.በርበሬ ቀንጣሹ አካል ጉዳተኛ
ከረፋዱ አምስት ሰዓት አካባቢ ነው። በአጋጣሚ መርካቶ በርበሬ በረንዳ ተገኝቻለሁ። የበርበሬው ግብይት መድራት ጀምሯል። ሻጭና ገዢ ዛላውን በእጃቸው እያገለባበጡ ዋጋ ይነጋገራሉ። ጭንቅላታቸው ላይ የሰሌን ኮፊያ ያደረጉ ሴቶች መተላለፊያ መንገዱ ላይ ቁጭ ቁጭ ብለው በርበሬ ይቀነጥሳሉ።
አላፊ አግዳሚው እያስነጠሰ፣ አንዳንዱም ዓይኑን እያሻሸ ላይ ታች ይላል። እኔም ሁኔታውን እያስተዋልኩ ቁልቁል ወደ ፔፕሲ ፋብሪካ መጓዝ ጀመርኩ።
አብዛኛዎቹ ሻጮች ወንዶች ሲሆኑ ቀንጣሾቹ ሴቶች ናቸው። ለምን ሻጮቹ ወንዶች ቀንጣሾቹ ሴቶች ሆኑ? የሚል ጥያቄ ተፈጥሮብኝ እሱን እያብሰለሰልኩ ትንሽ እንደተጓዝኩ ከአስፓልቱ ባሻገር በርበሬ የሚቀነጥስ ጎልማሳ ወንድ አየሁና ድምዳሜዬ ትክክል አለመሆኑን ተረዳሁ። ሰውየው የሰሌን ኮፊያና መነጽር አድርጓል። አጠገቡ ክራንች አለ።
አካል ጉዳተኛ ሊሆን እንደሚችል መገመት አልከበደኝም። ጠጋ ብዬ ሰላምታ አቀረብኩለት። ቀና ብሎ በፈገግታ ምላሽ ሲሰጠኝ እግሩ ብቻ ሳይሆን አንድ ዓይኑም ጉዳት እንዳለበት ተመለከትኩ። እጆቹ ፋታ የላቸውም፤ ዓይኑን ወደ ፈለገው ቦታ እየወረወረ የበርበሬውን ዛላ በፍጥነት እየቀነጠሰ ያስቀምጣል። ትንሽ ሰዓት አወጋሁት፤ የሕይወት ታሪኩን ያጫውተኝ ጀመር። ሲበዛ ቅን እና ግልጽ ሰው ነው።
ሰውየው የገጠመውን የአካል ጉዳት ተቋቁሞ በርበሬ እየቀነጠሰ ከራሱ ጋር ስድስት የቤተሰብ አባላትን የሚያስተዳድር መሆኑን ነገረኝ። የሕይወት ተሞክሮው ለሌሎች አስተማሪ ስለሚሆን የዚህ አምድ እንግዳ እንዳደርገው ፈቅዶልኝ ወደ ቃለ መጠይቅ ገባሁ። ወጉ ሽብሩ ይባላል።
የተወለደው በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ጉንችሬ ወረዳ ልዩ ስሙ ጠረደ በሚባል ገጠራማ መንደር ነው። ሲወለድ ጤናማ ነበር። የሁለት ዓመት ልጅ እያለ ታላቅ ወንድሙ እንደቀልድ ቁም ሳጥን ላይ አስተኝቶት በድንገት ወድቆ ግራ እግሩ ይጎዳል። ለጊዜው ቤተሰቦቹ ወጌሻ ቤት እየወሰዱ ቢያሳሹትም ሳይሻለው ይቀራል።
በዚሁ ጉዳት ላይ እያለ ይባስ ብሎ የአስራ አንድ ዓመት ልጅ ሲሆን በአካባቢው የኩፍኝ ወረርሽኝ ተከስቶ አንድ ዓይኑን ያጠፋዋል። አንድ እህቱም በዚሁ ወረርሽኝ ምክንያት ትሞትና ቤተሰቡ ኀዘን ውስጥ ይገባል። በዚህ ጊዜ የወጉ ሕመም ትኩረት ሳያገኝ ይቀርና በተደራራቢ የጤና ችግር ምክንያት ታማሚ ሆኖ እቤት ይቀመጣል።
ወጉ የልጅነት አስተዳደጉን እንዲህ ያታውሳል ‹‹ከቁም ሳጥን ላይ ወድቄ አንድ እግሬ ተጎዳ፣ አንድ ዓይኔም በኩፍኝ ምክንያት ጠፋ፤ ያኔ ከሰፈር ልጆች እራሴን አገል ነበር። እንደልቤ መንቀሳቀስ ስለማልችል አብሬያቸው አልጫወትም፤ በጣም ይከፋኝ ነበር፤ ለምን እንዲህ ዓይነት ችግር ሊገጥመኝ ቻለ እያልኩ አዝን ነበር።›› አንድ ቀን የወጉ እናት አንገታቸው ላይ እባጭ ይወጣባቸውና እዚያው አካባቢያቸው በሚገኘው አጣጥ ሆስፒታል ሊታከሙ ይሄዳሉ። ኦፕሬሽን ተደርገው ለቀናት ተኝተው ሕክምናቸውን ይከታተላሉ።
የአስራ አንድ ዓመቱ ልጃቸው ደጉ አባቱ በጀርባቸው አዝለውት እናቱን ለመጠየቅ ሆስፒታል ይሄዳል። በዚህን ጊዜ ጀርመናዊው ሐኪም ይመለከተውና ስለተደረገላት ሕክምና ይጠይቃቸዋል። በአቅም ውስንነት ምክንያት የተሻለ ሕክምና እንዳላገኙ ይገልጹለታል።
ጀርመናዊው ሀኪም ቤተሰቦቹ ፈቃደኛ ከሆኑ ያለምንም ወጪ የሕክምና እርዳታ ሊያደርግለት እንደሚፈልግ ይገልጽላቸዋል። አባቱም እናቱም ፈቃደኛ ይሆናሉ። ደጉ እዚያው አጣጥ ሆስፒታል አልጋ እንዲይዝ ይደረግና ሕክምና ይጀምራል። አንድ ዓይኑ በቀዶ ሕክምና ተወግዶ በሽታው ወደ ሁለተኛው ዓይኑ እንዳይዛመት ይደረጋል። በዚህም እፎይታ ያገኛል። በተመሳሳይ የተጎዳው እግሩም በብረት ተወጥሮ በክራንች መንቀሳቀስ ይጀምራል። እግሩ በወቅቱ ሕክምና ባለማግኘቱ የታሰበውን ያህል ለውጥ ሳይመጣ ይቀራል።
ነገር ግን የክራንች እገዛ ማግኘቱ ከበፊቱ የተሻለ ከቦታ ቦታ እንዲንቀሳቀስ አድርጎታል። ከዚያም በኋላ የእግሩን ሕክምና ለመከታተል ያለሰው እገዛ ወደ ሆስፒታሉ መመላለስ ችሏል።
ቤተሰቦቹ በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ ቢሆኑም በቂ የእርሻ መሬት አልነበራቸውም። ባለቻቸው ማሳ ላይ እንሰት፣ ጫት፣ ቡና፣ ባህርዛፍ እየተከሉ በሚያገኟት ገቢ ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩ ነበሩ። እያደር የቤተሰቡ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ መቸገር ይጀምራሉ። በዚህ የተነሳ የደጉ ታላላቆች አዲስ አበባ መጥተው በንግድ ሥራ ለመሰማራት ይገደዳሉ። ወጉ አስራ አምስት ዓመት እስኪሞላው ድረስ የአቅሙን ያህል ለቤተሰቦቹ እየታዘዘ በተለይም ከብት እየጠበቀ፤ እግረ መንገዱንም የራሱን ዶሮዎችና በጎችን እያረባ ገንዘብ ያጠራቅም ነበር።
ሁልጊዜ የመስቀል በዓል ሲደርስ አብሮ አደጎቹና ታላላቅ ወንድሞቹ አዳዲስ ልብስ ለብሰው ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ ሲመጡ እያየ እርሱም ከአካባቢው ርቆ በመሄድ ሠርቶ ለመኖር ይመኝ ነበር።
በጉራጌ ባህል ልምና ነውር ነው የሚለው ወጉ እንደእርሱ ዓይነት አካል ጉዳተኞች ሳይቀሩ ሠርተው እንዲበሉ ይበረታታሉ እንጂ እንዲለምኑ አይፈለግም ይላል። አካል ጉዳተኛው ታዳጊ አዲስ አበባ ሄዶ ሠርቶ የመኖር ፍላጎት እንዳለው ለቤተሰቦቹ ሲነግራቸው ሊያስቀሩት አልፈለጉም።
ወንድሞቹ ገና ያልተደራጁ በመሆናቸው ትንሽ አቅም ሲፈጥሩ እንዲመጣ ቢነግሩትም ሊሰማቸው አልወደደም። ወንድሞቹን ትቶ ከአብሮ አደግ ጓደኞቹ ጋር ወደ አዲስ አበባ ይመጣል። አዲስ አበባ መጥቶ ሥራ ሲያፈላልግ አንዳንዶች ተስፋ ያስቆርጡት እንደነበር ያስታውሳል።
አስፋልት ዳር ቁጭ ብሎ ምጽዋት እየተመጸወተ እንዲኖር የሚመክሩትም ነበሩ። እርሱ ግን እንኳን የሌላ ሰው እጅ ማየት ይቅርና የወንድሞቹን እገዛ እንኳን አልፈለገም ነበር። መርካቶ አካባቢ ሀ ብሎ ሥራ ሲጀምር እጁን ያፍታታው ሽንኩርት ከገለባ በመለየት ነው።
በአንድ ኩንታል ሁለት ብር እየተከፈለው ቢያንስ በቀን ከአራት እስከ አምስት ኩንታል ሽንኩርት ይለቅም ነበር። ወጉ ሽንኩርት ከገለባው የመለየቱን ሥራ እንደጀመረ በብረት የተወጠረውን እግሩን አጥፎ ለመቀመጥ ይቸገር ነበር። ለረዥም ሰዓት እግሩን ዘርግቶ መቀመጡ ምቾት ስላልሰጠው ብረቱን አስወልቆ እንደልቡ እግሩን እያጣጠፈ መሥራት ይጀምራል። ጥሩ ገቢ አገኘ ከተባለ ቢያንስ በቀን ከስምንት እስከ አሥር ብር ያገኛል።
ያኔ አንድ እንጀራ በሽሮ ወጥ አንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም፤ አንድ ብርጭቆ ሻይ አስራ አምስት ሳንቲም ይጠቀም ነበር። ቀን ሲሠራ ከዋለ በኋላ ማታ አውቶቡስ ተራ አካባቢ በመሄድ ሰሌን ብቻ በተነጠፈበት ባዶ ቤት / በእርሱ አጠራር /ኬሻ በጠረባ / በሚባለው ማረፊያ ቤት በቀን ሰላሳ አምስት ሳንቲም / በወር አሥር ብር ከሃምሳ ሳንቲም/ እየከፈለ ያድር ነበር።
አንዳንድ ጊዜ የቤቱ ባለቤት የወሩን ሂሳብ ተጠቃሎ እንዲከፈላቸው ሲጠይቁ ወጉ የሚከፍለው ገንዘብ ስለማይኖረው ይጨነቅ እንደነበር ያስታውሳል። አካል ጉዳተኛ በመሆኑ ሌሎች እንደተባሉት ሲከፍሉ እርሱ ግን ባገኘ ጊዜ እንዲሰጥ ይደረግ ነበር። ወጉ ሽንኩርት ከገለባ የመለየቱን ሥራ ለአምስት ዓመት ያህል ሠርቷል። የኑሮ ውድነቱ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ወጉ ኑሮው እየተፈተነ መጣ፤ በአንድ ኩንታል ሁለት ብር ይከፈለው የነበረው ዋጋም እያደገ ሄዶ ወደ አስር ብር ተሸጋገረ፤ ያም ሆኖ ከቀን ወጪው የሚተርፍ አልነበረም።
በዚህ የተነሳ የሽንኩርቱን ሥራ ትቶ ወደ በርበሬ ቅንጠሳ ተሸጋገረ። ወጉ እንደሚለው የበርበሬ ቅንጠሳው ሽንኩርትን ከገለባው እንደመለየት ቀላል አልነበረም። ፊት ይለበልባል፤ ዓይን ያስለቅሳል፤ ያስነጥሳል፤ ጣት ያሳምማል።
ይሁንና ክፍያው ከሽንኩርቱ የተሻለ ነበር። ሥራውን እንደጀመረ ሰሞን በአንድ ኩንታል ከአሥራ አምስት እስከ ሃያ ብር ይከፈለው ነበር። ያኔ በቀን ከአንድ ኩንታል በላይ የመቀንጠስ ልምድ አልነበረውም። አሁን ግን ሥራው ከተገኘ በቀን እስከ አራት ኩንታል የመቀንጠስ ልምድ ማዳበሩን ይናገራል። ወጉ በርበሬ መቀንጠስ ከጀመረ በኋላ የቀን ገቢው እየተሻሻለ ይመጣል። የ‹‹ኬሻ በጠረባ» መኝታውን በመተው ለሥራው ቀረብ በሚል አካባቢ አንዲት ክፍል ቤት በአራት መቶ ብር ተከራይቶ መኖር ይጀምራል። ከዚያም አልፎ ቤተሰቦቹን ለመርዳት ይበቃል።
ከዚያም ያስፈልጋሉ የሚላቸውን የቤት ዕቃዎች ካሟላ በኋላ ትዳር መስርቶ መኖር ይጀምራል። ትዳር ከመሠረተ አስራ ሦስት ዓመት ሆኖታል፤ አራት ልጆችን አፍርቷል፤ ሦስት ልጆቹን በመንግሥት ትምህርት ቤት ያስተምራል። መንግሥት የምግብ፣ የዩኒፎርም፣ የጫማ፣ የቦርሳ፣ የደብተር ድጋፍ ማድረግ ከጀመረ ወዲህ ወጉ ደስተኛ ሆኗል። ያም ሆኖ ኑሮ ፈታኝ ሆኖበታል። በወር አራት መቶ ብር ተከራይቶ ይኖርበት የነበረው አንድ ክፍል ቤት ከአስር ዓመት ቆይታ በኋላ ሁለት ሺ ብር ገብቷል።
ለቤት አስቤዛና ለአልባሳትም የሚያወጣው ገንዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሄዷል። ቀደም ሲል ከሰል በአንድ ብር፣ ስኳር በ50 ሳንቲም፣ ቡና በ50 ሳንቲም፣ ለምለም እንጀራ በአርባ ሳንቲም፣ ጨው በአስር ሳንቲም እየገዛ ወደ ቤቱ ይገባ እንደነበር ያስታውሳል። አሁን ያን ዘመን እንደ ታሪክ ይጠቅሰዋል። እርሱ በአስር ብር ይቀነጥስ የነበረው አንድ ፈረሱላ / አስራ ሰባት ኪሎግራም / በርበሬ እንኳ ሰማኒያ ብር ገብቷል።
ወጉ ዕድል ሲቀናው እስከ አራት ፈረሱላ በርበሬ ሊቀነጥስ ይችላል፤ አንዳንድ ቀን ደግሞ ምንም ሳይሰራ የትራንስፖርቱንና የምግብ ወጪውን ከስሮ የሚገባበት አጋጣሚ አለ። ባለቤቱ የቤት እመቤት ነች።
በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እያለ ግን ከቅርብ ዓመታት በፊት ቅሊንጦ አካባቢ ኮንዶሚኒየም ቤት / ስቱዲዮ / ደርሶት መኖር ጀምሯል። የቤት ጥያቄው ቢመለስለትም ከሥራ ቦታው ርቆ ስለሚኖር በቀን የሚያወጣው የትራንስፖርት ዋጋ በብዙ እጥፍ እንደጨመረ ይናጋራል።
በዚህም ላይ ወደ ሥራ ቦታው ለመሄድ በየቀኑ አስራ አንድ ሰዓት ተነስቶ የአንበሳ አውቶቡስ ሰልፍ መያዝ ይኖርበታል። ማታ ወደ ቤቱ ሲመለስም ሥራ ላይ ቢሆን እንኳ አቋርጦ በጊዜ ወረፋ ይዞ ሳይመሽበት ወደ ቤቱ ይሄዳል።
ወጉ አሁን ፈተና የሆነበት የሚያገኘውን ገንዘብ ሁሉ ለኮንዶሚኒየም ክፍያ እያዋለ እጁ ላይ ገንዘብ አልይዝ ማለቱ ነው። በ20 ዓመት ውስጥ ዕዳውን የመጨረስ ውል ስለገባ በየወሩ ስምንት መቶ ሃምሳ ብር የመክፈል ግዴታ አለበት።
መንግሥት የልጆቹን የትምህርት ቤት ወጪ ባይሸፍንለት ኖሮ ዕዳውን መክፈል ይቅርና በልቶ ለማደር እንደሚቸገር ይናገራል። በዚህ ላይ ደግሞ የልጆቻቸውን እጅ እያዩ የሚኖሩ አባትና እናቱን የመጠየቅ ኃላፊነት አለበት። በየአመቱ ለመስቀል ወደ አገር ቤት ሲሄድ የሆነ ነገር ቋጥሮ እየሄደ የወላጆቹን ምርቃት ተቀብሎ መምጣት አለበት።
ወጉ እነዚህን ሁሉ ችግሮች ለማለፍ ጠንክሮ እየሠራ ቢሆንም ሥራው ሁልጊዜ እርሱ እንደሚፈልገው ስለማይገኝ ያሰበውን ሊያሳካ አልቻለም። ከሁሉ በላይ ዘወትር አስራ አንድ ሰዓት ከእንቅልፉ ተነስቶ ወደ ሥራ ቦታው ሲሄድ በመንገዱ ርቀት ምክንያት የሚያጠፋው ጊዜና ለትራንስፖርት የሚወጣው ገንዘብ እየጎዳው መሆኑን ይናገራል።
ባለሞትር ዊልቸር ቢያገኝ ይህ ሁሉ ችግሩ እንደሚቃለል ቢያምንም መግዛት የሚያስችል አቅም ስለሌው ከምኞት መዝለል አልቻለም። አንዲት ቀን ከሥራው ቢቀር ቤተሰቦቹ ለከፋ ችግር ስለሚጋለጡ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር ሄዶ ድጋፍ መጠየቅ እንኳን አልቻለም። በዚህ አጋጣሚ ግለሰቦች፣ በጎ አድራጎት ድርጅቶችም ይሁኑ የመንግሥት ተቋማት እገዛ እንዲያደርጉለት ይማጸናል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን የካቲት 26 /2014