የ 2014 ዓ.ምን ከተቀበልን ስድስት ወራቶች አሳልፈናል። ወደ ክረምቱ እየተቃረብን ነው። ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከዛም እስከ መንደር ድረስ ዘልቆ የሚከናወነውና ከልጅ እስከ አዋቂ የሚያሳተፍበት አረንጓዴ አሻራን የማሳረፍ መርሐ ግብር አራተኛው ዙር ላይ ደርሷል። በመሆኑም ይህ ወቅት በብዙዎች የሚጠበቅ ሆኗል።
ሁሉም በአካባቢው የዛፍ ተክል ችግኞችንና የተለያዩ እጽዋቶችን ወቅቱን ጠብቆ የመትከል ባህል እንዲያዳብር መንገድ ከፍቷል። ተነሳሽነቱን ወስደው በአረንጓዴ አሻራ የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሐግብርን ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ አራተኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ መርሐግብር መድረሱን ከሰሞኑ አስታውሰውናል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር እንቅስቃሴ የአራት ዓመቱን ዕቅድ ለማሳካት ብቻ መሆን የለበትም ብለዋል። ታሪከ የሚለውጥ ውጤት የሚያስገኝ ሥራ መሥራት እንዳለበትም ነው በመልዕክታቸው ያስተላለፉት።
ለአራተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ከወዲሁ የዛፍ ችግኞች የማፍላት ሥራ ዝግጅት መጀመሩንም አብስረዋል።
አረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የደን ሽፋን እንዲጨምር ብቻ ሳይሆን፣በምግብ እህል እራስን ለመቻል እንደአገር እየተከናወነ ያለውን እንቅስቃሴ ጭምር የሚደግፍ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይም ትኩረት ያደረገ መሆኑ አይዘነጋም። አገራዊ ንቅናቄ ተፈጥሮ በሶስት ዙሮች በተካሄደው እንቅስቃሴ የተለያዩ ክፍተቶች ቢያጋጥሙም መልካም የሆኑ ተሞክሮች መገኘታቸው በተለያየ ጊዜ ተወስቷል።
ክፍተቶችን በማረም፣ጠንካራ ጎኑንም አጠናክሮ በመቀጠል አሁን ላይ መድረስ መቻሉም እንደስኬት ይቆጠራል። እየተቃረበ ላለው የአራተኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ቅድመ ዝግጅትና በሶስቱ ዙሮች በተከናወነው ሥራ የተገኘው ለውጥ በተለይም በደን ሽፋን፣ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ ስላበረከተው አስተዋጽኦ፣ የደን ልማቱ ኢኮኖሚው ላይ አበርክቶ እንዲኖረው ከማድረግ አንጻር የተሰጠውን ትኩረት፣ በተለይ ደግሞ በደን ልማቱ ላይ የሚሳተፈው ማኅበረሰብ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተከናወነ ስላለው ተግባርና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሲዳማ ክልል የአካባቢ፣ የደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ከአቶ ሽታዬ ይሙራ ጋር ቆይታ አድርገናል።
እንደ አቶ ሽታዬ ማብራሪያ በተያዘው በጀት ዓመት ክልሉ ለአረንጓዴ አሻራ የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ቅድመ ዝግጅት አድርጓል። በቅድመ ዝግጅት ሥራም በሶስት ተከታታይ ዓመታት የተከናወኑትን የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብሮች መነሻ በማድረግ ውጤቱንና ክፍተቱ ላይ ከከተማና ከወረዳ አስተዳደሮች ጋር ግምገማ ተደርጓል።
በያዝነው ክረምት ደግሞ ስለሚተከለው የችግኝ መጠንና ተከላ የሚከናወንባቸውን ስፍራዎች በተመለከተ እንዲሁ ምክክር ተካሂዷል። በዚሁ መሠረት ወደ ሶስት መቶ ሚሊየን ችግኝ ለማፍላት በዕቅድ ተይዟል።
ክልሉ ሁለት አቅጣጫዎችን በመያዝ ነው መርሐ ግብሩን ለማከናወን ዝግጅት ያደረገው። አንዱ አቅጣጫ የደን ልማት ሲሆን፣የደን ሽፋኑን ሊያሳድግ የሚችል የዛፍ ችግኝ ነው የሚዘጋጀው። ሁለተኛው አቅጣጫ የምግብ ዋስትናን ሊያረጋግጡ የሚችሉ (አግሮፎረስትሪ) የልማት ሥራ ጋር የተያያዙ ችግኞችን ታሳቢ ያደረገ አቅጣጫ ነው። በዚህ አቅጣጫ ዘር የማዘጋጀቱ ሥራ ተጀምሯል።
ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችሉ ተግባራት ቀድመው መጀመራቸው ዕቅዱን ለመፈጸም ስለሚያስችሉ ዕቅዱ ይተገበራል የሚል ተስፋ አላቸው። ለደንና ለምግብ ዋስትና እንዲውሉ ተለይተው እንዲዘጋጁ በዕቅድ ተይዞ እየተከናወነ ስላለው ተግባር ዋና ዳይሬክተሩ እንዳስረዱት፤በምግብ ዋስትና መርሐ ግብር ውስጥ ከተካተቱት የልማት ሥራዎች አንዱ በአትክልትና ፍራፍሬ የአቮካዶ፣ፓፓያ ልማት ሲሆን፣የአቮካዶ ልማቱ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል።
ክልሉ የአቮካዶ ልማት ሥራውን ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ እያከናወነ ይገኛል ። ከደን ልማት አንጻር የሚከናወነው ልማት ደግሞ በቆላማው የክልሉ አካባቢ በሚገኙ የተጎዱ አካባቢዎች ላይ ሲሆን አፈርና ውሃን ሊጠብቁና መልሶ እንዲያገግም ለማድረግ የሚያስችሉ ችግኞች ናቸው የሚዘጋጁት።
የችግኝ ዝርያዎቹም የተጎዳውን መሬት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያገግም የሚያስችሉ እንዲሆኑ የታሰቡ ናቸው። በአጠቃላይ ለአረንጓዴ አሻራ የሚዘጋጁት የዛፍ ችግኞች 70 በመቶ ያህሉ አገር በቀል እንዲሆኑ ነው ትኩረት የተሰጠው።
ክልሉ በቡና ተክል የሚታወቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም አገር በቀል የዛፍ ችግኞች ይመረጣሉ። ለቡና ጥላ ተብሎ የሚተከሉ እንደ ብርብራ፣ ዋንዛ የመሳሰሉ ዛፎች እግረ መንገድ ለደን ልማቱ አጋዥ ሆነው ጥቅም ይሰጣሉ። ክልሉ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልና ከቻይና ሀገር ባስመጣው የቆላ ቀርከሃ ችግኝ ልማት በቆላማ አካባቢዎች በቅርቡ የተጀመረውን ልማት አጠናክሮ ይቀጥላል።
የችግኝ ዝግጅት ሥራው በአርሶ አደር፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ እንዲሁም በግለሰቦች በመሆኑ ከዚህ አንጻር በማፍላቱ ሥራ ላይ ስላለው ጥንቃቄ ዋና ዳይሬክተሩ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ፤ በተለይ አርሶ አደሩ የደን ፀባይ ያላቸውን ችግኞች በማዘጋጀትም ሆነ ተክሎ በመንከባከብ ተሞክሮ ስላለውና በማኅበርም ተደራጅቶ የመሥራት ባህል በማዳበሩ ስጋቱ ከፍተኛ አይደለም። ሆኖም ግን ብክነትን ለመቀነስና የተሻለ ጥራት ለማምጣት በባለሙያዎች ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅ ቢሮውም በመገንዘቡ እየሠራ ይገኛል።
የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ የደን ሽፋንን በመጨመር የአካባቢ ሥነምህዳር እንዲጠበቅ ማድረግ ቢሆንም ከተሞችም ውብና ጽዱ እንዲሆኑ ስለሚያስፈልግ ከተሞችን ታሳቢ ተደርገው ልማቱ እንደሚከናወን ገልጸዋል። ከዚህ አንጻር ሀዋሳና የተለያዩ አካባቢዎችን በአረንጓዴ ልማት ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። በከተሞች የአረንጓዴ ልማቱን የሚረብሹ ደረቅ እና ፍሳሽ ቆሻሻን ማስወገድ ይገባል። የከተማ አስተዳደሮች በዚህ ላይ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
በሶስት ዙር በተካሄደ የአረንጓዴ አሻራ የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ክልሉ በስፋት ቢንቀሳቀስም ነባር የሆነ ደን እንዳለው የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ ለአብነትም ሲዳማ ውስጥ በሕዝብ ተጠብቆ የቆየ ደን እንደሚገኝና ደኑን ለመጎብኘትም ከተለያዩ አካባቢዎች ሰዎች ወደስፍራው እንደሚሄዱ ነው ያስረዱት። ከሶስት አመት በፊት በአገር ደረጃ በሕዝብ ንቅናቄ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በነበረው ላይ ተጨማሪ ስለሚሆን ይበረታታል ብለዋል።
እንዲህ ባለው መርሐ ግብር እየተከናወነ ያለው ሥራ ለአካባቢ ሥነምህዳር መጠበቅ ትልቅ ዋጋ ያለው፣ለምርትና ምርታማነትም ማደግ ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑ ይታወቃል። የሕዝብ ንቅናቄ በመፍጠር የሚሠራው ሥራ መልሶ ለሕዝብ ጥቅም መዋል እንዳለበትም ተደጋግሞ ይነሳል። ይህ ካልሆነ በዘመቻ የተተከለው የዛፍ ችግኝ ተገቢውን እንክብካቤ አያገኝም። ደን ከሆነ ለሕገወጥ ጭፍጨፋ ይጋለጣል።
ይህን ሁሉ ለመከላከል ደግሞ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቃል። ክልሉ ይህን ታሳቢ አድርጎ ከመሥራት አንጻር ስላለው ጥረት አቶ ሽታው ሲያስረዱ፤አካባቢው ቡና አምራች በመሆኑ ዛፍና ቡና አይነጣጠሉም።
በመሆኑም በቡና ልማት አርሶአደሩ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ነው። የማር ልማቱም ከእጽዋት ጋር ተያያዥ በመሆኑ በዚህ ረገድም ከማር ምርት ገቢ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል ። ይርጋለም ላይ ማር አቀነባብሮ የሚያቀርብ ፋብሪካ በመቋቋሙ አርሶ አደሩ ምርቱን ያቀርባል።
ለኢንዱስትሪ ግብዓት በማዋል ረገድም በአካባቢው ለሚገኘው የችፑድ ፋብሪካ ግብአት በማቅረብም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተጠቃሚነት አለ።
ይሁን እንጂ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ በመሥራት የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚጠበቅና በዚህ ላይም መሥራት እንዳለባቸው ኃላፊው ያምናሉ ።
ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በማሳደግ የእኔነት ስሜትን እያጎለበቱ መሄድ ካልተቻለ በአንድ በኩል ልማቱ ቢከናወንም ጥፋት መኖሩ አይቅርምና በተለይም የደን መጨፍጨፍን ለመከላከል በክልሉ በኩል ስላለው ዝግጁነት አቶ ሽታዬ እንደገለጹት፤ችግሩ የለም ለማለት ባያስደፍርም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በአካባቢው አሮሬሳ፣ ጭሪ በሚባሉ አካባቢዎች የደን ጭፍጨፋ ይካሄዳል። መሻሻሎች ግን አሉ።
ችግሩን በኃይል ማስቀረትም ሆነ በማስጠበቅ ማስወገድ ስለማይቻል ማኅበረሰቡ ሀብቱ የራሱ እንደሆነ አውቆ እንዲጠብቀው ተከታታይ የሆነ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ይጠበቃል።
ባለፉት ሶስት ዙሮች በሕዝብ ንቅናቄ በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርና ቀደም ሲል የነበረውም ሥራ ታክሎበት በአካባቢው የደን ሽፋን መጨመርና በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እድገት ላይ ስላበረከተው አስተዋጽኦ አቶ ሽታዬ ላቀርብኩላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤በባለሙያዎች በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት በተወሰደ ናሙና በ2012 ዓ.ም የተተከሉት ችግኞች የጽድቀት መጠናቸው ወደ 79፣ በ2013 ደግሞ ወደ 82 ነጥብ 5 ሲሆን የደን ሽፋኑም ከአካባቢው የቡና ልማት ጋር ተያይዞ ነው መረጃው የሚቀርበው። በዚሁ መሰረት የክልሉ የደን ሽፋን ከ 19 ነጥብ ሶስት ወደ 23 ነጥብ አራት በመቶ መድረሱን ከወንዶገነት ኮሌጅ ጋር በተደረገ የጋራ ግምገማ ማረጋገጥ ተችሏል።
በሳተላይት የመረጃ አያያዝ ዘዴ ቢታገዝ አሁን ካለው በላይ ሽፋኑ ከፍ እንደሚል ይገመታል። በፌዴራል ደረጃ ከሚመለከተው አካል ጋር ለመሥራት በዕቅድ ተይዟል። ምርትና ምርታማነትን ከፍ ከማድረግ ጋር ተያይዞ ለተነሳው፤ የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ግቡም ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ማስቻል ነው።
በክልሉ ቦርቻና ሎካ በሚባሉ ቆላማ አካባቢዎች በተለያየ ምክንያቶች ለምነቱን ያጣ የተጎዳ መሬት ነበር። በተከናወነው የአረንጓዴ ልማት ሥራ መሬቱ መልሶ ሊያገግምና ለምርታማነት ሊበቃ ችሏል። አካባቢው ላይ የሚለማው ቡና ከማዳበሪያ የፀዳ የተፈጥሮ ቡና ነው። ለቡና ጥላ ተስማሚ የሆኑ እንደ ዋንዛና ብርብራ የመሳሰሉ አገር በቀል የዛፍ ችግኞች በመተከላቸው የቡና ምርታማነት እንዲጨምር አግዟል።
እንስሳትና ቦሎቄም በተመሳሳይ በስፋት መልማቱ አንድ ለውጥና ዕድገት ነው። አረንጓዴ ልማቱ ሲጠናከር ግብርናው ከዚህም በላይ ከፍ ብሎ ምርትና ምርታማነት ይጨምራል። በአጠቃላይ ተስፋ ሰጭ የሆነ ነገር መኖሩን ካለው ነባራዊ ሁኔታ መገንዘብ ይቻላል።
ለሶስት ተከታታይ የክረምት ወቅቶች በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተገኙ ተሞክሮዎችና ክፍተቶች ምን እንደነበሩ፣ክፍተቶችን አርሞ ጠንካራውን አጠናክሮ ለመቀጠል ስላለው ዝግጁነትም አቶ ሽታዬ እንዳስረዱት፤ጠንካራ ለሚባለው ለመነሳት ቀደም ሲል በነበረው የመንግሥት አስተዳደር በ2002 ዓ.ም ላይ የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴ ቢኖርም ተከታታይነት ያለው ሥራ ባለመሠራቱ ውጤቱም አጥጋቢ አልነበርም።
የመንግሥት ለውጥ ከተደረገ ወዲህ ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በወሰዱት ተነሳሽነት ሳይቆራረጥ አጀንዳ ተደርጎ ተይዞ በአንድ ጊዜም በሚሊየን የሚቆጠር የዛፍ ችግኝ በመትከልና እያንዳንዱ የማኅበረሰብ ክፍልም ስለተከለው ችግኝ ተጨንቆ እንክብካቤ ሲያደርግ ማየት በራሱ ውጤት ነው። መስተካከል አለበት ተብሎ እንደክፍተት የሚወሰደው ደግሞ ሀብቱ የጋራ መሆኑን ከማሰብ ይልቅ የባለቤትነት ጥያቄ ማንሳት፣መንግሥት ይወስደዋል የሚል ስጋት መኖር ይስተዋላል።
እንዲህ ያሉ ስጋቶችን ለማስወገድ ወረዳዎች ከአርሶአደሩ ጋር የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት ክፍተቱን እንዲያስተካክሉ፣በክልል ደረጃም በመከታተል እየተሠራ ይገኛል። ሲዳማ ክልል ከተማን ጨምሮ በ37 ወረዳና በ514 ቀበሌዎች የተዋቀረች ሲሆን፣የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም በነዚህ ሁሉ አካባቢዎች ነው በመከናወን ላይ የሚገኘው።
በአገር አቀፍ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለአራት ተከታታይ ዓመታት ለማከናወን የታቀደው ኢትዮጵያን በደን የመሸፈን ዓላማን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን፣እስካሁን በተከናወነው የአረንጓዴ ልማት ሥራም አበረታች ውጤት መገኘቱን፣በተከናወነው ሳይንሳዊ የሳተላይት ቆጠራ 15ነጥብ5 በመቶ የነበረው የአገሪቱ የደን ሽፋን ወደ 17ነጥብ ሁለት በመቶ ከፍ ማለቱን፣እኤአ በ2030 ዘላቂ የልማት ግብ ደግሞ የኢትዮጵያን የደን ሽፋን 30 በመቶ ለማድረስ ግብ ተቀምጦ እየተሠራ እንደሆነና በአራት አመቱ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐግብርም 20ቢሊየን ችግኞች በመትከል የልማት ግብ ዕቅዱን ለመሳካት ታቅዶ እየተሠራ እንደሆነና የደን ልማት ሥራው የአጠቃላይ አገራዊ ስትራተጄካዊ ግብ አካል በመሆኑ በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን ባለፈው ዓመት አካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽንን ዋቢ አድርገን ለንባብ ማብቃታችን ይታወሳል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 /2014