ሌላኛው በዚህ ሳምንት ልናስታውሰው የሚገባ ጉዳይ በአገራችን የመጀመሪያ የሆነው የስኳር ፋብሪካ ነው። በኢትዮጵያ የስኳር ኢንዱስትሪ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያ የሆነውና በሆላንዱ ኤች.ቪ.ኤ ኩባንያ የተገነባው ይህ ፋብሪካ የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ይባላል። ፋብሪካው ከ68 ዓመታት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን መጋቢት 11 ቀን 1946 ዓ.ም በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ተመርቆ ሥራ ጀምሯል። በአገራችን የስኳር ኢንዱስትሪም ፈር ቀዳጁ በመሆን ይታወቃል።
ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በ2006 ዓ.ም ከሰራው ዘገባ ባገኘነው ሰነድ፤ በወቅቱ ፋብሪካው በቀን 3 ሺህ 500 ኩንታል አገዳ የመፍጨት አቅም ነበረው። በዚሁ ዓመት ብቻ 2 ሺህ 261 ቶን ስኳር ለማምረት በቃ። ካፒታሉም ከ17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ደረሰ። ፋብሪካው በወቅቱ ሦስት ሺህ ያህል ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞችም እንደነበሩት ድርሳናት ያወሳሉ።
‹‹በኢትዮጵያ የተሰራ›› የሚል ጽሑፍ ያለበት ስኳር የያዘ ጆንያ በመላ አገሪቱ ለእይታ የበቃውም በዚያን ወቅት ነበር። ኤች.ቪ.ኤ ኔዘርላንድስ የኢትዮጵያ ዕድገት ተምሳሌት ሆኖም ተወስዷል። በሠራተኞች ቅጥር ብዛትና በመንግሥት ግብር ክፍያ በወቅቱ ትልቁን ሥፍራ ይዞ ቆይቷል።
ፋብሪካው ሥራውን ከጀመረ አምስት ዓመታት በኋላም ሸንኮራ የመፍጨት አቅሙን በእጥፍ ማሳደግ ችሏል። በ1953 ዓ.ም ደግሞ የወንጂ ከረሜላ ፋብሪካ ተቋቋመ። ‹‹ደስታ›› የተባለ ከረሜላም መመረት ጀመረ። በዚህም ጣፋጭን ለሕብረተሰቡ ማስተዋወቅ ተቻለ። የአገሪቱ የስኳር ፍላጎትም እየጨመረ መጣ። ይህንኑ መነሻ በማድረግ ሁለተኛው የሸዋ ስኳር ፋብሪካም ህዳር 2 ቀን 1955 ዓ.ም በአፄ ኃይለስላሴ ተመረቀ።
በ1962 ዓ.ም ደግሞ ‹‹ኤች.ቪ.ኤ መተሐራ›› በሚል ስያሜ ሦስተኛው የስኳር ፋብሪካ በተመሳሳይ ሁኔታ ሥራ ጀመረ። በ16 ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ሦስት የስኳር ፋብሪካዎች ተቋቋሙ ማለት ነው።
የኤች.ቪ.ኤ ኔዘርላንድስ የኢትዮጵያ ቆይታ በደርግ ወደ ሥልጣን መምጣት አበቃ። ደርግ መሬትና የግል ሀብትን በአዋጅ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ሲያውል ፋብሪካዎቹንም መንግሥት ወረሰ። ይህን ተከትሎም ኤች.ቪ.ኤ ኔዘርላንድስ ኩባንያ ከኢትዮጵያ ወጣ።
በእነዚህና በሌሎች መልኩ ስኳር ፋብሪካዎቹ በተለያዩ አደረጃጀቶች አወቃቀሮች ሲተዳደሩ ከቆዩ በኋላ፤ የኢፌዴሪ መንግሥት በቀየሰው የትኩረት አቅጣጫ መሠረት የዘርፉን የልማት እንቅስቃሴ ለመምራትና ለማስፈጸም ስኳር ኮርፖሬሽን ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ኃላፊነቱን ወስዶ እንዲሰራ ተደረገ።
የስኳር ፋብሪካዎችን የማስፋፋትና አዳዲስ ፋብሪካዎችን የመገንባት ሥራ ውስጥ ተገባ። በአሁኑ ወቅትም በአገሪቱ በርካታ የስኳር ፋብሪካዎች ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል። ነባሮቹም ፋብሪካዎች ማስፋፊያ ተደርጎላቸዋል። ሌሎች ግንባታቸው ያልተጠናቀቀ ፋብሪካዎችንም ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም