
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሲካሄድ የቆየው የሰላም ድርድር ማብቃቱን በመግለጽ በዩክሬን ምሥራቃዊ ክፍል ተገንጥለው ለሚገኙ አማፂ ክልሎችን ዕውቅና ሰጡ።
ለራሳቸው ነጻነታቸውን ያወጁት የዶኔስክ እና የሉሃንስክ ሕዝባዊ ሪፐብሊኮች በሩሲያ የሚደገፉ አማፂያን ሲሆኑ እአአ ከ2014 ጀምሮ ከዩክሬይን ጦር ጋር ሲዋጉ የነበሩ።
የሩሲያ ወታደሮች በሁለቱም ክልሎች “የሰላም ማስከበር ሚናቸውን” እንዲወጡ ታዘዋል።
ሩሲያ ሆን ብላ ሉዓላዊነታችንን እየጣሰች ነው ሲሉ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ከሰዋል።
ፕሬዚደንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ በቴሌቭዥን ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር ዩክሬን ሰላም እንደምትፈልግ ገልጸዋል።
አክለውም “አንፈራም” ካሉ በኋላ “ለማንም አሳልፈን የምንሰጠው ነገር አይኖርም” ብለዋል።
ኪዬቭ ከዓለም አቀፍ አጋሮቿ “ግልጽ እና ውጤታማ የድጋፍ እርምጃዎች” እንደሚያስፈልጋት ጨምረው ጠቅሰዋል።
“አሁን እውነተኛ ወዳጃችን እና አጋራችን ማን እንደሆነ እና የሩስያ ፌዴሬሽንን በቃላት ብቻ ማስፈራራትን የሚቀጥል ማን እንደሆነ ማየት በጣም አስፈላጊ ነው” ብለዋል።
የምዕራቡ ኃያላን አገራት ፑቲን በአማፂያኑ ቁጥጥር ሥር ላሉ አካባቢዎች ዕውቅና መስጠታቸው የሩስያ ወታደሮች ወደ ዩክሬን ምሥራቃዊ ክፍል በይፋ እንዲገቡ መንገድ ይከፍታል የሚል ስጋት አድሮባቸዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲያ የሩስያ ፓስፖርት በዶኔስክ እና በሉሃንስክ ለብዙ ሰዎች ተሰጥቷል።
የምዕራባውያኑ ስጋትም ሩሲያ ዜጎቼን ለመጠበቅ በሚል ሽፋን ወታደሮቿን ልታንቀሳቅስ ትችላለች የሚል ነው።
ከሰኞው መግለጫ በኋላ አንድ ሰዓት የሚፈጅ ንግግር ያደረጉት ፑቲን ዘመናዊዋ ዩክሬን በሶቪየት ሩሲያ “የተፈጠረች” ናት ብለው “የጥንታዊት ሩሲያ መሬት” በማለትም ገልጸዋታል።
እአአ በ1991 በተካሄደው የሶቭየት ኅብረት ውድቀት ወቅት ሩሲያ “ተዘርፋለች” ብለዋል።
ዩክሬንን በአሻንጉሊት መንግሥት የምትመራ “የአሜሪካ ቅኝ ግዛት ናት” በማለት የጠቀሱ ሲሆን፤ አሁን ባለው አመራር ዜጎች እየተሰቃዩ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
እአአ በ2014 የተካሄደውን እና በሩሲያ የሚደገፍ የነበረውን አመራር ከሥልጣን ያወረደውን ተቃውሞ መፈንቅለ መንግሥት ሲሉ ገልጸውታል።
ዩናይትድ ስቴትስ የፑቲንን እርምጃ በፍጥነት አውግዛለች።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም መገንጠል በሚፈልጉት ክልሎች የአሜሪካውያንን አዲስ ኢንቨስትመንት፣ ንግድ እና ፋይናንስን የሚከለክል ትዕዛዝ ፈርመዋል።
እርምጃዎቹ “ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች” ለመጣል ዝግጁ ከሆኑት የምዕራባውያን ማዕቀቦች የተለዩ መሆናቸውን ኋይት ሃውስ አስታውቋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የሩስያ ድርጊት ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጻረር “የዩክሬንን ሉዓላዊነትን በግልፅ የጣሰ ነው” ብለዋል።
“ጥሩ ያልሆነ ምልክት እና ጥቁር ምልክት” ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊዝ ትሩስ በበኩላቸው እንግሊዝ ማክሰኞ ዕለት በሩሲያ ላይ አዲስ ማዕቀብ እንደምትጥል አስታውቀዋል።
የአውሮፓ ኅብረት “ከዩክሬን ጎን በመቆም በአንድነት፣ በጥንካሬ እና በቁርጠኝነት ምላሽ ለመስጠት” ቃል ገብቷል።
የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን በበኩላቸው የሩስያ ወታደሮችን የሰላም ማስከበር መግለጫ ሐሳብ ውድቅ በማድረግ “ተቀባይነት የሌለው፣ ያልተመጣጠነ፣ ያልተገባ፣ ከንቱ ሐሳብ ነው” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የቭላድሚር ፑቲን እርምጃ ከ150,000 በሚበልጡ የሩስያ ወታደሮች ድንበሯ ለተከበበው ዩክሬን የነበረውን ቀውስ የበለጠ ያጠናክረዋል።
ሩሲያ ለመውረር አቅዳለች መባሉን ውድቅ ስታደርግ አሜሪካ ደግሞ ጥቃት አይቀሬ እንደሆነ ታምናለች።
የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ሾልስ እና የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከመግለጫቸው በፊት የሩስያውን መሪ አነጋግረዋል።
ምዕራባውያን አገራት ከዩክሬን ጀርባ በመሆን ሩሲያ ወረራ ከፈጸመች ከባድ ማዕቀብ እንደሚጠብቃት ቃል ገብተዋል።
ለአሁኑ የሩሲያ እርምጃ ምላሹ ምን እንደሆነ እስካሁን ግልጽ አይደለም።
ከአወዛጋቢው ውሳኔ ቀደም ብሎ ፑቲን የሩሲያን የፀጥታ ምክር ቤት ሰብስበው ክልሎቹ ራሳቸውን የቻሉ ነጻ ሪፐብሊካኖች መሆናቸውን በማረጋገጥ ጉዳይ ሲወያዩ ነበር።
የፑቲን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሐሳባቸውን ለመስጠት ወደ መድረክ የተጠሩ ሲሆን ሁሉም እርምጃውን እንደሚደግፉ ተናግረዋል። በቴሌቭዥን የተሰራጨው የሰኞው ስብሰባ ግን ሙሉ በሙሉ የተሳካ አልነበረም።
ከፑቲን ጋር በተደረገው ውይይት ወቅት ሁለት ባለሥልጣናት ክልሎቹን ወደ ሩሲያ “የማካተት” ዕድልን የሚጠቅሱ መስለው ነበር። በሁለቱም አጋጣሚዎች ፑቲን አርመዋቸዋል።
“እየተነጋገርን ያለነው ለነፃነታቸው ዕውቅና ስለመስጠት ወይም ስላለመስጠት ነው” ሲሉ ለተደመጡት አንድ ባለሥልጣን “እኛ ስለእሱ እየተወያየን አይደለም” በማለት አንገታቸውን ነቅንቀዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2014