ሀገር የትውልዶች ቅብብሎሽ ውጤት ናት። በዚህ መሃል መወለድ ማደግ መታመም መሞት ቢኖርም የተወለደው የሞተውን እየተካ ሕይወት ቀጥሏል። በዚህ ሂደትም ቅጠል በጥሶ የዳነ፤ ዳማከሴን አሻሽቶ የተፈወሰ ጥቂት አይደለም። በማናውቃቸው ባሕላዊ መድኃኒቶች ፈውስን ያገኙም በርካታ ናቸው። ለዚህም ቀደምቶቻችን ሊመሰገኑ ይገባል። በእነርሱ ጥረት ሕመሞች ተለይተው ታውቀዋል። በሽታዎች መፍትሔ አግኝተዋል። ሲማቅቁ የነበሩ ሰዎች ቀና ብለው እንዲሄዱ ሆነዋል። ሕይወታቸውን ሊያጡ የነበሩም አዲስ ሕይወታቸውን ቀጥለዋል። ለዚህም ነው ባሕላዊ መድኃኒቶቻችን ዛሬ ድረስ በትውልድ ቅብብሎሽ እዚህ ላይ የደረሱት።
በሀገራችን የባሕል መድኃኒትን ለትውልድ በማስተላለፍ የሚታወቁ ሕዝቦች አሉ። ዛሬ በምናባችን የምንጓዘው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከሚገኘው የም ዞን ነው። የዞኑ ዋና ከተማ የሆነችው ሳጃ ከአዲስ አበባ በ239 ኪሎ ሜትር ርቀት ከክልሉ ዋና ከተማ ሆሳዕና በ221 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።
የየም ማህበረሰቡ ከእጽዋት ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው። አብዛኛው ማህበረሰብ በግብርና የሚተዳደር ሲሆን፤ በተለይ እንሰት የኑሮው መሠረት ነው። ከእንሰት ዎቶ፣ ናቱ፣ ዳኣ፣ ባራሳ(ባራሲኛ)፣ ኡዋ፣ ኬራ፣ እርካ የተሰኙ ጣፋጭ ምግቦቹን አዘጋጅቶ ይመገባል። ሾሮዶ (ባሕላዊ የልብስ ሳጥን)፣ ኦፖ(ጂባ)፣ ጋዱ(ገመድ) የተሰኙ የቤት መገልገያዎችን ከእንሰት አዘጋጅቶ ለቤት ፍጆታ ያውላል። በተመሳሳይ እነዚህን ሥራዎቹን ሸጦ ከሚያገኘው ገቢ ይጠቀማል።
የየም ሕዝብ ከእጽዋት ጋር ያለውን ቁርኝት የዞኑን መልክዓ ምድር ያየ ሰው ይገምታል። አካባቢው በአረንጓዴ እጽዋት ያጌጠ ነው። በተለይ ከባሕር ጠለል 2939 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘው የቦር ተራራ ሙሉ አረንጓዴ ለብሶ መመልከት ለዓይን ከመማረኩም በላይ የአዕምሮን ሰላም ያድሳል።
ለየም ሕዝብ ጥቅምት 17 ልዩ ቀን ነው። ስለዚህም አረንጓዴ ከለበሰው ቦር ተራራ ያለ ቀጠሮ ይገናኛል። ከአባቶቹ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የመድኃኒት ቀለቡን በነፃ ሊሸምት በማለዳ ከተራራው ይከትማል። በዕለቱ ቁርስ ስጡኝ፤ ስንቅ አዘጋጁልኝ ሳይሉ ሁሉም ፀሐይን ቀድመው ከተራራው አናት ላይ ይከትማሉ።
የዞኑ ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ሞጋ እንደሚሉት፤ የየም ማህበረሰብ ከተፈጥሮ እጽዋት መድኃኒት ለቅሞ በመቀመም ሕይወትን ታድጎ የቆዬ ነው። በአካባቢው ጤንነትን ጠብቆ የሚኖር ስለሆነም ምድሩን የፈውስ ምድር እስከ ማለት ይደርሳል። ለዚህ ደግሞ ጥቅምት 17 በቦር ተራራ ላይ የሚበቅሉ እጽዋት እና አበቦች ምስክር ይሆናሉ። እነዚህ እጽዋት ምድሪቱን ሞልተው ለሕዝቡ ጥንካሬን ያላብሳሉ፤ እስትንፋስንም ይመልሳሉ። በመሆኑም ጥቅምት 17ን “አጋማሽ ወር” በመሆኑ እና ከዚህ ወቅት ካለፈ ደግሞ የሚደርቁ በመሆኑ ዕለቱ ተመርጦ የመድኃኒት መሰብሰቢያ ቀን እንዲደረግ ሆኗል።
በየዓመቱ የመድኃኒት እጽዋት የሚለቀምበት 2939 ሜትር የሚረዝመው ቦር ተራራ ሲሆን፤ በዞኑ ከፍ ብሎ የሚታይ ቦታ ነው። የመጀመሪያውን የማለዳ የፀሐይ ብርሃን ቀድሞ የሚያገኝ መሆኑ ደግሞ ተመራጭ አድርጎታል። ቦታው ላይ የሚገኘው እፅዋት የበሽታ መከላከልና ፈዋሽነት አቅም ከፍተኛ እንደሆነም ይታመናል። የሞች ፈጣሪ ፈቅዶ በሰላምና በጤና ለጥቅምት 17 ከደረሱ በማለዳ መገኛቸው ቦር ተራራ ነው። የበረታው በእግሩ፣ ካልሆነም ባገኘው የመጓጓዣ አማራጭ በቡድንም ሆነ በተናጠል ሳይታመም ከመድኃኒቱ ሊገናኝ ይጓዛል። ታሞ አልጋ ከያዘ፣ በእድሜ ምክንያት አቅም ካነሳቸው አዛውንቶች በስተቀር ማንም አይቀርም።
ዕለቱ የዓመት የመድኃኒት ስንቅ የሚሰበሰብበት ነውና ለሰበሰቡት መድኃኒት መያዣ ማዳበሪያ፣ ጆንያ፣ ላስቲክና ሌሎች የሰበሰቡትን ሊይዙ የሚችሉ መያዣዎችን ይዘው ከተራራው ይገኛሉ። መድኃኒት መሰብሰቡ ቅጠል ከመቁረጥ አለፍ ሲል ሥሮችን ወደ ማውጣት፣ የዛፍ ቅርፊት ወደ መሰብሰብና ቅርንጫፎች ወደ መቁረጥ ይሻገራል። ስለዚህም መቆፈሪያና መቁረጫዎችም የያዙ የተሻለ ሰብሳቢ ይሆናሉ።
ዓመታዊ የመድኃኒት ለቀማ ትዕይንቱ ማራኪና ለየት ያለ ባሕላዊ እውቀት የሚንፀባረቅበት ነው የሚሉት የቢሮ ኃላፊው፤ መድኃኒቱ የሚለቀመው ከተለያዩ የዛፍ፣ የሣር እና የሀረግ ዓይነቶች መሆኑን ይናገራሉ። በቦር ተራራ ላይ የደረሰው ሁሉ ያለ ምንም ከልካይና ጠያቂ ከተከለከለው እጽዋት ውጭ ያሉትንና ይጠቅሙኛል ያላቸውን ለይቶ መልቀም ይችላል። መድኃኒት ሰብሳቢዎቹ የዛፍና የሣር ዝርያዎችን ቅጠሉን ቅርፊቱንና ሥሩን መልቀም ይጀምራሉ። በዕለቱ ሕብረተሰቡ ለዓመት የሚጠቅመውን መድኃኒት የሚሰበስብ ይሰበስባል።
የሞች የሚሰበስቡት መድኃኒት ለሰው ብቻ ሳይሆን ለእንስሳትም ያገለግላል። እንስሳቱም የእነሱ አካል ናቸውና እነርሱን ማከሚያ ብልሀቱን ከነመድኃኒቱ ከአባቶቻቸው ወርሰዋል። በቦር ተራራ ላይ የተለመዱ እስከ 210 ዝርያዎች ያሉት እጽዋት መኖሩን የሚገልጹት አቶ መስፍን፤ ከእዚህ ውስጥ የ106 እጽዋት ጥቅማቸው ተለይቶ መታወቁንና ለመድኃኒትነት የሚያገለግሉ መሆናቸውን ያስረዳሉ። መድኃኒቱ በአካባቢው ማህበረሰብ ሳሞ-ኤታ በመባል የሚታወቅ ሲሆን፤ ትርጉሙም የከረመ መድኃኒት ማለት ነው። ሳሞ-ኤታ ባሕላዊ መድኃኒት ከተለያዩ በሽታዎች የሚፈውስ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ለዘመናዊ ህክምና የሚያወጣውን ወጪ ከመቀነሱም ባሻገር የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የሚያስተሳስር መሆኑን ይጠቁማሉ።
እንደ አቶ መስፍን ማብራሪያ፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣውን የቦር ተራራ በፈዋሽነቱና ቦታው ላይ ብዙ እፅዋት ስለሚገኝ፤ በርካታ የመድኃኒት እጽዋት በአንድ ቦታ በማግኘት በርካታ መድኃኒት መቀመም ይቻላል በሚል እሳቤ ማሕበረሰቡ ፈዋሽ ብሎ ተስማምቶበታል። ለጤና ጠንቅ የሆነውን በሽታ ለመከላከልና ለማስወገድ ሲባል በባሕላዊ መንገድ ጤንነትን የመጠበቅ ዘዴ ከጥንት ጀምሮ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ በመሆኑ የባሕላዊ መድኃኒት ለቀማው፣ቅመማውና ህክምናው በስፋት በብሔረሰቡ ውስጥ ሰርፆ የቆየ ሀገር በቀል ዕውቀት ነው። ዘመኑ የዘመናዊ ህክምና ተስፋፍቶበታል ተብሎ የሚታሰብበት ቢሆንም በዞኑ ባሕላዊ መድኃኒት በቀላሉ እና ነፃ በሚባል ደረጃ በመገኘቱ አሁን ድረስ ተፈላጊ ሊሆን ችሏል። የባሕል መድኃኒቱ የጎንዮሽ ጉዳት የሌለበት መሆኑን በማንሳት ሕብረተሰቡ በሰፊው ይጠቀመዋልም።
ጥቅምት 17 ሁሉም ያለ ከልካይ በቦሩ ተራራ ላይ ለዓመት ይበቁኛል ብሎ የሚያስባቸውን የመድኃኒት ግልጋሎት ያላቸው ቅጠላ ቅጠሎች፣ ስራስሮች፣ ቅርፊቶች ወደ መኖሪያ ቤት ተወስደው የሚለዩ ናቸው። ከተራራው የተሰበሰበውን የመድኃኒት ዝርያ በዓይነት ማደራጀትና ወደ መድኃኒትነት መቀየር ቀናትን ይወስዳል። የሚደርቀውን ማድረቅ፣ የሚወቀጠውን መውቀጥ፣ እንደ አስፈላጊነቱም ከሌላ እጽዋት ጋር መቀላቀል የግድ ይላል። በዚህም በተቀሩት የጥቅምት ቀናት አብዛኛው ሰው በአካባቢው መድኃኒት ያዘጋጃል።
የተቀመመው መድኃኒት በንፁህ ዕቃ ተቀምጦ እስከ መጪው ዓመት ድረስ ብቻ አገልግሎት ይሰጣል። ዓመት ካለፈው በኋላ የተረፈ መድኃኒትም ካለ የአገልግሎት ጊዜው አልፏልና ይወገዳል እንጂ አገልግሎት ላይ እንደማይውል የሚናገሩት አቶ መስፍን፤ ከመድኃኒት እጽዋት ልየታው፣ እስከ ቅመማ፣ እንዲሁም አወጋገድ ድረስ ያለው ሂደት እውቀት ይፈልጋልና እውቀቱን ከወላጅ የወረሱ የዛሬ ወላጆች እነሱም በተራቸው ለትውልድ ያስተላልፋሉ ይላሉ።
በዕለቱ የመድኃኒት ለቀማው ሥርዓት በተለያዩ አካባቢዎች የሚካሔድ ቢሆንም በዋናነት የፆታ፤ የሃይማኖት፤ የዕድሜ ልዩነት ሳይኖር ሰዎች ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ቦር ተራራ በመውጣት ይለቅማሉ። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተሠራው ባሕሉን የማስተዋወቅ ሥራ ከየሞች በተጨማሪ ጥቅምት 17 በቦር ተራራ ላይ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና በርካታ ቱሪስቶች በመድኃኒት ለቀማው ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ። በዕለቱ በቦር ተራራ ላይ ከሚገኙት ሱሉቶ እና ቶቱ ከሚባሉት የእፅዋት ዓይነቶች በስተቀር ሁሉም ይለቀማል። እነዚህ እጽዋት ለጊዜው ጥናት ስላልተደረገባቸው እንጂ ለመድኃኒትነት አገልግሎት ባይውሉም መርዛማነት ያላቸው በመሆኑ ለተባይ ማጥፊያና ለሌሎች አገልግሎቶች መዋል የሚችሉ ናቸው ተብሎ እንደሚገመትም አቶ መስፍን ያስረዳሉ።
በተለያዩ ምክንያቶች በሳሞ-ኤታ ላይ ሳይሳተፍ የቀረ መድኃኒት ፈላጊ የፈለገውን መድኃኒት ቢጠይቅ የሄዱት አይከለክሉትም። በየሞች እያለ የለም ማለት አይታሰብም። ሲጀመር መድኃኒቱን ሲሰበስቡም በተለያየ ምክንያት ወደ ተራራው የማይመጡትን ታሳቢ ያደርጋሉ። ስለዚህም በየም ሕዝብ ዘንድ የሰበሰቡትን መድኃኒት ማካፈል ባሕል ነው። መጀመሪያውንም ከአቅም በላይ ምክንያት ካልገጠማቸው የሞች ከሥርዓቱ አይቀሩም።
የቢሮ ኃላፊው በማህበረሰቡ በሀገር በቀል እውቀት ከ60 በላይ ለሚሆኑ ዋና በሽታዎች ፍቱን የሚሆኑ መድኃኒቶች ተለቅመውና ተቀምመው ለሰው እና ለእንስሳት ይሰጣሉ ይላሉ። የየም ብሔረሰብ የባሕል መድኃኒት አጠቃቀም ሀገር በቀል እሴት ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ልዩ የሆነ እና ሕብረተሰቡ በሙሉ የሚጠቀምበትና የሚጠብቀው ነው። ባሕሉ በደንብ ቢተዋወቅ ለሀገሪቱ የቱሪስት መስህብ ከመሆን ተጨማሪ የገቢ ምንጭ መሆን የሚችል እሴት እንደሆነ ይጠቅሳሉ። የዞኑ አስተዳደር ሳሞ-ኤታን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመንቀሳቀስ ላይ እንዳለም ያነሳሉ።
የሞች ሰውነታቸው ገብቷቸዋል። ዛሬን በጤና ቢንቀሳቀሱ የዛሬ ጤንነታቸው ለነገ ዋስትና እንደ ማይሆናቸው ተረድተዋል። ለዚህም መድኃኒታቸውን ቀድመው አዘጋጅተው መጠበቅን ምርጫቸው አድርገዋል። በትውልድ ቅብብሎሽ እዚህ የደረሰን ባሕል ማዳበር ደግሞ የዚህ ዘመን ቀጣይ የቤት ሥራ ነውና ባሕሉን እንንከባከበው።
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም