አባቴ የሕይወት ዘመኔ ያልተመለሰ ጥያቄዬ ነው፣ አድጌ እንኳን ሮጬ ያልደረስኩበት ከፍታዬ ነው። እዚህ ምድር ላይ ሮጬ ያልደረስኩበት አባቴና ሀሳቡ ናቸው። ሀሳቡ ይገርመኛል፤ ድሆች የሌሉበት የባለጸጋ ሀሳብ የለውም። አባቴ ሁልጊዜ ከድሆች ርካሽ ዕቃዎችን በውድ ይገዛል፤ እኔ ከስሩ ኩስ ኩስ የምለው ልጁ በአባቴ እንግዳ ባህሪ እደነቃለሁ።
ያ ዕቃ እኛ ቤት ገብቶ ምንም እንደማይሠራ እኔም እሱም እናውቀዋለን። ግን አባቴ ይገዛል፤ ሳይከራከር፤ ለዚያውም ከጠየቁት ዋጋ በእጥፍ ከፍሎ። ሰፈራችን ውስጥ፣ ዓለም ላይ ከአባቴ በቀር ማንም የማይጠቅመውን ዕቃ በውድ ዋጋ ይሸምታል የሚል መረጃ አላገኘሁም። አባቴ ያስደንቀኛል፤ ግራም ያጋባኛል። አንድ ቀን ሰፈራችን ካሉት ድሀ ሴትዮ አንድ እንጀራ እንድበደር ላከኝ። አባዬ ምን ነካው? ቤታችን ውስጥ እንጀራ ሳይጠፋ እንዴት እንጀራ እንድበደር ወደ ድሀ ሰው ቤት ይልከኛል እያልኩ ወደ ተላኩበት ቤት ሄድኩኝ። እንጀራ የሚሸጡት እናት ዘንድ ስደርስ እንግዳ አለም ጠበቀኝ። በሕይወቴ እንደዚያ ዓይነት እንጀራ ያየሁት እዛች ድሀ እመበለት ቤት ነው።
ፊትና ጀርባው የማይለይ፣ ከአፈር ተፈጭቶ የተጋገረ የሚመስል ማዲያታም እንጀራ ይዤ ወደ ቤት ተመለስኩ። አባቴ ያን እንጀራ ምን ሊያደርገው ተበድረህ ና እንዳለኝ ለማወቅ ብዙ ጣርኩ። ምሳ ሰዓት ላይ ቤተሰቡ ቀርቦ ምግብ ስንበላ ያ እንጀራ ፊታችን ላይ ቀረበ፣ ያ እንጀራ ወደ ሆዴ እንዲገባ የተቸገርኩትን መቸገር መቼም አረሳውም።
አባዬ ግራ ማጋባቱን እንደቀጠለበት ነው፤ አንድ ቅዳሜበልደቴ ዋዜማ ከሰፈር ወጣ ብለን በእግር እንራመዳለን። እጁ ከእጄ ላይ የተለየበትን ቀን አላስታውስም። አባቴ ሳይዘኝ፣ እናቴ ሳታቅፈኝ የተራመድኩበት ጊዜ ትዝ አይለኝም።
‹ነገ ልደትህ ነው፤ ለዚህ ያደረሰህን አምላክህን እሱ በሚወደው መንገድ በማክበር እሱን ማስደሰት አለብህ› አለኝ። ‹እሱ የሚወደው እንዴት ያለ ከብር ነው? ስል ጠየኩት። ዕድሜ በጎ ሥራ ነው። ራስህን በማስደሰት፣ ለራስህ በመኖር የምታከብረው ልደትህ ከዛሬ ጀምሮ ያቆማል። ዕድሜ ምርቃት ነው፣ ዕድሜ በአንተ መኖር ሌሎች ሲስቁ ማየት ነው፤ ስለዚህ ዛሬ በልደትህ ዋዜማ የሆነ ሰው በማስደሰት እንጀምራለን አለኝ። ሳይገባኝ እሺ አልኩት…።
እንደ አባዬ የሚወደኝ ማንም ስለሌለ በሚለው ሁሉ እስማማለሁ። ‹እዛ ጋ አንድ ሽማግሌ ይታዩሀል? አለኝ ወደ ፊቱ በጣቱ እየጠቆመኝ። ‹አዎ ይታዩኛል› አልኩት። ‹እንካ ይሄን ብር ሳያዩህ አጠገባቸው ካለው ፌስታል ውስጥ አስቀምጠህ ና› አለኝ። እሺ ብዬ እንዳለኝ አደረኩ። ስመለስ ለምን እንደዚያ እንዳደርግ አዘዝከኝ? ስል አንድ ጥያቄ ጠየኩት።
እርሱም ‹እኚህ ሽማግሌ ከእንቅልፋቸው ነቅተው ብሩን ሲያዩ የሚሰማቸውን ደስታ በምን ትለካዋለህ? እኚህ አባት ምድር ላይ የሚያግዛቸው አንድም ሰው የለም፤ ዛሬ ባደረክላቸው መልካም ነገር ብዙ ስቃያቸውን ቀንሰህላቸዋል።
በባዶነታቸው ውስጥ ተስፋን አስቀምጠሃል፣ በሽምግልናቸው ውስጥ ደስታን ትተሀል› አለኝ። አባዬ ሰፈራችን ውስጥ ባለጸጋ ከሚባሉ ሰዎች አንዱ ነው። ግንባራቸው መሬት እስኪነጋ ድረስ ጎንበስ ቀና የሚሉለት ብዙ ሰዎችን አውቃለሁ። አንድም ቀን ግን እንደ ባለጸጋ ሲሆን አይቼው አላውቅም። የነዛ ሰዎች ጎንበስ ቀና ለአባቴ አንድም ቀን ምንዳ ሲሆነው አላየሁም። እጄን በእጁ ይይዝና የሰፈራችንን የባለጸጎች መንደር አልፈን ሁሌ ጠዋት ከማይቀርበት አጥቢያ እንደርሳለን
። ውድ ሱሪው የአካባቢውን አቧራ እስኪቅም ድረስ በረንዳው ላይ ተደፍቶ ይጸልያል። አባቴ የድሆች ሳቅ ነው፤ አባቴ እዚህ ዓለም ላይ ሰው የሆነው ለድሆች ደስታ ሲባል ነው እላለሁ። በበዓል ሰሞን ሰፈራችን ውስጥ ወዳሉ ምንም ወደሌላቸው ድሆች ቤት ስጦታ ይዞ ይሄዳል። ድሆቹ አባቴን ሲያዩት የሚስቁትን ሳቅ፣ የሚሆኑትን መሆን መቼም አረሳውም።
ምን እንደሚያቀርቡለት፣ ምን እንደሚሉት ሲሽቆጠቆጡ አቅፎ ሰላም ይላቸዋል። አጠገባቸው ካለ መደብ ላይ ቁጭ ይላል። ለበዓል መዋያ የሚሆን ዳጎስ ያለ ገንዘብ ሲሰጣቸው አየዋለሁ። ከዚያ በኋላ አባቴ ሌላ ይሆንብኛል።
የማላውቀው መንፈስ ውስጤ ገብቶ የማውቀውን አባቴን ይቀይርብኛል። አባቴ ወደ እግዚአብሔርነት ሲቀየር፣ ወደ መላዕክትነት ሲመጥቅ ይታየኛል። በዚያ የልጅነት ዕድሜዬ ከአባቴ በቀር ማንንም በእንደዚያ ባለ የመባረክና የመታደስ መንፈስ አይቼ አላቀውቅም። በቃ በእግዚአብሔራዊ ሞገስ አየዋለሁ።
መጨረሻ ከሌለው የድሆቹ ደስታ በኋላ አባቴ ወደ እኔ በመዞር ‹ይሄን ሳቅ አየኸው? ይለኛል። ይሄ ሳቅ እዚህ ምድር ላይ ማንም የማይስቀው እግዚአብሔራዊ ሳቅ ነው። እንዲህ የምትስቀው በሕይወት ዘመንህ አንድ ጊዜ ነው፤ እንደ እነዚህ ድሆች ተስፋ ስታጣ። ሕይወት ተስፋ ላጡ ተስፋ መሆን፣ ደስታ ለራቃቸው ደስታን መፍጠር ነው። ይሄ ሳቅ ብቻ እንዳይመስልህ፣ በዚህ ሳቅ ውስጥ እኔና አንተ ዘላለማዊ ቤታችንን እየሠራን ነው።
በዚህ ፈገግታ ውስጥ እኔና አንተ ለዘላለም እንዳንሞት ሆነን እየኖርን ነው። በልደትህ ዋዜማ በዚያ አዛውንት ልብ ውስጥ የፈጠርከው ደስታ ይታወስሀል? ሕይወት ያ ነው አለኝ። አባቴ ሲናገር ማድመጥ ስለምወድ ቢገባኝም ባይገባኝም ዝም ነው የምለው። ግን ግን እስካደኩበት ጊዜ ድረስ አባቴ ነግሮኝ የገባኝ አንድም ነገር አልነበረም። መኪናውን ለድሀ ሲያቆም ነው የማውቀው።
ትናንት የገዛውን ጃኬት ራቁቱን ለሚሄድ እብድ ሲያለብስ ነው የማውቀው። ያልጠገብኩትን አባትነቱን አባት ለሌላቸው ሲያጋራ ነው የማውቀው። ሰፈራችን ካሉት ባለጸጎች ልዩ ሆኖ ስለማየው አባቴ ያመራምረኝ ነበር። ሳድግ የገባኝ የአባቴ እውነት ነው። እንዲያውም እላለሁ በዘመኔ ሙሉ የአባቴን ያክል ሀሳብ አልተከተለኝም። እነዛ ሳቆች፣ እነዛ ፊቶች የዘመኔ አውራ ሆነው ዛሬም ነፍሴ ውስጥ አሉ። ዛሬ ላይ በጽናት ያቆሙኝ እነዚያ ሀሳቦች ይመስሉኛል።
ዛሬ ላይ እንዳልናወጥ እግሮቼን ያጸኑት ከአባቴ ጋር ሄጄ ያየኋቸው እነዚያ ሳቆች፣ እነዚያ ፈገግተኛ ፊቶች ናቸው እላለሁ። ያ ሳቅ ዛሬ ላይ እኔና አባዬን ከልሎናል..ሞገስ ሆኖናል። እንደ አባቴ እግዚአብሔርን የሚያውቀው ማንም የለም፣ ፈጣሪም ምድር ላይ ካሉ ወንዶች ሁሉ አብዝተህ የምትወደው ማንን ነው ቢባል አባቴን እንደሚል አልጠራጠርም። በፈጣሪ ሀሳብ ውስጥ አባቴ፣ በአባቴ ሀሳብ ውስጥ ደግሞ እኔ ተፈጥረናል።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መጋቢት 9 /2014