አለም አስር ሞልታ አታውቅም እንላለን ብዙ ነገሮች ቢሟሉልንም:: ሁልጊዜ ዓለም ዘጠኝ ናትም ዘፈናችን ነው:: ሕይወት ከአምስት በታች የሆነባቸው ስንቶች እንደሆኑ ብናነሳ ቤት ይቁጠረው ከማለት ውጪ ምላሽ አይኖረንም:: በተለይም እናት ለሆኑ ሴቶች ጎዶሎነት በብዙ መልኩ የሚተረጎም ነው:: በቁጥር የሚተነተንም አይሆንም:: ዘጠኝ አስርም አያስብልም::
ምክንያቱም እናት ስትራብ ማህበረሰብ አብሮ ይራባል:: እናት ስትጠማም እንዲሁ:: በእርሷ መራብ ውስጥ ብዙ ልጆችና ቤተሰቦች አሉና:: ተራበች የሚል ስያሜንም የምንሰጠው በራሷ ብቻ ሳይሆን በልጆቿና በመላው ቤተሰቦቿ ጭምር ነው:: እርሷ ባዶ ሆዷን ቀናትን ታሳልፋለች፤ ሳምንታትና ወራት እንዲሁም ዓመታት በቁራሽ ምግብ ሊያልፉባት ይችላሉ:: ምክንያቱም የመራቧ ምስጢር የእርሷ ሳይሆን የሌሎች ነው:: እናም እናት የሌሎች ጦም ማደር ሲገታ ነው ብዙ ነገሯ የሚሞላው:: ለመሆኑ ይህንን ለምን አነሳን ከተባለ ከብዙዎች መካከል አንዷንና ብርቱዋን እንስት ከነመከራዋ ልናነሳ ስለፈለግን ነው::
ብርቱዋ ሴት ወይዘሮ አስናቀች አጥናፉ ትባላለች:: ከልጅነቷ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እየተፈተነች ሕይወቷ በስቃይ ውስጥ እያሳለፈች ያለች እንስት ናት:: በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በደብረብርሃን አካባቢ ባለች አንድ የገጠር ቀበሌ ውስጥ ነው የተወለደችው::
ይሁን እንጂ የተወለደችበትን ቀበሌ ምንም አታስታውሰውም:: ምክንያቱም አሳዳጊዎቿ እናትና አባቷ አልነበሩም:: እስከ አራት ዓመቷ ድረስ ያለውን የእንቦቀቅላነት ዘመኗን ያሳለፈችው በአክስቶቿ ቤት ነው:: ከአራት ዓመቷ በኋላ ደግሞ አዲስ አበባ ሌላኛዋ አክስቷ ጋር አድጋለች:: ሁሉም ጊዜያት የተለያየ የፈተና አጋጣሚዎች ነበረባቸው:: ደብረብርሃን አካባቢ የኖረችባት አክስቷ እጅግ ስሱና አዛኝ ናት፤ ለእርሷ ጥሩ እናቷ እንደነበረችም አትረሳውም::
መጥፎ አጋጣሚ ባይፈጠር ኖሮ ለዛሬ የመከራ ጊዜ አትጋለጥም ነበር:: ግን ነገሩ በፈለገችው መንገድ አልተጓዘም:: እንደውም ባልጠበቀችው መልኩ ሆነ:: ይህ ክስተት እጅግ ዘግናኝ ነበር:: ዛሬ ድረስ ጠባሳው ይታወሳታል:: ለእርሷ ብቻ ሳይሆን ለአክስቷም ጭምር ህመም ሆኖ የቀጠለ ነበር:: ምክንያቱም ገጠመኙ የአክስቷን ልጅ የነጠቀና እርሷን በእሳት የለበለበ ነው::
ነገሩ የተከሰተበት አጋጣሚ የተፈጠረውም አክስት ልጇን በመዳር ድግስ ላይ ሳለች ነው:: እንደውም ድርጊቱ የተፈጸመው ሙሽራው ሙሽሪትን ይዞ ለመምጣት ሲወጣ እንደሆነ ሰምታለች:: መንስኤው ደግሞ የቤት ሰራተኛዋ ሙሽራውን መውደዷ ነበር:: ማግባቱ ክፉኛ አስቀንቷታልና ባለታሪካችንን ጨምሮ መላ የሙሽራው ቤተሰብ መቃጠል አለበት ብላ ወስናለች:: በዚህም ሰርገኛው ከቤት የወጣበትን ቅጽበት ጠብቃ ቤቱ ላይ እሳት ለቀቀችበት::
በወቅቱ ሕጻኗ አስናቀችና ሌሎች የአክስቷ ልጆች ተኝተው ነበር:: እሳቱም ወዲያው ነበር ያገኛቸው፤ አቃጠላቸውም:: አንዱ ልጅ ወዲያውም ሲሞት እርሷና ሌሎቹ ልጆች ወደ ህክምና ተወሰዱ:: ይህ ደግሞ ለአክስትየው የምትይዘው የምትጨብጠውን አሳጥቷታል::
የንብረቷ ሳይበቃ የልጆቿ ስቃይ ብርቱ ሆኖባታል:: ራሷን ለመቆጣጠር በራሱ ዓመታት ፈጅተውባታል:: በዚህ መካከል ነው አስናቀችም ለህክምና በሚል ወደ አዲስ አበባ ሌላኛዋ አክስቷ ቤት የተላከችውና ኑሮዋን በዚያው ያደረገችው::
ሕጻን አስናቀች ዓመት ያህል ህክምና ላይ ያሳለፈች ሲሆን፤ በቂ ህክምና በማግኘቷና ልጅም በመሆኗ ቶሎ መዳን ችላለች:: ለዚህም የእናቷን እህት ጥሩነሽን ታመሰግናታለች:: እርሷ ከትምህርት አለመማሯ በስተቀር ምንም ያጎደለችባት አልነበረም:: በዚህም ደስተኛ ሆና ቆይታለች:: ከፍ ማለትና መሥራት ስትጀምር ግን ነገሮች ተቀየሩ:: ጉልበቷ የሚሰጠው ጥቅም ብቻ መታየት ጀመረ:: በተለይም የመጠጥ ቤት ሥራ የእርሷ ኃላፊነት ነበር:መማር የሚባል እንዳታስብ ሆነች::
ትምህርት ቤት ገብታ ያለመማሯ ሁኔታ ደግሞ ሁሌ ያንገበግባታል:: እናም ጫና ፈጥራም ቢሆን በማታ ገባች:: ነገር ግን ይህም ቢሆን በፈለገችው መልኩ የምትማርበት አልነበረም:: በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ነው የሚፈቀድላት::
የአክስቷ ቤት ህይወት ሆዷን ከመሙላት ባለፈ ብዙ ምቾት አልሰጣትም:: ስለዚህም ሌላ ምርጫ ውስጥ ገባች:: ይህም በጋብቻ መተሳሰሩ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ትዳሯን መሰረተች:: የሁለት ልጆችም እናት ሆነች:: ግን ይህም እንዳሰበችው አልሆነም:: ብዙ መከራ የበዛበት ነው:: ምክንያቱም የእርሷም ሆኑ የእርሱ ቤተሰቦች እያደር ትዳሩ ላይ ጫናቸውን ማሳረፍ ጀመሩ::
አብረው መኖር የለባቸውም ወደማለቱ ገቡ:: በተለይ የእርሱ ቤተሰቦች ከእርሷ ጋር መኖሩን አልወደዱትም:: እናም በየጊዜው ጫና ያሳድሩበት ጀመር:: ባልም የቤተሰቦቹን ምክር ይሰማልና ሁለቱንም ልጆች ጥሎ ሄደ::
በእርግጥ ከመጀመሪያም ቢሆን ባል በሚስቱ ይቀና ስለነበር አስሮ የማስቀመጥ ያህል ነው ያኖራት:: ወጥታ እንኳን እንድትሠራ አይፈቅድላትም:: ቤት ውስጥ ሰራተኛ ቀጥሮላት ልጆቿን እንድታሳድግ ያደርጋታል:: እርሱ በአናጺነትና ግንበኝት በሚያመጣው ገንዘብ ብቻም ትተዳደራለች:: ጥሩ ኑሮ ነበራቸው::
ግን የቤተሰቡ ጫናና የእርሱም አለማመን ተደማምሮ ትቷት እንዲሄድ አደረገው:: ይህ ደግሞ ብቻዋን ሁለት ልጆችን እንድታሳድግ አስገደዳት:: አራስ ነበረችና ስቃዩዋን አበረከተባት:: በዚህም የምትልሰው የምትቀምሰው ስታጣ የሚያርሳት ፍለጋ ገጠር ሄዳ ከረመች:: ከዚያ መልስም ቤት ለማግኘት ብዙ ተንገላታለች:: ምክንያቱም ልጅ ይዞ የሚያስጠጋ የለም::
ግን ለነፍሴ ያለ የአካባቢው ሰው ሁለቱን ልጆቿን ይዛ በጥገኝነት የምታርፍበት የውሃ ትቦ መተላለፊያ ላይ በቆርቆሮ የታጠረ ቤት ሰሩላት:: እርሷም አንገት ማስገቢያ ያስፈልጋታልና አመስግና ተቀበለች:: ቤቱ አንድም ቀን ተደስታበት የኖረችበት አልነበረም::
እያንዳንዱ ቀናቶች በስቃይ የምታሳልፍበት ነው:: ምክንያቱም በፍሳሽ መልክ የሚመጣው ውሃና ሌሎች ፍሳሾች ከፍራሽ አልፈው ሰውነታቸውን ያረጥበዋል:: ሽታውም ቢሆን የሚቋቋሙት አይነት አልነበረም:: በተለይ ክረምት ሲሆንማ የሚተኙበት ጭምር አይኖራቸውም::
እንደውም ከዚህ ጋር ተያይዞ ዛሬ ድረስ የሚሰቀጥጣት ገጠመኝ አግኝቷታል:: ይህም ኃይለኛ ጎርፍ መጥቶ ልጇን የወሰደባት ሲሆን፤ ብዙ ርቀት ይዞት ሄዶ ነበር:: ሰዎች ባይታደጉላት ኖሮ በሕይወት የመኖሩ ጉዳይ አጠያያቂ እንደነበር ታወሳለች:: በእዚህ ቤት ብዙ ጊዜ ፍራሹ ርጥብ ስለሚሆን ለመተኛት ያዳግታል::
እናም ጠፈፍ እስኪልላት ድረስ ልጆቿን ይዛ ጎረቤት እየለመነች ታድራለች:: ይህ የሆነውም ከሰባት ዓመት በላይ ነው:: ይህ ቢሆንም አንድም ቀን ተስፋ ቆርጣ አታውቅም፤ ልጆቿን ላለማስራብ ሁሌ ትተጋለች:: እርሷ መቀመጥ የሚባል ነገር አታውቅም::
በሰው ቤት ውስጥ ድግስ ካለ ባለሙያ በመሆኗ ሁሉም ይፈልጋታልና ገንዘብ የሚያመጣ ሥራን ሁሉ ትሠራለች:: ልጆቿ አንዳይራቡባትም ከፍተኛ የውሃ እጥረት ባለበት ቡራዩ ከታ አካባቢ የተሻለ ገንዘብ አገኝበታለሁ ብላ ያሰበቸውን ሥራ ለራሷም ፈጥራለች::
ይህም በጄሪካን ውሃ እየተሸከሙ መሸጥ ሲሆን፤ ከቡራዮ ወደ ከታ ውሃ በጄሪካን እያመላለሰች በአንድ ጄሪካን ዋጋ ብር ከሃምሳ ሳንቲም እየተቀበለች ትሠራለች:: በየቀኑ ረጅሙን ኪሎ ሜትር በእግሯ እየተጓዘች 20 ወይም 30 ጄሪካን ትቀዳለች:: ጎን ለጎን ለሲሚንቶ የሚሆን ውሃም እንዲሁ ከወንዝ እየቀዳች ለልጆቿ ሆድ መሙያ የሚሆን ገቢ ታሰባስባለች:: አንድ ቀን ግን ይህን ማድረግ አልቻለችም::
ምክንያቱም የውሃ ችግር ያሰቃየው የነበርው የከታ አካበቢ ነዋሪ ውሃ በየቤቱ መጣለት:: እናም በጉልበቷ የምትሰራበትን ሥራ አቆመው:: እነዚህን ሥራዎች ስታከናውን የምታገኘውን ገንዘብ ለእለት ጉርሳቸው ብቻ ነበር የምታወጣው:: ከዚያ ያለፈ ነገር ስለሌላት ልጆቿን ማስገረዝ ቢኖርባትም ልታደርገው አልቻለችም:: ዛሬም ድረስ ሁለቱ ወንድ ልጆቿ አልተገረዙም::
ግን ባዶ ሆዳቸውን ስላላሳደረቻቸው አልተከፋችም በእድሏ ከማዘን ውጪ:: ልጆቿን ከመመገብ ጋር በተያያዘ ከሦስት ዓመት በፊት መራር ነገር ገጥሟት ነበር:: እንደውም ‹‹ዳግም እግዚአብሔር ያንን ፈተና አያምጣብኝ›› ትላለች:: ለማንም እናት ይህንን ፈተና አይስጣትም ባይ ነች:: ምክንያቱም የልጅ መራብ ለእናት ምን እንደሆነ ስለምታወቅ:: የገጠማት ነገር እንዲህ ነው:: ልጆቿ ራበን እያሉ ይጠይቋታል:: በቤት ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ ግን የለም::
የዚህ ጊዜ ምን እንደምታደርግ ግራ ገባት:: በቀላሉ የምታደርገው እንደሌለም ታውቃለች:: እናም የማትወደውን፤ ልትጠቅሰው የማትፈልገውን ነገር አደረገች:: ለልጆቿ ስትል ራሷን ለማዋረድም ወስና ለልመና የማትታወቅበት ቦታ ላይ ሄደች:: ሻርፕዋን ዘርግታ ሰዎችን መማጸን ጀመረች::
የሰውን ፊት አሰቃቂነት ተጋፈጠች:: በዚህም ልጇ ፍርፋሪ ሲያገኝ እርሷ ሦስት መቶ ብር አግኝታ ወደ ቤቷ አመራች:: ለጊዜው እፎይ ብትልም ዳግም ነገሩን ማንሳት ግን አትፈልግም:: ምክንያቱም ለልጆቿ የሚነገር ነገር አይደለም:: ለእኛም ቢሆን ይህንን ስትነግረን ለማንም ያልተናገርኩት ምስጢሬ ነው በማለት ነበር::
እርሷ ልመና አሳፋሪና አዋራጅ እንደሆነ ታምናለች:: ሰዎች ሰርተው እንጂ ለምነው ማንንም መመገብ የለባቸውም አቋሟ ነው:: ስለዚህም ለልጆቿ መንገር የምትፈልገው የሰው ቤት ሠራተኛ ሆና ለዚህ እንዳበቃቻቸው እንጂ ለምና በአመጣችው ገንዘብ እንደኖሩ አይደለም::
ሰዎችም ልመና ውስጥ ወደው ባይገቡም መለመንን ግን አብልጠው መውደድ የለባቸውም፤ የኑሯቸው መሰረትም ሊያደርጉት አይገባም ስትል ትመክራለች:: አስናቀች ብዙ መከራና ስቃይ አሳልፋለች:: በዚህም ትንሽ እንኳን ፋታ ባገኝ በሚል ሌላ ባል አግብታለች:: እርሱም በጣም ጎበዝና ጠንካራ ሰራተኛ ነበር:: በተለይም በከሰሉ ንግድ ማንም አያክለውም:: ሕይወቷ መለስ ያለውም በእርሱ ሥራ ጭምር እንደነበር ትናገራለች:: ምክንያቱም ሁለቱ እየተረዳዱ ብዙ ነገራቸውን ለውጠዋል:: ሁለት ልጆችን ጨምረው ደስተኛ ኑሮም እየኖሩ ነበር::
ግን አትረፊ ያላት ነብስ አሁንም ፈተና ገጠማት:: ይህም በአዕምሮ ህመምና ጭንቀት ምክንያት የባለቤቷ ሥራ ቆመ:: ለዚህ መንስኤው ደግሞ የሚወደውን ሥራ ባልጠበቀው አጋጣሚ ማጣቱ ነው:: ከሰል ቤት ከፍቶ እየሠራ ሳለ ከሰል የሚያመጣለት የአጎቱ ልጅ ስልክ ደውሎ ‹‹መንገድ ላይ ከሰሉ ተያዘብኝ 50 ሺህ ብር ካልሰጣችሁኝ አይለቀቅም›› አላቸው::
እነርሱም ተመካክረው በእርሷ አማካኝነት ያላቸውን ገንዘብ ላኩለት:: ይሁን እንጂ ከሰሉም ሆነ ሰውዬው የውሃ ሽታ ሆኑ:: ይህ ሳይበቃቸውም ‹‹በእቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ ሌላ ተጨማሪ ችግር ገጠማቸው::
ይህም የመዘረፍ አደጋ ሲሆን፤ የሚኖሩበትና የከሰል ቤታቸው የተራራቀ በመሆኑ አንድ ቁምጣ ከሰል ሳይተርፍላቸው ተዘረፉ:: የሚሠሩበት ገንዘብ ከማጣት አልፈው በቤት ውስጥ ለሚበላ ለሚጠጣ እንኳን አጡ:: ሁኔታው ከመጠን በላይ መከራን አበዛባቸው::
በዚህም እርሷ ብትጠነክርም ባለቤቷ ግን መቋቋም ተሳነው:: ስለዚህም የአዕምሮ ህመምተኛ ሆነ:: አሁንም ድረስ ምንም አይሰራም:: ይህ ደግሞ ከአራቱ ልጆች በተጨማሪ ባሏን ጭምር እንድታስተዳድር አስገድዷታል:: ሥራ አልቆባት የማያውቀው መከረኛዋ እናት ሌላ ሥራ ውስጥ የገባች ሲሆን፤ የኮሮና ወረርሽኝ መከሰትን ምክንያት በማድረግ የፈጠረችው ሥራ ነው:: በእርግጥ ይህንን ያሰበችው ያለምክንያት አልነበረም:: ወቅቱ ሁሉም እርስ በርሱ ለመገናኘት የተፈራራበት፤ መንግስትም ቢሆን ማንም ሰው ከቤቱ እንዳይወጣ ብሎ ያወጀበት ነው:: እናም ለሥራ ፈላጊዋ አስናቀች ብዙ ነገሮች ተዘግተውባታል:: ስለዚህም በነጻነት የምትሠራበትን አማራጭ ስትፈልግ ማስክ መሸጥን መፍትሄ አደረገች::
ነገር ግን በደንቦች ተደጋጋሚ ንጥቂያ ብዙ ኪሳራ ገጥሟት ያውቃልና መሥራቱን አቆመች:: ግን ቁጭ ብትል ልጆቿን የምትመግበው ነገር አይኖራትምና በቆሎ እየጠበሰችና በደረቁ መሸጡን ተያያዘችው::
ክረምትን የተወጣችውም በዚህ ሁኔታ ነበር:: ከዚያ በኋላ ወይም በጠዋት ተነስታ ልጇን አዝላ ጭምር ልብስ ታጥባለች:: ያጊዜ እጅግ ሁለተኛ ስቃይ ያበረታባት እንደነበር የምታስታውሰው ባለታሪካችን፤ ሕይወት ከየትኛም ጊዜ በበለጠ አስቸጋሪ እና አስከፊ የሆነበት፣ ለልጆቿ ምን እንደምታበላቸው የተጨነቀችበት ነበር:: ቤት ውስጥ ከአንድ ነገር በስተቀር ምንም የለም::
ይህም የበሰበሰ ምስር ሲሆን፤ ያንን መስጠት ደግሞ እጅግ ከባድ ነው:: ግን ምርጫ አልነበራትምና አድርገዋለች:: ሁለት ቀንም በዚያ ቆይተውላታል:: አሁን ያለችበት ሁኔታም ከበፊቱ የሚሻል አይደለም::
በጣም ችግርና መከራ የበዛበት ነው:: ከምትኖርበት ቤት ብንነሳ ፍራሽ አያዘረጋም፤ ሽንት ቤትም የለውም:: ኪራዩም እንዲሁ ከፍተኛ ነው:: በዚያ ላይ ጋግራ የምትመግብበት ኩሽና እንኳን አልተሰራላትም:: ስለዚህም ገዝታ እንጂ ሰርታ የምትመግብበት ሁኔታ የላትም::
ያ ብቻ ሳይበቃ ከጥበቱ የተነሳ አይደለም ስድስት ሰው ሁለትም አያስተኛም:: ስለዚህም መተኛትም ይከለከላሉ:: የጭቃ ቤት በመሆኑ ሽታውም አያስቀምጥም:: በዚህ ምክንያት ልጆቿ ብቻ ሳይሆኑ ባለቤቷም ጭምር ታማሚ ሆኗል:: እርሷም ብትሆን የአስም በሽተኛ ናት::
ይህ ደግሞ ለህክምና ሌላ ወጪ እንድትጨምር አድርጓታል:: እርሷ ሠርታ ከምታመጣው ውጪ ምንም የገቢ ምንጭ ለሌለው ቤተሰብ ደግሞ ኑሮው ምን ያህል ከባድ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም::
ለአንዱ ልጇ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን በዓመት አንድ ጊዜ ድጋፍ ያደርግለት ነበር:: ይህም በዚህ ዓመት ቀርቷል:: እናም እጅግ ከባድ ፈተና ውስጥ ወድቃ ትገኛለች:: በንጽህና ጉድለት፣ በምግብ እጦትና እንቅልፍ ማጣት ችግር ልጆቿ ይታመማሉ:: ትምህርት ቤትም በተለያየ ምክንያት መሄድ አልቻሉም::
ባለቤቷም ቢሆን ብዙ እገዛን የሚፈልግ ነው:: ስለሆነም ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግሬን ይይልኝ፤ የቻለውን ያድርግልኝ›› ስትል ትማጸናለች:: በተለይም ኮልፌ ወረዳ 14 የጉልት ቦታና የቀበሌ ቤት ቢያመቻችላት ለጉልበቷ ሳትሳሳ እንደምትሠራና ለእርሷና ለቤተሰቦቿ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ምሳሌ እንደምትሆንም አውግታናለች:: እኛም የሚመለከተው አካል ይህንን ፍላጎቷን ቢያሳካላትና ለባለቤቷም እገዛ ቢያደርግለት ብዙ ነገሮች ይለወጣሉና ለሰው ደራሽ ሰው በመሆኑ ይድረስላት ስንል መልዕክታችንን እናስተላልፋለን:: ሰላም!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን የካቲት 19 /2014