የስፖርት እንቅስቃሴን በማስፋፋት የኅብረተሰቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በየደረጃው ለረጅም ዘመናት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ይህን ጥረት ለማጠናከር በተቀረፀው ብሔራዊ የስፖርት ፖሊሲ ላይ በተቀመጠው የአፈፃፀም ስልት ሕዝባዊ መሠረት ያላቸው የስፖርት አደረጃጀቶችን በመፍጠር የስፖርት ማኅበራት ለስፖርቱ ልማት ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ መንግሥት ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።
በዚሁ መሠረት የአህጉርና ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽኖችን ሕግ፣ ደንብና መመሪያ መነሻ በማድረግ የአገር አቀፍ ስፖርት ማኅበራት እንዲቋቋሙበት በተዘጋጀው መመሪያ መሠረት 20 ፌዴሬሽኖች ፤3 ኮሚቴዎችና 8 አሶሴሽኖች በድምሩ 31 ስፖርት ማኅበራቶች በአገር አቀፍ ደረጃ ተቋቁመው ሰፊ የስፖርት እንቅስቃሴ ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ ከስፖርቱ ዓላማ ውጭ የሚያፈነግጡ የግለሰቦችን ፍላጎት በሚያንፀባርቅ መልኩ በየወቅቱ የሚፈጠሩ የአደረጃጀትና አሠራር ሥርዓት ጥሰት እንዲሁም እሰጥ አገባዎች የስፖርቱን እንቅስቃሴ በሚፈለገው ፍጥነት ወደፊት ለማራመድና ለማዘመን ከፍተኛ ችግር ሆነው መቆየታቸው በየወቅቱ ከሚደረጉ የአፈፃፀም ግምገማዎች መገንዘብ ይቻላል። ስፖርቱን የሚመራው የመንግሥት አካልም ይህን ከግምት በማስገባት ለሚገጥሙት ተግዳሮቶች አፋጣኝ መፍትሔ ለማስቀመጥ የተለያዩ ጥናቶችና ምክረ-ሀሳቦችን ያቀርባል።
በአሁኑ ወቅት ስፖርቱን በበላይነት እየመራ የሚገኘው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርም በስፖርት ማኅበራት የአደረጃጀትና አሠራር ሥርዓት ዙሪያ በሚስተዋሉ ችግሮች ለመወያየት ባለፈው ዓርብና ቅዳሜ በአዳማ ከተማ ባዘጋጀው የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ላይ አገር አቀፍ የስፖርት ማኅበራት ስፖርቱን ማሳደግ በሚችሉበት ቁመና ላይ እንደማይገኙ ባቀረበው ሰነድ አረጋግጧል። ሰነዱ ማኅበራቱ ከአደረጃጀት አንጻር ያሉባቸውን ክፍተቶችም ነቅሶ አውጥቷል።
በአሁኑ ወቅት አገር አቀፍ ስፖርት ማኅበራት በክልልና ከተማ አስተዳደር ያሉ አባል የስፖርት ማኅበራት አደረጃጀት ወጥ እንዲሁም ተመጋጋቢ አለመሆን አገር አቀፍ ማኅበራቱ ስፖርቱን ለማሳደግ በሚችሉበት አቋም ላይ እንዳይገኙ ማድረጉ ተጠቁሟል።
የማኅበራቱ የጽሕፈት ቤት አደረጃጀት ወይም የመዋቅር ችግር ስፖርቱን ማስፋፋትና ማሳደግ የሚችልበት ቅርጽ አለመኖሩን የጠቆመው ሰነዱ፣ የክልልና ከተማ አስተዳደር ስፖርት ማኅበራት አደረጃጀት ከአገር አቀፉ ጋር ተመጋጋቢ አለመሆኑና ኢንተርናሽናል አደረጃጀትን ተከትለው ያልተደራጁ ከመሆናቸው በተጨማሪ አብዛኛዎቹ የስፖርት ማኅበራት የክለብ አደረጃጀት እንደሌላቸው አስቀምጧል።
ማኅበራቱን ለመምራት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች ከተለያዩ የሙያ መስኮች የተውጣጡ ከመሆናቸው አኳያ በስፖርቱ ዘርፍ (በዓለም አቀፍና አገራዊ ሕጎች፣ መመሪያዎች፣ ደንቦች፣ የአሠራር ሥርዓቶች፣ወዘተ) ዙሪያ ያላቸው ግንዛቤ ውስን መሆኑም እንደ አንድ ተግዳሮት ተቀምጧል።
መንግስት ለማኅበራቱ ከሚመድባቸው የጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ጋር ሥራ አስፈጻሚዎች ተናበው ሥራዎችን አለመምራት አንዱ ክፍተት ሆኖ የተገለጸ ሲሆን፣ በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት መካከል የሚፈጠሩ የጥቅም ግጭቶች፣ግለሰባዊ የስልጣን አጠቃቀም፣ በሥራዎች ሒደት በግብዓትና ውጤት ላይ ያልተመሠረተ ደካማ ድርጅታዊ መዋቅር፣ ብቁ የሆነ የሰው ኃይል እጥረት እንዲሁም ውስን የፋይናንስ አቅም ጠንካራ አደረጃጀቶችን ከመፍጠር አኳያ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን እንዳሳደሩ ተጠቁሟል።
ስፖርቱ በከፍተኛ ደረጃ ከሚነሱበት የአደረጃጀት ጥያቄዎች መካከል አንዱ የውክልና ጉዳይ ሲሆን፣ ይህም ሕዝብ በትክክል ተወክሎበታል? የሚለው ጥያቄ አሟጋች ነው። በዚህ ረገድ የቀረበው ሰነድ የማኅበራት የሥራ አስፈፃሚዎች ምርጫ ሥርዓት ጥያቄ ውስጥ የወደቀና ከስፖርት መርህ ውጭ መሆኑን አስቀምጧል። ከዚህ ባሻገር በአደረጃጀት ሂደት በመንግሥታዊና ሕዝባዊ መዋቅሮች መካከል መደበላለቅ እንዳለም ተጠቁሟል።
የስፖርት ማኅበራት ስፖርቱን ለማሣደግ በሚያስችል የአደረጃጀት ቁመና ላይ አለመኖራቸው በተለይም ወደ ክልሎች ሲወርድ ሰፊ ክፍተት እንዳለ በሰነዱ ተብራርቷል። በክልልና በከተማ አስተዳደር ደረጃ የተጠናከረ ስፖርት ማኅበራቶችን አለማዋቅር ለዚህ አንዱ ምክንያት ተደርጎ የተቀመጠ ሲሆን፣ ፌዴሬሽኖች የራሳቸው የሆነ ራዕይና ስትራቴጂዎችን ቀርጸው የመመራት ችግር እንዳለባቸው በጥናት ጭምር መረጋገጡ ታውቋል።
በአብዛኛው የክልልና የከተማ አስተዳደር ፌዴሬሽኖች የራሳቸውን ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ አለመቻላቸውም አንዱ ክፍተት ሆኖ ተነስቷል። የሕዝባዊ አመራር የስፖርት ማኅበራትን አቅም ለማሳደግ የጎላ ክፍተት እንዳለበት መታየቱ፣ ክለቦችን በጠንካራ ሕዝባዊ መሠረት ማደራጀት ያለመቻል፣ ክለቦች የተቋቁመበትን ዓላማ ያለማወቅና በየጊዜው የሚገጥማቸው የመፍረስ አደጋ እንዲሁም ሴቶች በተለያየ የአመራር እርከን (አደረጃጀት)ላይ ቁጥራቸው አናሳ መሆኑ ማኅበራቱ ስፖርቱን ለማሳደግ የሚያስችል ቁመና ላይ እንዳይገኙ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ትልቁን ድርሻ እንደሚይዙ ሰነዱ በዝርዝር አስቀምጧል።
ሰነዱ እነዚህን ክፍተቶች ለመድፈን መፍትሔ ይሆናሉ ያላቸውን አቅጣጫዎችም ጠቁሟል። ሙያተኞች ተቀራርበው በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ብሔራዊ ቡድኖችን በቅብብሎሽ የሚሠሩበት አሠራር መዘረጋት እንደ አንድ መፍትሔ የተቀመጠ ሲሆን፣ ክለቦች የታዳጊ የወጣቶች ልማት ሥራ የሚሠሩበት ጠንካራ የአሠራር ሥርዓት ማስፈን፣ ወጣቱን ያማከለ ሥራ በሁሉም ደረጃ መሥራት፣ጥራት ያለው ተጫዋቾች በበቂ ሁኔታ ማፍራት የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋትና ተከታታይነት ያለው የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት እንደ መፍትሔ ተቀምጧል።
መንግሥት ለክለቦች እንጂ ለታዳጊ ወጣቶች ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ ማስቻል፣የሥነ-ምግባር መመሪያ በየደረጃው ማውጣት፣ መረጃ አያያዝን ማዘመን፣ የተደራጀ የፌዴሬሽን ሠራተኞች የሞያና የክህሎት ክፍተትን በአጭርና በረጅም ስልጠናዎች መሙላት እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል። ከዚህ ባሻገር የስፖርት ማኅበራትን የሚዲያ ሽፋን ተደራሽ ለማድረግ በእቅድ መመራት፣በጥናት የተደገፉ ችግር ፈቺ ሥራዎችን እንዲሁም የረጅም ጊዜ የስፖርት ልማትን ትኩረት ያደረገ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ከባለድርሻ አካላት ግብረመልስ ተሰጥቶበታል።-
በተጨማሪም ጠንካራ የሆነ የክትትልና ግምገማ እንዲሁም የድጋፍ ዘዴን መዘርጋት፣ማንኛውንም ዓይነት ውድድርና ስልጠና በበላይነትና በባለቤትነት መምራት፣ በታዳጊዎች ልማት ላይ ትምህርት ቤቶችን ትኩረት አድርጎ መሥራት የመፍትሔ አቅጣጫ ተደርገው አስተያየት ከተሰጠባቸው ምክረ ሃሳቦች መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 28 ቀን 2014 ዓ.ም