ሕይወት ወጥ የሆነ መስመር የላትም፤ በፈተና መንገድ ታጅባ ላይና ታች ትዋዥቃለች፤ ግራና ቀኝ ትዋልላለች፤ ፊትና ኋላ ትመላለሳለች። ከስኬታችንም ይሁን ከውድቀታችን በፊት በርካታ ውጣ ውረዶችን ታስቃኘናለች።
ሩቅ አሳቢ ሆነን ቅርብ አዳሪ ወይም ቅርብ አሳቢ ሆነን ሩቅ አዳሪ ልታደርገን ትችላለች። ሕይወት እንዲህ ነች፤ ባሰብንበት ሳይሆን ባላሰብንበት ታውለናለች። የዛሬው እንግዳችን ጥበብ የሕይወቱ ጥሪ መሆኗን ተቀብሎ ከሰላሳ አምስት ዓመት በላይ በድምጻዊነት የኖረ ነው። በደርግ ዘመነ መንግሥት የወለጋ ክፍለ ሀገር አብዮታዊ ኪነት ጓድ ሲመሠረት ከመስራቾቹ አንዱ ነው። ከእነ ሰለሞን ደነቀ፣ ዘሪሁን ወዳጆና እልፍነሽ ቀኖ ጋር ዘፍኗል።
አንድ በጋራ፤ አንድ ለብቻው በድምሩ ሁለት የሙዚቃ አልበሞችን አሳትሟል። በራስ ቴያትር፣ በብሔራዊ ቴያትር፣ በአገር ፍቅር ቴያትር ቤቶች እየተጋበዘ ተወዳጅ የኦሮምኛ ዘፈኖቹን ተጫውቷል።
ከገዳ ባንድ ጋር ሆኖ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተዟዟረ ሥራዎቹን አቅርቧል። በኦሮሞ ኪነጥበብ እድገት ላይ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ቀደምት ድምጻውያንም አንዱ ነው። ዛሬ የጤና ችግር ገጥሞት፣ በአዲስ አበባ ከተማ በአስቸጋሪ ሕይወት ውስጥ ይኖራል። የማረፊያ ቤት የለውም፤ ጓደኞቹና የሚያውቁት ሰዎች በሚያደርጉለት ድጋፍ በቀን ከሰላሳ እስከ አርባ ብር እየከፈለ ሰሌን ላይ ይተኛል።
እኛም የአርቲስቱን ችግር ተመልክቶ የሚደርስለት አካል ቢገኝ በሚል የዚህ አምድ እንግዳ ልናደርገው ወደናል። አርቲስት ኢቲአና ቶሎሳ ይባላል። የተወለደው በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ከነቀምቴ ከተማ ወጣ ብላ በምትገኝ በሰቃ በምትባል አነስተኛ የገጠር መንደር ነው። የልጅነት ጊዜውን ከአካባቢው ልጆች ጋር እየተጫወተ ማደጉን ይናገራል። እስከ ዘጠኝ ዓመቱ ትምህርት ቤት አልገባም።
ከብቶችን በመጠበቅና አነስተኛ የግብርና ሥራዎችን በመሥራት አሳልፏል። በልጅነቱ እሮጦ እንደማይጠግብ ይናገራል። ተልኮ ከሄደበት ቦታ በፍጥነት በመመለስ የሚስተካከለው የሰፈር ልጅ አልነበረም።
ተልኮ ሲሮጥ እሾህ ቢወጋው እንኳን የተተፋችው ምራቅ ሳትደርቅ መድረስ ስላለበት ቁጭብሎ የወጋውን እሾህ ማውጣት አይፈልግም። ኢቲአና የልጅነት አስተዳደጉን ሲያስታውስ ይባባል፤ እየቦረቀና ከብት እያገደ ያደገበት ሜዳና ተራራ፣ ውሃ እየተራጨና እየዋኘ ያደገበትን የጨሩ ወንዝን ትውስታ ሲናገር አይኖቹ እንባ እያዘሉ ነው።
ኢቲአና ያደገበትን መንደር ትቶ ወደ ወሎ ክፍለ ሀገር የሄደው የዘጠኝ ዓመት ታዳጊ እያለ ነበር። አጎቱ /የእናቱ ወንድም/ ናቸው መማር አለበት ብለው ወላጆቹን በማሳመን ነበር ወደ ወሎ የወሰዱት። ወሎ ከካራ ቆሬ እልፍ ብሎ በሚገኝ አርጡማ በሚባል አካባቢ ከአጎቱ ጋር እየኖረ አንደኛ ከፍል ገብቶ ፊደል መቁጠር ይጀምራል። አጎቱ ፖሊስ ናቸው፤ ያከብራቸዋል፤ ይፈራቸዋልም።
ተምሮ ሰው እንዲሆን ከፍተኛ ጉጉት ስለነበራቸው ቁጭ ብሎ እንዲያነብ ያደርጉት ነበር። እርሳቸውም ያስጠኑት ነበር። ስላደረጉለት አንዳንድ ነገሮች ሲያወሳ ዛሬም ድረስ ስለውለታቸው ያመሰግናቸዋል። ኢቲአና ወሎ ከሄደ በኋላ እንቅስቃሴው በሙሉ ከቤት ወደ ትምህርት ቤት፤ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ብቻ ሆነ። ሮጦ የማይጠግበው ብላቴና በውስን ቦታ ተገታ።
ያኔ መተንፈሻው የስፖርት ክፍለ ጊዜ ብቻ ነበር። በስፖርት ክፍለ ጊዜ ከክፍሉ ተማሪዎች ሁሉ ቀድሞ ከፊት የሚሮጠው እርሱ ነው። አርጡማ እስከ ስድስተኛ ክፍል ሲማር በሚደረጉት የክፍል ውድድሮች በሩጫው ዘርፍ ኢቲአና የተመሰከረለት ነበር።
የስድስት ዓመት የወሎ ቆይታውን ጨርሶ ወደ ቤተሰቦቹ ጋር ሲመለስ ከሰባተኛ እስከ አስራ አንደኛ ክፍል የተማረው በነቀምቴ ከተማ ነው። አንዳንዴ እየተመላለሰ አንዳንዴም ነቀምቴ ከተማ እየተቀመጠ ትምህርቱን ሲማር፤ ጎን ለጎን የሩጫ ልምምድም ያደርግ ነበር።
ያኔ ምኞቱ እንደነ አበበ ቢቂላ፣ ቶሎሳ ቆቱና ምሩጽ ይፍጠር ስሙን በሬዲዮና በጋዜጣ ማስጠራት ነበር እንጂ እንደአሁን ሩጫ የሚያስገኘውን የኢኮኖሚ ጥቅም በመረዳት አልነበረም። ሩጫ ገንዘብ እንደሚያስገኝ ቢያውቅ ኖሮ ጠንክሮ በመሥራት አንድ ነገር ላይ ይደርስ እንደነበር በመተማመን ይናገራል። በትምህርት ቤቶች ውድድር ግን አውራጃን በመወከል በማራቶን ተወዳድሮ አንደኛ ደረጃ ይይዝ እንደነበር ይገልጻል።
ኢተና ከሩጫ ወደ ድምጻዊነት የተሸጋገረበትን ሁኔታ እንዲህ ያስረዳል። ‹‹ጊዜው 1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው። የደርግ መንግሥት የሚከተለውን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ወደ ሕዝቡ ለማስረጽ ኪነጥበብን እንደ መሣሪያ ይጠቀምበት ነበር። በዚሁ መሠረት ወጣቶች በየቀበሌው እየተደራጁ የኪነጥበብ ሥራዎችን ይሠሩ ነበር።
እኔም በሙዚቃ ክፍለ ጊዜ እና በትምህርት ቤት የሙዚቃ፣ ድራማና ሥነጽሑፍ ክበብ ውስጥ አባል ሆኜ ዘፈኖችን እዘፍን ስለነበር የሚያውቁኝ ጓደኞቼ በቀበሌ ኪነት ውስጥ እንድሳተፍ ገፋፉኝና ገባሁ። ቀስ በቀስ ስሜቴ ከስፖርት ይልቅ ወደ ኪነጥበቡ እያዘነበለ ሄደ፤ ከትምህርት ሰዓት ውጭ ያለውን ጊዜዬን በሙሉ ለኪነጥበቡ ሰጠሁ።
በመለማመጃ ቦታዎች እየሄድኩ ከጓደኞቼ ጋር ዘፈን እየተለማመድን በተለያዩ የመንግሥት ክብረ በዓሎች ላይ ሥራዎቻችንን እናቀርብ ጀመር። ድምጽና ውዝዋዜ የሚያስተምሩን ሰዎች ተመድበውልን ጠንከር ያሉ ልምምዶችን መሥራት ቀጠልን። ከቀበሌ ወደ ወረዳ ከወረዳ ወደ አውራጃ በመጨረሻ ከስድስት አውራጃዎች ድምጻዊና ተወዛዋዦች ተመርጠው የወለጋ አብዮታዊ ኪነት ጓድ የሚል ተዋቀረ።
ድምጻውያኑንና ተወዛዋዦቹን ሲመለምሉ ከነበሩት አንዱ ሳህሌ ደጋጎ ነው። ከብሔራዊ ቴያትር ቤት የመጡ ሌሎችም ፈታኞች ነበሩ። እያንዳንዱ ተመልማይ በድምጽ፣ በውዝዋዜ ወይም በሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋችነት ነው የሚመረጠው። በዚህም ላይ በስልጠና ይታገዛል። በወቅቱ የወለጋ አካባቢን ባህላዊ ጨዋታ በመጫወት በስድስቱም አውራጃዎች እየተዟዟርን የሙዚቃ ኮንሰርት እንሠራ ነበር። አመራሩም ሕዝቡም ይደግፈናል።
የኪነት ቡድኑ በባህል ሚኒስቴር ስር የሚተዳደር ነበር። በወቅቱ ይከፈለኝ የነበረው የወር ደመወዝ መቶ ሃያ ሰባት ብር ነው። ከደሞዙ ባሻገር በየመድረኩ እየወጣን ስንዘፍንም ሽልማት እናገኝ ነበር። እነሰለሞን ደነቀ፣ እልፍነሽ ቀኖ፣ ዘሪሁን ወዳጆ፣ ያያ አደም፣ ዳንኤል ታደሰን ከመሳሰሉ አርቲስቶች ጋር ነበር የምንሠራው። በደርግ ዘመን የኪነት ጓዶች ከአስራ አራቱም ክፍለ ሀገር እየተጠሩ እዚህ አዲስ አበባ ሥራዎቻቸውን ያቀርቡ ነበር።
እኛም ከወለጋ መጥተን እንጦጦ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተቀምጠን በተለያዩ ቴያትር ቤቶችና በኢሠፓኮ ጽሕፈት ቤት እየተገኘን ሥራዎቻችንን እናቀርብ ነበር።
ከዚያም ብሔራዊ ሎተሪ ስፖንሰር ሆኖን በወቅቱ አዲስ አበባ ሬስቶራንት በሚባል አዳራሽ በእራትና በምሳ ግብዣዎች ላይ ሥራዎቻችንን ስናቀርብ ቆይተን እንደገና ወደ ወለጋ ተመልሰናል። እነሰለሞን ደነቀ፣ እልፍነሽ ቀኖና ዘሪሁን ወዳጆ አስቀድመው የዘፈን አልበሞችን የመሥራት እንቅስቃሴ ውስጥ ስለነበሩ ከነቀምት ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል።
የተቀሩትም የኪነት ጓዱ አባላት ወደ አዲስ አበባ እየመጡ በምሽት ቤቶችና በአንዳንድ ባንዶች ውስጥ ታቅፈው መሥራት ጀመሩ።
በዚህን ጊዜ የወለጋ አብዮታዊ ኪነት ጓድ መዳከም ጀመረ። እንደገና ስሙ ተቀይሮ ታዳጊው የወለጋ ክፍለሀገር ኪነት ጓድ በሚል በአዲስ መልክ ተዋቀረ። ከ1983 ዓ.ም በኋላ የደርግ መንግሥትን መውደቅ ተከትሎ የክፍለሀገሩ የኪነት ጓድ እንደገና መፈራረስ ጀመረ። ከወለጋ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ። ገዳ ባንድ፣ ሜጫና ቱለማ ባንድ፣ ኡርጂ ባንድና ሌሎችም በኦሮምኛ ቋንቋ የሚዘፍኑ ባንዶች መቋቋም ጀመሩ። እኔም ከገዳ ባንድ ጋር ሆኜ መዝፈን ጀመርኩ። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በሚያዘጋጃቸው አንዳንድ ፕሮግራሞችና በሠርግ ሥነሥርዓት ላይ እዘፍን ነበር።
አንዳንዴም ከባንዱ ጋር ወደ ክፍለ ሀገር እየሄድኩ እዘፍን ነበር። በወቅቱ ደሞዝ አልነበረኝም። መድረክ ላይ በሚሰጠኝ ሽልማት ነበር የምኖረው። በዚህ አጋጣሚም ከነ አድናን መሐመድ፣ አዲሱ ፉርጋሳ፣ ታደሰ ፊጤ ጋር አብረን እንጫወት ነበር።
ከነዚህ ድምጻውያን ጋር አንድ ኮሌክሽን አልበም እስከ ማውጣት ደረስን። በ1993 ዓ.ም ደግሞ ‹‹ፋቻ›› የተባለውን የራሴን አልበም ሠራሁ። ግን የረባ ጥቅም አላገኘሁበትም። አራት ሺህ ብር ነው የተከፈለኝ። አልበም የመሥራት ፍላጐቴን ትቼ ዝም ብዬ ባገኘሁት መድረክ መዝፈን ይሻለኛል በሚል ትኩረቴን ወደ መድረክ ሥራዎች አደረግኩኝ።
ሥራው የሚገኘው ከረዥም ከቆይታ በኋላ በመሆኑ የገቢ አቅሜ እያነሰ ሄደ። በዚህ የተነሳ አመጋገቤንም አለባበሴንም ማስተካከል አቃተኝ። ፐርሰናሊቲዬን መጠበቅ ስላቃተኝ ይባስ ከመድረክ እየራቅኩኝ ሄድኩኝ። ከመድረክ ያራቀኝ የአቅም ማነስ ነው፤ ዘፈኖቼ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ ናቸው።
እንደምታየኝ አለባበሴም አቋሜም ጥሩ አይደለም፤ በእንዲህ አይነት ሁኔታ መድረክ ላይ ወጥቼ መጫወት አልፈልግም።ቢያንስ የምቀያይረው ልብስ ያስፈልገኛል። አንዳንድ የማውቃቸው ጓደኞቼ ዘፈን እንዳቀርብ ሲጋብዙኝ ልብስ በማጣት ምክንያት የምቀርበት አጋጣሚ አለ። አሁን አሁን እንደውም ከመድረክ ርቄ ስለምኖር ችግሬ እየተባባሰ ሄዷል።
ከዓመታት በፊት ቢያንስ ለቤት ኪራይ የሚሆን ገንዘብ እየሠራሁ አገኝ ነበር። አሁን ያቺንም ታህል እንቅስቃሴ ማድረግ ባለመቻሌ ለከፋ ችግር ተጋልጫለሁ። ማረፊያ ቤት የለኝም፤ ቀደም ሲል የሚያውቁኝ አንዳንድ ሰዎች በሚደርጉልኝ ድጋፍ በቀን ከሰላሳ እስከ አርባ ብር እየከፈልኩኝ ሰሌን ብቻ በተነጠፈበት ቤት ውስጥ አንዴ ፒያሳ አንዴ መርካቶ እየሄድኩ አድራለሁ።
ምግብም የሚያበሉኝ ድሮ በሙዚቃ ውስጥ እያለሁ የሚያውቁኝ ሰዎች ናቸው። አሁን እድሜዬም እየገፋ ስለሆነ በሙዚቃው ሥራ ሕይወቴን አስቀጥላለሁ ማለት አልችልም። ግን ከአዲስ አበባ ከተማ ወጣ ብዬ ዶሮ እንኳን እያረባሁ እንድኖር የሚተባበረኝ ሰው ቢኖር ደስ ይለኛል።
እራሴን ሳልቀይር ትዳር አልመሰርትም ብዬ ቤተሰብ እንኳን አላፈራሁም። ልጅም አልወለድኩም። በዚህ ላይ የኤች. አይ.ቪ ታማሚ ነኝ። እራሴን መንከባከብ ነበረብኝ፤ ግን አልቻልኩም። ምግብ ሳልበላ መድኃኒት ብቻ ውጬ የማድርበት ቀን አለ።
አንዳንድ ዘፋኞች የራሴን ግጥምና ዜማ እየቆነጣጠሩ በመውሰድ የራሳቸው እያስመሰሉ ሲዘፍኑ እሰማለሁ። አንዳንዶቹም አስፈቅደውኝ ይወስዳሉ። ቋንቋው እንዲያድግ ስለምፈልግ ለምን ሳታስፈቅዱኝ ወሰዳችሁ አልላቸውም። ግን ባለቤቱ ማግኘት የሚገባውን ጥቅምና እውቅና ቢሰጡ መልካም ይመስለኛል።
እኔ በኦሮሞ ኪነጥበብ እድገት ላይ የራሴን አስተዋጽኦ ስላበረከትኩ ደስተኛ ነኝ፤ ሰዎች የእኔን ግጥምና ዜማ ሲጠቀሙ የማይከፋኝ አርቱ እንዲያድግ ስለምፈልግ ነው። በኦሮሞ ኪነጥበብ እድገት ስላበረከትኩት አስተዋጽኦ ግን ልታወስ ይገባኝ ነበር።
ውለታዬ ተረሳና ዛሬ ከኤች.አይ.ቪ ኤድስ ቫይረስ ጋር እየኖርኩ የቀበሌ ቤት እንኳን የሚሰጠኝ አጥቼ ሜዳ ላይ ወደቅኩኝ። በፌዴራል ባህል ሚኒስትርም ይሁን በኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በርካታ ጊዜ እየተመላለስኩ ያለሁበትን ሁኔታ በማስረዳት ድጋፍ እንዲያደርጉልኝ ጠይቄ አለሁ።
ተስፋ ከመስጠት ውጭ እስከ አሁን ያደረጉልኝ ነገር የለም። አሁንም በዚህ አጋጣሚ እባካችሁ መጠለያ ስጡኝ ብዬ እማጸናቸዋለሁ። ምናልባት ብሞት አርቲስት ኢቲአና ቶሎሳ ሞተ ተብሎ በሚዲያ ሊተላለፍ ይችላል። ይሄ ለእኔ ምንም አያደርግልኝም።
በተለይም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ለኦሮሞ ኪነ ጥበብ እድገት አስተዋጽኦ አበርክተሃል ካለ ሳልሞት እንዲረዳኝ እጠይቃለሁ፤ ሲል ስለተጫነው ችግር እና ሊደረግለት ስለሚፈልገው ሁሉ በተማጽኖ አስረድቷል። እኛም የዚህን የአገር እና አርት ባለውለታ ችግር ተገንዝቦ ሊያግዘው የሚፈልግ ሁሉ እንዲያግዘው መልዕክታችን ነው።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን መጋቢት 10 /2014