
ምንም እንኳን የዓለም የነዳጅ ዋጋ በሰባት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ከፍ ቢልም ትልልቅ የሚባሉት ነዳጅ አምራች አገራት ግን የነዳጅ ምርታቸው ላይ የተጋነነ ጭማሪ እንደማያደርጉ አስታውቀዋል።
በሩሲያ የሚመራው የነዳጅ ላኪ አገራት ድርጅት ኦፔክ እና አጋሮቹ በምንም ዓይነት ሁኔታ ከድንበራቸው የሚወጣ ነዳጅ እምብዛም ከፍ እንደማያደርጉ ነው የተገለጸው።
23 አባል አገራት ያሉት ድርጅቱ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ በየቀኑ ተጨማሪ 400 ሺ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ብቻ ለገበያ እንደሚያቀርቡ ተገልጿል።
ድርጅቱ በአውሮፓውያኑ 2021 አባል አገራት በተስማሙበት የምርት ሂደትን ይከተላል።
አገራቱ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ቀንሶ የነበረውን ምርት ቀስ በቀስ ለማስተካከል ነበር የተስማሙት። በወቅቱ የነዳጅ ፍላጎት በመቀነሱ አገራት የምርት መጠናቸውን ለመቀነስ ተገድደው ነበር።
ነገር ግን ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ የአንድ ድፍድፍ በርሜል ነዳጅ ዋጋ 113 ዶላር ደርሷል።
ኦፔክ የሰሞኑን የነዳጅ ዋጋ መጨመርና ስጋት በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ በአሁኑ ወቅት የነዳጅ ምርት እጥረት እንደሌለ ገልጿል።
በሌላ በኩል የዓለም አቀፉ ኢነርጂ ኤጀንሲ አባል አገራት በበኩላቸው ከወሳኝ መጠባበቂያዎቻቸው ተጨማሪ ነዳጅ 60 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ለመልቀቅ ተስማምተዋል።
ከዚህ ነዳጅ ግማሽ የሚሆነው የሚመጣው ከአሜሪካ እንደሚሆን ይጠበቃል። ነገር ግን ይህ ውሳኔ እንኳን የስቶክ ገበያውንም ሆነ እየጨመረ የመጣውን የነዳጅ ዋጋ ግሽበት በአፋጣኝ ያስተካክለዋል ተብሎ አይጠበቅም።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት የነዳጅ ዋጋ በቅርብ ወራት ውስጥ ወደነበረበት የመመለስ ዕድሉ ጠባብ ነው። እንደ ቢፒ እና ሼል ያሉ ትልልቅ የነዳጅ አጣሪና አከፋፋይ ድርጅቶች ከሩሲያ ለቅቀው እንደሚወጡ ማስታወቃቸው ደግሞ ገበያው እንዳይረጋጋ እንደሚያደርገው ተገልጿል።
እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት የሩሲያ የነዳጅ ደንበኞች ትልቅ ችግር እየገጠማቸው ነው። የምዕራቡ ዓለም አገራት ሩሲያ ላይ የጣሉትን ማዕቀብ ተከትሎ ድርጅቶቹ ክፍያ መፈጸም ሆነ መቀበል እንዲሁም የነዳጅ ዝውውር ላይ ከፍተኛ ጫና እያጋጠማቸው ነው።
«በአጭር ጊዜ ውስጥ የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር እየተመለከትን ነው። ከሩሲያ ጋር በተያያዘ ያለው ግራ መጋባት የነዳጅ ገበያው እንዳይረጋጋ አድርጎታል» ይላሉ በዋሽንግተን የስትራቴጂክ እና ዓለም አቀፍ ጥናት ባለሙያው ቤን ካሂል።
ቁልፍ የሚባሉት ነዳጅ አምራች አገራት አሁን ላይ ያለውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር በሚል ምርት ብንጨምር በሚቀጥለው ዓመት ላይ ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ ምርት ገበያው ላይ ሊትረፈረፍ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው። ይህ ደግሞ የነዳጅ ዋጋን በእጅጉ ያወርደዋል።
ምንም እንኳን አንዳንድ የነዳጅ ላኪ ድርጅቶች ከሩሲያ የሚመጣውን አንደኛ ደረጃ ነዳጅ በርካሽ ዋጋ ለማሸጥ ቢሞክሩም ገዢ እንደጠፋ እየተነገረ ነው።
ሩሲያ ከአሜሪካ እና ሳኡዲ አረቢያ በመቀጠል የዓለማችን ሦስተኛዋ የነዳጅ አምራች አገር ነች። በዚህም ከዓለማችን የነዳጅ ፍላጎት ከ8 እስከ 10 በመቶ የሚሆነውን የምታሟላው ሩሲያ ነች።
ከዚህ በተጨማሪ አብዛኛው አውሮፓ 40 በመቶ የሚሆነውን የተፈጥሮ ጋዝ የሚያገኘው ከሩሲያ ነው። ለዚህም ይመስላል የምዕራቡ ዓለም አገራት ሩሲያ ላይ ከነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ጋር በተያያዘ ጠንካራ ማዕቀብ መጣል የከበዳቸው።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት የኦፔክ አባል አገራት በዩክሬን ሩሲያ ቀውስ ምክንያት ወደፊት ሊከሰት የሚችለውን ቀውስ ከማየት ይልቅ አሁን ላይ ገበያው ምን ይመስላል የሚለውን ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚፈልጉ ይገልጻሉ።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እየጨመረ በመጣው የነዳጅ ዋጋ ምክንያት ትንሽ የተደናገጡ ይመስላል። እንደ ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ያሉ የኦፔክ አባል አገራት ላይ ጫና ለማሳደር ቢሞክሩም እምብዛም አልተሳካላቸውም።
በሌላ በኩል ደግሞ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከአቡ ዳቢ ልዑል ሼክ ሞሀመድ ቢን ዛይድ ጋር ውይይት አድርገዋል። በውይይታቸውም የኦፔክ አባል አገራት የወሰኑት በወሰኑት ውሳኔ ላይ ስለመጽናት ተነጋግረዋል።
እስካሁን ድረስ በርካታ የመካከለኛው ምሥራቅ ነዳጅ አምራች አገራት ከዩክሬን ጉዳይ ጋር በተያያዘ ዝምታን የመረጡ ይመስላል።
ባሳለፍነው ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት የሩሲያን ወረራ የሚቃወም የአቋም መግለጫ ሲያወጣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በድምጸ ታቅቦ አልፋለች። ተንታኞች እንደሚሉት ዩኤኢ እና ሳዑዲ አረቢያ በጉዳዩ ላይ የገለልተኝነት ውሳኔ እየተከተሉ ነው ብለዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2014