢ በ20 ሄክታር መሬት ሲሆን በቀዳሚነት የፅጌረዳ አበባን በማምረት ለአውሮፓ ገበያ ይልክ ነበር።
ከአበባ ምርት በተጨማሪም ትኩረቱን ዕፀ ጣዕም በሚባሉ በኢትዮጵያ በተለምዶ በቅመምነት በሚያገለግሉ ምርቶች ላይ በማድረግ 80 ሄክታር መሬት ተጨማሪ በማድረግ በ100 ሄክታር መሬት ላይ የእርሻ ሥራውን ቀጥሏል። በአሁኑ ወቅትም የእርሻ ሥራውን ለማስፋፋት ቢሾፍቱ ከሚገኘው በተጨማሪ ለገዳዲ ለገጣፎ አካባቢ 20 ሄክታር የማምረቻ ቦታ ተረክቦ በቅርቡ ሥራውን ለመጀመር በዝግጅት ላይ ይገኛል ያሉት አቶ ብስራት፤ ሥራውን በማስፋፋት ተጨማሪ አትክልትና የእፀ ጣዕም ምርቶችን ለውጭ ገበያ እያቀረበ የሚገኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
ድርጅቱ ምርቶቹን ወደ ውጭ ገበያ ከመላክ ባሻገር በተመሰሳይ በአትክልት የማመረት ሥራ ላይ ለተሰማሩ ገበሬዎች ችግኝ አፍልቶ የሚያቀርብ ሲሆን ለአገልግሎቱ የሚጠይቀው ክፍያም ተመጣጣኝ ነው። ከ18 አይነት በላይ የተለያዩ ትኩስ አትክልቶችንና የእፀ ጣዕም ዝርያዎችን የሚያመርተው ድርጅት ሦስት የተለያዩ የንግድ ዘርፎችን በመከተል የተቆረጡ ጽጌረዳዎችን እና የበጋ አበቦችን ለውጭ ገበያ መላክ፤ እንዲሁም ተክሎች እና ችግኞችን የማራባት ሥራን ይሰራል።
የሥራ ዕድልን አስመልክቶም 1500 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ሲሆን፤ 70 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። 50 በመቶ የሚጠጉትም የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ናቸው፡፡ የተማሩ ሰዎች ቁጥር በድርጅቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሲሆን ከፍተኛ ትምህርት ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን አዋጭ የሥራ እድሎችን መፍጠር የሚያስችል እንደሆነ ያነሱት አቶ ብስራት፤ የሥራ እድሎችን አስተማማኝ ለማድረግ ግለሰቦች በተለያዩ ስፖንሰር በሚደረጉ የሥልጠና፣ የማስተማርና ትምህርታዊ ፕሮግራሞችን ተጠቅመው ሙያቸውን እንዲያሻሽሉ የመደገፍ ሥራም ይሰራል ብለዋል።
ድርጅቱ ወደ ሥራ ሲገባ 16 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር መነሻ ካፒታል የነበረው ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከሶስት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማፍራት ችሏል። አብዛኛው ምርቶች ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ እንደመሆናቸው በዓመት ከ12 እስከ 15 ሚሊዮን ዶላር በማስገባት በአገሪቱ ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለማቃለል የድርሻውን እየተወጣ የሚገኝ ድርጅት ነው።
ከአበባና ከአትክልት በተጨማሪ እፀ ጣዕምን አንዱ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ መንገድ አድርጎ እየተጠቀመበት ሲሆን በአገር ውስጥ በአብዛኛው የእፀ ጣዕም ምርት በምግባችን ውስጥ እጅግ በጣም በትንሽ መጠን አገልግሎት ላይ የሚውሉ ናቸው። ከእነዚህም መካከል እንደ ናና፤ ሮዝመሪ፤ ጠጅ ሳርና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ እነዚህ በአነስተኛ መጠን አግልግሎት ላይ የሚውሉና አንዳንዶች ለጤና ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጡ የአትክልት አይነቶች የመድሃኒትነት ባህሪ ያላቸው በመሆኑ ለካንሰር፤ ለኩላሊት፤ ለራስ ምታት ማስታገሻ የሚሸተቱና በእንፋሎታቸው የሚያድኑ መሆናቸውን አቶ ብስራት አስረድተዋል።
አያይዘውም ምርቶቹ በአብዛኛው በአገሪቱ የተለመዱ ባይሆኑም ኤክስፖርት ከማድረግ በሻገር እነዚህን ለመድሃኒትነትና ለምግብ ማጣፈጫነት እንዲውሉና ማሕበረሰቡ እንዲለምዳቸው የማድረግ ሥራም ይሰራል። በተለይም በሬስቶራንቶች፣ በሆቴሎችና አጠቃላይ ከምግብ ሥራዎች ጋር ተያያዥ በሆኑ ዘርፎች የማለማመድ ሥራ እየተሰራ ይገኛል። በመሆኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ ፍላጎቱ እየጨመረ ነው፡፡ ይህም የአገር ኢኮኖሚን ከማሳዳግ አንፃር በውጭ ንግዱ ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል።
በአትክልቱ ዘርፍም እንደ ኩከንበርግ፣ ቼሪ ቶማቶ፣ ከተለመደው የቲማቲም አይነት የተለየ ደቃቅ ቲማቲም፤ ሰላጣ፤ ጣፋጭ ቃሪያና ተያያዥ የሆኑ የአትክልት አይነቶች የድርጅቱን የአመራረት መንገድ ተከትሎ በግሪን ሀውስ ውስጥ በመሳደግ ወደ ውጭ ኤክስፖርት እየተደረገ ይገኛል።
ምርቱ ጣዕም ያለው፤ ትኩስና ጣፋጭ እንዲሆን ለማድረግ ተከታታይነት ያለው ተክሎችን የመንከባከብ ሥርዓትን ይከተላል፡፡ የጠብታ መስኖን፣ የአየር ንብረት ቁጥጥርን፣ ማቀዝቀዣንና ተከታታይነት ያለው የላቀ የምግብ ደህንነት ልምዶችን በመከተል ጤናማና ትኩስ አትክልቶችን ተጠቃሚው ጋር ለማድረስ እየተጋ ያለ ተቋም ነው እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ብስራት፤ የተመረቱትን ምርቶች በማሸግ እና በማጓጓዝ ሂደትም አንድም ስህተት እንዳይፈጠር ክትትል ይደረጋል፡፡ ይህም የደንበኞችን ተአማኒነት አስጠብቆ ለማቆየት ጠቅሞናል ብለዋል። ከሚወሰዱ ጥንቃቄዎች መካከልም የግሪን ሃውስ ቤቶች፣ በጥንቃቄ የመደርደር እና የማሸግ ሥራ፣ የመጓጓዣ ተሽከርካሪዎችና አጠቃላይ ለዚህ ሥራ የተመረጡት በሙሉ ዘመናዊ ሥርዓትን የተከተሉ መሆናቸው ተጠቃሽ ነው።
ድርጅቱ በባህላዊ መንገድ አፈር ላይ ከሚያከናውነው የእርሻ ሥራ በተጨማሪ የላቁ የሃይድሮፖኒክ የማምረት ሥርዓቶችን ይከተላል፡፡ ይህም ማለት (ከአፈር ነፃ በሆነ ዘዴ ተክሎችን ውሃ ላይ በመትከል የማዕድን ንጥረ ነገሮችን የሚወስዱበት ሥርዓት ነው) ግሪን ሃውስ ውስጥ ፀረ-ተባይ መድሃኒቶች በቀጥታ ተክሎች ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት መቀነስ፤ ለፈጣን እድገት ለውሃ ቁጠባ አውቶማቲክ መስኖ መጠቀም፤ እና ጥሩ የእድገት ሁኔታዎችን ለማረጋገጥ የአየር ንብረት ቁጥጥር ሥርዓቶች ላይ አተኩሮ ከሚሰራባቸው ስራዎች መካከል የሚጠቀሱ እንደሆነ አቶ ብስራት ይናገራሉ።
ምርቶቹ ከተሰበሰቡበት ጊዜ ጀምሮም እንዲሁ በሁሉም የማከማቻ፣ የማሸጊያና የማከፋፈያ ሥራዎች ዙሪያ ጥብቅ የሆነ የቀዝቃዛ ሰንሰለት ተዘርግቷል። ይህም ማለት ተመሳሳይ የሆኑ የሙቀት መጠኖች ከማሳ አንስቶ እስከ መጨረሻው መዳረሻ በሚተላለፉበት ደረጃዎች ውስጥ እንዲቆዩ እና እንዳይቆራረጡ የማድረግ ተግባርን ይከተላል። በየእለቱ ትኩስ ዕፅዋትን እንዲሁም አበባዎችን ወደ መዳረሻቸው ለማጓጓዝ ዘመናዊ ማቀዝቀዣ ያላቸው መኪናዎችን በመጠቀም ቀዝቃዛ የጭነት መኪናዎቹ (በ2⁰ ሴልሺየስ የሚቆዩ) በትራንስፖርት ሂደት ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ይጠበቃሉ።
ዋነኛ የገበያ መዳረሻዎቹ በሆኑት በአውሮፓ ጀርመን፣ ኔዘር ላንድ፣ ኖርዌይ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጃፓን፣ ሲንጋፖር፣ ሩሲያ እና መካከለኛው ምስራቅ ምርቶቹን ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በየዕለቱ እየላከ የሚገኝ ሲሆን የገበያው መዳረሻ በሆኑ አገራትም የበረራ ሰአት ማጠሩ ምርቶች ሳይበላሹ በፍጥነት መድረስ እንዲችሉ አድርጓል፡፡
ድርጅቱ የአውሮፓ ምግብ-ደህንነት ደረጃዎችን ጠብቆ የሚያመርታቸውን ባሲል፣ ቺብስ፣ ሚንት፣ ታራጎን እና ሌሎች ምርቶችንም በተለያዩ የኤክስፖርት ክልሎች ለሚገኙ ምርት ተቀባዮች፣ አሻጊዎችና ጅምላ አከፋፋዮች ጋር እንዲደርስ ባልተቋረጠ ክትትል ይሰራል።
‹‹በዘርፉ ከሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች መካከል አገሪቱ ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ይህም ማለት ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያለች አገር እንደመሆኗ የምግብ ዋስትናዋን ሳታረጋግጥ እንዴት ምግብ ነክ ምርት አምርታ በውጭ ገበያ ተወዳዳሪ ሆና ትቆያለች የሚለው ከባድ ፈተና ነው›› የሚሉት አቶ ብስራት፤ ጠግቦ መብላት ያልቻለ ማህበረሰብ ባለበት እንዴት ምግብ አምርቶ ለውጭ ገበያ ያቀርባል የሚል ሙግት መኖሩን እና ቀጣይነት ያለው ስለመሆኑም የሚጠራጠሩ ስለመኖራቸው በማንሳት ይህን ማሳመን እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነም ያስረዳሉ።
ያደጉት አገሮች የምግብ ደህንነት ሥርዓት በአግባቡ መሟላቱን ማረጋገጥ የሚፈልጉ በመሆኑ የኦዲት ስታንዳርድና ሰርተፊኬሽን በመያዝ የብቃት ማረጋገጫ ለመያዝ ያልተቋረጠ ሥራ ይሰራል። በዋናነት ከአመራረት ሁኔታ ከሰው ሃይል አያያዝ ከአካባቢ አጠባበቅ ጋር ተያይዞ ከውጭ የመጡ ባለሙያዎች ማረጋገጫ ይሰጣሉ።
አሁን መንግሥት እየተከተላቸው ያለው ፖሊሲ በተለይም በብሄራዊ ባንክ በኩል የወጣው መመሪያ ሊታይ ይገባል የሚሉት አቶ ብስራት ይህ ሲባል ድርጅቱ ሰርቶ ያመጣውን የውጭ ምንዛሪ መንግሥት 70 በመቶውን ዶላር ለብሄራዊ ባንክ 10 በመቶው ለአገር ውስጥ ሥራዎች በወረፋ የሚሰጥ በመሆኑ 20 በመቶው ለድርጅቱ መጠቀሚያ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ በመሆኑም ዘርፉ የሚጠቀማቸውን ግብአቶች ከውጭ እንደማስገባቱ በሚፈልገው መጠን ለማግኘት አለመቻሉ ለሥራው ማነቆ ከሆኑ ችግሮች አንዱ ነው ስለሆነም ዘርፉን በስፋት ተደራሽ ካለማድረግ በተጨማሪ በውጭ ምንዛሪ ዕድገት ላይም ተጽዕኖ ያሳድራል ብለዋል።
እንደ ማንኛውም ኢንቨስትመንት ድርጅቱ የኃይል አቅርቦት ችግርም እየገጠመው ሲሆን የማስፋፊያ ቦታዎችን የማግኘት ችግር መኖሩንም አቶ ብስራት ጠቅሰዋል፡፡ በተለይም ለሥራው የሚሆኑ ግብአቶች በግብርና ሚኒስቴር በኩል የሚገቡት በተለያዩ ቢሮክራሲዎች በመሆኑ መጓተት፤ የአይር ካርጎ መወደድ፤ የቅዝቃዜ ሰንሰለትን ጠብቆ በሚደረግ ጥረት ላይ በካርጎ ላይ የተለያዩ ችግሮች ምርት የሚበላሽበት ሁኔታ ደግሞ ደንበኝነትን ጠብቆ ለማቆየት አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።
በመጨረሻም ግብርና እየዘመነ የመጣ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ብስራት፤ ይህን ዘመናዊነት በመጠቀም የዓለም ገበያን ለመቆጣጠር ከመስራትም ባሻገር በዘመናዊ ግብርና የአገር ውስጥ ፍላጎትን ለማሟላት መሰራት አለበት። ምርት በሜትር እስኩዌር ባለ ቦታ ላይ ወደ ጎን ከመለጠጥ በአጭር ቦታ ብዙ ምርት የሚያመረቱበት ቴክኖሎጂ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት እውቀቱም በአገር ውስጥ እንዲቀር ታስቦ መሠራት ይኖርበታል በማለት ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።
አሥመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም