አዲስ አበባ፡- ሸባሪው ትህነግ በወረራ ይዟቸው በነበሩ የአማራና አፋር ክልሎች የስፖርት ተቋማት እና አገልግሎት መስጫዎች ላይ ከሶስት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት ማድረሱ ተጠቆመ፡፡ ተቋማቱን ለማቋቋምና መልሶ ሥራ ለማስጀመርም የማገገሚያ እቅድ እያዘጋጀ መሆኑን የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ከሚኒስቴሩ ድረ ገጽ የተገኘው መረጃ እንዳመለከተው፤ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በወረራ ይዟቸው በነበሩ የአማራ እና አፋር ክልሎች ከፍተኛ ሰብዓዊ ጉዳት ማድረሱ ይታወቃል፡፡ ከሰብዓዊ ጉዳቱ በተጨማሪም ሕዝብ የሚገለገልባቸውን ማሕበራዊ ተቋማት የዘረፈና ያወደመ ሲሆን፤ የጥፋት አሻራው ካረፈባቸው መካከል የባህልና የስፖርት ተቋማት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
እስካሁን ባለው መረጃ መሰረትም በስፖርት ዘርፍ ከነበሩ ተቋማት እና አገልግሎቶች 339 ሚሊዮን 883 ሲ 579 ( ሶስመቶ ሰላሳ ዘጠኝ ሚሊዮን ስምንት መቶ ሰማንያ ሶስት ሺ አምስት መቶ ሰባ ዘጠኝ ብር) በላይ የሚገመት ጉዳት ማድረሱን መረጃው ጠቁሟል፡፡ በባህል ዘርፍ ከነበሩ ተቋማት እና አገልግሎቶች ደግሞ 120 ሚሊዮን 824 ሺ 938 (አንድ መቶ ሃያ ሚሊዮን ስምንት መቶ ሃያ አራት ሺ ዘጠኝ መቶ ሰላሳ ስምንት ብር) የሚገመት ውድመት መድረሱን የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በድረገጹ አስነብቧል፡፡
በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት የደረሰባቸውን የባህልና የስፖርት ተቋማት ለማቋቋምና መልሶ ሥራ ለማስጀመር እንዲቻልም ሚኒስቴሩ የማገገሚያ እቅድ ማዘጋጀቱን ገልጿል፡፡ በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ‹‹ሕብረተሰቡ ቀጣይነት ያለው አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችል እና አገልግሎቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ ሁሉንም ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችን ያሳተፈ የአስቸኳይ ጊዜ ሥራ መስራት በአስቸኳይ ይጠበቃል›› ማለታቸውም በመረጃው ተመላክቷል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው፤ በባህልና ስፖርት ዘርፍ የሕብረተሰቡን ተስፋ የሚያለመልም የሥነ ልቦና ሥራ በዓይነት፣ በቁሳቁስና በሥነ ልቦና ህክምና ላይ መስራት ከሚኒስቴሩ እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል። የመልሶ ማቋቋም ስራውን የሚያስተባብር ግብረኃይል ተቋቁሞ በአስቸኳይ ወደ ተግባር ተገብቶ ስራዎችን እያቀናጁ መስራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2014