የአገር ሰላም፣ እድገትና ሥልጣኔ ሲታሰብ በሥነምግባር፣ በእውቀትና በአካል የበለጸገ ወጣት ሊኖር ግድ ይላል። ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ቁጥር ከስልሳ እስከ ሰባ በመቶ የሚሆነው ወጣት እንደሆነ ጥናቶች ያመላክታሉ።
ይህን ትኩስ ሃይል በሥነምግባር አንጾና በእውቀት ገንብቶ ወደ ሥራ ማስገባት የሚያስችል አሠራር ቢዘረጋ ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ተስፈንጥሮ መውጣት የማይቻልበት ምክንያት አይኖርም። ወጣትነት መሉዕነት ነው።
ያልደከመ አዕምሮ፣ ያልዛለ ጉልበት፣ የለመለመ ተስፋ ይታይበታል። ከሌላው የሕብረተሰብ ክፍል በተለየ ቴክኖሎጂን ለመቀበል ዝግጁነትና ፍጥነት ያለው ወጣቶች ጋር ነው። ለውጡን ተከትሎ ባለፉት ሶስት ዓመታት ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል። ካለው የሥራ አጥ ቁጥር ብዛት አንጻር የተፈጠረው የሥራ እድል በቂ ነው ማለት ባይቻልም በርካቶችን ተጠቃሚ ያደረገ ስለመሆኑ ግን አይካድም። የሕዝብ ቁጥር መጨመርን ተከትሎ በየጊዜው የሥራ አጥ ቁጥር እያደገ መሆኑ ባይካድም የዚያኑ ያህል ጊዜውን በአልባሌ ነገር የሚያሳልፍ፣ ለሱስ ተጋላጭ የሆነ፣ የጠባቂነት መንፈስ የተጸናወተው፣ አገሩ ከእርሱ ምን እንደምትጠብቅ በቅጡ ያልገባው፣ ሥራ ከመፍጠር ይልቅ ሥራ የለም ብሎ እጁን አጣጥፎ የሚቀመጥ ወጣት በርካታ ነው። ችግሩ ዓመታትን ተሻግሮ እዚህ የደረሰ መሆኑ ይታወቃል።
አሁን መንግሥት በያዘው የልማትና እድገት አቅጣጫ መሰረት አገሩን የሚወድ፣ በሥነ ምግባር የታነጸ፣ በሥራ የሚያምንና ለሥራ ዝግጁ የሆነ፣ የነገዋን ኢትዮጵያ የሚረከብ ትውልድ ለማፍራት በተለያዩ ተቋማት አማካኝነት መርሃ ግብሮችን ዘርግቶ እየሠራ ይገኛል።
ከሰሞኑም የሴቶችና ማሕበራዊ ጉደዳይ ሚኒስቴር ሁለት ሚሊዮን ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ‹‹ከፍታ›› የተሰኘ መርሃግብር ይፋ አድርጓል። ፕሮጀክቱ ከአሜሪካ የልማት ተራድኦ /USAID/ በተገኘ የስልሳ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ በአምሬፍ ሄልዝ አፍሪካ /Amref Health Africa/ አጋርነት የሚተገበር መሆኑ ታውቋል።
የዛሬው የወጣቶች አምድ ዝግጅታችን ‹‹ከፍታ የተቀናጀ የወጣቶች ልማት የፕሮጀክት››ን ዓላማና አተገባበር አስመልክቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ያደረገውን ቆይታ የሚያስቃኝ ይሆናል። አቶ አድነው አበራ በሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ሃላፊ ስለጉዳዩ ሲያስረዱ፤ ወጣቶች በአገራችን ኢትዮጵያ በሚስተዋለው ሁለንተናዊ ችግር የመፍትሄ አካል በመሆን ከሚገኘው ውጤት ተቋዳሽ /ተጠቃሚ/ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
ይህም ተግባራዊ የሚሆነው በዘመቻ ሳይሆን በእቅድና በፕሮግራም ሲመራ ነው ይላሉ። በዚሁ መሰረት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ፕሮጀክት ቀርጾ ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ የሚያስፈልገውን የፋይናንስ ድጋፍ ካገኘ በኋላ በተቀመጡ መመዘኛዎች የት የት አካባቢዎች እና ከተሞች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ያስፈልጋል የሚለው ከተጠና በኋላ ወደ ሥራ እንደተገባ ገልጸዋል።
በዋናነት ትኩረቱ የወጣቶችን ስብዕና መገንባት ሲሆን ጎን ለጎንም የሥራ ፈጠራ ክሂላቸውን እንዲያዳብሩ ያግዛል። የመርሃ ግብሩ ዓላማ ወደፊት ኢትዮጵያን የሚረከቧት የዛሬዎቹ ወጣቶች በሥነምግባር የታነጹና የሥራ ባህልን ያዳበሩ፣ የመተባበር፣ የመፈቃቀርና የአንድነት መንፈስን ያጎለበቱ፣ መርምሮ መረዳትን፣ ምክንያታዊነትን የተለማመዱና ሃላፊነትን መሸከም የሚችሉ ትውልዶችን ማፍራት ነው። የተሟላ ሰብእና ያላቸው ወጣቶችን በማፍራት የኢትዮጵያ መጻኤ እድል በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ እንዲሆን ማስቻል ነው።
በአካልና በአዕምሮ የዳበሩ ጊዜያቸውን በአልባሌ ነገር ላይ ከማዋል ይልቅ በቁምነገር በማሳለፍ ለነገ የሚጠቅማቸውን አቅም የሚገነቡ ትውልዶችን ማፍራት የመርሃ ግብሩ ዓላማ እንደሆነ አቶ አድነው ይገልጻሉ። በጉዳዩ ዙሪያ አስቀድሞ ከክልሎች ጋር ውይይት እንደተደረገ የተነገሩት ኃላፊው በውይይቱ ወቅትም በርካታ ቁምነገሮች እንደተንሸራሸሩ ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በአዳማ ከተማ በተካሄደው ውይይት የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አህመድ ባለፉት ዓመታት በአገር አቀፍ ደረጃ ከሶስት ሺህ በላይ ወጣቶች በሰብእና ልማት ማእከላት ተገንብተው አካላዊ፣ አዕምሯዊ፣ ስሜታዊና ሌሎችም የማሕበራዊ ጤና አገልግሎቶች ተሳታፊ መሆናቸውን አስታውሰዋል።
በፋይናንስና በተለያዩ ምክንያቶች አብዛኛዎቹ ማእከላት አገልግሎት መስጠት የተሳናቸው መሆኑና በአሁኑ ወቅትም አንድ ሺህ አምስት መቶ አርባ አምስት የሚሆኑት ብቻ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ተወስቷል። የማዕከላቱን ችግር ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ ከተቋቋሙለት ዓላማ አንጻር ለወጣቱም ሆነ ለሕብረተሰቡ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑ ተገልጿል።
ማእከላቱ ከሚገጥማቸው ተግዳሮት መካከል አንዱ የፋይናንስ ችግር እንደሆነ ተገምግሞ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በአሁኑ ወቅት የራሳቸውን ገቢ እንዲያመነጩ የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያግዝ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱ ተጠቅሷል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ጤና ላይ ከሚሠራው ሥራ በተጨማሪ በወጣቶች ሰብዕና ላይ ያተኮረና ‹‹ከፍታ የተቀናጀ የወጣቶች ልማት›› የተሰኘ ፕሮጀክት በተመረጡ አስራ ስምንት የአገራችን ከተሞች ለመተግበር ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱን አቶ አድነው ይገልጻሉ። ከተሞቹ የተመረጡት በርካታ ወጣቶች የሚገኙባቸው መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ነው። ሰብዕናው የተገነባ ወጣት እራሱንም አገሩንም ለማሳደግ አቅም ይኖረዋል ያሉት አቶ አድነው ሥራ ጠባቂ ሳይሆን ሥራ ፈጣሪ መሆን ይችላል።
ከፍታ የተቀናጀ የወጣቶች ልማት መርሃግብርም ወጣቶች ከሚላበሱት መልካም ሰብእና በተጨማሪ በኢኮኖሚው ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት እያጎለበቱ እንዲሄዱ ግንዛቤ የሚፈጥርላቸው ነው ብለዋል።
ወጣቶች የሚውሉባቸውና የሚያዘወትሩባቸው ቦታዎች፤ የሚያይዋቸው ነገሮች፤ አዕምሯቸውን የሚገነቡ ተስፋቸው እንዲያብብ የሚያደርጉ ሊሆኑ ይገባል። የሰብእና ግንባታ ማእከላቱ እንዲህ አይነት ገጽታን የተላበሱ ሆነው እንደሚገነቡ ተናግረዋል። በዚሁ መሰረት ቀደም ሲል የነበሩት ማዕከላት ትርጉም መስጠት በሚያስችል ልክ እንዲጠናከሩና አዳዲሶችም በተሟላ ሁኔታ እንዲገነቡ በማድረግ በአምስት ዓመት ውስጥ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ ወጣቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል። የማእከላቱ መገንባት ወጣቶች በአገራቸው ፖለቲካ ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ ሆነው የአመራርና ውሳኔ ሰጪነት ክሂል እንዲያዳብሩ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር የሚያስችልም እንደሆነም ገልጸዋል።
ለራሳቸው፣ ለማሕበራሰባቸውና ለአገራቸው ጠቃሚ የሆኑ ሃሳቦችን እንዲያፈልቁ፤ ተቀራርበው እንዲነጋገሩና ስለአገራቸው ጉዳይ እንዲመክሩ፤ ሃሳብ እንዲለዋወጡና የሃሳብ ልእልናን የማክበር ልምምድ እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል። ወጣቶች ማሕበራዊ እሴቶቻቸውን እንዲያውቁና እንዲያከብሩ፣ ልምድና ተሞክሮዎቻቸውን እንዲለዋወጡ የሚያደርግ ነው።
በተመረጡት አስራ ስምንት ከተሞች የሚገነቡት የሰብዕና ማዕከላት በፌዴራልና በክልል መንግሥታት ክትትልና ድጋፍ ይደረግላቸዋል ያሉት የኮሙኒኬሽን ሃላፊው ማእከላቱ ምን ምን ማሟላት አለባቸው የሚለው በተቀመጠላቸው ስታንዳርድ መሰረት እየተገመገመ እንዲሟላ ይደረጋል፤ የበጀት ድጋፍ፣ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እና የምክር አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል። እስከ አሁን የነበሩት ማእከላት ለወጣቱ የሚፈለገውን ሰብእና አላብሰዋል ተብሎ አይታሰብም ያሉት አቶ አድነው ከዚህ በኋላ ግን ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራና ወጣቱ ከማእከሉ የሚገኘውን ጥቅም ተገንዝቦ በሌላ ሰው ግፊት ሳይሆን በራሱ ተነሳሽነት ወደ ማእከሉ እየሄደ ሁለንተናዊ ጥቅሞችን እንዲያገኝ የሚያስችል አሠራር ይዘረጋል ብለዋል።
የወጣትነት እድሜ በአግባቡ ካልተመራ ለተለያዩ ችግሮች ያጋልጣል ያሉት አቶ አድነው ማእከሉ እንደወላጅ ሃላፊነት ተሰምቶት በለጋ እድሜ ላሉ ታዳጊዎች ጭምር ጠቃሚውን መንገድ እንዲከተሉ ያግዛቸዋል። ይህ ሲሆን ለሥራ ፈጠራና ለልማት የተዘጋጀ ሃላፊነት የሚሰማው ትውልድ ይፈጠራል ነው ያሉት። ዶክተር ማስተዋል መኮንን የሥነ ልቦና ምሁር ናቸው፤ በወጣቶች መልካም ሥብዕና ግንባታ በስሜት መስከንና በስሜት ብስለት ወዘተ ሙያዊ ሥልጠናዎችን የመስጠት ልምድ አላቸው። በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጡን ጋብዝናቸው ተከታዩን ብለዋል።
የሴቶችና የማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው ‹‹ከፍታ የተቀናጀ የወጣቶች ልማት ግንባታ›› ብቁ ዜጎችን ከማፍራት አንጻር የማይተካ ሚና ሊጫወት የሚችል ነው ይላሉ። እንደሚታወቀው ወጣቶች በተለያዩ አሉታዊ ነገሮች እየተጠለፉ ነው። አብዛኛዎቻችን የደረሰባቸውን ጫና እና ያሉበትን ሁኔታ ሳንመለከት የአሁን ዘመን ትውልድ፤ የአሁን ዘመን ወጣት እያልን ጣቶቻችንን እንቀስርባቸዋለን።
በምን መንገድ እናግዛቸው? እንዴት መልካም ስብእና እንዲኖራቸው እናድርግ? ብለን አናስብም። ከዚህ አንጻር የማእከሉ ግንባታ እነዚህን ጥያቄዎች ሊመልስ ስለሚችል ወሳኝ ነው ይላሉ። ወጣቶች፣ ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚዊ ጉዳዮች ላይ ቀድመው ግንዛቤ ካልፈጠሩ በማሕበራዊ ሚዲያና በሌላም ጉዳይ ተጠልፈው ቀናውን መንገድ ሊስቱ ይችላሉ።
አምራችና አገር ተረካቢ መሆን የሚገባቸው ወጣቶች የሱስና የመጥፎ አስተሳሰብ ተገዢ እንዳይሆኑ በሰብእና ግንባታ ሊደረግላቸው ይገባል። የሰብእና ግንባታ አገርንና ትውልድን የማስቀጠል ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።
ወጣቶቻችንን አስቀድመን ጥሩ ነገር አሳየናቸው ማለት መጥፎ ነገሮችን እንዳያደርጉ መንገድ መራናቸው ማለት ነው። ትውልድ አገርን የሚረከበው በተስተካከለ ቁመና ላይ ሲገኝ በመሆኑ ይህ የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው መርሃግብር በአግባቡ የሚተገበር ከሆነ ትልቅ ጥቅም አለው። አሁን የሚታየውን አገራዊ አለመግባባትና ውዝግብ ማስቀረት የሚችል ነው። እራሱን፣ አካባቢውን፣ ማሕበረሰቡንና አገሩን የሚወድ ትውልድ ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።
ከመቶ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ባለበትና ከዚህም ውስጥ አብዛኛው ወጣት በሆነበት አገር ሁለት ሚሊዮን ወጣቶችን ብቻ ታላሚ ያደረገ ማእከል መገንባቱ ብዙኋኑን ተደራሽ የማያደርግ ቢሆንም አንድ ሳይባል ሁለት አይባልምና ለቀጣዩ መሰረት የሚጥል ነው። ይህ መርሃ ግብር እንደ ሙከራ ሊያገለግል ይችላል።
ዶክተር ማስተዋል በራሳቸው ተነሳሽነት አሜሪካን አገር ከሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በመተባበር በአንድ ከተማ ላይ የሰብእና ግንባታ የባህሪና የግንዛቤ ለውጥ የሚያላብሱ ሥልጠናዎችን ሰጥተው አበረታች ለውጦችን ማየታቸውን ይናገራሉ። ወጣቶቹ ራሳቸውንና አካባቢያቸውን ከተገነዘቡ በኋላ ከጠባቂነት ተላቀው ሥራ የመፍጠር ኪሂል እንዲያገኙ ተደርጓል። ይህ መርሃ ግብር በመንግሥት ደረጃ መጀመሩም አስደስቷቸዋል፤ አስፈላጊ ከሆነም የራሳቸውን ተሞክሮ ለማጋራትና ሙያዊ እገዛ ለማድረግ ፍቃደኛ መሆናቸውን ገልጸውልናል።
ተቋሙ መመስረት ብቻ ሳይሆን በባለሙያዎች እገዛ የሚደረግለት መሆን አለበት የሚሉት ዶክተር ማስተዋል አንዳንድ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ ወጣት ማእከል ተብለው የሚገነቡ ማእከሎች በወጣቱ ላይ የባህሪ ለውጥ በሚያመጡ መልኩ ሲመሩ አይታይም።
የሥራ እድል ፈጠራ ተብሎ ኮንቴኔር ተሰጥቷቸው ጫት ሲቅሙ የተመከቷቸው እንዳሉም ጠቅሰዋል። ስለዚህ ዝም ብሎ ተገነባ ለማለት ብቻ ሳይሆን የሥልጠና ማንዋሎች ተዘጋጅተው ባለሙዎች እገዛ የሚያደርጉበት ቢሆን የበለጠ ውጤታማ መሆን ይቻላል ብለዋል።
አሁን በአገራችን እየታየ ያለው ችግርና አለመግባባት የመሬት ወይም የተፈጥሮ ሀብት ችግር ሳይሆን የምእራባውያን ተጽእኖና ያንን ተንትኖ የመገንዘብ ችግር ነው ይላሉ።
ስሜታችንን መግዛትና መስከን አቅቶን አርስ በእርሳችን እየተጠላለፍን ነው ለዚህ የተዳረግነው። ያለፈው አልፏል፣ እሳት ነዶ ጠፍቷል። አሁን ችግሮቻችን በአገራዊ ምክክር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው።
እንግዲህ አገራዊ ምክክሩን እንዲመሩ የተመረጡት ሰዎች ካላቸው መልካም ሰብዕና፣ አስተሳሰብና አገራዊ ፍቅር አንጻር ነው። ያ ማለት ከዚህ ተቋም ምስረታ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት አለው ማለት ነው። ምክያቱም መልካም ስብዕና ያለው ሰው አገራዊ ምክክሩን እንዲያሳልጥ ከተመረጠ ይህ የወጣቶች ሰብእና ማጎልበቻ ማዕከልም መልካም ሰብእና ያለውን ሰው የሚያፈራ ስለሆነ አገራዊ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው።
የሰብእና ግንባታ ውስጣዊም ውጫዊም ሁኔታዎችን አካቶ ስለሚይዝ ማእከላቱ በባለሙያ ቢደገፉ የሚል ምክር ሰጥተዋል። ማእከሎቹ ወጣቱ ከአባቶቹ የወረሳቸውን የእርቅ፣ የሰላም፣ የመከባባርና የአብሮነት እሴቶቹን እንዲያስቀጥሉ ጭምር የሚያግዙ ሊሆኑ ይገባል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን መጋቢት 2 /2014