በታዳጊዎች መካከል የሚደረግ የሥዕል ውድድር ላይ እንዲህ ሆነ፡፡ ውድድሩ ሰላምን በቁጥርና በምስል መግለጽ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ታዳጊዎቹ በገባቸው ልክ ለውድድሩ ዝግጁ ሆነው ድግሳቸውን የሚያቀርቡበትን ጊዜ በጉጉት እየተጠባበቁ ነው። ሥዕሎቻቸውን ለእይታ አቅርበው እያንዳንዱ ተመልካች በሚሰጠው ነጥብ መሰረት አሸናፊ የሚሆነው ይለያል፡፡
ታዳጊዎችም ስለሽልማቱ ከወዲሁ ልባቸው ተንጠልጥሏል። የውድድሩ አሸናፊ የሚመረጥበት መንገድ ግን ከተለመደው ወጣ ያለ መሆኑ የታዳጊዎች ግርታ ነበር፡፡ ከሁሉም ዝቅተኛውን ነጥብ ያመጣው ታዳጊ የውድድሩ አሸናፊ ይሆናል፡፡ አዎን ያልተለመደ የውድድር አካሄድ። የመጀመሪያው ሳይሆን፤ የመጨረሻው የሚሸለምበት፡፡
የውድድሩ አዘጋጆች ይህን ያደረጉበት ምክንያት በመጨረሻ የሚወጣው ሥዕል አንደኛ ከወጣው ያልተወደደ ቢሆንም ስለሰላም ግን የሚያስተላልፈው ዝቅተኛው መልእክት እንኳን መተግበር ቢችል የሰውን ልጅ ስቃይ መቀነስ ይችላል ብለው በማመን ነው፡፡ ሁሉም ልጆች ሥዕላቸው የሰላምን አስፈላጊነት የሚገልጽ፤ ጦርነት ፈጽሞውኑ መታሰብ ያለበት ነገር አለመሆኑን የሚያስረዳ መሆን ስለነበረበት በተባለው መሰረት አዘጋጁ፡፡
ከዚያም የመጨረሻው ዝቅተኛውን ተወዳዳሪ ለማግኘት ውጤት ማሰጠት ተጀመረ። ተመልካቾች የውድድሩን ህግ አያውቁም ነበርና በገባቸው መንገድ አሪፍ ለሚሉት ሥዕል ከፍተኛውን ነጥብ እየሰጡ ዋሉ፡፡ ተወዳዳሪዎች የተሰጣቸው ነጥብ ተደምሮ አሸናፊው እስኪለይ ድረስ፤ ሲጎበኟቸው ከዋሉት ጎብኚዎች መካከል የአንድ ጎብኚን አስተያየት ጽፈው በንባብ ማቅረብ ነበረባቸው፡፡
በዚሁ አግባብ አስተያየት እየተሰማ ነበር። አንዱ ታዳጊ የተሰጠውን አስተያየት እንዲህ ሲል አነበበ “ሥዕልህ ጥሩ ነው፤ ነገር ግን ቀለም በዝቶበታል፡፡” ታዳጊው ሲያብራራው ለሥዕሉ የተጠቀመው ቀለም በመብዛቱ የተሰጠው አስተያየት መሆኑን አስረዳ፡፡ ሌላኛው ታዳጊ የተጻፈለት አስተያየት “ታዳጊው በርታ ሥዕሉን ግን በጣም ቀላል አደረከው፤ ትንሽ ጥበባዊና አመራማሪ ቢሆን ጥሩ ነበር” የሚል ነው፡፡ ሦስተኛው ታዳጊ ቀጥለ “ሥዕል ነው የቁጥር ማስተማሪያ ሙሉ ሥዕሉን ቁጥር አደረከው” ወዘተ ይላል፡፡
ታዳጊው በቁጥር የጦርነትን አስከፊነት ለመግለጽ፤ በቁጥር የሰላምን ዋጋ ለመክፈል የሳለው ሥዕል ነበር፡፡ ሁሉም ተራ በተራ የተሰጧቸውን አስተያየቶች አንብበው ጨረሱ፡፡ የመጀመሪያው ታዳጊ ቀለም የበዛበት ሥዕል ያቀረበ በመሆኑ የተሰጠው አስተያየት ምን ትርጉም ይሰጠናል? ሥዕል ላይ ከመጠን በላይ ቀለም ከበዛ የሥዕሉን ድምቀት የሚያበላሸው በመሆኑ ነው፡፡
ሰው የቀለም ምርጫው ቢለያየም ሲበዛ ለእይታ አስቸጋሪ ስለሚሆንበት የበዛን ቀለም አይወድም፡፡ በሚረብሽ ቀለም ምክንያት አንድ ክፍል ውስጥ ተረጋግተን መቀመጥ እንዳንችልም ልንሆን እንችላለን፡፡ የቀለም ኬሜስቶች ቀለምን ትርጉም ያለው እንዲሆን አድርገው ይመራመሩበታል፤ ደግሞም ይመክሩበታል፡፡ ቀለም ሲበዛ እይታን የመረበሹን እውነት ይዘን በቀለሙ ቦታ የሰውን ደም እያሰብን እንዝለቅ፤ ሰላም ማጣት የሰውን ደም እያበዛ ስለሆነ፡፡
ሁለተኛው አስተያየት ሥዕሉ ቀላል መሆኑንና የተወሰነ ውስብስብ በማድረግ ጥበባዊ ማድረግ እንደሚገባ የሚያሳይ ነው፡፡ ውስብስብ ነገር ለምን እንደምንወድ ራሳችንን በመጠየቅ እንቀጥል፡፡ ሥዕሉ ቀለል ባለ መንገድ መቅረቡ ጥበብ የጎደለው ተደርጎ ተወስዷል፡፡ በሆነ ንግግር መካከል ትንሽ ወሰብሰብ ያለ ነገር ካልጨመርን ጥሩ ንግግር ያደረግን የማይመስለን ስንቶቻችን እንሆን? የታዳጊው ሥዕል ውስብስብ አለመሆኑ አስተያየት ሰጪው እንዲናገርበት አድርጎታልና አነሳነው፡፡ ዛሬም ቀላል የሚባሉ የሕይወት እሴቶች ወደ ጎን ብለው በውስብስብ መንገድ ውስጥ ሰላምን ፍለጋ ላይ እንገኛለን፡፡
ሦስተኛው አስተያየት ሰጪ ስለ ቁጥር የተናገረው ነው፡፡ ሥዕሉ ላይ ቁጥር በዛ ስለሆነም የሥዕሉን ውበት ቀነሰው የሚል አንድምታ ያለው አስተያየት ነው ታዳጊው የተሰጠው፡፡ በብዙ ጉዳዮች ላይ የተደረጉ ጥናቶች በቁጥር እውነታን የሚገልጹ ሰነዶች አሉ። በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ በሥዕል ላይ ቁጥር ብቻ ሲሆን ለተመልካቹ ምቾት የሚሰጥ አልሆነም፡፡ በቁጥር የተገለጸው ጉዳይ ምንድን ነው ከሚለው ጥያቄ ባለፈ ግርታን ስለፈጠረ። ሰላምን በቁጥር ለመግለጽ የተደረገውን ሙከራ አድንቀን፤ ጦርነትም ሆነ ሰላም በቁጥር ሲገለጹ ጉዳትና ጥቅማቸውን በቀላሉ መረዳት የሚያስችለን መሆኑ ጥርጥር የለውም።
ተጨባጭ እውነታዎች በቁጥር ውስጥ የመገኘታቸውን ሃቅ ከተመለከትን ሰላም በመፈለግ ጉዞ ውስጥ ቁጥሮች ምን እንደሚሉን እንመርምር፡፡ በጦርነት ውስጥ የተመዘገበውን ኪሳራም እንዲሁ፡፡ የሥዕል ጉብኝቱ ተጠናቆ፤ አስተያየት ተሰጥቶ፤ ነጥብም ተደምሮ አሸናፊው የሚታወቅበት ሰዓት ደረሰች። ሰላምን በቁጥር የገለጸው መጨረሻ ላይ በመውጣቱ የውድድሩ አሸናፊ ሆነ፡፡ የተሸለመውንም መኪና በቁጥር አስጊጦ መኪናውን የሰላም አምባሳደር አድርጎ ሰየማት፡፡ ውድ አንባቢ ስለ ሰላም በብዙ አይነት መንገድ ብዙ ተብሏል፡፡
ዓለማችን ሰላምን አጥታ በምታርበት ዛሬ እያንዳንዱ ሰው ስለሰላም ሚናውን እንዲወጣ በሚሻ ልብ ይህ ጽሁፍ ተዘጋጅቷል፡፡ መዳረሻችን ስለ ሰላም የሚገኘን አንድ የሰላም ሰው ከትላንት ቁጥሮች ተምሮ የነገውን የተሻለ ለማድረግ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ነው፡፡
የበዛው ቀለም
በማንኛውም ነገር ውስጥ ከመጠን በላይ የሆነ ነገር ተቀባይነት የለውም፡፡ “ማር ሲበዛ ይመራል” ሲባል ማር ተፈጥሮዊ ትርጉሙን ይቀይራል ማለት አይደለም፡፡ ወጥ ውስጥ ጨው ሲበዛ የጨውነት ትርጉሙ ጠፍቶ ውጤቱ የማይጠበቅ ይሆናል፡፡ ሁሉም ነገር በአጭሩ በመጠን ሲሆን በመልካም የሚታይ፤ መጠኑን ሲያልፍ ደግሞ በተቃራኒው፡፡ የቀለም መብዛት የአንድን ሠዓሊ ስራ እንዳይመረጥ ሊያደርገው መቻሉ ከእዚህ አንጻር ያስኬዳል፡፡
ወደ ኋላ ሄደን የዓለምን ታሪክ በምንመለከትበት ጊዜ ስለ በዛ ቀለም ሳይሆን የምናገኘው ስለ በዛው የደም ጎርፍ ነው። በጦርነት ምክንያት የሰው ልጅ አሰቃቂ መከራዎችን ተጋፍጧል፤ ዛሬም መከራውን እየተጋፈጠ ይገኛል፡፡ መንገድ ላይ ሰዎች ሲደባደቡ ገጥሞን ያውቅ ይሆን? ገጥሞንስ ከነበረ ምን ተሰማን? በተለይ በድንጋይ፣ በዱላ፣ በስለት ወዘተ የታገዘ ድብድብ ከሆነ በአይናችን ሙሉ ማየት መቻላችን አጠራጣሪ ነው፡፡
ሰዎች እየተደባደቡ ደማቸው ሲፈስ እንዲሁ እንደቀላሉ ማየት የምንችለው ስላልሆነ፡፡ ምክንያቱም አይደለም የሰው ደም ይቅርና፤ የእንስሳትም ቢሆን አስደንጋጭ ስለሆነ። ቀለም ሲበዛ ለአይን ምቾት የማይሰጥ መሆኑ ከሰው ደም አንጻር አብሮ የሚቀርብ አይደለም፡፡
በተጨባጭ ግን የበዛው የሰው ልጅ ደም መፍሰስ ከበዛው የሰዓሊ ቀለም አይነት ድንጋጤን የማይፈጥርበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ በዓለማችን ውስጥ በተደረጉ ጦርነቶች ሚሊዮኖች ሕይወታቸውን እንዲያጡ ሆነዋል፡፡
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የ60 ሚሊዮን ሕዝብን ሕይወት መንጠቁን ከታሪክ ማህደር እንረዳለን፡፡ የበዛው የደም ጎርፍ፤ የበዛው የሰው ልጅ መከራ እንዲሁ በታሪክ መዝገብ ውስጥ ለትምህርታችን ይገኛል፡፡
የሰው ልጅ ግን ዛሬም የክቡሩ ሰው ሞት ያን ያህል ቁብ ሳይሰጥ አሁንም በብረት ችግሩን ለመፍታት ሲጣደፍ እንመለከታለን፡፡ ሰላምን መፈለግ ላይ የሚደረገው ጉዞ ከብእር ቀለም ይልቅ በሰው ልጅ ደም መሆን የለበትም፡፡ ሙስና ሲበዛ፤ ፍትህ ሲዛባ፤ ሰዎች በማንነታቸው ሲገለሉ፤ የክቡራን ደም እንዲሁ ሲፈስ ነገሮች ግራ ያጋባሉ የሰላም መጥፋትም ችግር ጎልቶ ይሰማናል፡፡
ቀላሎቹ መንገዶች
የውስብስብ ችግሮች መፍቻው ቀላል ተብሎ የሚታስብ እሴት ነው፡፡ ሰላም ፈላጊነት የደካማ ሰዎች ወይንም የፈሪ ሰዎች መገለጫ ተደርጎ ይታሰብም ይሆናል። ፍቅርም ሆነ ይቅርታ፤ መደማመጥም ሆነ በራስ ጫማ ሌላውን ማሰብ በቀላል መንገድ ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ቀላል ማለት ዋጋ የሌላቸው ማለት ሳይሆን ብዙ ዋጋ ሳያስከፍሉ ትልቅ ውጤት የሚያስገኙ በመሆናቸው ነው።
ሠዓሊው ታዳጊ ይዞ የቀረበው ጽሁፍ ውስብስብነት የጎደለው በመሆኑ ከተመልካቹ ዘንድ አስተያየት እንዲቀርብለት ምክንያት ቢሆንም ባልተወሳሰበው ሥዕል የተላለፈውን መልእክት የሰው ልጅ ቢኖር ሰላሙን ባገኘው ነበር፡፡ የእውቀት መለኪያው ችግርን መፍታት መቻል እንጂ ችግርን መፍጠር አይደለም ብለን የምናስብ ከሆነ ችግርን መፍታት የሚቻልባቸውን መንገዶች ስናጤን የምናገኘው ምላሽ ቀላል የሚባሉ እሴቶች ሆነው እናገኛለን፡፡
ጣሊያኖች ዳግም ሊወሩን በመጡ ጊዜ እኛንም እንደ ሕዝብ እያንዳንዱን ዜጋ እንደ ሰው በመቁጠር በቀላሉ የመተሳሰብ መንገድ ላይ ቢገኙ ኖሮ ወደ 300ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ለመሞታቸው ምክንያት ባልሆኑ ነበር። በእርጋታ ቁጭ ብሎ አንዱ በሌላው መነጽር ለማየት እየሞከረ፤ አንዱ በሌላው ጫማ እየተገኘ ችግሩን እየፈታ ካልሄደ በመወሳሰብ ውስጥ ዘመናችንን እንጨርሳለን፡፡ የመፍትሄ ሰው በአጠገቡ ያለውን ችግር ቆጥሩ ለችግሩም ምላሽ ለመስጠት የበኩሉን ያዋጣል፤ ችግርን በመፍታት ውስጥ ራሱን ይሰይማል፡፡
ለመፍትሄውም ሁሉም ሰው የሚያውቃቸው ቀላል የሚባሉ መንገዶች የተሻሉ መሆናቸውን ይረዳል፡፡ የጦርነት መነሻ ዋና ምክንያት ተብለው የተለዩ ስምንት ነጥቦች አሉ፡፡ ሁሉም ግልጽ የሆኑና መተሳሰብ ቢቻል፤ አንዱ በሌላው ጫማ ሆኖ ማሰብ ቢቻል ምክንያት የተባሉት ነጥቦች ምክንያት መሆን ባልቻሉ ነበር፡፡
ስምንቱ ነጥቦች የኢኮኖሚ ጥቅም፣ የድንበር ጥቅም፣ ሐይማኖት፣ ብሔርተኝነት፣ ብቀላ፣ ሕዝብ ለሕዝብ ግጭት፣ አብዮት እና ተከላካይነት ናቸው። ወደ ጦርነት የሚገቡ አካላት ከእኒህ ስምንት ነጥቦች ቢያንስ በአንዱ ምክንያት የሚገቡ እንደሆነ በሰፊው ይታመናል። ስምንቱን ነጥቦች አንድ በአንድ በአትኩሮት ብንመለከታቸው ሁሉም ቀላል ተብሎ ሊጠቀስ በሚችሉ መርሆች ሁለቱም ወገኖች ቢገዙ ከጦርነት እንዲመለሱ ማድረግ የሚቻሉ ናቸው፡፡
ለምሳሌ የኢኮኖሚ ጥቅምን ለማስፋት የሚነሳ ጦርነት በመተሳሰብ ውስጥ ወደ መፍትሄ መድረስ የሚቻል ነበር፡፡ በመስጠትና በመቀበል አንዱ የሌላውን ችግር በመረዳት ወደ መፍትሄ መድረስ የሚቻል ሆኖ ሳለ የሰው ልጅ ብረት አንስቶ ይዋደቃል። የተጣላበትን ኢኮኖሚ አብሮ ያጠፋውና አብሮ ይቸገራል። ጦርነት አንዳንዴ በግዴታ የሚገባበት መሆኑ እሙን ነው፡፡
ብቀላ ግን በግዴታ የሚገባበት አይደለም፡፡ ከስምንቱ አንዱ በብቀላ ምክንያት የሚነሳ ጦርነት ነው። የወቅቱ የአገራችን ፖለቲካ ችግር ከትላንት የተሻገረ ብቀላን ልብስ ያደረገ መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ይመስላል። ነገር ግን የጦርነቱን የመጀመሪያ ጥይት የሚተኩሰው አካል ቀላል በሚባሉት የመተሳሰብ መንገድ ውስጥ የሚፈልገውን አግኝቶ ሰላምን አስጠብቆ የመሄድ ሰፊ እድል እንዲኖረው መንገዱን ቢመርጥ ከብቀላ ይልቅ ልቆ ለመውጣት እድል ነበረው፡፡
እድል ጠፍቶ ወደ ጦርነት ያመሩ የመኖራቸውን ያህል በደካማ ምክንያቶች ሚሊዮኖችን ማገዶ ያደረጉ መሪዎች መኖራቸውን የታሪክ ዶሴ ውስጥ እውነቱ ይገኛል፡፡
ቁጥር ሲናገር
ቁጥር ስለጦርነት ብዙ ይናገራል፡፡ ቁጥር ሰላምን ለማንበር ብዙ ስለደከሙ ጥቂቶችም ይናገራል፡፡ ቁጥር ሰላም የማጣት ሰለባዎች ድንገት ቤታቸው ተበትኖ አሳዛኙን ገፈት ሲጋቱ ራሳቸውን እንደ ፊልም በቅጽበት ማግኘታቸውን ይናገራል፡፡ ቁጥር ብዙ ነገሮችን የሚናገር መሆኑን መነሻ በማድረግ ታዳጊው ሰዓሊ ሰላምን ስለመፈለግ ቁጥሮችን ደረደረ፡፡ በቁጥር ጦርነትን ገለጸው፤ በቁጥር የሰላምን አስፈላጊነት አወጀ፡፡
የሰው ልጅ በትላንት በሆኑት ነገሮች መካከል በቁጥር ትምህርት ቢወስድ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ባልተነሳ ነበር፡፡ የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት የ20 ሚሊዮን ሕዝብን ሕይወት ቀጥፎ ሲያልፍ ከትላንቱ መማር ያልቻለው ዓለም በተመሳሳይ አገር በጀርመን አማካኝነት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መነሻ ሆኖ ከመጀመሪያው የከፋ ሦስት እጥፍ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፎ ሪከርዱን 60 ሚሊዮን አደረሰው፡፡
ቁጥር የሚናገረውን ችላ ማለት ከእዚህ በላይ ምን ሊኖር ይችላል? ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ቢነሳ የትላንትናው ቁጥር በስንት ተባዝቶ የሙታን ክምር ስንት ይደርሳል? ለመቁጠርስ የሚችሉ ሰዎች ይገኙ ይሆን? በሚሊዮኖች የሰው ልጅን በጦርነት እየገበሩ ከመኖር የሰው ልጅ ለምን የሰላምን መንገድ መከተል አቃተው? ምድር የተፈጥሮ ከፍተኛ ጥገኛ በሆነችበት ሁኔታ እንዴት የሰው ልጅ ራሱንም ተፈጥሮንም እያወደመ የአላዋቂነት መንገድ ውስጥ መኖርን መረጠ? የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ውጭ በራሱ መኖር እንደማይችል መረዳትን ሳይችል ቀርቶ ዛሬም በመገዳደል ውስጥ መፍትሄን ከመፈለግ የትላንት ቁጥሮች ሊያስተምሩት ይገባል፡፡
ጦርነትን በቁጥር በመመልከት መሪዎች ራሳቸውን በእያንዳንዱ ሟች ስሜት ውስጥ በመጨመር የአንድን ሰው ዋጋ ግምት ውስጥ ያስገባ የመፍትሄን መንገድ መራመድ ይገባቸዋል፡፡ ዓለማችን ሃይማኖትን መነሻ አድርጋ ባደረገችው ጦርነትም እንዲሁ ሕይወታቸውን ያጡ ጥቂቶች አይደሉም፡፡
ክሩሴድና የሰላሳ አመታቱ ጦርነት ታሪኮችን ስናጠና የምናገኘው ለሃይማኖት ተብሎ ብረት ማንሳት የሚያስከፍለውን ዋጋ ነው፡፡ በጦርነት ምክንያት እምነትን ማስፋፋት በምን አይነት መንፈሳዊ ስሌት እንደሆነ መገንዘብ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሃይማኖት ሰላም የሚሰጥ እንጂ ሰላምን የሚያሳጣ ሊሆን አይገባውምና፡፡ በሰይፍ የተገኘ፤ በሰይፍ እንደሚጠፋ ባለመረዳት ዛሬም የሰው ልጅ ከሰይፍ ውስጥ መፍትሄን ፍለጋ ይገኛል፡፡ በቁጥር የተገለጸው የታዳጊው ሥዕል ብዙም ተመልካቾችን የሚያስደስት ሳይሆን ቀርቶ መጨረሻ ወጣ፤ መጨረሻም በመውጣቱም ተሸለመ፡፡
አዘጋጆቹ የሸለሙት መጨረሻ የወጣው ሥዕልም የሚናገረው ብዙ ኖረው፡፡ ስለ ሳለም ብዙ ጥናት ሳይደረግ ቁጥሮችን ብቻ ተመልክተን አላስፈላጊ ዋጋ እንደ ሰው እየከፈልን መሆኑን መመልከት እንደምንችል የሚያስረዳ ነውና። የኢትዮጵያ ሕዝብ ግምታዊ ቁጥሩ ወደ 120 ሚሊዮን መድረሱን በሚነገርበት ሰሞን ውስጥ ሆነን 60 ሚሊዮን ሕዝብ በጦርነት ያጣቸው ዓለማችን የኢትዮጵያን ግማሽ ያህሉን ሕዝብ አጥታ እንደነበር ብናስብ የአደጋውን ብዛት በደንብ ያሳየናል፡፡ ትላንት ይህን ታሪክ ያሳለፈችው ምድር ከሰሞኑን ለሦስተኛው የዓለም ጦርነት የምታደርገው እንቅስቃሴ የሰው ልጅ መቼ ነው የሚሰለጥነው? የስልጣኔስ ትርጉም ምንድን ነው? ወዘተ የሚል ጥያቄን ለመጠየቅ ምክንያት ይሆናል፡፡ እያንዳንዱ የጦርነት ታሪክ ውስጥ ጊዜ አሳልፈን ጥናት እናደርግ ብንል ቁጥሮች ብዙ የሚሉት አላቸው።
የሞተው፤ የቆሰለው፤ ከቤተሰቡ እስከወዲያኛው ተለያይቶ የቀረው፤ ወላጆች ያጣው፤ አካል ጉዳተኛ የሆነው፤ አሰቃቂ ሞትን የሞተው፤ አዕምሮ መታወክ የገጠመው ወዘተን በቁጥር አስቀምጠን ልናይ እንችላለን፡፡
ለሥዕል ተመልካቹ ደስ ባይሉም ቁጥሮች ግን ብዙ ታሪክ ተሸክመዋል፡፡ ለአስራ ሰባት አመት በኢትዮጵያ ውስጥ የተደረገው የእርስ በእርስ ጦርነት 500ሺ ገደማ ሕዝባችንን ጨርሶ የመጣው ለውጥና የኢትዮጵያ ሕዝብ የዛሬ ኑሮውን አመሳክረን “ለምን ይህን ሁሉ?” ብለን ብንጠይቅ ያስኬዳል፡፡ እንዴት ትርጉም በሌለው ሕይወት ውስጥ ራሳችንን ላለመጨመር ቀላል የሚባለው የሰላም መንገድ አይገዛንም? ብረት ያነሳችሁ ብረት አስቀምጡ። የጎደለው ፍትህ በሰላም ይተካ፡፡
ከጦርነት ከሚገኘው ቀላል በተሰኙ እሴት ወለድ መንገዶች የሚገኘው ዘላቂ ነው፤ ደግሞም የተሻለ፡፡ ከ60 ሚሊዮን ሕዝብ እልቂት በኋላም የሰው ልጅ ዳግም ብረት እየሳለ ነው፡፡ መፍትሔው ቀላል ያልናቸው የእሴት መንገዶች ናቸው፤ ትላንትም ዛሬም፡፡
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን መጋቢት 3 /2014