ከትምህርት ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ በትብብር መስራት በኢትዮጵያ የሚስተዋለውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ እጥረት ሊፍታት እንደሚያስችል ተገለጸ።
በስፖርት መሰረተ ልማት ዙሪያ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአዳማ ከተማ ሲካሄድ በቆየው የባለድርሻ አካላት ውይይት ላይ እንደተጠቆመው፤ በተለያዩ አካባቢዎች ያለውን የማዘውተሪያ ስፍራ እጥረት ለመፍታት ከትምህርት ተቋማት ጋር መስራት መፍትሄ እንደሚሆን ታምኖበታል።
በውይይት መድረኩ ላይ በትምህርት ቤቶች በሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አስተዳደርና አጠቃቀም ዙሪያ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ የዳሰሰ ጽሑፍ በዶክተር ዋቅጅራ ሲማ ቀርቧል።
በተጨማሪ የስፖርት ኢንቨስትመንት ላይም የሌሎች አገሮች ተሞክሮና የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ የዳሰሰ፣ ችግሮችና የመፍትሄ ሃሳቦች በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኢንቨስትመንት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መሠረት ታደገ ቀርቧል።
በቀረቡት ሰነዶች ላይ ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ የሚስተዋሉትን የማዘውተሪያ ስፍራ እጥረቶች ለመፍታት ከትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅትና በትብብር መሠራት እንዳለበት ስምምነት ላይ ተደርሷል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ በቀጣይ ትኩረት ላይ ዕቅድ በማዘጋጀት የማዘውተሪያ ስፍራዎችን መረጃ ወቅታዊ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ግንባታው ያልተጠናቀቀ ስቴድየሞች በሚጠናቀቁበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ
መስራት እንደሚያስፈልግ ያሳሰቡት አምባሳደር መስፍን፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመነሻ መግባቢያ ሰነዶችን በማዘጋጀት አፈጻጸሙን እንደሚከታተል ጠቁመዋል።
የስፖርት ኢንቨስትመንትን በተመለከተም ባለሀብቱን ያሳተፈ መድረክ ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፣ የስፖርት መሰረተ ልማት ፎረሙ ከትምህርት ተቋማት ጋር ለመስራት ከየት መጀመር እንዳለበት ጠንቅቆ ለማወቅ ይረዳል።
የትምህርት ተቋማት ተጨባጭ ሁኔታን ማወቅ ብቻ ሳይሆን በትምህርት ቤት ውስጥ ችግሩን ለመቅረፍ የሚረዳ አቅም መኖሩን በማረጋገጥ በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ምንም ዓይነት አሉታዊ ተፅዕኖ ሳይፈጥር ተገቢ በሆነ አግባብ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ መልኩ መጠቀም ያስፈልጋል።
የስፖርት ኢንቨስትመንት ላይ ባለሀብቱን ለመሳብ ጥናቶችን በማድረግ አዋጭነቱ ላይ ለባለሀብቱ ግንዛቤን መፍጠር እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል።
በአዲስ አበባ እየተገነባ የሚገኘው የብሔራዊ ስቴድየምን ጨምሮ በየደረጃቸው እየተገነቡ የሚገኙ ስቴድየሞችን ለማጠናቀቅም በትኩረት መሠራት እንዳለባለቸው ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል።
የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ማልማት ስፖርትን በመላ አገሪቱ ለማስፋፋት እንደሚረዳ መድረኩን በንግግር የከፈቱት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ የተናገሩ ሲሆኑ፣ የትኛውም አሰራር ከአቅርቦት ጀምሮ የተለያዩ ግብአቶች ተሟልቶለት በአግባቡ ከተመራ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል ገልጸዋል።
የስፖርት መሰረተ ልማቶችን ለማሳደግ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በአግባቡ ካልተመራና ሳይንሳዊ በሆነ መለኪያ ካልተገመገመ የታለመለትን ውጤት ማስመዝገብ እንደማይችልም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ “እኛ እንደ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ብሎም እንደ ባለድርሻ አካላትም ከማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ እስከ ቁሳቁስ አቅርቦት ድረስ ያሉትን ግብአቶች ለማሟላት የተጣለብንን ኃላፊነት ለመወጣት በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅብናል” ብለዋል።
የማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታን በተመለከተ ከህግ ማዕቀፍ አኳያ አዋጆችን መሰረት በማድረግ የህግ ማዕቀፎች እንዲወጡና ተፈጻሚ እንዲሆን መከታተል የፌዴራል መንግስት ስልጣን መሆን እንዳለበት ከመድረኩ ተሳታፊዎች አስተያየት ተሰጥቶበታል። የተለያዩ ስፖርቶችን ለማስፋፋትና ህብረተሰቡን ተሳታፊ ለማድረግ የማዘውተሪያ ስፍራዎች እጥረት ትልቁ ችግር ሆኖ ዓመታትን አስቆጥሯል።
ካለፉት አስር አመታት ወዲህ ይህን ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ ግዙፍ ስቴድየሞች በተለያዩ ክልሎች እየተገነቡ መሆናቸው ይታወቃል። ሆኖም የስቴድየሞቹ ግንባታ እስካሁን መጠናቀቅ አልቻሉም። ይህም የስቴዲየሞቹ ግንባታ ያልታሰበበትና የማዘውተሪያ ስፍራዎች እጥረትን አይፈታም የሚል ትችት ሲሰነዘርበት ቆይቷል።
ለዚህም መንግስት የማዘውተሪያ ስፍራዎችን እጥረት ለመፍታት ግዙፍ ስቴድየሞችን ከመገንባት ይልቅ አነስተኛ ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ለመገንባት ትኩረት መስጠት እንዳለበት የስፖርት ቤተሰቡና ባለሙያዎች አስተያየት ይሰጣሉ።
በተለይም በትልልቅ ከተሞች ያሉ ጥርጊያ ሜዳዎችና ትንንሽ ማዘውተሪያ ስፍራዎች ለሌላ ግንባታ እንዳይውሉ መንግስት ጥበቃ ሊያደርግላቸው ይገባል ሲሉ ብዙዎች አስተያየት ሰጥተዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 30 /2014