የዓይን ብርሃኑን ያጣው ገና በልጅነቱ ነው። እንደብዙዎቹ ታዳጊዎች ቦርቆ ለመጫወት አልታደለም፡፡ የትምህርት ሕይወቱም በቤተ- ክህነት እንጂ በዓለማዊው የቀለም ትምህርት አልተጀመረም።
ዘግይቶም ቢሆን ግን የቀለም ትምህርቱን በጎንደርና በአዲስ አበባ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ድረስ ተከታትሏል፡፡ በመቀጠል ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ወስዶ ውጤት ስለመጣለት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ሲከታተል ቢቆይም ባጋጠመው የጆሮ ህመም ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገዷል፡፡
ሆኖም ያጋጠመውን ፈተና በመቋቋም እንደገና በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ የመምህርነት ሙያ ተከታትሎ በዲፕሎማ ተመርቋል፡፡ ከምርቃት በኋላ በዚሁ በተማረበት የመምህርነት ሙያ ተቀጥሮ ለመስራት በብርቱ ቢለፋም ጠብ የሚል ነገር ማግኘት አልቻለም። የዕለት ጉርሱን ማሟላት ነበረበትና ፊቱን ወደ ልመና አዞረ፡፡
ግን አልጣመውም፣ የሰው ፊት እየገረፈው እንደሆነ ተሰማው፡፡ እናም ልመናውን እርግፍ አድርጎ በመተው ጎዳና ላይ የውሃና የሻይ ብርጭቆዎችን መነገድ ጀመረ፡፡ ዛሬም በዚሁ የንግድ ስራ ራሱን እየደጎመ ይገኛል፡፡
ይህ የተሟላ ሰውነት ይዘው ከሚሰሩ ሰዎች ባልተናነሰ መልኩ ኑሮን ለማሸነፍ እየተፍጨረጨረ የሚገኘውና በኢትዮጵያ ማየትና መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማህበር የቦርድ አባል የሆነው የዛሬው ‹‹የእንዲህም ይኖራል›› እንግዳችን አቶ መርሃዊ ምህረቱ ይባላል፡፡
አቶ መርሃዊ ውልደትና እድገቱ በደቡብ ጎንደር ዞን ጋይንት ወረዳ ልዩ ስሙ ሳፍዳ ጊዮርጊስ በሚባለው አካባቢ ነው፡፡ ገና የስምንት ዓመት ታዳጊ እያለ ባጋጠመው የዓይን ህመም ምክንያት ነው የማየት ችሎታውን ያጣው፡፡ በዚህም ምክንያት ከዓለማዊው የቀለም ትምህርት ይልቅ ወደ መንፈሳዊው በማድላት የቤተ- ክህነት ትምህርት መከታተል ጀመረ፡፡
በቤተክህነት ትምህርቱ ብዙም ሳይገፋበት የሆድ ህመም አጋጥሞት በብዙ ተሰቃየ፡፡ ትምህርቱንም አንዴ ሲያቋርጥ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲጀምር ግዚያቶች አለፉ፡፡
የቤተ-ክህነት ተማሪ እግሩ አያርፍምና ከእርሱ ጋር ሲማሩ የነበሩ ተማሪዎች ወደ ከተማ የመግባት ሀሳብ ሲጠነስሱ እርሱም ከነርሱ ጋር ተስማምቶ ጎንደር ከተማ ገባ፡፡ ጎንደር ከተማ ከገባ በኋላም ያቋረጠውን የቤተክህነት ትምህርቱን ቀጠለ፡፡
ጎንደር ከተማ በመግባቱም የአለማዊ የቀለም ትምህርት እንደሚሰጥ ተረዳ፡፡ በጊዜው በጎንደር ከተማ ቅርንጫፍ የነበረው የዓይነ ስውራን ማህበር ህፃናትን እየመለመለ ወደ አዳሪ ትምህርት ቤት ሲያስገባ እርሱም አስመራ አዳሪ ትምህርት ቤት የመግባት አጋጣሚ ተፈጠረለት፡፡
ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያለውን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱንም በዛው አስመራ አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ ተከታተለ፡፡ አቶ መርሃዊ ከመንግስት ለውጥ በኋላ በ1984 ዓ.ም ትምህርቱን አቋርጦ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡ ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ በመንግስት ሰበታ የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት እንዲገባ ተደረገ፡፡
የስድስተኛ ክፍል ትምህርቱን ተከታትሎ የመልቀቂያ ፈተና ከወሰደ በኋላ እንደገና ወደ ጎንደር አቀና፡፡ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለውን ትምህርቱን በአፄ ባካፋ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአፄ ፋሲለደስ ትምህርት ቤት ተከታትሎ አጠናቀቀ፡፡ ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ የሚሆነውን ነጥብ በማ ሟላቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ በታሪክ የትምህርት ዘርፍ በዲግሪ መከታተል ጀመረ፡፡
አብዝቶ እያጠና ሲያድር ታዲያ ጆሮውን ታመመ፡፡ ጆሮውን ለመታከምም በርካታ የጤና ተቋማትን ረገጠ፡፡ ሆኖም መፍትሄ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ በዚህ መሀል የኢትዮጵያ ማየትና መስማት የተሳናቸው ብሄራዊ ማህበር እየተቋቋመ ነበርና እርሱም ከመስራቾቹ ውስጥ አንዱ ለመሆን በቃ፡፡
ባጋጠመው የጆሮ ህመም ምክንያትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጀመረውን የዲግሪ ትምህርት አቋርጦ እንደገና ወደ ጎንደር ተመልሶ የቤተ ክህነት ትምህርት መከታተሉን ቀጠለ፡፡ ከጆሮ ህመሙ ጋር እየታገለ የቤተ ክህነት ትምህርቱን መከታተል ቀጠለ፡፡ ግን አልቻለም። የጆሮ ህመሙ እየተባባሰበት ሄዶ ተስፋ አስቆረጠው። በዚህም ተበሳጭቶ ጎዳና ላይ እስከመውጣት ደረሰ፡፡
ልመናም ጀመረ፡፡ በኋላ ላይ ግን የማየትና መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማህበር ፕሬዝዳንት አበራታችነትና ግፊት እንደገና ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡ ቀን ቀን አራት ኪሎ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት የውሃና የሻይ ብርጭቆዎችን፣ ብርጭቆ ማስቀመጫዎችን፣ የእቃ ማጠቢያዎችን፣ ማራገቢያዎችን፣ የሳሙና ማስቀ መጫዎችን፣ የካሮት መፈቅፈቂያዎችን፣ ቢላዎችን፣ የጨው እቃዎችን፣ ሳህኖችንና ሌሎችንም የቤት እቃዎችን መሸጥ ጀመረ፡፡
ሕይወት ከተጠቀሙባት ዳግም እድል ትሰጣለችና አቶ መርሃዊም ያጋጠመውን ችግር ተቋቁሞ ቀን ቀን እየሰራ ማታ ማታ በኮተቤ ትምህርት ኮሌጅ በስነዜጋና ስነ-ምግባር ትምህርት ለሁለት ዓመት ትምህርቱን ሲከታተል ቆይቶ በ2009 ዓ.ም በዲፕሎማ ተመረቀ።
በተማረበት የመምህርነት ሙያ ተቀጥሮ ለመስራት ተደጋጋሚ ጥረቶችን ቢያደርግም ታዲያ እስካሁን ድረስ ሊሳካለት አልቻለም፡፡ ራሱን ለመደጎም መስራት የግድ ነውና አሁንም የቤት እቃዎችን መሬት ላይ ዘርግቶ ‹‹ ያለቀበት የሻይ ብርጭቆ!፣ የውሃ ብርጭቆ! ›› እያለ ይሸጣል፡፡
ከቤት እቃዎች ሽያጭ በቀን ምን ያህል እንደሚገኝ ከመናገር የተቆጠበው አቶ መርሃዊ፤ እቃዎቹን ሽጦ በቀን ከሚያገኘው ገቢ ራሱን መደጎም እንደሚችል ግን አልሸሸገም፡፡
ከዚህ በፊት ያስተማረው ፈለገ ካርሎስ የተሰኘ ድርጅት አፍንጮ በር አካባቢ ለቢሮ በተከራየው ቤት ውስጥ ማታ ማታ እንደሚያድርበትም ይናገራል፡፡ እስካሁን ድረስ ትዳር እንዳልያዘና ለብቻው እንደሚኖርም ይገልፃል፡፡
‹‹የሰው ፊት እሳት ነው›› የሚለው አቶ መርሃዊ፤ በተለይ መስራት እየቻሉ ሙሉ ጤነኛ ሰውነት ይዘው የሚለምኑ ሰዎች ሱስ ሊሆንባቸው ስለሚችል የሰው ፊት ከማየት በራሳቸው ጥረው ግረው ሰርተው ራሳቸውን ማኖር እንዳለባቸው ያስጠነቅቃል፡፡
እርሱም በአንድ ወቅት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እንዳቋረጠ ተስፋ ቆርጦ ወደ ልመና መግባቱን አስታውሶ፤ ሙሉ ጤነኛ የሆኑ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ አካል ጉዳተኞችም ቢሆኑ በራሳቸው ለመቆም ያገኙትን ስራ መስራትና ኑሮን ለማሸነፍ መፍጨርጨር እንደሚገባቸውም ይመክራል፡፡ ልመናን ፍፁም መፀየፍ እንዳለባቸውም ይጠቁማል፡፡
ሰዎች ለመለወጥ ዝግጁ እስከሆኑ ድረስ በትንሽ ገንዘብ መነሳት እንደሚችሉና እርሱም የኢትዮጵያ መስማትና ማየት የተሳናቸው ብሔራዊ ማህበር በሰጠው አነስተኛ ገንዘብ የተወሰኑ የቤት እቃዎችን ከመርካቶ በመግዛት ወደ ንግድ ውስጥ እንደገባ ያስታውሳል። ከዛ በፊት ግን ክብደት መመዘን /ሚዛን/ ስራ ሞክሮ እንደነበር ይገልፃል፡፡ ሆኖም ስራው አክስሮት በቀጥታ ወደ እቃ ንግዱ እንደገባም ይናገራል፡፡
ከዚህ ቀደም ለትንሽ ጊዜም ቢሆን ለምኖ የእለት ጉርሱን ያሟላ እንደነበርም ተናግሮ፤ ዛሬ ላይ ግን በንግድ ስራ ራሱን ማስተዳደር መቻሉ ትልቅ የአእምሮ እርካታ እንደሚሰጠውና እንደሚያስደስተው ይገልፃል፡፡ ሌሎች ደሞዝተኛ ማየት የተሳናቸው ጓደኞቹ ከሚያገኙት ገቢ የእርሱ ገቢ እንደማያንስም ያስረዳል፡፡ ከእነርሱ ባለተናነሰ መልኩ በልቶና ጠጥቶ እንደሚያድርም ይጠቁማል፡፡ በልመና ላይ እያለ ግን ጓደኞቼ አዩኝ አላዩኝ እያለ ሲሳቀቅ እንደነበር አስታውሶ፤ ሆኖም ዛሬ በልበ ሙሉነት ስራውን ሰርቶ ወደ ቤቱ እንደሚገባም ይገልፃል፡፡
በተማረበት የስነ-ዜጋና ስነ -ምግባር ትምህርት የማስተማር ፍላጎት እንዳለው የሚገልፀው አቶ መርሃዊ፤ በተደጋጋሚ ለአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ማመልከቻ መፃፉንና እስካሁን ድረስ ምላሽ እንዳላገኘ ይጠቁማል፡፡
የማስተማር ህልሙ እስኪሳካ ግን ጥረቱን እንደሚቀጥል ይጠቅሳል፡፡ በዚህ አጋጣሚም ችግሩን አይቶ ቢሮው አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግለት ይጠይቃል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ማየትና መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማህበር ውስጥ የቦርድ አባል ሆኖ እየሰራ የሚገኘው አቶ መርሃዊ፤ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ማህበር አባል እንደነበር ያስታውሳል፡፡
ይሁንና ማየትና መስማት ከተሳናቸው ማህበር ከዓይነ ስውራን ማህበር ጋር ሲነፃፀር ገና ልጅ መሆኑንና በርካታ ድጋፎች ከመንግስት፣ ግለሰቦችና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንደሚያስፈልገው ይጠቁማል፡፡ አሁን በደረሰበት አቅሙም አባላቱንና የአባላቱን ቤተሰቦች ለመደገፍ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም ይመሰክራል፡፡ በተለይ ደግሞ ለአባላቱ መነሻ ገንዘብ በመስጠት በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው ራሳቸውን እንዲችሉ ጠንካራ ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ ማህበር መሆኑንም ያስረዳል፡፡
በኢትዮጵያ አይደለም በሶስትና በአራት የአካል ጉዳት በአንድ የአካል ጉዳት ራስን ችሎ ለመኖር ፈተና በሆነበት በዚህ ጊዜ አብዛኛው የአካል ጉዳተኛ በተለይ ማየትና መስማት የተሳናው ለምኖ ከመብላት ውጭ ብዙም አማራጭ እንደሌለው አቶ መርሃዊ ይናገራል። እርሱም ቢሆን በመንገድ ላይ ሲሄድ ዓይነስውር መሆኑን የተመለከቱ ሰዎች የምፅዋት እጃቸውን የሚዘረጉ እንዳሉና ይህ ተገቢ አለመሆኑን ይጠቅሳል፡፡
ሰዎች ምፅዋት ከመስጠት ይልቅ አካል ጉዳተኞች ሲሰሩ ካዩ ቢያበረታቱና ቢደግፉ መልካም ነው ይላል። በተመሳሳይ ማህበሩንም ቢደግፉ በተለይ ደግሞ የተደበቁ ማየትና መስማት የተሳናቸውን ወገኖች ወደ አደባባይ እንዲወጡ በማድረጉ ሂደት ቢሳተፉ የተሻለ መሆኑንም ይጠቁማል፡፡ ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ ባለው አቅም እየዞረ ተደብቀው የነበሩ ማየትና መስማት የተሳናቸው ወገኖችን እያወጣና እያሰለጠነ እንደሚገኝም ይጠቁማል፡፡
በተለያዩ ሙያዎች እያሰለጠነና ራሳቸውን እንዲችሉ እያደረገ እንደሚገኝም ይጠቅሳል፡፡ ከዚህ አኳያ በየቤቱ ተደብቀው ያሉ ማየትና መስማት የተሳናቸውን አካል ጉዳተኞች ማውጣት የሁሉም አካላት ድርሻ ሊሆን እንደሚገባ ያሳስባል። በሚቻለው አቅም ሁሉ ማህበሩንም መደገፍና ማበረታታት ከሁሉም እንደሚጠበቅ ይጠይቃል፡፡
የሚዲያ ተቋማትን ማህበሩን ከማስተዋወቅ አንፃር ሰፊ ስራ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ያሳስባል፡፡ ሕይወት የሁሉም ሰዎች መጫወቻ ሜዳ ናት። ጨዋታውን በአግባቡ የተጫወተ አሸናፊ ሆኖ ይወጣል፡፡ በተቃራኒው በተሰጠው የመጫወቻ ሜዳ ላይ በተገቢው ያልተጫወተ ተሸናፊ ይሆናል፡፡
እናም አቶ መርሃዊ የመስማትና የማየት ችግር ቢያጋጥመውም ከችግሩ ጋር ሆኖ በሕይወት መጫወቻ ሜዳ ላይ ከሙሉ ጤነኞች እኩል ተፎካክሮ እየተጫወተ ነው። አሸናፊ እንደሚሆንም ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
ብዙዎችም በተለይ ደግሞ ሙሉ ጤነኛ ሆነው የስራ ፍላጎት የሌላቸው ወገኖች ከአቶ መርሃዊ ሕይወት በብዙ ይማራሉ ብለን እናምናለን፡፡ ሰላም!::
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 3 /2014