የብዙዎቻችን ወቅታዊና ታላቅ ጉዳይ፤ የመወያያችን ቀዳሚ አጀንዳ።የኑሮ ውድነት።እኔምለው ይህ ስያሜ ግን ተገቢ ነው? ኑሮ ውድ መሆን የለበትም እንዴ።ስለምን ኑሮ ይረክሳል ጎበዝ! ኑሮማ መወደድ አለበት።ኑሮ ውድ ካልሆነ እንዴት ሊጥመን ይችላል።
በፍፁም መርከስ የለበትም።መኖርማ ውድ ሊሆን ይገባል። እኔ ሰዎች ኑሮ ተወደደ ሲሉ ደስ ይለኛል ብላችሁ ምን ትሉ ይሆን? ኑሮ መርከስ የለበትም ብዬ ስለማምን ነው።ኑሮማ እጅጉን መወደድ ይገባዋል።
መርከስ ያለበት መኖሪያው ነው፤ ለመኖር የሚያስፈልገን ነገር።እኔ ለመኖር የሚያስፈልግን ጉዳይ ሁሉ ነው መኖሪያ የምለው።ለመኖር የሚያስፈልጉ መኖሪያ ቤት፣ ምግብ፣ አገልግሎት እና የመሳሰሉት እንጂ ዋንኛው ኑሮማ መርከስ የለበትም። እናም ወገን እኔም ስለመኖሪያው መወደድ እጅጉን አሳስቦኛል።
መኖሪያው መወደዱ እጅጉን ተባብሶ ቀጥሏል።መኖሪያ ስል ቤትን ብቻ ማለቴ አይደለም። ቤት ያለምግብ ኑሮ ያለ መሰረታዊ ፍላጎት አይሆንማ።እነዚህ ተጠቃለው ነው መኖሪያን የሚወክሉት። የኑሮ ውድነት ወደሚለው ተመልሻለሁ።ዛሬ ሱቅ ሄደን የምንፈልገውን ዕቃ ስጠን ብለን ባለሱቁን መጠየቁን ትተን የመጀመሪያና ቀዳሚው ጥያቄያችን “እ… ስንት ገባ?” የሚለው ሆኗል።
ስግብግብ ነጋዴ በበዛበት፣ ህገወጥን መቆጣጠር ትኩረት ባልተሰጠበትና በከበደበት፣ አንዱ ራሱን ባልተገባ መልክ ሊለውጥ የሌላውን ኑሮ መልክ የሚያሳጣ ተግባር የሚፈፀምበት ጊዜ ላይ ነን።ይህ ሁኔታ እየከፋ መጥቷል፡፡
በእርግጥ የነጋዴዎች ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪና ህገወጥ የንግድ ሰንሰለት መንሰራፋት የመኖርን ጣዕም ያሳጣ የዋጋ ንረት ቢያስከትልም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሸቀጦች፣ ማጓጓዝና ነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር፣ ኮሮናና የሰላም መደፍረስ ጉዳዩን የባሳ እንዲወሳሰብና አደርጎውታል።ዓለም አቀፍና አገራዊ ሁኔታዎችን ብንሸከምም በንግዱ ማኅበረሰብ የሚፈጠሩ የገበያ አሻጥሮች ግን ገበያው እንዳይረጋጋ ያደረጉ ዋንኛ ምክንያቶች ሆነው ይታያሉ፡፡
ነጋዴው አከፋፋዮች በአንድ ካርቶን ሸቀጥ ላይ 5 ብር ሲጨመሩበት ወደ ሱቅ አምጥቶ በእያንዳንዱ ነጠላ እቃ ላይ 10 ብር ማትረፉን ልማዱ አድርጎታል።ለእያንዳንዷ ምክንያት ጭማሪ ማድረግ ላይ ያተኩራል፤፤
ለምን ሲባል ዋጋ ጨምሯል ሆኗል መልሱ፤ ማኅበረሰቡ ከየት አምጥቶ ያንን ይሞላል የሚለው ለሱ ጉዳዩ አይደለም።በእዚህ ዋጋ አትሸጥም? ተብሎ ሲጠየቅ መልሱ ከቦታውም አልመጣ፤ እኔም ባገኝ አገዛሃለሁ ሆኗል መልሱ።ነጋዴው ብሶበታል ወገን። በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ በነዳጅ ዋጋ ላይ እየተፈጠረ ላለው የአቅርቦት እጥረት አንዱ ምክንያት በድጎማ ለሕዝብ የሚቀርበው ነዳጅ በህገወጥ ነጋዴዎች ለጎረቤት አገራት መሸጡ ነው።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይላሉ ይሄ ነው።በነዳጅ ምክንያት እያንዳንዱ አገልግሎትና ቁስ ምን ያህል በሰንሰለት እንደሚንርና ለዋጋ ጭማሪ መነሻ እንደሚሆን እየታወቀ፣ ከአገር ይልቅ ራሳቸውን የሚወዱ ህገወጥ ዘራፊዎች በዚህ ተግባር መሰማራታቸው በእጅጉ ያስቆጫል።ኢትዮጵያ ነዳጅ አምራች እስከምትመስል ድረስ ወደ ጎረቤት አገር በህገወጥ ንግድ ነዳጅ መሸጡ በእርግጥም ሌላ አሳሳቢ ችግር ነው፡
ይህ ህገወጥ ድርጊት ምን ያህል ኢኮኖሚያዊ ጫና እንደሚያስከትል መገንዘብ አያዳግትም።በዚህ ሰንሰለት ውስጥ ያሉ አካላት መሰል ተግባር ላይ እንዳይገኙ የሚመለከተው አካል ሚናውን እንዲወጣ ጥሪም ማሳሰቢያም ተሰጥቶበታል።ይህን ተከትሎም ከወደዚያ የሚሰማ እርምጃ እንጠብቃለን። በየመንደሩ የሚካሄደው መሰል ህገወጥ ተግባር ለዋጋ መናር ትልቁን ድርሻ አለው።
ሕዝብ የሌለበት አካባቢ፣ ሰዎች የማይደርሱበት መንደር የለምና ከህግ አስከባሪው የላቀ አይንና ጆሮ ያለው ማህበረሰብ መፈጠር ከቻለ ህገወጡን ለህግ ማስገዛት እጅጉን ይቀላል። እንኳን ተነናጥሎ ተደጋግፎም ቆሞ በሚከብድ ጊዜ ላይ እንገኛለን።በአገራችን ችግርን የሚያከብዱ የዋጋ መናርና የኑሮ ውድነትን የሚባብሱ የብዙ ጉዳዮች በበረከቱበት በአሁኑ ወቅት ህገወጦችን በጋራ መታገልን የገድ ነው።
ሰው ሆኖ ስለሰው ማሰብ ቁጥብ ሆኖ እንደ አገር መቆም ይገባል። ህገወጥ ነጋዴውም ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም የሚያኖረውን ማህበረሰብ ባይበዘብዝ መልካም ነው።ወዳጅህ ማር ቢሆን ጨርሰህ አትላሰው እንደሚባለው ተጠቃሚው አማራጭ አጥቶ ህገወጥ ነጋዴው በጠራው ዋጋ ቢገዛም፣ ለእምነትም፣ ለህግም ለሰብአዊነትም በመገዛት በህጉ አግባብ መነገድ መልካም ነው፡፡
ኮሮና የእርስ በርስ ግጭትና የሰላም እጦት የዚህች አገር ታላቅ ችግር ሆነው ሳለ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ፣ የሸቀጦች፣ የሎጂስቲክስ ዋጋ በእጅጉ ጨምሮ ሳለ በተለመደው እና ከተመለደውም በላይ አዳዲስ ህገወጥ ተግባሮችን በመፈጸም ሸማቹን ማራቆት አይገባም።የሸማቹ መራቆት ሸማቹ ዘንድ ብቻ አያቆምም አገራዊ ጉዳይ ፣ የመንግስት ፈተና ይሆናል።
መንግስትም ሕዝቡን ሲታድግባቸው የቆየባቸውን የመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት ይበልጥ አጠናክሮ ሊቀጥልበት ይገባል።ከዚህ ባሻገርም ለዋጋ ንረቱ ምክንያት የሆኑ ሌሎች ምክንያቶች ካሉ በባለሙያ ማስጠናት ሌሎች አዳዲስ መፍትሄዎችንም መፈለግ ይኖርበታል። በዓለም ዙሪያ እየተፈጠሩ ባሉ ግጭቶች ምክንያትም የገበያ ሁኔታ ይበልጥ አለመረጋጋት ውስጥ ሊገባና የዋጋ መናር በእያንዳንዱ አገልግሎትና አቅርቦት ላይ ሊደራረብ ይችላልና፤ የንግዱን ሂደት ስርዓት በማስያዙ ተግባር ላይ አሁንም ርብርብ ማድረግ ይገባል።
ለእዚህ ደግሞ ማህበረሰቡ ከህግ አስከባሪዎች ጋር አብሮ መቆም ይኖርበታል። ጉዳዩ ለመንግስት ብቻ የሚተው መሆንም የለበትም።በእያንዳንዱ እንቅስቃሴና ተግባራችን ውስጥ ትልቅ የሆነችዋን አገራችንን ከዚህ ነባራዊ ሁኔታ አሻግረን ማየት ይኖርብናል።
ነገ ለሁላችንም ምቹና ለሌሎች አገራት ምርኩዝ ትሆን ዘንድ የዛሬን አስቸጋሪ ሁኔታ አብሮ ተደጋግፎ ማለፍ፣ አስቸጋሪ ሁኔታውን የሚፈጥሩ አካላትንም በቆራጥነት አንድ ሆኖ መታገል ይገባል።
በእርግጥም በእያንዳንዱ ተግባር ሀላፊነት የሚሰማው ማህበረሰብ በችግሮች ውስጥ መፍትሄን ወልዶ ለሌላ ስኬት በር የሚከፍት ነውና ይህን ጊዜ በብልሀትና በአንድነት አልፈን ቀጣይ ጊዜን ብሩህ ማድረግ የእያንዳንዳችን ጥረት ይጠይቃል።አበቃሁ፤ቸር ያሰማን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን የካቲት 19 /2014