ሴትና አገር፤ አገርና ሴት ከአንድ ወንዝ የተቀዱ ይመስሉኛል። በአገር ውስጥ ሴትነት፣ በሴትነት ውስጥ አገር ጥዑም ዜማ ናቸው። በአገር ውስጥ ሴት ቅኔ ናት፣ በሴትነት ውስጥ አገር ዜማ ናት።
በተለይ ሄለንን ሳይ ይሄ ሀሳቤ እውነትነትን ተላብሶ አገኘዋለሁ። ድሮ ህጻን እያለን እኛ የሰፈር ልጆች በቴሌቪዥን ያየነውን ጫማና ልብስ ስናስገዛ እሷ ግን አረንጓዴ ቢጫ የተጠለፈበትን የሀበሻ ቀሚስ ካልተገዛልኝ ብላ ታለቅስ እንደነበር እናቴ ነግራኛለች። ልብሷ፣ ጫማዋ፣ ጸጉር ማሲያዣዋ፣ ደብተሯ ሁሉ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ አለው። የሕይወትህ ትልቁ ትዝታ ምንድነው ብባል ሄለንና የኢትዮጵያ ባንዲራ ያለበት ልጅነቴ እላችሁ ነበር።
ሁሉ ነገሯ ላይ በሀበሻ ድርና ማግ የተጠለፈ ጥልፍ አይ ነበር። ልጅ ሆኜ ኢትዮጵያ ሄለንን ትመስለኝ ነበር። በልጅነቴ ብቀርባት ደስ የሚለኝ ሴት ሄለን ነበረች፤ ቆንጆ ስለነበረች ግን እፈራት ነበር። ልጅ ሆኜ ኢትዮጵያን ያስተዋወቀችኝ እሷ ነበረች። እናት እና አባቴ እንኳን የእሷን ያህል ኢትዮጵያን የሚያውቋት አይመስለኝም።
እርግጥ አባቴ በብዙ ተጋድሎ ኢትዮጵያን ከጠላት ከታደጉት ውስጥ አንዱ እንደሆነ አውቃለሁ። እናቴም እስከ ዛሬ ድረስ የማይረሳኝን ባለባንዲራ መቀነቷን ታጥቃ ቤቱ ውስጥ ስትንጎማለል አስታውሳለሁ።
ይሄ አልበቃ ብሏት ይሄንኑ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ የተሸመነ መቀነቷን በመታጠቅ በየገበያው፣ በየመንደሩ በመዞር ኢትዮጵያን አስተዋውቃለች። እኛ ቤት ከእኔ በቀር ለኢትዮጵያ ዋጋ ያልከፈለ ማንም የለም።
ሁለቱ ታላላቅ ወንድሞቼ እንኳን እንደ አባቴ ለአገር ህልውና በጦር ሜዳ ዋጋ የከፈሉ ናቸው። ቤት ፊት ለፊት የአባቴ የአርበኝነት ፎቶና የሁለት ታላላቅ ወንድሞቼ የጦር ሜዳ ፎቶግራፍ በባለ ወርቃማ ፍሬም ውስጥ ይታያል። የሄለን ግን ይለያል፤ ዛሬም ድረስ እንደ እሷ ኢትዮጵያን የሚመስል ሰው አላየሁም። ትምህርት ቤት የዜግነት ክብር ስንዘምር፣ አሁን አድጌ መስሪያ ቤታችን ባንዲራ ሲወጣና ሲወርድ ፊቴ የምትመጣው እሷ ናት። በጣም የሚገርመው ደግሞ አድጌ ስለ እሷ ማሰቤ ነበር።
ልጅነቴ ወጣትነቴ ፊት እየመጣ ስለሄለን እያሰብኩ ዛሬን መኖር እያቃተኝ መጥቷል። ሄለን ጥላብኝ የሄደችው የልጅነት አሻራ ነው መሰለኝ ልቤ በዛሬዬ ውስጥ እንደ እሷ ያለች አገር ወዳድ ሴት አምጣ ይለኛል። ከየት ላምጣ? ሁሉ ዳንኪረኛ ነው፣ ሁሉ ፈረንጅኛ ነው። የሚዜመው ፈረንጅኛ፣ ዳንሱ ጭፈራው ሁሉ ሌላ.. ከዚህ ዓለም ውስጥ ሄለንን ከየት ፈልጌ ላምጣት። መስሪያ ቤታችን ውስጥ ከቀረብኳቸው አራት ሴቶች ውስጥ ሁለቱ ኢትዮጵያን ከነጭራሹ አያውቋትም። ጠዋት ከቤት ወደ ስራ ሲመጡ በፈረንጅኛ ነው ሰላም የሚሉኝ።
ማታ ወደ ቤት ሲሄዱ ጆሯቸው ላይ ማዳመጫ ሰክተው ፈረንጅኛ ያደምጣሉ። ቅዳሜና እሁድ ሲሆን መገኛቸው ጭፈራ ቤት ውስጥ ነው። የቀሩት ሁለቱ ደግሞ እንዴት የኢትዮጵያ ዜግነት እንዳገኙ አላውቅም። ወሬአቸው ሁሉ አሜሪካ ናት። አብሬአቸው አምስት አመት ስሰራ ውጭ ከመሄድ ውጭ ደስታ እንዳላቸው አልሰማሁም።
ኢትዮጵያን እንደማያውቋት ያረጋገጥኩት አንድ ጊዜ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ ጋር ተዋግታ ያመጣችው እንደሆነ ሲከራከሩ ሰምቼ ነው። ከአራት ሴቶች ነፍስ ውስጥ ሄለንን አጣኋት…። ከተማው ውስጥ ብዙ ሴቶች አሉ። በፈረንጅኛ የዘመኑ፣ የኢትዮጵያዊነትን ውብ መልክ ከባዕድ ጋር የቀየጡ።
በአማርኛ መሀል እንግሊዝኛ ካልቀላቀሉ ያልዘመኑ የሚመስላቸው፣ ገላቸውን ካልገለጡና እንብርታቸውን ካላሳዩ ያማሩ የማይመስላቸው። ከወንድ ወንድ፣ ከሴት ሴት ካልዞሩ ዘመናዊነት የሚጠፋቸው፣ አድምቆ ባሳደጋቸው ባህል ላይ በነውር የቆሙ ብዙ ጭንጋፍ ትውልዶችን አውቃለሁ። ሄለን ግን የተለየች ነበረች፤ ነፍሷን የት ልድረስባት? እዚህ ዓለም ላይ እንደ ሄለን ያለ አራዳ አላየሁም፤ ከልጅነቴ እስከ እውቀቴ ድረስ የምታስደንቀኝ ሴት ናት።
ለካ አራዳነት ራስን መሆን ነው። ለካ አራዳነት አገርን መውደድ ነው። በዚያ የልጅነት ነፍሷ ውስጥ ያን የሚያህል ገናና እውነት ማን ሰጣት እላለሁ። ዛሬም ድረስ እኔና መሰሎቼ ያልደረስንበትን የአገር ፍቅር ስሜት ከወዴት አገኘችው ስል እቆዝማለሁ። ሄለን የተለየች ነበረች፤ ነፍሷን የት ልድረስባት? አንድ ቀን አንድ ቅዳሜ እንዲህ እያሰብኩ እያለ ነበር እናቴ ድንገት ወደ መኝታ ክፍሌ መጥታ የልጅነት ጓደኛህ ሄለን መጥታለች ሂድና ጠይቃት ያለችኝ።
ያን እለት፤ ያን ቅዳሜ መቼም አረሳውም። እናቴ ከመላዕክቶች አንዱን ሆና ፊቴ የቆመች ነበር የመሰለኝ። እንደዛ ቀን አፍጥጬ አይቻት አላውቅም፤ ፊቴ ላይ በርካታ ጥያቄዎች ነበሩ፤ አንዱንም ሳልጠይቃት ምን ያደናብረሀል ብላኝ ከክፍሌ ወጣች። አልጋዬ ላይ ነፍስ ዘራሁ፤ ለዝንተ ዓለም የማልረሳውን አዲስነት ተከናነብኩ። ሄለን የደስታዬ አጥቢያ ነበረች፤ በልጅነቴ ውስጥ አብቅዬ በወጣትነቴ ውስጥ እንዳሳደኳት ያን ቀን ገባኝ። ግን ያን ቀን ወደ ሄለን አልሄድኩም፤ ፈራኋት። ወጣትነቷን ፈራሁት።
በሕይወቴ የወሰንኩት ትልቁ ውሳኔ ያ ይመስለኛል፤ ወደ ሄለን አለመሄዴ። አንድ ወንድ ለዘመናት የናፈቃትን ሴት ለማየት አሻፈረኝ ሲል ይሄ እውነት በምን ይገለጻል? ሲፈልጋት ኖሮ በአንድ አመሻሽ መምጣቷን ሲሰማ ካለችበት ላለመሄድ ምን ምክንያት ይኖረዋል? የኔ ምክንያት…ሄለንን ዳግም እንዳላፈቅራት መፍራት ነበር።
ዛሬም ድረስ የምወዳት ሴት፣ በዓለም ላይ አምሳሏን ፈልጌ ያጣኋት ሴት በልጅነቷ ነፍሴ ላመል በጨረፍታ ያየኋት ሴት ናት። ዛሬ በደርባባነት፣ በብዙ ውበት፣ በብዙ ማማር ፊቴ ቆማ ሳያት በሕይወት የምኖር አይመስለኝም፤ ፍቅሯ የሚገለኝ ይመስለኛል። ለዚህም ባልሄድ፣ ባላገኛት ስል ወሰንኩ።
ሄለን ጋ ሳልሄድ መሸ ፤ እናቴም እዛ ሄዳ ነው መሰለኝ ድምጽዋ ጠፋ። ጠዋት የጀመርኩትን መጽሐፍ ገልጬ ሳሎን ቁጭ ብያለሁ። ከወደ ውጭ ከእናቴ ድምጽ ጋር የሚላተም አንድ ወጣት ድምጽ ተሰማኝ። ይሄ ድምጽ በልጅነቴ ውስጥ የሆነ ቦታ ላይ ነፍስ ዘርቶ ነበር።
እኔንና ወንድነቴን አራቁቶ ዛሬም ድረስ ይሰማኛል። ሄለን ነበረች። ነፍሴ ተራቆተች፤ ደግሞም ደስ አላት። የእናቴን ዳና ተከትላ ወደ ቤት ስትገባ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት ግንባሯ ላይ ያደረገችውን የኢትዮጵያ ባንዲራ ነበር።
በትረሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን የካቲት 18 /2014